የአፈጉባኤው መልቀቂያ በኦህዴድ ሰፈር | ኢትዮጵያ | DW | 10.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የአፈጉባኤው መልቀቂያ በኦህዴድ ሰፈር

ጎምቱው ባለስልጣን አቶ አባዱላ ገመዳ ከፊታቸው ፈገግታ እና ሳቅ አይጠፋም፡፡ እሁድ ምሽት ነጭ የስፖርት ጃኬት እና ቲሸርት አድርገው፣ የኢትዮጵያ እና ኦሮሚያ ክልል ባንዲራዎች ከኋላቸው እንደደቆሙ፣ በቴሌቪዥን ቀርበው የሥራ መልቀቂያ ውሳኔያቸውን ሲያሳውቁ ግን ፊታቸው ፈገግታ ርቆት ነበር፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:01
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:01 ደቂቃ

የአቶ አባዱላ ውሳኔ ማነጋገሩን ቀጥሏል

አቶ አባዱላ በአዲስ አበባ መሿለኪያ አካባቢ በሚገኘው የኦህዴድ ጽህፈት ቤት በሰጡት በእሁዱ አጭር ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ደስተኛ አለመሆናቸው በግልጽ ያስታውቅ እንደነበር በአካባቢው የነበሩ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፡፡ ያልተጠበቀው የአባዱላ ውሳኔ ትላንት የተካሄደውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመክፈቻ ስነ ስርዓት ተጠባቂ አድርጎት ነበር፡፡ አቶ አባዱላ በመክፈቻው ስነ ስርዓት ሙሉ ሱፍ ለብሰው ከፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ እና ከፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ያለው አባተ ጋር ብቅ ሲሉ ቆፍጠን የማለት ስሜት ይታይባቸው ነበር፡፡ በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል ግጭት ህይወታቸው ለጠፋ ሰዎች የሕሊና ጸሎት ሲደረግም ሆነ ብሔራዊ መዝሙር ሲዘመር ይኼው ስሜት አብሯቸው ነበር፡፡  

የተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶችን የጋራ የመክፈቻ ስብሰባን ከዚህ ቀደም እንደተለመደው ሲመሩ የነበሩት አቶ አባዱላ በአጀንዳነት ካስተዋወቋቸው ውስጥ የሥራ መልቀቂያቸው ጉዳይ አልነበረበትም፡፡ ጉዳዩ መቼ ወደ ምክር ቤት እንደሚቀርብ እስካሁን ግልጽ የተደረገ ነገር የለም፡፡ ሆኖም የስራ መልቀቂያቸው በ“አዲስ ስታንደርድ” ድረ ገጽ በኩል ቅዳሜ መስከረም 27 ይፋ ከተደረገ አንስቶ ላለፉት ሦስት ቀናት ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡ በእናት ፓርቲያቸው በኦህዴድ አባላትም ዘንድ ሞቅ ያሉ ውይይቶች ቀስቅሷል፡፡ በሻሸመኔ የሚገኙ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የኦህዴድ አባል የአቶ አባዱላ ውሳኔ ደጋፊ ናቸው፡፡

“የአባዱላ ውሳኔ እንደ አንድ ሰው ማድረግ የሚገባህን በተገቢው መንገድ ካላደረግህ የመጨረሻ ውሳኔ ሊሆን የሚችለው፣ የሌሎችም ዕጣ ፈንታ ሊሆን የሚችለው ይሄው ነው፡፡ ምክንያቱም እዚያ ጋር ተቀምጠህ፣ የህዝብ ውክልና ወስደህ፣ ተነጋግረህ፣ ከሚመለከተው አካል ጋር ውሳኔ ሰጥተህ የህዝቡን ችግር ማስተካከል በማትችልበት ሁኔታ ላይ ስትደርስ እንደ አንድ መሪም፣ እንደ አንድ የኦሮሞ ህዝብ ተወካይም፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋም ማድረግ የሚገባህ ነገር ያው ከስራ መልቀቅ ነው፡፡ ከአንድ ታማኝ ሰው፣ ከአንድ ታጋይ ሰው የሚጠበቀውም ይኸው ነው፡፡ የሚጠበቀውን ነው ያደረገው፡፡ እኔም በእርሳቸው ቦታ ብሆን ይህንኑ ነው የማደርገው” ይላሉ የሻሸመኔው የፓርቲ ጓዳቸው፡፡

ከሥራቸው ጋር በተያያዘ የህዝብ አስተያየት እንደሚያሰባስቡ የተናገሩት የኦህዴዱ አባል የአቶ አባዱላ ውሳኔ በተለይ በወጣት ኦሮሞዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱን ይናገራሉ፡፡ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የሚሹ በሰበታ ያሉ ሌላ የኦህዴድ አባል ደግሞ አቶ አባዱላ አሁን ባሉበት የአፈጉባኤ ቦታ ቢቆዩ ይመርጣሉ፡፡ በውሳኔያቸው ቅር ቢሰኙም ስራ መልቀቃቸውን በጥሩ ጎኑ ይመለከቱታል፡፡ 

“እንግዲህ እንደ አንድ የኦህዴድ አባል የተሰማኝ ነገር አንደኛ በፍቃደኝነት ስራ መልቀቅ እምብዛም አልተለመደም፡፡ ሊለመድ የሚገባው ነገር ነው ምክንያቱም እዚያ ቦታ መቆየት ሳይፈልጉ ያለፍላጎት መቆየቱ ብዙ የጎንዮሽ ጉዳት ስላለው ጥሩ ነው፡፡ እንደ አንድ አባል እዚያ በተለይ ቆይተው ቢሰሩ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግን እንደምረዳው ከራሳቸው ጋር የህሊና ዳኝነት ወስደው ነው መቀጠል የለብኝም ብለው የመልቀቂያ ደብዳቤውን ያስገቡት፡፡ ስለዚህ ለሌሎቹ ምሳሌ ሊሆኑ ይገባል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከሰሩ ከልብ አንድ ለውጥ ሊያመጣ በሚችል መልኩ ካልሆነ ደግሞ መልቀቅን እንደ አንድ አማራጭ መውሰዳቸው ጥሩ ነው ብዬ ነው የምወስደው” ይላሉ የሰበታው አባል፡፡    

ኦህዴድ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ “ህዝባዊ የሆነ ድርጅት ሆኖ ለመንቀሳቀስ ጥረት እያደረገ ነው” የሚሉት የፓርቲው አባል የአቶ አባዱላ ከፌደራል ስልጣን ለመሰናበት መወሰን “የድርጅታችንን ጠንካራ ጎን ነው የሚያሳየው” ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ ተቀማጭነታቸውን በአዳማ ያደረጉ እና የኦሮሞን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ታዛቢም ተመሳሳይ አስተያየት አላቸው፡፡ 

“ለኦህዴድ ትልቅ ድል ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ከንግግራቸው ሲታይ ‘ለመረጠኝ ህዝብ ክብር አለኝ፣ የትም አልሄድም፣ እሰራለሁ ነው’ ያሉት፡፡ እርሳቸው አሁን መስራት የማይፈልጉት የአፈ ጉባኤነቱን ጉዳይ ነው እንጂ ለድርጅቱ እንደሚሰሩ ነው፡፡ በመግለጫቸው ላይ የሚያሳየው አለመግባባት ወይም ደግሞ ያልተመቻቸው ነገር እንዳለ ነው፡፡ ለኦህዴድ ያለው አንደምታ እንግዲህ ኦህዴድ አሁን ባለው ሁኔታ ወይም አካሄድ በአሁኑ ጊዜ ሀገሪቷ ውስጥ ይሻላል፡፡ ይሻላል ብቻም ሳይሆን ለውጥ ላይ ናቸው፡፡ ይሄን ለማገዝ ያደረጉት፣ የወሰዱት ይመስለኛል፡፡ የሚታየውም፣ አሁን ኦህዴድ ውስጥ እየተሰራ ያለው ነገርም ከእርሳቸው ጋር የተያያዘ ይመስላል፡፡ ከአስተዳደሩ፣ ከንቲባው፣ ፕሬዝዳንቱ ሁሉም ከእርሳቸው ጋር የተያያዘ ነገር ይመስላል፡፡ ይህንን ነገር ከኋላ ሆኖ ለማገዝ እና ድርጅቱን ለማጠናከር የወሰዱት እርምጃ ይመስላል እና ለኦህዴድ ያለው አንደምታ ጥሩ ይመስለኛል” ይላሉ ታዛቢው፡፡ 

በኢትዮጵያ የፌደራሊዝም ስርዓት እየተተገበረ ነው ይባል እንጂ ሁሉም ቦታ የሚሰራ ፌደራሊዝም እንዳልነበር የሚከራከሩት የፖለቲካ ታዛቢው አሁን ወደ ትክክለኛው መልክ የቀረበ ይመስላል ባይ ናቸው፡፡ ለዚህም በምሳሌነት የሚያነሱት “ለፌደራል ታዛዥ የሆኑ” የሚሏቸውን አመራሮች ተክተው በኦሮሚያ ክልል ወደ ስልጣን የመጡ ሹማምንት የሚያደርጓቸውን በህዝብ የተደገፉ እንቅስቃሴዎች ነው፡፡ በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልል ከነበረው ግጭት ጋር በተያያዘ በፌደራል መንግሥት እና በኦህዴድ መካከል ያለው ግንኙነት ሻክሯል የሚሉት የፖለቲካ ታዛቢው ህዝቡ የፌደራል መንግሥትን ተጠየቂ እንደሚያደርግ ይገልጻሉ፡፡ 

አቶ አባዱላ በባሌ በግጭቱ የተጎዱ ሰዎችን ለመነጋገር ከሁለት ሳምንት በፊት በተጓዙ ጊዜ ተመሳሳይ አስተያየቶች እንደገጠሟቸውም ያብራራሉ፡፡ የባሌውን ጉብኝት የተቀረጸ ቪዲዮ መመልከታቸውን የሚናገሩት ታዛቢው አቶ አባዱላ በተለይ ከአካባቢው ሽማግሌዎች በሰሙት እና ባዩት “ልባቸው ተነክቶ ነበር” ይላሉ፡፡ እንደእሳቸዉ ግምትም አቶ አባዱላ ከስልጣናቸው ለመልቀቅ ካሰቡ ቆየት ቢልም የባሌው ጉብኝታቸው “ቶሎ ለመልቀቃቸው አንድ ምክንያት ነው”፡፡  

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ    

Audios and videos on the topic