የአዜያን የነጻ ገበያ ራዕይ | ኤኮኖሚ | DW | 21.11.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአዜያን የነጻ ገበያ ራዕይ

በአሕጽሮት አዜያን በመባል የሚታወቀው የደቡብ ምሥራቅ እሢያ መንግሥታት ማሕበር ካምቦጃ ርዕሰ-ከተማ ፍኖም-ፔንህ ላይ ሲካሄድ የሰነበተውን በነጻ ንግድና በአካባቢው የኤኮኖሚ ትስስር ላይ ያተኮረ ዓመታዊ ጉባዔውን ትናንት አጠቃሏል።

በአሕጽሮት አዜያን በመባል የሚታወቀው የደቡብ ምሥራቅ እሢያ መንግሥታት ማሕበር ካምቦጃ ርዕሰ-ከተማ ፍኖም-ፔንህ ላይ ሲካሄድ የሰነበተውን በነጻ ንግድና በአካባቢው የኤኮኖሚ ትስስር ላይ ያተኮረ ዓመታዊ ጉባዔውን ትናንት አጠቃሏል። ጉባዔው ምንም እንኳ በኤኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ቢያልምም የአካባቢው ሃገራት ከቻይና ጋር ባላቸው የባሕር ግዛት ውዝግብ መጋረዱም አልቀረም።

ከዚሁ ሌላ የሰብዓዊ መብት ጉዳይም በተለይም በቅርቡ ለሁለተኛ የሥልጣን ዘመን የተመረጡት የአሜሪካ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ አካባቢውን እየጎበኙ ባሉበት ሰዓት የተለየ ትኩረት ማግኘቱ አልቀረም። እርግጥ የአሜሪካው ፕሬዚደንት የእሢያ ጉብኝት ዋሺንግተን በኤኮኖሚ ፖሊሲ ረገድ ለአካባቢው የበለጠ ክብደት ለመስጠት መነሳቷም የሚንጸባረቅበት ነው። ባራክ ኦባማ ትናንት በአዜያን ጉባዔ አኳያ ከቻይናው ጠቅላይ ሚኒስትር ከዌን ጂያባዎ ተገናኝተው ሲነጋገሩም ከትችት ይልቅ ትብብርን ማጉላቱን ነበር የመረጡት።

«በሁለት ወገን ግንኙነታችንና በትብብራችን በጣም ነው የምደሰተው። ትብብሩ ለሁለቱም አገሮቻችንና ለዓለምም ጭምር የሚበጅ ነው። ሁለቱ በዓለም ላይ ታላላቁ የኤኮኖሚ ሃይል የሆኑት አገሮቻችን ብልጽግናንና ዕድገትን ለማራመድ እንዲችሉ ቻይና ግልጽ የሆነ ዓለምአቀፍ የንግድና የመዋዕለ ነዋይ ደምቦችን ማስፈን ይኖርባታል»

የአዜያን መንግሥታት ስብስብ በበኩሉ ዘላቂ በሆኑ የነጻ ገበያና የኤኮኖሚ ሕብረት ዕቅዶች ላይ ሲነጋገር ነው የሰነበተው። ዓላማው Regional Comprehensive Economic Partnership(RCEP)ወይም አጠቃላይ የአካባቢ ኤኮኖሚ ሽርክናን ማስፈን ሲሆን ዓላማውም አሥሩን የአዜያን መንግሥታትና ቶጎራባቹን ሃገራት ጃፓንን፣ ቻይናን፣ ደቡብ ኮሪያን፣ ሕንድን፣ እንዲሁም አውስትራሊያንና ኒውዚላንድን ማስተሳሰር ነው። ይህ ደግሞ ግዙፍ ገበያን የሚፈጥር ለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

በመሆኑም ታይላንድን የመሳሰሉት ከትስስሩ አዲስ የኤኮኖሚ ዕድገት የሚጠብቁ የአዜያን ዓባል ሃገራት በመንግሥታቱ ጉባዔ ላይ በጉዳዩ ብርቱ ቅስቀሣ ማድረጋቸው አልቀረም። ዕቅዱ ዕውን ቢሆን የተሳሰረው ገበያ 3,5 ሚሊያርድ ፍጆተኞችን የሚያቅፍና ከዓለም የኤኮኖሚ አቅምም ሶሦውን የሚጠቀልል ነው የሚሆነው። ይህንኑ አጠቃላይ የአካባቢ የኤኮኖሚ ሽርክና ለመመስረት የሚካሄደውን ድርድርም በሶሥት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠቃለል ተወጥኖ ቆይቷል።

ከዚሁ ግብ ለመድረስ የተለያዩት ከዚህ ቀደም አዜያን መንግሥታት ከስድሥት ሸሪክ ሃገራት ጋር ያደረጓቸው አምሥት መለስተኛ የነጻ ገበያ ውሎች ይረዳሉ ተብሎ ነው የሚታመነው። በመሠረቱ የሽርክናውም ዓላማ እነዚህን ስምምነቶች በአንድ ማዋሃድ እንጂ ሌላ አይደለም። አዜያን በ 2015 ዓም ASEAN Economic Community በአህጽሮት AEC ተብሎ የሚጠራ የኤኮኖሚ ማሕበረሰቡን ለማስፈንም ያቅዳል። በዚሁ የሚታሰበው ያለ ብዙ ገደብ የሚደረግ ሰፊ የሆነ የምርትና የአገልግሎት እንቅስቃሴን ገሃድ ማድረግ ነው።

ይህን ዓላማ የአዜያን ሃገራት በተለያየ መጠን ከሰባኛዎቹ ዓመታት አንስተው ሲያራምዱ ቆይተዋል። ሂደቱንም የተለያዩት ሃገራት የዕድገት ደረጃ፣ ማሕበራዊና መንግሥታዊ ስርዓታት እንዲሁ ውጣ ውረድ የበዛው አድርገውት ነው የኖሩት። የአዜያን ዓባል ሃገራት ቁጥር ዛሬ አሥር ሲደርስ ድሃዋን ንያንማርን፤ የቀድሞዋን በርማና ሃብታሟን ሲንጋፑርን መጠቅለሉ ልዩነቱን አጉልቶ የሚያሳይ ነው።

ንያንማርን ካነሣን ባራክ ኦባማ በለውጥ ላይ በምትገኘው አገር ታሪካዊ ግምት የተሰጠው ጉብኝት ሲያደርጉ በዚያቅ ባሰሙት ይፋ ንግግር ያለ ብሄራዊ ዕርቅ ዕድገትና ብልጽግና ሊሰፍን እንደማይችል አስገንዝበዋል።

«ማንኛውም የለውጥ ጥረት ያለ ብሄራዊ ዕርቅ ሊሰምር አይችልም። እናም ሁሉም ዕድል በሚያገኝበት በዚህ መንገድ ከተሰራ የኤኮኖሚ ዕድገትን ማስፈኑ የሚገድ አይሆንም። በታታሪነት ከሰሩ ስኬት ይኖራል። ይህ ነው የአንድን አገር ልማት በተፋጠነ ሁኔታ ሊያራምድ የሚችለው። ግን ይህን መሰሉ ዕድገት የሚገኘው ሙስናንም ማስወገድ ሲቻል ብቻ ነው»

በአዜያን አካባቢ ነጻ ንግድንና ሰፊ የኤኮኖሚ ትስስርን በማሰፈን ብልጽግናን ዕውን ለማድረግ ያለው ራዕይ በደቡብ ቻይና ባሕር የግዛት ውዝግብ መጋረዱም አልቀረም። ቻይና ባለፈው ዓመት እንደገና ከሞላ ጎደል በጠቅላላው የባሕር አካባቢ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ስታነሣ ጉዳዩ በባሕሩ አኳያ የሚገኙ መንግሥታትን ተቃውሞ መቀስቀሱ ይታወቃል። እነዚሁ ሃገራትም ለምሳሌ ፊሊፒንስ፣ ቪየትናም፤ ማሌይዚያና ብሩናይ ናቸው። ለችግሩ መፍትሄ ለማግኘት በአዜያንና በቻይና መካከል አንዳንድ ጥረቶች ቢደረጉም እስካሁን የተረደሰበት ጭብጥ ውጤት ግን የለም።

በደቡብ ምሥራቅ እሢያ መንግሥታት ማሕበር በአዜያን ጉባዔ ላይ ሌላው አከራካሪ የፖለቲካ ነጥብ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ነበር። የደቡብ ምሥራቅ እሢያው መንግሥታት ማሕበር ባለፈው ዕሑድ የሰብዓዊ መብት መግለጫ አጽድቋል። ይሁንና ይሄው ገና በይፋ ታትሞ ያልወጣው ሰነድ ለብሄራዊ ጸጥታ ወይም ለሕብረተሰብ ስርዓት አስፈላጊ ከሆነ በሚል ገደብ የሚያበጅ በመሆኑ አከራካሪ መሆኑ አልቀረም። የአዜያን ሃገራት ባለሥልጣናት መግለጫውን በመብት ጥበቃ ረገድ ታላቅ ዕርምጃ ነው በማለት ቢያወድሱም ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሜሣር ግን ትችትና ስጋት ነው የሰነዘሩት።

ወደ ኤኮኖሚው መለስ እንበልና የአሜሪካው ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማም በሶሥት ቀናት የእሢያ ጉብኝታቸው ቀደም ሲል ታይላንድና ንያንማርን ከጎበኙ በኋላ በፍኖም-ፔንህ የአዜያን ጉባዔ ላይ ተገኝተዋል። ኦባማ ወደ አካባቢው የተጓዙት በተለይም አገራቸው ከእሢያ ጋር የጠበቀ የኤኮኖሚ ትብብር እንደምትሻ ለማስረገጥ ነው። ዋሺንግተን በተፋጠነ ዕድገት ላይ ከምትገኘው ከእሢያ ጋር በመተባበር በፍጥነት ወደ ቀድሞ የኤኮኖሚ ጥንካሬዋ ለመመለስ ተነስታለች።

የእሢያ-ፓሢፊክ አካባቢ ፈጣኑ በኤኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኝ አካባቢ እንደመሆኑ መጠን ዋሺንግተን የማታስበው ዕርምጃው እስከ መጪው ምዕተ-ዓመት ለአሜሪካ ሕዝብ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ለሚያስፈልገው ጽጥታና ብልጽግና ወሣኝነት እንደሚኖረው ነው።

ይህ ነው እንግዲህ የአሜሪካ መንግሥት አዲስ የእሢያ-ፓሢፊክ ስልታዊ መርህ መሠረታዊ ዓላማ። ኦባማ በእሢያ ጉብኝታቸው መጀመሪያ በታይላንድ ርዕስ-ከተማ በባንግኮክ ያተኮሩትም በሁለቱ ወገን የኤኮኖሚ ግንኙነት ላይ ነበር። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሂላሪይ ክሊንተን የአሜሪካን መንግሥት የኤኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫ ሲያስረዱ በበኩላቸው እንዲህ ብለዋል።

«አሜሪካ ለመጪዎቹ በርካታ ዓመታት ጥንካሬዋን ይዛ ለመቀጠል አሁን የተገኘውን አጋጣሚ መጠቀም አለባት። ይህም በእሢያ-ፓሢፊክ አካባቢ ጥረታችንን ማስፋትና በዓለምአቀፍ ደረጃም የኤኮኖሚን ሚና ከፍ ማድረግ ማለት ነው»

ሂደቱ እያደር የሚታይ ይሆናል። ለማንኛውም የታይላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ዪንግሉክ ሺናዋትራም አገራቸው ትራንስ-ፓሢፊኩን ሽርክና ለመቀላቀልና የነጻ ንግድ ውል ለመፈራረም ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል።

«ታይላንድ አሁን ትራንስ-አትላንቲክ ሽርክና ለመጀመርና ሁሉንም ተጠቃሚ ወገኖች ለማሳተፍ ትፈልጋለች። ለዚሁ አስፈላጊው የፓርላማ ድጋፍ ከተገኘ በኋላም ውሉ የሚፈረም ይሆናል»

ለማጠቃለል የእሢያ-ፓሢፊክ አካባቢ መንግሥታት በዓለም ላይ ታላቁ የሚሆነውን የነጻ ንግድ አካካቢ ለመፍጠር ድርድራቸውን በመጨው ዓመት ለመጀመር ተስማምተዋል።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic