1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮጳ ህብረት እና የቱርክ ውዝግብ  

የአውሮጳ ህብረት እና የቱርክ ውዝግብ ተባብሶ ቀጥሏል ። የአውሮጳ ህብረት ፓርላማ ባለፈው ሳምንት የቱርክ የህብረቱ አባልነት ድርድር እንዲቆም ድምጽ ከሰጠ በኋላ ቱርክ ያስጠጋቻቸውን ስደተኞችን እለቅባችኋለሁ ስትል የህብረቱን አባል ሀገራት እያስፈራራች ነው ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:01

የአውሮጳ ህብረት እና የቱርክ ውዝግብ

ቱርክ የጎረቤቶቿ የአውሮጳ ሀገራት ማህበር አባል ለመሆን የመጀመሪያ ማመልከቻ ያስገባችው የዛሬ 29 ዓመት ነበር ። በዚያን ጊዜ መጠሪያው «የአውሮፓ የኤኮኖሚ ማህበረሰብ» አባል ለመሆን ነበር ያመለከተችው ። በሂደት የአውሮጳ ህብረት ለሆነው ለዚህ ማህበር አባልነት የታጨችው በታህሳስ 1999 ነበር ። ለአባልነት መደራደር ከጀመረች ደግሞ ባለፈው ጥቅምት 11 ዓመት አለፈ ።   በተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ችግሮች ሲጓተት የቆየው ድርድር ለጊዜው እንዲቆም ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ድምፅ ሰጥቶበታል ።ፓርላማው ይህን ተፈጻሚነት የሌለው ውሳኔ ያሳለፈው የቱርክ መንግሥት ከመፈንቅለ መንግስት ሙከራው በኋላ በዜጎች ላይ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በመቃወም ነው ። ባለፈው ሳምንት  ሽትራስቡርግ ፈረንሳይ ውስጥ በጉዳዩ ላይ ድምጻቸውን የሰጡት የፓርላማው አባላት የአንካራ መንግሥት ከከሸፈው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኋላ የሚወስዳቸውን ተመጣጣኝ ያልሆኑ እና ጨቋኝ ያሏቸውን እርምጃዎች አውግዘዋል ። የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን እና አባል ሀገራት በመካሄድ ላይ ያለው የቱርክ የአባልነት ድርድር ለጊዜው እንዲቆም እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል ።በአውሮጳ ህብረት ፓርላማ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ቡድን ሊቀመንበር ማንፍሬድ ቬበር ቱርክ በዜጎቿ ላይ የምትወስዳቸው እርምጃዎች በዝምታ መታለፍ የለባቸውም ሲሉ ለምክር ቤቱ አሳስበዋል ። 
«በዚህ ጉዳይ ላይ አውሮጳ ምንም ሳይናገር ማለፍ አይችልም ፤ግልፅ መልስ መስጠት አለብን ።እናም ልንወስድ የምንችለው ዝቅተኛ እርምጃ ቱርክ ውስጥ አስተማማኝ ሁኔታ እስከሌለ ድረስ የአባልነት ድርድሩን ማቆም ነው ።»

በጎርጎሮሳዊው ሐምሌ 15፣2016 ከተሞከረው የቱርክ መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ቢያንስ 37 ሺህ ሰዎች ወህኒ ወርደዋል ። ከታሰሩት ውስጥ በሀገሪቱ ፓርላማ የተወከሉ ኩርዶችን የሚደግፈው የህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ  ፓርቲ በምህጻሩ HDP 10 አባላት እና ከ120 በላይ ጋዜጠኞች ይገኙበታል ። የመፈንቅለ መንግሥቱ ደጋፊ ተብለው ከስራ የታገዱት ወታደሮች ምሁራን ዳኞች ጋዜጠኞች  የፖለቲካ አቀንቃኞች እንዲሁም የኩርድ መሪዎች ቁጥር ወደ 75 ሺህ ይደርሳል ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ልዩ ልዩ ማህበራት እና መገናኛ ብዙሀን ተዘግተዋል ። ፓርላማው ድርድሩ ለጊዜው እንዲቋረጥ የሚጠይቀውን ተፈጻሚነት የሌለው ውሳኔ ያሳለፈው በ479 ድጋፍ እና በ37 ተቃውሞ እንዲሁም በ107 ተአቅቦ ነበር ። የአውሮፓ ህብረት እና ቱርክ ሊገባደድ አንድ ወር ያህል ጊዜ በቀረው በጎርጎሮሳዊው 2016 በቱርክ አድርገው ወደ ህብረቱ አባል ሀገራት ለመግባት የሚሞክሩ  ስደተኞችን ቱርክ በሀገርዋ እንድታቆይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ። በቀደመው በ2015 ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞች አውሮጳ ገብተዋል ። ከመካከላቸው በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩት ከ2 ሚሊዮን በላይ የሶሪያ ስደተኞችን ከምታስተናግደው ከቱርክ ነው የመጡት ። ቱርክ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ የምታገኝበት የአውሮፓ ህብረት እና ቱርክ ስምምነት ወደ አውሮጳ ሀገራት የሚመጣው ስደተኛ ቁጥር እንዲቀንስ አድርጓል ። ከዚህ ሌላ በጎርጎሮሳዊው 2016 መጀመሪያ ላይ በተፈረመው በዚህ ውል መሠረት አንካራ ማሻሻያዎችን ካደረገች ቱርኮች በአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ያለ ቪዛ እንዲጓዙ ለመፍቀድ ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር ። ስምምነቱ ለአውሮጳ መንግሥታት ትልቅ እፎይታ ቢያስገኝም ከቱርክ ጋር አለመግባባት በተፈጠረ ቁጥር ግን ቱርክ ስምምነቱን  እንደ ማስፈራሪያ መጠቀሟ አልቀረም ። የአውሮጳ ህብረት ፓርላማ ከቱርክ ጋር የሚካሄደው የአባልነት ድርድር እንዲቆም በጠየቀ በማግስቱ  የቱርኩ ፕሬዝዳንት ጠይብ ሬቼፕ ኤርዶሀን ስምምነቱ እንደሚያፈርሱ ነበር የዛቱት ።  
«50 ሺህ ስደተኞች የድንበር ከተማዋ ካፒኩሌ ሲደርሱ ጮሀችሁ ።ቱርክ ድንበርዋን ብትከፍት ምን እናደርጋለን ስትሉ በቅጡ አሰባችሁበት ።ልብ በሉ ከዚህ በላይ የሚሄድ ከሆነ እነዚህ የድንበር በሮች ይከፈታሉ ። ይህን ማወቅ አለባችሁ ። እኔም ሆንኩ ህዝቡ ለባዶ ዛቻዎች ስሜት አይሰጠንም ።»
የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኦሜር ሴሌክም የፓርላማውን ውሳኔ ዋጋ ቢስ ሲሉ አጣጥለውታል ። ከዛም አልፎ እርምጃው የአውሮፓውያንን እሴቶች የሚጥስ ነው ያሉት ። ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ የአውሮጳ ህብረት በጥብቅ የሚቃወመውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለተጨማሪ 3 ወራት እንደሚያራዝሙ የሞት ቅጣትንም እንደገና ህጋዊ ሊያደርጉ

እንደሚችሉም አስታውቀዋል ። በፓርላማው እርምጃ በእጅጉ የተበሳጩት  ኤርዶሀን «የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማራዘም ውሳኔ  የመንግሥት እና የህዝብ ውሳኔ መሆኑን አስታውቀው የብዙ አውሮጳውያን መጠሪያ የሆኑትን ሃንስ እና ጆርጅ የተባሉትን ስሞች በመጥቀስ እነርሱ የሚሉትን ሳይሆን ህዝባቸው የሚላቸውን ማድመጥ እንደሚመርጡ ባለፈው ቅዳሜ ተናግረዋል ። ለዚህ የኤርዶሀን ንግግር የአውሮጳ ህብረት ባለሥልጣናት በሰጡት መልስ ፣ ለቱርክ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክት ነው ያስተላለፉት ። የቱርክ መሪዎች በርግጥ የአውሮጳ ህብረት አባል መሆን ይፈልጉ አይፈልጉ እንደሆነ መወሰን እንዳለባቸው አሳስበዋል ።ከዚህ ሌላ ቱርክ ዜጎቿ በአውሮጳ አባል ሀገራት ያለ መግቢያ ቪዛ እንዲንቀሳቀሱ እንዲፈቀድላቸው ያቀረበችው ጥያቄ መልስ እንዲያገኝ ፍላጎት እንዳላቸው እና እንደሌላቸው እንዲያስቡበት ጠይቀዋቸዋል ። ማሳሰቢያውን የሰጡት የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዦን ክሎድ ዩንከር ኤርዶሀን ህብረቱን መውቀስ ትታ ፊቷን ወደ ራስዋ በመመለስ ዜጎቿ በአውሮፓ እንደልባቸው እንዳይንቀሳቀሱ ለመደረጉ ሃላፊነቱ የርሳቸው ወይስ የኛ መሆኑን በቅጡ ያጢኑት ሲሉ ጠይቀዋል ።የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ለቱርክ የአውሮጳ ህብረት አባልነት የሚካሄደው ድርድር እንዲቆም በአብላጫ ድምፅ ያሳለፉት ውሳኔ በአንዳንድ የአውሮጳ ህብረት ባለሥልጣናት ዘንድ በጥሩ እርምጃነት አልተወሰደም ። ለምሳሌ የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ፌደሪካ ሞጎሮኒ እርምጃው ጥሩ መንገድ ነው ብለው እንደማያስቡ ነው የተናገሩት ። በርሳቸው አስተያየት ከቱርክ ጋር በመነጋገር የቱርክን ዴሞክራሲ ለማጠናከር በመሞከር ችግሮችን ለመፍታት መጣሩ እንጂ መፋጠጡ አይበጅም። እንደ ሞጎሮኒ ቱርክ አባል ለማድረግ የሚካሄደው ድርድር እንዲቆም ከተደረገ ማንም አሸናፊ ሊሆን

አይችልም ። የአውሮጳ ህብረትም ቱርክም ተሸናፊ ይሆናሉ ነው ያሉት ሞጎሮኒ ።በቱርክ የአውሮጳ ህብረት አባልነት ማመልከቻ ላይ ኦስትሪያ እና ላክስምበርግ ድርድሩ እንዲቆም ነው የሚፈልጉት ጀርመን ፈረንሳይ እና አብዛኛዎቹ የአህብረቱ አባል ሀገራት ደግሞ ከአንካራ ጋር የቅርብ ግንኙነታቸው እንዲቀጥል ይፈልጋሉ ።ሆኖም አባል ሀገራት በሙሉ የቱርክ መንግስት የሞት ቅጣትን እንደገና ህጋዊ የሚad,ርግ ከሆነ ንግግሩ በመቆሙ ነው የሚስማሙት ። የጀርመን መራሂተ ምንግሥት አንጌላ ሜርክል በሰጡት አስተያየት የቱርክ መንግሥት በፀረ ሽብር እርምጃ ሰበብ በዜጎች ላይ የሚፈጽማቸውን በደሎች ተቃውመዋል ። 
«የጀርመን ፌደራል መንግሥት እንደ ሌሎቹ የአውሮፓ መንግሥታት ሁሉ ሽብርን በቁርጠኝነት ይዋጋል ።ይሁንና  ክቡራትና እና ክቡራን ይህ ግን የፕሬስ ነጻነትን ለመገደብ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለማሰር ምክንያት መሆን የለበትም ። በዚህ ረገድ ይህን እርምጃ በግልጽ ማውገዝ አለብን ከዚሁ ጋርም ከቱርክ ጋር ንግግሩ እንዲቀጥል እፈልጋለሁ ።»
የአውሮፓ ህብረት እና የቱርክ ውዝግብ ቀጥሏል ። ቱርክ ህብረቱ በኔ ጉዳይ ጣልቃ አይግባ ስትel አጥብቃ ታሳስባለች የአውሮጳ ህብረት ደግሞ ሀገሪቱ እንድታሟላ የተጠየቀችውን ካላደረገች የህብረቱ አባልነት አይታሰብም እያለ ነው ። በዚህ መሀል ሁለቱ ወገኖች የተፈራረሙት የስደተኞች ጉዳይ ውል አደጋ ላይ ወድቋል ። የውሉ እጣ ምን እንደሚሆን ከወዲሁ ለመገመት ያስቸግራል ። ኤርዶሀን እንደ ማስፈራሪያ የሚጠቀሙበት ihe ውል ያሰቡትን ለማሳካት ያስችላቸው አያስችላቸው ወደፊት የሚታይ ይሆናል ።   

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች