የአዉሮጳ ሕብረትና የባሮሶ ንግግር | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 08.09.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአዉሮጳ ሕብረትና የባሮሶ ንግግር

«ይሕን በስም መጥራት ይቻላል።ይሕ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት የኒኮላ ሳርኮዚ፥ የጠቅላይ ሚንስትር ፍራንሷ ፊሎን፥ እና የዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ብሪስ ሆርትፉ መንግሥት ነዉ።----»

default

ባሮሶ

08 09 10

የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳት ሆሴ ማኑኤል ባሮሶ በሕብረቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕብረቱን አጠቃላይ መርሕ የዳሰሰ-ንግግር ትናንት ሽትራስቡርግ ለተሰየመዉ ለሕብረቱ ምክር ቤት አሰምተዋል።ባሮሶ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንቶች ከሚያደርጉት «State of the union» ከተሰኘዉ ንግግር ጋር በተመሳሰለዉ ንግግራቸዉ ከጠቀሷቸዉ ጉዳዮች አንዳዶቹ ከሃያ-ሰባቱ የሕብረቱ አባል ሐገራት የተናጥል መርሕ ጋር የሚቃርኑ ናቸዉ።ክርስቶፍ ሐሰልባሕ የዘገበዉን ነጋሽ መሐመድ አጠናቅሮታል።

የንግግሩ መልዕክት በከፊል እስካሁንና አሁን ያሉ ጉዳዮችን የነካካ-ከፊሉ በወደፊቱ ላይ ያተኮረ ነበር።አብዛኛዉን አለም የጎነጠዉ የገንዘብና የምጣኔ ሐብት ድቀት ግን ከዋነኞቹ ነጥቦችም ቀዳሚዉ ነበር።ችግሩን ለማስወገድ የሕብረቱ አባል ሐገራት እስካሁን የሚከተሉትን የተናጥል እርምጃ ግን የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት አልፈቀዱትም።
«ጊዜዉ አዉሮጳ ሐቁን የምታይበት ወቅት ነዉ።አዉሮጳ ከሃያ-ሰባት የተለያዩ ብሔራዊ መፍትሔዎች የበለጠች መሆንዋን ማሳየት አለብን።አንድም በጋራ እንዋኛለን።አለያም በተናጥል እንሰምጣለን።»

Symbolbild Kroatien Slowenien EU

የሕብረቱ አርማ

ከሕብረቱ አባል ሐገራት አንዳዶቹ-እንዲሕ አይነቱን መልዕክት ከማለት ባለፍ አይቀበሉቱም።
ፕሬዝዳንቱ የአዉሮጳ ሕብረት የጋራ የቀረጥ ሥርዓት ሊኖረዉ ይገባል አይነት መልዕክትም ተናግረዋል።ይሕም የአባል ሐገራትን አቋም የሚቃረን ነዉ።የዚያኑ ያክል አብዛኞቹን የምክር ቤት አባላት ባንድ-ያቆመ መልዕክትም ነበራቸዉ።

«አዉሮጳ ዉስጥ የሚኖር ማንኛዉም ሰዉ ሕግ ማክበር አለበት።መንግሥታት ደግሞ የሕዳጣንን ጨምሮ ሠብአዊ መብት ማክበር አለባቸዉ።አዉሮጳ ዉስጥ ዘረኝነትና ጥላቻ ሥፍራ የላቸዉም።ጥንቃቄ የሚጠይቁ ጉዳዮች እና ችግሮች ሲያጋጥሙ የሚወሰደዉ እርምጃ ሐላፊነት የተሞላበት መሆን አለበት።እዚሕጋ አበክሬ የማሳስበዉ ጉዳይ አለ።ያለፈዉ የአዉሮጳ እኩይ መንፈስ መቀስቀስ የለበትም።»

ባሮሶ እንዲያዉ በጥቅሉ-ሰብአዊ መብት፥ የሕዳጣኖች-ደሕንነት እያሉ ያድበሰበሱትን ጉዳይ ፍርጥ አድርገዉ አለመናገራቸዉ ያበሳጫቸዉ የምክር ቤት እንደራሴዎችም አሉ።የሮማ ጎሳ አባልትን ከሐገሩ የሚያግዘዉ የፈረንሳይ መንግሥት በቀጥታ-አለመነቀፍ-መወገዙ ጀርመናዊዉን የሶሻልዲሞክራቶቹ እንደራሴዎች ሊቀመንበር ማርቲን ሹልትስን የመሳሰሉ አባላትን ማናደዱ አልቀረም።

«ይሕ አንድ መንግሥትን ይመለከታል።ሕዳጣናትን በመደፍለቅ የዉስጥ ፖለቲካዊ ጫናዉን ለመቋቋም የሚሞክረዉን መንግሥት።እና ይሕን በስም መጥራት ይቻላል።ይሕ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳት የኒኮላ ሳርኮዚ፥ የጠቅላይ ሚንስትር ፍራንሷ ፊሎን፥ እና የዉስጥ ጉዳይ ሚንስትር ብሪስ ሆርትፉ መንግሥት ነዉ።----»

ባሮሶ የዉጪ መርሕን በሚመለከት ሕብረታቸዉ ከአዳጊዎቹ ሐገራት በጣሙን ከአፍሪቃ ጋር ይበልጥ መቀራረብ እንዳለበት መክረዋል።የድሆቹን ሐገራት ችግሮች ለማቃለል-የተነደፈዉን የአመአቱን ግብ ለማስፈፀም ሕብረቱ መርዳት እንደሚገባዉ አስታዉቀዋል።
«ለአለም ግልፅ መሆን ማለት ከአዳጊ ሐገራት በተለይም ከአፍሪቃ ጋር ጎን ለጎን መቆም ማለትም ጭምር ነዉ።ከሁለት ሳምንት በሕዋላ ኒዮርክ ዉስጥ በሚሰየመዉ የአመአቱ ግብ ጉባኤ ላይ ለመካፈል ስሔድ፥ ለእቅዱ ማስፈፀሚያ በናንተ ድጋፍና በአዉሮጳ ሕብረት ስም አንድ ቢሊዮን ዩሮ ተጨማሪ ርዳታ ለመስጠት አቅጃለሁ።»

Europaparlament Straßburg

የአሕ ምክር ቤት

አዉሮጶች በአለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን የጋራ ተሳትፎ-ማጠናከር፥ገንቢ አስተዋፅኦቸዉን ማጎልበት እንደሚገባቸዉም ባሮሶ ገልፀዋል።«ግን እንዴት?»-ፈረንሳዊዉ የክርስቲያን ዲሞክራቲክ እንደራሴዎች መሪ ዮሴፍ ዳዉል ጠየቁ-ምሳሌም አላቸዉ።
«እኛ ለምሳሌ (ለመካከለኛዉ ምሥራቅ) ከፍተኛዉን ገንዘብ እየረዳን በእስራኤልና በፍልስጤሞች ድርድር ላይ አለመሳተፋችንን እንዴት ምክንያታዊ ልናደርገዉ እንችላለን።»

ንግግሩ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንቶች የስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን ጋር ቢመሳሰልም በአዳራሹ ከታደሙት እንደራሴዎች በስተቀር ብዙ አድማጭ አልነበረዉም።

ክርስቶፈር ሐሰልባሕ
ነጋሽ መሐመድ
ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic