የአካባቢ አየር ለውጥን የተመለከተ ስብሰባ በቦን | ጤና እና አካባቢ | DW | 08.05.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የአካባቢ አየር ለውጥን የተመለከተ ስብሰባ በቦን

የአካባቢ አየር ለውጥ ያስከተለውን አደጋ ለመቋቋም በሚደረገው ዓለምአቀፍ ጥረት በዚህ በቦን ሁለት ሣምንታት የሚፈጅ የአዋቂዎች ስብሰባ በትናንትናው ዕለት ተከፍቷል። ሁለት ሺህ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ በፊታችን ታሕሣስ ወር ኢንዶኔዚያ ደሴት ባሊ ላይ ለሚካሄደው የመንግሥታት መሪዎች የተፈጥሮ ጥበቃ ጉባዔ የሚደረገው ዝግጅት አንድ አካል መሆኑ ነው።

ኢፎ-ዴ-ቦር

ኢፎ-ዴ-ቦር

ትናንት በዚህ በቦን የተከፈተው ለሁለት ሣምንታት የሚዘልቅ የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ አየር ጥበቃ የዝግጅት ስብሰባ በታላላቅ ጉባዔዎች ላይ እንደተለመደው ቀደምት ፖለቲከኞች በመገናኛ አውታሮች የራሳቸውን ዝና የሚያራምዱበትና የበጎ ፈቃድ መግለጫ የሚሰጡበት መድረክ አይደለም። ከፎቶግራፍ ካሜራዎች በስተጀርባ ገቢር መሆን የሚገባቸው ጭብጥ ዘዴዎችና ዕርምጃዎች የሚፈለጉበት የጠበብት ስብሰባ ነው። አዳዲስ የቴክኖሎጂ አማራጮችም ይነሳሉ።

ሁለት ሺህ ገደማ የሚጠጉት የተለያዩ ሃገራት ባለሙያዎች በዝግጅት ስብሰባቸው አብዛኞቹ የዓለም መንግሥታት ከወዲሁ በተስማሙበት፤ ማለት የአካባቢ አየር ለውጥን በተቻለ መጠን በመግታቱ ሃሣብ በሰፊው ይመክራሉ። ተጽዕኖው እየጎላ የመጣውን የአየር ለውጥ ለማለዘብ ባለፈው 2006 ዓ.ም. ናይሮቢ ላይ ተካሂዶ በነበረው የአካባቢ አየር የመንግሥታት ጉባዔ ተወስኖ እንደነበረው አስፈላጊው ገንዘብ በጊዜው መቅረብ እንዳለበትም ማስረገጣቸው የማይቀር ነው። የአካባቢ አየር ለውጥና ይሄው ያስከተለው ተጽዕኖ የተባበሩት መንግሥታት የአካባቢ አየር ጥበቃ ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አካል ዋና ጸሐፊ ኡፎ-ዴ-ቦር እንደሚሉት ዓቢይ ጉዳይ እየሆነ መሄዱ አልቀረም።

“በየጊዜው የበለጠ ትኩረት እያገኘ የሚሄድ ዘርፍ ነው። ምክንያቱም በከፊል ሕዝብ የአየር ጠባይ መለወጥ በሚያስከትለው መዘዝ ላይ የበለጠ ንቃተ-ህሊና እያገኘ መሄዱ፤ በሌላም መንግሥታት ምንም እንኳ የድንገተኛ መከላከያ ዕርምጃዎች ፍቱንነት ቢኖራችውም ከመዘዙ ጋር ይበልጥ እየተጋፈጡ መሄዳችውን መለየታቸው ነው። የአካባቢው አየር ለውጥ በተለይ የሚጎዳው ድሆች አገሮችን በመሆኑም ሰፊ ግንዛቤ አለ”

በእርግጥም በተለይ በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ነው የአካባቢ አየር ለውጥ የጣለው አሻራ ከሁሉም የበለጠ ጎልቶ የሚታየው። የምድረ-በዳ መስፋፋት ቀጥሏል፤ የዝናብ ጨርሶ መጥፋት ድርቅንና የመጠጥ ውሃ እጥረትን ሲያስከትል በሌላ በኩል ደግሞ ከመጠን በላይ የሚጥል ዝናብ ብርቱ መጥለቅለቅንና ቀውስን ማስከተሉ ተፈራራቂ ነገር ሆኗል። ከችግሩ የተጋፈጡት አገሮች የአካባቢው አየር ለውጥ ያስከተለውን ጉዳት መቋቋም እንዲችሉ በሚቀጥሉት አምሥት ዓመታት ውስጥ ለተለያዩ ፕሮዤዎች እስከ 400 ሚሊዮን ዶላር ገንዘብ መውጣት እንዳለበት ነው የሚነገረው።

በሌላ በኩል ማነው ገንዘቡን የሚያገኘው፤ በክፍፍሉ ረገድ ምን ቅድመ ሁኔታ ይኖራል ወይም ማነው የማከፋፈሉን ተግባርስ የሚያቀናብረው፤ ይህ ሰሞኑን በቦኑ ስብሰባ የሚያነጋግር ጉዳይ ነው። ሌላው በቦን የተሰበሰቡት ጠበብት ትኩረት የሚያርፍበት ዓቢይ ጉዳይ የታዳጊ አገሮች የደን ሃብት እየተመነጠረ መሄድ መቀጠሉ ይሆናል። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት የደኖች መመንጠር ዛሬ ሰው-ሰራሽ ለሆነው ሩቡ ወደ አካባቢ አየር የሚተን በካይ ጋዝ ምንጩ ነው። ይህ ሂደት መገታት እንዳለበት ደግሞ የሚጠራጠር ማንም የለም። እንዴት? መልስ ማግኘት ይኖርበታል።

የቦኑ ስብሰባ ምንም እንኳ በርከት ባሉ ቴክኒካዊና ዝግጅት-ነክ ጉዳዮች የሚያተኩር ቢሆንም በስተጀርባ ሌላም አነጋጋሪ ጉዳይ መገኝቱ አልቀረም። ይሄውም ባለፈው ሣምንት ይፋ የሆነው የተባበሩት መንግሥታት ሶሥተኛ የዓለም የአየር ይዞታ ዘገባ ይዘት ነው። ድርጅቱ በዚሁ በመደበኛ ዘገባው እስካሁን በጉዳዩ ብዙ ጥረት መደረጉ ባይቀርም የአካባቢው አየር ቀውስ ገና አልተቀወገደም ሲል አስጠንቅቋል። ዴ-ቦር እንዳሉት በፊታችን ቅዳሜ ጉዳዩ ከሣይንስ አንጻር ሰፊ ውይይት እንደሚደረግበትና ወቅታዊ መረጃዎችም እንደሚቀርቡ ነው የሚጠበቀው።

የቦኑ ጉባዔ በሁለተኛ ሣምንቱ ደግሞ ለሶሥተኛ ጊዜ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት መንግሥታት የበካይ ጋዛቸውን መጠን ለመቀነስ ቃል በገቡበት የክዮቶ ፕሮቶኮል ላይ ያተኩራል። የንግግሩ ዒላማ ከ 2012 ዓ.ም. በኋላ የክዮቶን ፕሮቶኮል የሚተካ የአካባቢ አየር ጥበቃ ውል ለማስፈን የሚደረገው ድርድር ሲሆን ዩ-ኤስ-አሜሪካን፣ ቻይናንና ሕንድን የመሳሰሉት ዋነኛ በካይ አገሮች ፕሮቶኮሉን እንዲፈርሙ የሚደረገው ግፊት ወደፊትም የረጅም ጊዜ ግብ ሆኖ ይቀጥላል። የቦኑ ስብሰባ በዚህ ጉዳይ ከአንድ ጭብጥ ውጤት መድረስ መቻሉን መናገሩ በወቅቱ የሚያዳግት ነው። ሆኖም ጠበብቱ ቢዘገይ እስከፊታችን ታሕሣስ የተባበሩት መንግሥታት ዓቢይ የባሊ ጉባዔ ድረስ ሃሣባቸውን አጠናቀው እንደሚቀርቡ አንድና ሁለት የለውም።