የአናን ተልዕኮ መቋረጥና የኢራን ትችት | ዓለም | DW | 03.08.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአናን ተልዕኮ መቋረጥና የኢራን ትችት

ኢራን ለሶርያ የሰላም መፍትሄ ለማፈላለግ የተሰየሙት የኮፊ አናን ተልዕኮ በምዕራቡ ዓለም ተጨናግፏል ሲትል ወቀሰች። የኢራን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ አክበር ሳልህ፤ በአናን የተሞከረዉ የሶሪያ ሰላም እቅድ ላለመሳካቱ ምዕራቡ ዓለም በተለይም፤

default

ኮፊ አናን

ዩናይትድ ስቴትስ ተጠያቂ ናት ማለታቸዉን አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ከቴህራን ዘግቧል። ሳልህ የፀጥታዉ ምክር ቤትን ተገቢ ድጋፍ በማጣት አናን ከተመድ እና የአረብ ሊግ የሶርያ የሰላም ልዑክነታቸዉ የተሰናበቱበት ዋና ምክንያት ሩሲያና ቻይና ሳይሆኑ በአሜሪካን አቋም አለመለሳለስ ነዉ ማለታቸዉም ተጠቅሷል። ኮፊ አናን ትናንት በተሰጣቸዉ የሰላም ልዑክነት ላለመቀጠል ለመወሰናቸዉ ያቀረቡት የሚከተለዉን ምክንያት ነዉ፤

Iran Kofi Annan mit Außenminister Ali-Akbar Salehi APRIL 2012

አናን እና አሊ አክበር ሳልህ

«ከልብ የታሰበበት፤ ዓላማ ያለዉ እና የተባበረ የአካባቢዉን ኃይሎች ጨምሮ ዓለም ዓቀፍ ጫና፤ ለእኔም ሆነ ለማንም በመጀመሪያ ደረጃ የሶርያን መንግስት እንዲሁም ተቃዋሚዎችን የፖለቲካ ሂደት እንዲጀመር አስፈላጊ ርምጃዎችን እንዲወስዱ ለማድረግ አዳጋች ነዉ። እኛም ሆንን የሶርያ ህዝብ አንዳች ርምጃ ሲወሰድ ለማየት ስንጠብቅ፤ በፀጥታዉ ምክር ቤት ዉስጥ አንዱ በሌላዉ ላይ ጣቱን መጠቆምና መወቃቀስ ጀመረ።»

ከተሰጣቸዉ ሃላፊነት በአምስት ወራት ዉስጥ ራሳቸዉን ያሰናበቱት አናን ለተረካቢ ለማሻገር የአንድ ወር ጊዜ እንዳላቸዉ ተገልጿል። ሩሲያ የመንግስታቱ ድርጅት ባስቸኳይ በአናን ቦታ የሰላም ልዑክ እንዲተካ ጠይቃለች። በመንግስታቱ ድርጅት የሩሲያ አምባሳደር ቪታሊ ስኮርኪን በአናን ዉሳኔ ማዘናቸዉን ነዉ የገለፁት፤

Genf Syrien Konferenz Kofi Annan

አናን ሶርያ ዉስጥ

«ዉሳኔያቸዉን እንረዳለን፤ ሆኖም ይህን በመምረጣቸዉ እናዝናለን። የኮፊ አናንን ጥረት በጥንካሬ ስንደግፍ ነበር። ለመሰናበት አንድ ወር ይቀራቸዋል፤ ይህ ወር በጣም ባስቸጋሪ ሁኔታ ዉስጥ ደም መፋሰስን አስቁሞ ሶሪያን ወደፖለቲካዉ ሂደት ለማምጣት ዉጤታማ በሆነ መልኩ ይጠቅማል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ዋና ፀሐፊዉ የሶሪያን ቀዉስ ለመግታት ኮፊ አናንን የሚተካ ለመሰየም በሚያደርጉት ጥረት ተበራትቻለሁ።»

ይህ በእንዲህ እንዳለም ሩሲያ ወደሶሪያ የጦር መርከብ ልትልክነዉ መባሉን አስተባብላለች።

ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ