የአትክልት ጣቢያ በጨረቃ፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 06.05.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የአትክልት ጣቢያ በጨረቃ፣

በዘንድሮው፣ ማለትም ጎርጎሪዮሳዊው 2009፣ ዓለም አቀፍ የሥነ-ፈለክ መታሰቢያ ዘመን ትኩረት ከሚሰጣቸው የሰማይ አካላት አንዷ ፣ ጨረቃ ናት።

default

ጨረቃ፣

የሰው ልጅ አንጋጦ ወደ ሰማይ ፣ በዓይኑ ብሌን ከሰማይ አካላት ሁሉ ግዙፍ ሆና ፣ ይበልጥ አምራና ደምቃ የምትታየው እርሷው በመሆኗ ሊሆን ይችላል፣ በጨረቃ ሲመሰጥ ኖሯል። ለብዙ ዘመናት ጨረቃ ምን እንደምትመስል አይታወቅም ነበር። ይሁንና ከ 400 ዓመት ገደማ በፊት፣ እውቁ የሥነ ፈለክ ተመራማሪ ጋሊሊዮ ጋሊሌይ፣ ጨረቃ ሙሉና ደማቅ ሆና፣ የነሀስ ቀለም ያለው ለስላሳ ምጣድ መስላ እንደምናያት እንዳልሆነች፣ አባጣ ጎባጣ፣ ሰርጎድጓዳ ገጽ እንዳላት ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ ላይ መዋል በጀመረው የቴሌስኮፕ እርዳታ አማካኝነት ማረጋገጥ ቻለ።

የዘንድሮውን የሥነ ፈለክ መታሰቢያ ዘመን መንስዔ በማድረግ ፣ በኮሎኝ ከተማ የ Wallraf-Richartz ቤተ-መዘክር፣ ካለፈው መጋቢት አንስቶ እስከመጪው ነሐሴ ወር ስለጨረቃ፣ የሥነ-ፍጥረት ተማራማሪዎችንና የሰዓሊዎችን ሥራዎች ያካተተ፣ ዐውደ-ራእይ በማቅረብ ላይ ሲሆን ፣ የቤተ-መዘክሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ Andreas Blühm ጋሊሊዮ ጋሊሌይ የጨረቃን ገጽ በቴሌስኮፕ ከተመለከተበኋላ ምን እንዳደረገ ሲገልጹ፣

«የመጀመሪያው ሰው መሆን ፈለገ፣ ታይቶ-ተሰምቶ ባልታወቀ ፍጥነትም መጽሐፍ ጻፈ። የመዳብ ቀለም እንዳላትም ያሠፈረ እርሱ ነው። መጻፍ ብቻ አይደለም ከዚሁ ከመዳብነት ቀለሟ አያይዞ ምልክቶችን ነድፏል፣ ስሏል፣ ይህ የማሳወቂያ ዘዴው ነበር።»

ከ20ኛውክፍለ-ዘመን አጋማሽ ወዲህ ፣ የያኔዋ ሶብዬት ኅብረት ያሁኗ ሩሲያ እስፑትኒክ የተሰኘችውን ሰው ሠራሽ ሳቴላይት አ ጎ አ ጥቅምት 4 ቀን 1957 ዓ ም ወደ ኅዋ ካመጠቀች ወዲህ ፣ የኅዋ ምርምር፣ የላቀ ትኩረት እያገኘ ሄዶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሐምሌ 21 ቀን 1969 ዓ ም፣ ጨፈርተኛው ኒል አርምስትሮንግ ጨረቃ ላይ ለማረፍ የመጀመሪያው ሰው እንዲባል አበቃች። ይህ ከሆነ በመጪው ሐምሌ 14 ቀን 2001 ዓ ም፣ ልክ 40 ዓመት ይሆናል ማለት ነው። ባለፉት ዓመታት ያን ያህል ለጨረቃ ግምት ሳይሰጥ ላቅ ያለ ትኩረት ሲደረግ የቆየው በማርስ ላይና ከፀሐያዊ ጭፍሮች ውጭ ከምድራችን ጋር ተመሳሳይነት ያላቸውን፣ ህይወት ያለውን ፍጡር ማኖር ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ፕላኔቶችን ፈልጎ ለማግኘት በሚደረግ ጥረት ላይ ነው። ራቅ ወዳሉ ፕላኔቶችም ሆነ ስባሪ ከዋክብት ለመጓዝ ፣ መናኸሪያዎች ስንቅና ትጥቅ አቅራቢ ጣቢያዎች ያስፈልጋሉ። ለዚህ ደግሞ በመጀመሪያ የታጨችው ጨረቃ ሆናለች። ጠፈርተኞች እስካሁን የሚመገቡት በማቀዝቀዣ የደረቀ ዱቄት መሰልና በከፊልም ፈሳሽነት ያለው የጥርስ ሳሙና መሰል ምግብ ነው። ወደፊት ግን አሜሪካውያን ሳይንቲስቶች ፣ ጨረቃ ላይ በአልሙኒየም በሚሠሩ፣ ድንኳን በሚመስሉ ጎጆዎች ውስጥ ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ለማልማት እንደሚፈልጉ ተገልጿል። ወደጠፈር መመላለሱ ይበልጥ የተለመደ ቢሆንም፣ አንድ የሳይንቲስቶች ቡድን እንዳስታወቀው የተሻለ አማራጭ ዘዴ መፈለግ ይኖርበታል።

«ጨረቃ ላይ የበረሃ ገነት » (Lunar Oasis )የሚባል ጣቢያ እገነባለሁ ብሎ የተነሳሳው፣ ከአሜሪካው የኅዋ ምርምር መሥሪያ ቤትና ከዓለም አቀፉ የኅዋ የምርምር ጣቢያም ጋር ተባብረው ሲሠሩ ከቆዩት ድርጅቶች መካከል Paragon Space Development Corporation የተባለው በአሪዞና ፌደራል ክፍል-ሀገር የሚገኝ ኩባንሻያ ነው። የኩባንያው ባለሥልጣናት እንደሚሉት ከሆነ፣ እ ጎ አ ከ2012 ዓ ም በፊት የተጠቀሰውን የረጅም ጊዜ አቅዱን ተግባራዊ ማድረግ አይችልም። NASA ጠፈርተኞችን ወደ ጨረቃ፣ በ 2020፣ ወደ ማርስ ደግሞ በ 2030 ለመላክ አቅድ አለው።

በአሪዞና ዩኒቨርስቲ በአትክልትነክ የሳይንስ ምርምር ያተኮሩት ፕሮፌሰር Gene A. Giacomelli በፕላኔታችን እጅግ ቀዝቃዛ መሆኑ በተመሠከረለት፣ በደቡብ የምድር ዋልታ፣ ከፍተኛ በሆነና ዝቅተኛ የአየር ግፊት ባለው፣ ከዜሮ በታች 100 ዶግሪ ሴንቲግሬድ ገደማ ቃዝቃዜ ባለው ቦታ፣ የተደረገው ሙከራ በጨረቃ ለሚዘረጋው ፕሮጀክት አርአያነት ያለው ነው። በደቡቡ የምድር ዋልታ የተቋቋመው ፕሮጀክት፣ 5ኛዓመቱን የያዘ ሲሆን፣ በዚያ በተተከለው ብረት ለበስ ድንኳን ውስጥ፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ሰላጣ፣ አውጥና ሌሎችም ምግብነት ያላቸው ቅጠላቅጠሎች የሚበቅሉ ሲሆን በየሳምንቱ 27 ኪሎ እንደመመረቱ መጠን ፣ በዚያ ለሚገ ኙት 75 ሳይንቲስቶች እያንዳንዳቸው በቀን የሚመገቡትን ሁለት ሰላጣ ያቀርባል።

ስለሆነም፣ ፕሮፌሰሩ አሁኑኑ ወደ ሌላ ፕላኔት መዛወር ብንችል፣ ራሳችን በመመገብ ኅልውናችንን መጠበቅ አይሳነንም ፣ ይህ ደግሞ ፣ የሳይንስ ተረት-ተረት አይደለም፣ ህ ይወትን መደገፍ የሚያስችለው የሥነ ቴክኒኩ ዕውቀት አለን» ማለታቸው ተጠቅሷል። ማርስ ደርሶ ለመመለስ የአትክልቶች ድርሻ ከፍ ያለና ዘርፈ-ብዙ ነው። በኅዋ ከሚተከለው ብረት ለበስ ድንኳን መርዛማነት ያለውን የአየር መጠንና እዳሪን ያጣራሉ፣ ኦክስጅን ያመነጫሉ፣ ለሌሎች አዝርእት ማዳባሪያ ይሆናሉ ፣ ራሳቸውም ምግብ ያመርታሉ።

ተክሌ የኋላ፣

ነጋሽ መሐመድ፣

►◄