የአቡነ ጴጥሮስ ሕያዉ ታሪክ | ባህል | DW | 11.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የአቡነ ጴጥሮስ ሕያዉ ታሪክ

«አዋጅ አዋጅ አዋጅ ጥር 29 ቀን 2008 ዓ.ም ሰምዓቱ ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ በቀደመ መካናቸው ላይ በክብር ይመለሳሉና የአዲስ አበባ እና የአካባቢው ህዝብ በሆታ እና በአጀብ አክብር ተብለሀል! » ሲሉ ዜናዉን ያበሰሩን የዝግጅታችን ተሳታፊና ተከታታይ፤ ያሪድ ሹመቴ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:38
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
16:38 ደቂቃ

የአቡነ ጴጥሮስ ሕያዉ ታሪክ


በአዲስ አበባ ከተማ ተጀመሮ በነበረዉ የቀላል ባቡር መሥመር ግንባታ ምክንያት ተነስቶ የነበረዉ የሰማዕቱና የአርበኛዉ የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት ዳግም በቦታዉ መመለስ በርካታ ኢትዮጵያዉያንን በተለይ የመዲናዋን ነዋሪዎች

አስፈንድቆአል።
አንጋፋዉ አርቲስት አብራር አብዶ «ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት» የተሰኘዉን የባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅንን ሙሉ ግጥም የአቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት ወደ ነበረበት ቦታዉ በተመለሰበት ሥነ-ስርዓት ላይም አቅርቦአል።
……
አዋጅ፣ የምሥራች ብዬ፣ የትብት ምግቤን ገድፌ
ከእናቴ ማኅፀን አርፌ
ከአፈርዋ አጥንቴን ቀፍፌ
ደሜን ከደሟ አጠንፍፌ
በሕፃ እግሬ ድሄባት፣ በህልም አክናፌ ከንፌ
እረኝነቴን በሰብሏ፣ በምድሯ ላብ አሳልፌ
ከጫጩት እና ከጥጃ፣ ከግልገል ጋር ተቃቅፌ …..
ያቺን ነው ኢትዮጵያ የምላት
እመ ብርሃን እረሳሻት?
አዛኚቱ እንዴት ብለሽ፣ ጥርሶችሽን ትነክሺባት?
የሐዉልቱ ወደ ቦታዉ መመለስ ደስታን ብቻ ሳይሆን የፈጠረዉ ሰማዕቱ በደማቀ ሥርዓት እንዲዘከሩም ነዉ፤ እድል የፈጠረዉ ያሉ ጥቂቶች አይደሉም። በእለቱ ዝግጅታችን የአቡነ ጴጥሮስ ሐዉልትን ወደነበረበት ስፍራ መመለስን ይዘን ታሪክን እንቃኛለን።


አዲስ አበባ የጀመረችዉ የቀላል ባቡር መሥመር ግንባታ ምክንያት ሚያዝያ 24 ቀን 2005 ዓ,ም ከቦታዉ የተነሳዉ የሰማዕቱና የአርበኛዉ የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት እንደሚመለስ ከተሰማ ከሳምንታት በፊት ከአዲስ አበባ ያሪድ ሹመቴ የተባሉ የዝግጅታችን ተከታታይ በፊስ ቡክ «አዋጅ አዋጅ አዋጅ ጥር 29 ቀን 2008 ዓ.ም ሰምዓቱ ብፁዕ አባታችን አቡነ ጴጥሮስ በቀደመ መካናቸው ላይ በክብር ይመለሳሉና የአዲስ አበባ እና የአካባቢው ህዝብ በሆታ እና በአጀብ አክብር ተብለሀል! » ሲሉ ዜናዉን ያበሰሩን። ታዋቂዉ ገጣሚ አበባዉ መላኩ የአቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት ወደ ቦታዉ መመለስን በተመለከተ እንዲህ ነዉ የገለፀልን።


« የሰማዕቱና የአርበኛዉ አባት የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት በክብር የመመለስ ሁኔታ፤ ብዙዉን የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ ነዋሪን በክብር ተግባራቸዉን እንዲያስታዉስ ነዉ ያደረገዉ። ከዚህ ባሻገር ደግሞ ምንም እንኳ ከልማት ጋር በተያያዘ ነዉ ሐዉልቱ የተነሳዉ ቢባልም፤ የአመላለሱ ሁኔታ የአርበኛዉን አባት ክብር በጠበቀ ሁኔታ ነበር። የአዲስ አበባ ሕዝብ በከፊል ግልብጥ ብሎ ያለ አስተባባሪ ወጥቶ ታላቅ የሆነ የአክብሮት መንፈስ ለአርበኛዉ አባት ሲሰጥ የነበረዉ። እና ይህንን ስንመለከት አቡነ ጴጥሮስ ምድሪቱ ለባዕድ እንዳትገዛ የገዘቱበት መንፈስ ዛሬም በአዲሱ ትዉልድ ልብ ዉስጥ ህያዉ ሆኖ መኖሩን ያመለክታል። እና እንኳንስ ሰዉ ምድሪቱም ጭምር ለፋሺስት ለባዕድ እንዳይገዛ ገዝቻለሁ ብለዉ ያሉት ቃል ምን ያህል ዘመን ተሻግሮ በትዉልዱ ልብ ዉስጥ እንደሳቸዉ ሐዉልት እንደቆመ ነዉ ያሳየን። በእድሜ ደረጃም ስንመለከት በዝግጅቱ ላይ በጣም ለጋ ወጣቶች፤ አዛዉንቶች፤ ጎልማሶች፤ እህቶ፤ች ወንድሞች የተገኙበት ነበር። ሐዉልቱን የማቆሙ ሥነ-ስርዓት ሂደት እንደ ትልቅ ክብረ በዓል ሆኖም ነበር አዲስ አበባ ላይ የታየዉ። ይህ በጣም ደስ የሚል ሃገራዊ እድገትንና የሃገርን መጠበቅ መንፈስ ለማደስ እድል የሚሰጥ ነገር ነዉ። »


አቡነ ጴጥሮስ የነጻነት ምልክት ናቸዉ ያሉን ዲያቆን ብርኃኑ አድማስ፤ በበኩላቸዉ እንደገለፁት
«አቡነ ጴጥሮስ በሕይወታቸዉ ዉስጥ ለእዉነት ብቻ የቆሙ ሰዉ መሆናቸዉን አሳይተዋል። እሳቸዉ እዉነትን መስክረዉ ከእዉነት ጋር ቆመዉ ለእዉነት የሞቱ እዉነተኛ መንፈሳዊ አባት ናቸዉ። የሐዉልቱ መልሶ መተከል ደግሞ በተለይ በኛ ዘመን ለእዉነት መቆምና መሞት ምን ያህል የሚከብር መሆኑን በወንጌል በቤተ-ክርስትያንም በዓለምም ለእዉነት የቆመ ምን ያህል ክብር የሚገባዉ መሆኑን የሚያሳይ ነዉና ለእዉነት የቆመ ሰዉ ለእዉነት የሞተ አንድ አባት ምስክር በኢትዮጵያ መዲና እንብርት ቦታ ላይ መቆሙ እንድንፅናና ይረዳናል። እና በዚህ ዘመን ለእዉነት የሚቆምን ምስክርን ከማቆም በላይ አስደሳች ነገር የለም። እሳቸዉ ለእዉነት እንደሞቱ አሁን ሐዉልታቸዉም እዉነት ሲመሰክር ይኖራል። ሰዎችንም ወደ እዉነት ሲጠራ ይኖራል። ለሁላችንም ደግሞ ማዳኛ ወይም ምስክር ይሆነናል። ማዳኛ ማለት የሚያዳኝብን የሚወቅሰን ለምን ለእዉነት አትቆምም የሚለን ስለሆነ እጅግ በልዩ ስሜት እመለከተዋለሁ ደስም ብሎኛል»
ስለጣልያን ወረራ በቅርቡ በእንጊዚዘኛ መጽሐፍ ያሳተሙት ቀሲስ ዶክተር ምክረስላሴ ገ/አማኑኤል፤ ለአቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት ወደ ቦታዉ መመለስ የተደረገዉ ዝግጅት ሲያንሳቸዉ ነዉ ሲሉ ነበር የተናገሩት።
« አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ጀግና፤ የኢትዮጵያ አባት ናቸዉ። የእሳቸዉ ሐዉልት ከቦታዉ በተነሳ ጊዜ ሕዝቡ ሁሉ ቅር ብሎት ነበር። ነገር ግን አሁን ሁሉ ሰዉ በመመለሱ በጣም በጣም ነዉ የተደሰተዉ። ደግሞ በፊት ከነበረዉ ከፍ ብሎ በመተከሉ ሁሉ ሰዉ ተደስቶአል፤ በእዉነቱ ማናቸዉንም ኢትዮጵያዊ የሚያስደስት ነገር ነዉ። ሐዉልቱ ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነዉ። ለኢትዮጵያ ህልዉና፤ ለኢትዮጵያ አንድነት የተጋደሉ ስለሆኑ ሐዉልቱ የሳቸዉን አርአያ መከተል እንደሚገባ የሚሳይ ነዉ ብዬ ነዉ የማስበዉ። የሐዉልት ጥቅሙም ዋና ነገር ይህ ነዉ»


በአዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ ባሉ ሐዉልቶችና ቅርጾች ዙርያ ለስምንት ዓመታት ጥናት ማድረጋቸዉን የነገሩን በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን ወደ ዓለም አቀፍ የቅርስ ማኅደር የሚገቡ የኢትዮጵያ የቅርስ አስተዳደር ሰነድ ዝግጅት ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ኃይለመለኮት አግዘዉ፤ ስለ አቡነ ጴጥሮስ ታሪክ በዝርዝር ገልጸዉልናል። የአቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት በአሁኑ ወቅት በፊቼ አንድ ሌላ ደግሞ በአዲስ አበባ ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስትያን እንደሚገኝ ገልጸዉልናል።
በሰሙን አሜሪካ ነዋሪ የሆኑትና በዓለም አቀፉ ኅብረት ለፍትህ የኢትዮጵያ ጉዳይ ተጠሪ አቶ ኪዳኔ አለማየሁ፤ የአቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት ቦታዉ ላይ ሲመለስ አዲስ አበባ ዉስጥ ነበሩ።
« ከዚህ ቀደም የአቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት ከቦታዉ ሲነሳ አንድ ጽሑፍ በይፋ እንዲወጣ አድርጌ ነበር። ጽሑፉ «ያልተመለሱ ጥያቄዎች » በሚል ርዕስ ነበረዉ፤ በጽሑፉ የአቡነ ጴጥሮስ ሐዉልት በቀላሉ የሚገመት አለመሆኑን ነበር ለመጠቆም የሞከርኩት። አሁን ቦታዉ ተመልሶ የሐዉልቱን ምስል እንዳየሁት በጣም በሚያኮራ መንገድ እንደዉም በፊት ከነበረዉ

በተሻለ ተደርጎ ነዉና የቀረበዉ፤ እኔ በበኩሌ በጣም ነዉ ደስ ያለኝ። ያን ለፈፀሙት ሁሉ ምስጋና ማቅረብ እወዳለሁ። በዚህ አጋጣሚ ማንሳት የምፈልገዉ አቡነ ጴጥሮስ የተሰዉበት ፋሽስቶች ለፈፀሙት ከባድ የጦር ወንጀል ወደ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ የተጨፈጨፈበት፤ ከዝያ ዉስጥ አዲስ አበባ ዉስጥ ብቻ በሦስት ቀን፤ ሠላሳ ሺህ ሰዉ የተሰዋበት፤ በደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳት ጭምር የተጨፈጨፉበት፤ የሚያመላክት ምስል ስለሆነ በቀጣይ በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚከበረዉ የካቲት 12 እንደሚዘከር ተስፋ አደርጋለሁ።»
ሐዉልት ማለት ሰሌዳ ላይ የተጻፈ ታሪክ ነዉ። ወጣቱ ታሪክን የሚጠይቅበት የሚያነብበ ት ነዉ ሲል ገጣሚ አበባዉ መላኩ፤ በዝርዝር ገልጾልናል።
በኢትዮጵያ ቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን ወደ ዓለም አቀፍ የቅርስ ማኅደር የሚገቡ የኢትዮጵያ የቅርስ አስተዳደር ሰነድ ዝግጅት ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ኃይለመለኮት በበኩላቸዉ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ቦታዎች የተነሱ የታሪክ ማሳያ ሐዉልቶች ወደ ቦታቸዉ ሊመለሱና ታሪክን ሊመሰክሩ ለወጣቱ ሊነግሩ ይገባል፤ አደባባዮች የድርጅቶች ማስታወቅያ መለጠፍያ ከሚሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ስማቸዉ ሕያዉ የሆኑ ኢትዮጵያዉያን የሚወሱበት ሐዉልት ሊቆም ይገባል ሲሉ ተናግረዋል። በዝግጅቱ ላይ ቃለ ምልልስ የሰጡንን እያመሰገንን ፤ ሙሉዉን መሰናዶ የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ


ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic