የአማርኛ ቋንቋ በመንግሥታት ለዉጥ | ባህል | DW | 02.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የአማርኛ ቋንቋ በመንግሥታት ለዉጥ

« በአማርኛ ቋንቋ አጠቃቀም በጣም እያሳሳበ የሆነዉ ከሌላ ቋንቋ ጋር በተለይ ደግሞ ከእንጊሊዘኛ ጋር በማደባለቅ የሚነገረዉ አይነት ነዉ። ለምሳሌ በጣም አመሰግናለሁ ብሎ በጠራ አማርኛ መናገር ሲቻል አሁን አሁኑ « በጣም ታንኪዉ» ሲሉ ይሰማል። ሌላዉ በአማርኛ ቃላቶች መጨረሻ አላስፈላጊ ያልሆኑ ምዕላዶችን የሚጨምሩት አሳሳቢና አስቂኝም ናቸዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:37

የመንግሥታት ለዉጥና አማርኛችን

ለምሳሌ «በላሁትኝ፤ ጠጣሁትኝ፤ ሰጠሁትኝ፤ ልንገርህ ማለት ሲቻል፤ ልንገርክ፤ አየህ የሚለዉን አየክ፤ ደህና ነህ ከማለት ይልቅ ፤ደህና ነክ» ሲሉ ይደመጣል። ከዚሁ ጋር የሚያያዘዉ በአብዛኛዉ ወጣቶች ሲናገሩት የሚሰማዉ « ሲጀምር እንደዚህ ነዉ፤ ሲቀጥል እንደዚህ ነዉ፤ ሲሰልስ እያሉ ፤ በሚያሰለች አይነት አነጋገር ስልት ሲጠቀሙም ይሰማል።»

በደቡባዊ ጀርመን ባየር ግዛት በሙኒክ ከተማ በሚገኝ ዩንቨርስቲ በምርምር ሥራ ላይ የሚገኙት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በጥንታዊ ጽሑፎች ጥናት ረዳት ፕሮፊሰር አምሳሉ ተፈራ ከዶይቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ የተናገሩት ነዉ። ቋንቋ፤ የምንኖርበትን ዓለም መግለጫ መሳርያ እንደዉም በምንኖርበት ዓለም የመሥራያ መሳርያ ነዉ ሲሉ ይገልፁታል፤ የዘርፉ ባለሞያዎች። የሃገራት መንግስታቶች ሲለዋወጡ ብቻ ሳይሆን በአንድ ሃገር በማንኛዉም ጊዜ የፖለቲካ፤ የማኅበራዊ፤ የባህል፤ የኤኮኖሚ ለዉጦች ሲኖሩ አብረዉ የሚመጡት አዳዲስ አስተሳሰቦች፤ ቁሶችና፤ ከአዲስ የአኗኗር ዘይቤዎች ጋር አዳዲስ

ቃላቶችና አባባሎች እንደሚፈጠሩ፤ ብሎም በአሮጌዉ ስርዓት ይነገሩ የነበሩ ቃላቶችም ሆኑ አባባሎች እንደሚጠፉም ምሑራን ይገልፃሉ። እንድያም ሆኖ አዲስ ቃላት፤ እንዲሁም አባባሎች ሲፈጠሩ በባለሞያ ተመክሮበት፤ በእንጊሊዘኛ የሚገለፁ ቃላትም የአማርኛ አቻ ቃላት ተሰጥቶአቸዉ ጥቅም ላይ እንዲዉሉ የቋንቋ ምሑራን ያሳስባሉ።

የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች በተለይ አብዛኞች በከተማ የሚገኙት ሊቅ የሆኑ እየመሰላቸዉ አማርኛን ለእንጎዚዘኛ እየቀላቀሉ በመናገር ቋንቋዉን እያበላሹ ናቸዉ የሚሉ ትችቶች ይሰማሉ። ተናጋሪዎቹ ብቻ ሳይሆኑ አንዳንድ ተቋማት፤ ሆቴል ቤቶች ሁሉ ስያሜያቸዉን የሚሰጡት በእንጊሊዘኛ ነዉ። ከዚህ ሌላ መንግሥታት ሲቀያየሩ፤ አዲሱ መጭዉ መንግስት የሚያራምደዉ ፖለቲካ እንዲሁም ኤኮኖሚያዊ ሁኔታን የተከተለ አዳዲስ ቃላቶች፤ አባባሎች ሁሉ ይሰማሉ። ይህ ለምን ይሆን? በባሕር ዳር ዩንቨርስቲ የዐባይ የባህልና ልማት ጥናትና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉቀን አንዷለም፤ ቋንቋ ይላሉ፤

«ጠቅለል አድርገን ስናየዉ ቋንቋ የሚለወጠዉ በሁለት አይነት መንገድ ነዉ። የመጀመርያዉ መንስኤ ዉስጣዊ መንስኤ ይባላል፤ ሁለተኛዉ ዉጫዊ መንስኤ ይባላል። የዉስጣዊዉን መንስኤ ስናይ፤ ለምሳሌ ህጻናትና ወጣቶች አዳዲስ ፈጠራዎች መልካምድራዊ መሰናክሎች፤ ፍልሰት፤ ታዋቂ ግለሰቦች፤ የመሳሰሉት ነገሮች ቋንቋ እንዲለወጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። የህጻናት ቃላቶች ያየን እንደሆነ ፤ ለመናገር በሚያደርጉት ሙከራ ቃላቱን እየሸራረፉ መናገር ነዉ የሚችሉት፤ ይህ ሁኔታ በሌላዉ በአዋቂዉ ማኅበረሰብ ይወደድላቸዋል፤ ሌላዉ የቋንቋ ተናጋሪ ይህን ልክ እንደ ህጻናቱ፤ ለህጻኑ ባለዉ ፍቅር ፤ አነጋገራቸዉን የሚይዝበትም ክስተት አለ። ሌላዉ ወጣቶች የቴሌቭዥን ፕሮግራሞችን ፊልሞችን አዲስ ነገር የመያዝ ትልቅ አቅም ስላላቸዉ፤ ይህ ቋንቋዉ እንዲቀየር፤ አባባሎች እንዲለወጡ የሚያዳርግ ሌላዉ ምክንያት ነዉ። ቋንቋ መለወጥ ዋና ምክንያት በማኅበረሰብ ዘንድ የሚገኙ ታዋቂ ሰዎች ናቸዉ። እኛ ሃገር ላይ በብዛት፤ ለቋንቋ መለወጥ ወይም ለቋንቋ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ታዋቂ ሰዎች ናቸዉ። ለምሳሌ ጋዜጠኞች የሚናገሩትን ዓርፍተ ነገር ብዙዎች ይከተሉታል። ከመሪዎች አንፃር ያየን እንደሆነ እኛ ሃገር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን በምሳሌነት መዉሰድ እንችላለን። ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ አዳዲስ ቃላቶችን እየጨመሩ ሲናገሩ ይሰሙ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታዋቂ በመሆናቸዉ እሳቸዉ ንግግር ሲያደርጉ ሁሉም ሰዉ በጥሞና ስለሚሰማቸዉ ፤ ከንግግራቸዉ በኋላ የሳቸዉን አነጋገር ይዞ የመከተል ሁኔታ ታይቶአል። አንዳንዴ እየተተረጎሙ የሚመጡ ቃላትም ይሰሙ ነበር። ለምሳሌ እንደ «ሙስና» የሚለዉ ቃል፤ በርግጥ ሙስና ግዕዝ ነዉ፤ ጥፋት እንደማለት ነዉ። እነዚህ ቃላት በአዲስ በኅብረተሰቡ ዘንድ በብዛት የሚሰሙ ቃላቶች ናቸዉ። በቀድሞዉ ስርዓት ይነገሩ የነበሩት ለምሳሌ አብዮት « ለዉጥ ማለት ነዉ»፤ አድሃሪ፤ አደርባይነት የመሳሰሉት ቃላቶች፤ ከግዕዝ የተወሰዱ ናቸዉ። በአሁኑ ወቅት በብዛት የሚሰማ ቃል ህዳሴ ነዉ። ህዳሴ « አዲስ አደረገ» ኅብረተሰቡ በሰፊዉ እየተጠቀመበት ያለ ከግዕዝ የተወሰደ ቃል ነዉ።»

በኢትዮጵያ የሚደመጠዉን አዲሱን የአማረኛ አባባሎች ስናይ አንዳንድ ጊዜ ሆነ ተብሎ ባለዉ አስተዳደር የሚፈጠሩ ቃላትና በዝያን ወቅት ላይ የመደመጡ ብዙ ስያሜዎችን እናያለን ሲሉ የሚገልፁት፤ በደቡባዊ ጀርመን ባየር ግዛት በሙኒክ ከተማ በሚገኝ ዩንቨርስቲ በምርምር ሥራ ላይ የሚገኙት ዶ/ር አምሳሉ ተፈራ፤ ለምሳሌ ይላሉ ፤

«ለምሳሌ፤ ኢሕአዴግን ጨምሮ ባለፉት ሦስት ስርዓቶች የተለያዩ ቃላቶችን እናስታዉሳለን፤ አንዳንዶቹ አሁንም አሉ፤ አንዳንዶቹ በነበረዉ ቃል ሌላ ተተክቶ እናገኛለን። ለምሳሌ ቀድም ባለዉ በንጉሰ ነገስቱ ዘመን ጥቅም ላይ የነበሩ ቃላትን ስናይ በተለይ በተለይ ከማዕረግ ስሞች ጋርና ከአንዳንድ መጠሪያዎች ጋር ያሉ ቃላት፤ በአሁኑ ሰዓት ጨርሶ የማንጠቀምባቸዉና በመዛግብት፤ መጽሐፍ ላይ በጽሑፎች ላይ የምናገኛቸዉ ናቸዉ። ለምሳሌ የክብር ስሞች፤ የማዕረግ ስሞች የምንላቸዉ ተጠቃሽ ናቸዉ። ራስ፤ ቢትወደድ ፤ ደጃዝማች፤ ጸሐፊ ትዕዛዝ፤ የተሰኙት በቀድሞ ጊዜ የክብር ስሞች የነበሩ አሁን የማንጠቀምባቸዉ ናቸዉ። የዚያን ጊዜ ልጅ እገሌ ሲባል፤ የማዕረግ ስም ነበር። በዝያን ጊዜ ክቡር እገሌ ሲባል ስልጣን ላላቸዉ ሰዎች መጠርያ ይጠቀሙበት ነበር። በርግጥ ክቡር የሚለዉ የክብሮት መጠርያ በአሁኑም ዘመን አልፎ አልፎ ሲጠቀሙበት ይታያል። ከዚህ ሌላ ያኔ በንጉሰ ነገስቱ ዘመን ይጠቀሙበት የነበረና ህዝባዊ ቃላት የምንላቸዉ ፤ ለምሳሌ ግብር ማብላት ፤ ግብር ማስገባት፤ ጢሰኛ ፤ ከበርቴ የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸዉ። በኃላ በዘመነ ደርግ ስንሰማቸዉ የነበሩት፤ አድሃሪ፤ አቆርቋዥ ሰርቶ አደር፤ አብዮት፤ ነጭ ሽብር፤ ቀይ ሽብር፤ አብዮት ጠባቂ ፍርድ ሸንጎ ፤ የመሳሰሉት ቃላት በደርግ ዘመን የነበሩና ፤ በዝያ ወቅት ያ ስርዓተ ማኅበር ሲያራምዳቸዉ ከነበሩ አንጻር በየጊዜዉ የሚሰሙና ይነገሩ የነበሩ ቃላቶች ናቸዉ።

በደርግ ሥርዓት ልጅ ስለነበርኩ ያለዉን ነገር ብዙም መግለፅ አልችልም፤ በ«ኢሕአዴግ » ዘመን የሚገርሙኝ አባባሎች አሉ፤ ያሉ ያሉን፤ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሥነ-ልሳንና ፊሎጂ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፊሰር ደርብ አዶ ለምሳሌ ይላሉ፤

« በማኅበረሰናችን በአሁኑ ወቅት በጣም የሚገርሙኝ አባባሎች አሉ። ለምሳሌ አንድ ሰዉ ይሄን ነገር እየሰራሁ ነዉ፤ ከማለት ይልቅ «ይሄን ነገር እየሰራሁ ያለበት ሁኔታ ነዉ። ወይም ደግሞ ይሄን ነገር በመስራት ሂደት ላይ ነኝ» ይላል። በተለይ «እንደዚህ አይነት ሁኔታ ያለበት ሁኔታ ነዉ» የሚለዉ አነጋገር መድረክ ላይ ይሰማል። ተጨማሪ የመጡና ስርዓቱ የሚጠቀምባቸዉ ለምሳሌ «አደረጃጀት፤ አመራር፤ ኪራይ ሰብሳቢ፤ ልማታዊ፤ የቋንቋ ልማት፤ ልማታዊ ባለኃብት፤ ልማታዊ ነጋዴ» የመሳሰሉ ነገሮች በስፋት ሰዎች ሲጠቀሙባቸዉ ይሰማል። ሌላዉ «መዉሰድ» የሚለዉ ቃል እንዲህ ነዉ ብለን እንረዳለን፤ ይህን ነገር ለማስተካከል ማስታወሻችን ላይ ይዘናል ወይም እናሰምርበታለን ለሚለዉ፤ ይሄን ነገር የኛ ድክመት ነዉ ብለን እንወስዳለን፤ የሚለዉ አዲስ የቋንቋ አጠቃቀም ነዉ። «ማድረስ» የሚለዉ ቃል ትክክለኛ ፍችዉ መልክት ፤ ወይም እቃን ሰዉ ሲያደርስ ነዉ። አሁን ግን ሙዚቃም ወደ እናንተ እናደርሳለን፤ አስተያየቶቻችሁን መልሰን እናደርሳለን፤ ሰላምታችንንም እናደርሳለን ሲሉ በተለይ በራድዮና በቴሌቭዝን የሚሰሩ ጋዜጠኞች ሲናገሩ ሲጠቀሙበት ይደመጣል።

በዩኤስ አሜሪካ ነዋሪ የሆኑትና የዶቼ ቬለ የረጅም ጊዜ ተከታታይ አቶ ሳምሶን ደምሴ ተፈራ በቅርቡ ኢትዮጵያን ሲጎበኙ ያካፈሉን ትችት አዘል መልክት እንዲህ ይላል። የዘንድሮ አማርኛ መላ ቅጡ እየጠፋ ነው ልበል? «እንደምነክ ደህና ነክ?» ብሎ የጀመረ ሰላምታ፤ «ፋዘር ላርፋት» በሚል መኪና ጠባቂ ይቀጥላል፣ወደ ተቃጠሩበት ሬስቶራንት መኪና አቁመው ሲያመሩ የምግቤቱን ግንብ ተደግፎ የቆመ ወጣት ያልተበጠረ ጸጉሩን እያሻሽ «አባ ይመችሽ» ይላል። በግርምት ወደ ጉዳዮ ያመራሉ ምግብና መጠጥ ይታዘዛል፤አስተናጋጅዋ መለስ ቀለስ ትላለች ምግቡ መበላቱን አረጋግጣ ከፍ ባለ ድምጽ «ተመቻችሁ»? ትላለች። ነገሩ እንዴት ነው? ሬስቶራንት ነው ወይንስ ሶፋ መሸጫ ቤት ነው የገባነው ያሰኛል። እኔ በበኩሌ ቋንቋ ሰበራው «አልተመቸኝም» እናንተስ? ሲሉ በጥያቄ አስተያየታቸዉን ይቋጫሉ። ይህ አይነቱ የአነጋገር ዘይቤ ወይም አባባል ከየት እንደተነሳ ይቸግረኛል ያሉን ረዳት ፕሮፊሰር ደርብ አዶ

« ይሄ እኔ ከየት እንደመጣለ ማወቅ ይቸግረኛል። ምናልባትም ወደ ኋላ እየሄድን ፤ይመስለኛል። በሆነ ጊዜ በሚዲያ እንደዚህ አይነት አነጋገር ተሰምቶ መሆን አለበት እንጂ ከመሪት ተነስቶ ሰዉ ወደ ከ «ህ» ወደ «ክ» ይመጣል ብዬ አላስብም። ለምሳሌ እነ «ጰ» ወደ «ፐ» ኢትዮጵያ ከማለት ይልቅ ኢትዮፕያ እንደዉም በቴሌቭዝን ማስታወቅያ ጭምር ኢትዮጵያ ሳይሆን ኢትዮፕያ ተብሎ ሲነገር ሰምቻለሁ።

የቋንቋ ለዉጥ እንዲህ በአንድ ጊዜ የሚከሰት አይደለም ግን ኢትዮጵያ ላይ የታየዉ እጅግ በፈጣን ሁኔታ ነዉ ያሉን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሥነ-ለሳን መምህርና በቋንቋ ጥናት ጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዘላለም ልየዉ

« የቋንቋ መለወጥ የማንኛዉም ቋንቋ ክስተት ሆኖ እያለ፤ የቋንቋ ለዉጥ እንዲህ በአንድ፤ በሁለት፤ በሶስት፤,,, በአምስት አስርተ ዓመታት የሚመጣ አይደለም። ይህ በታሪካዊ ሥነ-ልሳን የቋንቋን ለዉጥን ለማየት ከተፈለገ ብዙ ዘመናት ብዙ ምዕተ ዓመታትን የሚጠይቅ ነዉ። በአማርና ቋንቋ ላይ ግን በዚህ ሁለትና ሦስት አስርተ ዓመታት የታየዉ በሚገርም አይነት ፍጥነት ነዉ። ይህን ለየት ያለ ክስተት በመሆኑ፤ አንድ ሰዉ ብቻ የሚያጠናዉ ሳይሆን በርከት ያሉ ሰዎች ሊያጠኑት የሚገባ ጉዳይ ነዉ።

ምሑራኑ በአማርኛ ቋንቋ ላይ በሚታዩት ግድፈቶችና አዳዲስ ቃላቶች አመጣጥ ላይ የሰጡን አስተያየት አላበቃም። በዚሁ ርዕስ ላይ የዶይቼ የአማርኛዉ ቋንቋ የፊስ ቡክ ተከታታዮች መተካካት ተሻለ፤ ልማቱ ፈጠነ ፤ ቦንድነህ አባይ፤ ኑሮ ዉድነህ የተባሉ አዳዲስ ስሞች ያልዋቸዉን ጨምሮ ፤ በደርግ ዘመን አድሀሪ፣ወንበዴ፣አብዬታዊ እርምጃ፣አንድነት፣ነፃ እርምጃ፣ጓዶች የተሰኙትን አይነቶች ሁሉ አሰባስበን፤ በምሑራኑን ሰፋ ያለ ማብራርያ አዋዝት በሚቀጥለዉ ሳምንት ይዘን እንቀርባለን። አስተያየታችሁን በፊስቡክ አስከምጡልን አልያም በአድራሻዎቻችን ላኩልን እያልን ሙሉ ቅንብሩን እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic