1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የናይጄሪያ መቶኛ ዓመት በዓል

የባሮሶ እና የአቻዎቻቸዉ ንግግር ከአቡጃ ሲንቆረቆር የሰሜን ምሥራቅ ናጄሪያ ግዛት የአዳማዋ መንደሮች ጥይትና ቦምብ ይዘንብባቸዉ ነበር።አስራ-ሰወስት ሰዎች ተገደሉ።አንድ የክርስቲያን መንፈሳዊ ትምሕርት ቤት ጋየናይጄሪያ የዛሬዉ ሰሜናዊና ደቡባዊ ግዛትዋ

የተዋሐዱበትን አንድ መቶኛ ዓመት በዓል ዛሬ አክብራ ዉላለች።የናጄሪያ ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት በበዓሉ ላይ የአርባ ሐገራት መራሕያነ-መንግሥታት እና ርዕሳነ-ብሔራት ተገኝተዋል።በሕዝብ ብዛትና በነዳጅ ሐብት ከሠሐራ-በተደደቡብ ከሚገኙት የአፍሪቃ ሐገራት የመጀመሪያዉን ሥፍራ የምትይዘዉ ናጄሪያ በዓሉን የምታከብረዉ በፅንፈኞች ጥቃት በርካታ ዜጎችዋ በሚገደሉበት ወቅት መሆኑ ነዉ።በበአሉ የተገኙት መሪዎች የናጄሪያ መንግሥት ከሸባሪዎች ጋር የሚያደርገዉን ትግል ለመደገፍ ቃል ገብተዋል።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አለዉ።


የአቡጃዉ በዓል ደማቅ፥ ድግስ ፌስታዉ የቀለጠ፥ እንግዶቹም ብዙ ናቸዉ።አርባ መሪዎች።በየተራ ከተናገሩት መሪዎች የአዉሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳት ሆሴ ማኑኤል ባሮሶ ንግግር የአስተናጋጃቸዉን የፕሬዝዳት ጉድላክ ጆናታንን ቀልብ ፈጥኖ የነካ ነበር።

«አክራሪነት፥ ፅንፈኝነት እና ጥላቻ በኛ ማሕበረሰብ ዘንድ ሥፍራ የላቸዉም።በጥብቅ እናወግዛቸዋለን። ናጄሪያ ከአሸባሪዎች ጋር በምታደርገዉ ትግል የአዉሮጳ ሕብረት ከጎኗ ይቆማል።»

የባሮሶ እና የአቻዎቻቸዉ ንግግር ከአቡጃ ሲንቆረቆር የሰሜን ምሥራቅ ናጄሪያ ግዛት የአዳማዋ መንደሮች ጥይትና ቦምብ ይዘንብባቸዉ ነበር።አስራ-ሰወስት ሰዎች ተገደሉ።አንድ የክርስቲያን መንፈሳዊ ትምሕርት ቤት ጋየ።ገዳይ-አጥፊ።«ቦኩ ሐራም።» ይላሉ የአካባቢዉ ነዋሪዎች።

የአክራሪዉ ሙስሊም ፅንፈኛ ቡድን የቦኩ ሐራም ታጣቂዎች ከትናንት በስቲያ ሌሊት አንድ አዳሪ ትምሕር ቤት ወርረዉ ሐምሳ-ዘጠኝ ተማሪዎች ገድለዉ ነበር።የፕሬዝዳት ጉድላክ ጆናታን መንግሥት ሰሜናዊ ናጄሪያ የሸመቀዉን ፅንፈኛ ቡድን ለማጥፋት በርካታ ጦር አዝምቷል።ባካባቢዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጓልም።ዘመቻ-አዋጁ ከፀና ብዙ ወራት ተቆጠሩ።ጥቃቱ ግን ባሰ እንጂ አልቀነሰም።ጆናታን ለእንግዶቻቸዉ እንደነገሩት ግን መንግሥታቸዉ ሽብርተኝነትን ለማስወገድ የሚያደርገዉን ጥረት አሁንም ይቀጥላል።

«የዓለም አቀፍ ችግር የሆነዉ አሸባሪነት አፍሪቃ፥ በርግጥም ናጄሪያም ተሰራጭቷል።ከአካባቢዉና ከዓለም አቀፉ ወዳጆቻችን ጋር በመሆን ሥልታዊና ወሳኝ እርምጃዎችን እንወስዳለን።ከሕዝባችን ጋር በመሆንም ግድያ እና ሽብርተኝነት ለማስቆም አበክረን እንጥራለን።»

በዛሬዉ ድግስ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የዛሬ መቶ ዓመት ናጄሪያን አንድ አድርጋ ቅኝ የገዛችዉ የብሪታን መሪ አይደሉም።የኔያዋ የብሪታንያ ተቀናቃኝ ቅኝ ገዢ የፈረንሳይ ፕሬዝዳት ፍራንሷ ኦላንድ ናቸዉ-በተቃራኒዉ።ኦላንድ ልክ እንደ ባሮሱ ሁሉ መንግሥታቸዉ ናጄሪያ የከፈተችዉን ፀረ-ሽብር ዘመቻ እንደሚያግዝ ቃል ገብተዋል።

የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸዉ አፍሪቃ ዉስጥ በየሥፍራዉ የሚታየዉ ደም አፋሳሽ ግጭትና ጠብ ዋና መንስኤ የማሕበረሰብ ተባለጥ ነዉ ባይ ናቸዉ።

«የአፍሪቃ ግጭቶች ባብዛኛዉ የሚመነጩት፥-የፍራንሲስ ስትዋርትን ሐገረግ ልዋስና፥-ከማሕበረሰብ የጎንዮሽ ተባለጥ ነዉ።የፖለቲካ፥ የምጣኔ ሐብት ይሁን የማሕበራዊ ተባለጥ።ይሕ ተባለጥ ግጭትን ይወልዳል።የግጭት መንሠራፋት ደግሞ የሠብአዊና የብሔራዊ ፀጥታ መታወክን ያስከትላል።»

ቦኮ ሐራም ናጄሪያ ዉስጥ ያፈነዳል። አሸባብ ሶማሊያ።ደቡብ ሱዳን፥ ማዕከላዊ አፍሪቃ ሪፐብሊክ፥ ኮርዶፋንም ሰዎች ያልቃሉ።መሪዎቹም አጥፊዎችን ለማጥፋት ይዝቱ-ይፎክራሉ።በዓሉ አለፈ።የፉከራ-ዛቻ መጠፋፋቱ ዑደቱ ግን ቢያንስ ለጊዜዉ እንደቀጠለ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic