የታደሰ እንግዳዉ አጭር የህይወት ታሪክ | ኢትዮጵያ | DW | 16.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የታደሰ እንግዳዉ አጭር የህይወት ታሪክ

የታደሰ እንግዳዉ ድንገተኛ ሞት እጅግ አሳዝኖናል፣ አስደንግጦናል። በመስሪያ ቤታችን በዶቸ ቬለ ራድዮ ቢሮ ባገኘነዉ መረጃ መሰረት ታደሰ እንግዳዉ መስከረም 14/ 1965 አም በጎንደር ክፍለ ሃገር ተወለደ። የመጀመርያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዝያዉ በጎንደር ካጠቃለለ በኋላ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተመረቀ።

default

ታደሰ እንግዳዉ

የታደሰ እንግዳዉ ድንገተኛ ሞት እጅግ አሳዝኖናል፣ አስደንግጦናል። በመስሪያ ቤታችን በዶቸ ቬለ ራድዮ ቢሮ ባገኘነዉ መረጃ መሰረት ታደሰ እንግዳዉ መስከረም 14/ 1965 አም በጎንደር ክፍለ ሃገር ተወለደ። የመጀመርያ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በዝያዉ በጎንደር ካጠቃለለ በኋላ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እንደ ጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር ከ 1991 እስከ 1995 ዓም በእንግሊዘኛ ስነ-ጽሁፍ እና በጋዜጠኝነት ትምህርት በባችለር ዲግሪ ተመረቀ። በ 1998 የኮንፒዉተር አጠቃቀም ጥናት ፥ በ 1999 ዓ,ም አቡጃ ኮትዱቮአር ላይ አፍሪቃ ዉስጥ የመገናኛ ብዙሃን ዲሞክራሲን ለመገንባት በሚኖራቸዉ ሚና ላይ ለሁለት ሳምንት በተደረገ ጥናት ተሳትፎአል። በ2001 በናሚቢያ ዊንድሆክ ላይ በምርምር ጋዜጠኝነት በተደረገ ስልጠና ተሳትፎአል የአለም ባንክ ተቋም በጎርጎረሳዉያኑ 2003 ዓም የልማት ትምህርት ኔትዎርክ ስልጠና ላይ ተገኝቶ ልዩ ምስክር ወረቀትን ተቀብሎአል።
በጎርጎረሳዉያኑ 2004 ዓ,ም በዶቼ ቬለ የራድዮ ጣብያ የአዲስ አበባ ዘጋቢ ሆኖ ከመቀጠሩ በፊት በተለያዩ ጋዜጣዎች በአምደኝነት፣ በአድማስ ኮሌጅ የህዝብ ግንኙነት መምሪያ ሃላፊ፣ የፍኖተ አድማስ ወርሃዊ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ በካቶሊክ ካቴድራል የወንዶች ትምህርት ቤት የአንጊሊዘኛ ቋንቋ መምህር በመሆን አገልግሎአል። በፎቶግራፍ አንሽነት እና በፊልም ዝግጅት ስራም በዩኒ ብሪ ፊልም ማምረቻ ማዕከል ትልቅ የወዳጅነት መንፈስን እና ተባባሪነትን ያሟላ አስተዋጾ ማድረጉን የሚያመለክት ምስክር ወረቀትን ተቀብሎአል። ታደሰ እንግዳዉ ዶቼ ቬለ ራድዮን ከጎርጎረሳዉያኑ 2004 ዓም ጀምሮ ፣ ሳይደክም በልበ ቀናነት፣ ተባባሪነት እና ቆራጥነት ሲዘግብ ቆይቶአል።

ታዴ በሚል ቁልምጫ የምንጠራዉ ባልደረቦቹ ከዚህ አለም በሞት መለየቱን የሰማነዉ ትናንት አመሻሹ ላይ ከአዲስ አበባ በደረሰን የኢሜል መልክት ነበር። መልክቱ እዉነት መሆኑ ሁላችንንም አጠራጥሮናል። ስለደረሰዉ ሃዘንም ለመናገር ቃላቶች ጠፍነዉናል። የዶቼ ቬለ የአማረኛዉ ክፍል ዋና ተጠሪ ሉድገር ሻ ዶምስኪ በታደሰ እንግዳዉ በድንገት ከዚህ አለም በሞት መለየት እጅግ አዝነዋል፣ የሃዘን መግለጫም አስተላልፈዋል«አንዳንዴ ለጋዜጠኞችም ገላጭ ቃላት የሚያጥርበት አጋጣሚ ይከሠታል።በአሳዛኝ ሁኔታ በሞት የተለየን የታደሰ ሁኔታም ይኸዉ ነዉ።እዚህ በቦን የምንገኝ የዶቼ-ቬለ፤ ሰራተኞችም ሆኑ በአለም ዙርያ ያሉት ባልደረቦቹ በደረሰዉ ሃዘን እጅግ ደንግጠናል። ሃዘናችን ለታደሰ ቤተሰቦች፤ ወንድ ልጃቸዉን ላጡት ቤተሰቦቹ፣ ባልዋን ላጣችዉ ባለቤቱ እና በጣም ጥሩ አባትን ላጡት ልጆቹ መግለጽ እንወዳለን።
ባለፈዉ አርብ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአሸባሪነት ስለ ተከሰሱትን ጋዜጠኞችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ ብይን ማስተላለፉን የሚያመለክተዉን ዘገባ ከሰራ በኋላ በመጭዉ ሳምንት ስለሚሰራዉ ዘገባ ከታደሰ ጋር ተነጋግረን ነበር። እሁድ ማለዳ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ በአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ዘገባ ለመላክም ዝግጅት ላይ ነበር።

ታደሰ ምሳሌ የሚሆን ሁልግዜም በንቃት እና በትጋት በመስራት የተሻለች ኢትዮጵያን ለማየት የሚጥር ጋዜጠኛ እንደሆን እስታዉሳለሁ። የጋዜጠኝነት ስነ-ምግባሩም በአንድ ወገን ሳይሆን ሁልግዜ ሚዛናዊ በመሆን ከሁለት ወገን እንዲያዳምጥ አድርጎታል። ታደሰ በፖለቲካዉ በኢኮነሚዉ እና በማህበራዊ ጉዳዮች እዉቀት እንደ ጋዜጠኝነት ሞያዉ ከፍተኛ ፋላጎትና ችሎታን የተካነና ለአድማጮቹ በሚገባ ሁኔታ የሚዘግብ ነበር። ታደሰ ፈጣን እና ወጣት ጋዜጠኛ ስለነበር ድንገተኛ ሞቱ እጅግ አሳዛኝ ያደርገዋል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በጸረ ሽብር ህግጋት ከለላ ርጅም ግዜ እስራት በሚቀጡበት በአሁኑ ወቅት የባለስልጣናትን ሃይል እና ሙስና በሁሉም ደረጃ የሚያጋልጥ ደፋርና ቆራጥ ጋዜጠኛ አስፈላጊ በመሆኑ ነዉ።

ታደሰ- ምን ግዜም አንተን እና ቤተሰቦችህን አንረሳም። ምንግዜም በክብር ስናስታዉስህ እንኖራለን»
ታደሰ እንግዳዉ ባለፈዉ አርብ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያስቻለዉን ብይን በማስመልከት የቃለ ምልልስ ዘገባን በስልክ ሰጥቶን፣ ወንድሙን ለማስመረቅ ወደ አዋሳ እንደሚሄድ እንዲሁም የአባቱን 76ኛ የትዉልድ ቀን ከቤተሰቡ ጋር እንድሚያከብር ገልጾልን ነበር። የመጨረሻዉን ድምፁን ዘገባዉን የተወልን

የታደሰ እንግዳዉ የወንድሙ ምርቃት የአባቱ የልደት ቀን ድርብ ደስታን፣ለማክበር በችኮላ ላይ መሆኑን የነገርን ፣ ወንድሙን አስመርቆ ጉዳዩን ጨርሶ አዲስ አበባ በተሰየመዉ በአፍሪቃ መንግሥታት መሪዎች ጉባዔ መጠናቀቅያ ላይ ተገኝቶ ዘገባዉን ሊያስደምጠን እቅድ ይዞ ነበር። በግዜዉና በቦታዉ ተገኝቶ ለአድማጮቹ ሚዛናዊ ዘገባዉን በሰአቱ ያደርስልን የነበረዉ ታዴ ዛሪ አደጋ ገጠመዉና ቃል የገባዉን ሳይፈጽምልን ቀረ። ታደሰ እንግዳዉ የጋዜጠኝነት ተግባር ቀላል ባልሆነባት ኢትዮጵያ በደፋርነት፣ ሚዛናዊ ዘገባዉን ለህዝብ ያደርስ ነበር። በአዉዳመትም መጀመርያ ለህዝቡ በጆሮዉ የሚያደርሰዉ ሰርቶ ነበር የማታ ማታ ቤቱ ከቤተሰቡ ጋር በአልን የሚያከብረዉ። ታደሰ እንግዳዉ በዘጋቢነት ከኢትዮጵያ ካስተላለፈልን ስራዎች መካከል የስፖርት የፖለቲካ የመዝናኛ የሃይማኖት ባጠቃላይ የማህብረሰቡን ወቅታዊ ጉዳዮች ይዳስሳል፤ ከነዚህ በጣም በጥቂቱ ለትዉስታ «ያድምጡ»

Tadesse Engidaw

ታደሰ እንግዳዉ በጀርመን ጉብኝት ላይ


ታደሰ በዚህ ስራዉ ላይመለስ በድንገት ተለየን። ታደሰ እንግዳዉ እንደ ጋዜጠኛ ሁለገብ ሚዛናዊ ደፋር እና አገር ወዳድ እንደ ጓደኛ ታዛዥ አክባሪ ፣ እንደ አባት ልጆቹን ቤተሰቡን አፍቃሪ ታማኝ ነበር ። ታደሰ ሃምሌ 8/ 2004 አመተ ምህረት ማለዳ በደረሰበት የመኪና አደጋ በሰላሳ ዘጠኝ አመቱ ከዚህ አለም በሞት ተለየ። መጽናናትን ለባለቤቱ ለልጆቹ ለቤተሰቡና ለዘመድ ጓደኞቹ እንመኛለን።

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሀመድ