1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የተመድ ማዕቀብ እና ሰሜን ኮርያ

ሰሜን ኮርያ ላይ አዲስ ማዕቀብ በሙሉ ድምፅ ያሳለፈዉ የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት፤ የቦለስቲክ ሚሳኤል መርሃግብሯን ባስቸኳይ እስካላቆመች ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል አሳስቧል። ማዕቀቡ የሰሜን ኮርያ የጨርቅ ምርቶቿን ከገበያ ዉጭ የሚያደርግ ሲሆን፤ ለእሷም ድፍድፍም ሆነ የተጣራ የነዳጅ ዘይት ከተወሰነ መጠን በላይ ማስገባትን ይከለክላል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:37

በዉጭ የሚሠሩ የሰሜን ኮርያ ዜጎች የሥራ ዕድል፤

 

እንዲያም ሆኖ የፀጥታዉ ምክር ቤት ዲፕሎማሲያዊዉ ጥረት እንዲቀጥልም አሳስቧል። ማዕቀቡ ሲረቀቅ ዩናይትድ ስቴትስ ወደሰሜን ኮርያ የነዳጅ ዘይት ፈፅሞ እንዳይገባ ነበር ሃሳብ ያቀረበችዉ። በማዕቀቡ መሠረት ግን የድርጅቱ አባል ሃገራት ለፒዮንግያንግ የተፈጥሮ ጋዝም ሆነ ፔትሮሊየም ለመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት ከ500,000 በርሜል በላይ ማቅረብም ሆነ መሸጥ አይችሉም በማለት መጠኑን ቀንሷል። ለ12 ወራትም ከ2 ሚሊየን በርሜል በላይ ማቅረብን አግዷል። ሰሜን ኮርያ በዓመት 4,5 ሚሊየን በርሜል የተጣራ የፔትሮሊየም ምርት፤ ድፍድፉን ደግሞ 4 ሚሊየን በርሜል እንደምታስገባ ነዉ የተነገረዉ። ከዚህም ሌላ ማዕቀቡ በውጭ ሃገራት የሚሠሩ እና ለሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገቡ ዜጎቿ የሥራ ፈቃድ እንዳይታደስላቸዉ፤ እነሱን ቀጥረዉ የሚያሠሩ ሃገራትም የሥራ ውላቸዉ የሚያበቃበትን ጊዜ እንዲያሳዉቁ ሁሉ በፀጥታዉ ምክር ቤት ተደንግጓል።

ይህ ባለፈዉ ነሐሴ 28 2009ዓ,ም ፒዮንግያንግ ላካሄደችዉና አደገኛ ለተባለዉ ስድስተኛዉ የኒኩሊየር ሙከራ የተጣለባት ማዕቀብ የወዳጆቿን የሩሲያን እና የቻይናን ይሁንታ ያገኘ ነው። ከጎርጎሮሳዊዉ 2006ዓ,ም ጀምሮ ማዕቀብ የሚጣልባት ሰሜን ኮርያ ለዘጠነኛ ጊዜ ማዕቀብ ቢጣልባትም ያስከተለዉ ለዉጥ እንደሌለ ነዉ የሚነገረዉ። በውጭ ሀገር ሥራ እየሠሩ በሚገኙ የሰሜን ኮርያ ዜጎች ላይ የተጣለዉ የሥራ ፈቃድ ያለማደሱ ማዕቀብ ግን ምናልባት የኪም ዮንግ ዑን መንግሥት ክፉኛ የሚፈልገዉ የውጭ ምንዛሪ ገቢዉ ላይ ችግር ሊያስከትል ይችል ይሆናል የሚል ግምት አለ። ምንም እንኳን ሰሜን ኮርያ ዜጎቿን ወደሌሎች ሃገራት ለሥራ መላኳ ቢታወቅም ቁጥራቸዉ ይህን ያህል ነዉ ለማለት ተጨባጭ መረጃ እንደሌለ ነዉ የሚታመነዉ። የተመድ በበኩሉ ባርነት አከል ባለዉ የሥራ ሁኔታ ከ35 ሺህ እስከ 100ሺህ የሚገመቱ ሰሜን ኮርያዉያን ቻይና እና ሩሲያ ውስጥ ለሥራ መሰማራታቸዉን ያመለክታል። በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዉ፤ ወይም በእንጨት ሥራ ዘርፍ፣ ገሚሱም በማዕድን ማውጣት እና በግብርና ጭምር ሳይሠማሩ እንዳልቀሩም ይዘረዝራል። በተሠማሩበት ሥራ ላይም በቀን እስከ 12 ሰዓታት በሰሜን ኮርያ የስለላ ኃይላት ክትትል ሥር ሆነዉ ለመሥራት እንደሚገደዱም ከዚያ አምልጠዉ የሚፈለጉ ዜጎች ማጋለጣቸዉንም ያመለክታል። የሠሩበትን ደመወዛቸዉንም አብዛኛዉን እንደማያዩት እና በፒዮንግያንግ መንግሥት እንደሚሰበሰብም መናገራቸዉን ይገልጻል። እንደመንግሥታቱ ድርጅት ግምትም ሰሜን ኮርያ  በሰዉ ሀገር ለሥራ ካሰማራቻቸዉ ዜጎቿ በዓመት እስከ 2,3 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ትሰበስባለች።

 ከዚህ ገንዘብ ገሚሱ ደግሞ የሚገኘዉ ከአዉሮጳ ኅብረት  ነዉ። የሰሜን ኮርያ ዜጎች በተለያዩ የኅብረቱ አባል ሃገራት ተቀጥረዉ ይሠራሉ። ባለፈዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2016 አንድ የኔዘርላንድ ዩኒቨርሲቲ ይህን የተመለከተ ጥናት ይፋ አድርጓል። ጥናቱ እንደሚለዉም በወቅቱ አንድ ሺህ የሰሜን ኮርያ ዜጎች በተለይም በማልታ እና ፖላንድ ይገኛሉ። ከባድ እና ብዙ ጉልበት በሚጠይቁ እንደ የአበባ እርሻ፣ የመንገድ ግንባታ እና የመሳሰሉ ሥራዎች ላይ እንደተሰማሩ የተገለፀዉ ኮርያዉያን ውል እና የደሞዛቸዉ ጉዳይ ድርድር የሚወሰነዉ ደግሞ ንብረትነቱ የሰሜን ኮርያ በሆነ ድርጅት አማካኝነት መሆኑን ጥናቱ ዘርዝሯል። በዚህ መልኩ የተቀጠረ የሰሜን ኮርያ ዜጋ 100 ዩሮ በወር ካገኘ ዕድለኛ ነዉ። አብዛኞቹ በወር የሚጣልላቸዉ 50 ዩሮ ብቻ መሆኑን ነዉ የሚናገሩት። የዓለም የሠራተኞች ድርጅት ማለትም ILO እንዲህ ካሉት ሠራተኞች አስቀጣሪ ድርጅቶቹ በዓመት 30 ሺህ ዩሮ በማግኘት ይበዘብዛሉ ይላል። 

ጥናቱን ያዘጋጁት ኮርያዊዉ ፕሮፌሰር ሬምኮ ብሩከር አሁንም ከተባባሪዎቻቸዉ ጋር ቀጣይ ጥናት እያካሄዱ ነዉ። ብዙ ጥያቄዎች ዛሬም ክፍት ናቸዉ ይላሉ፤

«የአዉሮጳ ኅብረት የጣለዉ ማዕቀብ በዉጭ ሀገር በሚገኙ የሰሜን ኮርያ ሠራተኞች ላይ ለዉጥ ያመጣ ይሆን? ምክንያቱም እዚህ አዉሮጳ ዉስጥ በሚሠሩት የሰሜን ኮርያ ዜጎች ሰበብ የሚንቀሳቀስ ብዙ ገንዘብ አለ። በሃሳብ ደረጃ በኅብረቱ፤ በመንግሥታቱ ድርጅትም ሆነ በዩናይትድ ስቴትስ እንዲሁም በዓለም የሠራተኞች ድርጅት መካከል ትብብር ሊኖር ይገባል። እናም ከውጭ በሚገኘዉ እና የምናዉቀዉ ነገር ላይ ማዕቀብ ማድረግ እንችላለን። ከዚህም ሌላ ገና ምንነታቸዉን የማናዉቃቸዉ የገንዘብ እና የኤኮኖሚ ምንጮች ላይም ማዕቀብ መደረግ ይኖርበታል ከማለታችን በፊትም ማጥናት ይኖርብናል። እንደሚመስለኝ ሰሜን ኮርያ ከዉጭ በሥራ ገንዘብ የምታገኝባቸውን ስልቶች ገና ሙሉ በሙሉ አላወቅናቸዉም።»

መረጃ የማይገኝበት ዋናዉ ምክንያት ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት በዚህ ጉዳይ ዉስጥ ካሉ የኅብረቱ አባል ሃገራት ይህን በተመለከተ በቂ ማብራሪያ ማግኘት ስለሚያስቸግር ነዉ።

«የኅብረቱ አባል ሃገራት የማይተባበሩ ከሆነ ማዕቀቦች በወረቀት ላይ ብቻ የሚቀሩ ይሆናሉ። እናም ምንም የሚመጣ ለውጥ አይኖርም። አባል ሃገራት ካልተባበሩም ማዕቀቡ ዋጋ የለዉም።»

ባለፈዉ ሳምንት የአውሮጳ ኅብረት የበኩሉን ማዕቀብ እንደሚያጠብቅ ገልጿል። ሰሜን ኮርያ ግን የመንግሥታቱ ድርጅት ይህን መሰሉን ማዕቀብ እንደጣለባት ይፋ ካደረገ በኋላም ዳግም በጀመረችዉ የኒኩሊየር ሙከራዋ እንደምትገፋበት እየዛተች ነዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic