የቡርኪና ፋሶ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ | ይዘት | DW | 01.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ይዘት

የቡርኪና ፋሶ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ አሸናፊ

በቡርኪና ፋሶ ባለፈው እሁድ በተካሄደው አጠቃላይ ምርጫ በምህፃሩ «ኤም ፒ ፒ» በሚል መጠሪያ የሚታወቀው የመሻሻል የሕዝብ ንቅናቄ ፓርቲ እጩ ማርክ ሮኽ ክሪስቲያን ካቦሬ የፕሬዚደንታዊው ምርጫ አሸናፊ ሆኑ። ይህንን የሃገሪቱ ነፃ ብሔራዊ አስመራጭ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ባርተሌሚ ኬሬ ዛሬ አረጋገጠዋል።

« ካቦሬ ሮኽ ክሪስቲያን ማርክ አንድ ሚልዮን ስድስት መቶ ሰባ ሺህ፣ ማለትም 53,49 % የመራጩን ድምፅ አግኝተዋል። በምርጫው የተሳተፋችሁትን እጩዎች በሙሉም እንኳን ደስ አላችሁ እላለሁ። በምርጫ ዘመቻ ወቅት ባሳያችሁት ቅንነት፣ መቻቻል እና መከባበር የተነሳ እናንተም አሸናፊዎች ናችሁ። »

ካቦሬ በሃገሪቱ ከአራት አስርት ዓመት ገደማ በኋላ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡ የመጀመሪያው ፕሬዚደንት ናቸው። ከ27 ዓመታት አገዛዝ በኋላ ከአስራ ሶስት ወራት በፊት በሕዝብ ዓመፅ ከስልጣን በተወገዱት የቀድሞው የቡርኪና ፋሶ ፕሬዚደንት ብሌዝ ካምፓዎሬ መንግሥት ውስጥ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩ የ58 ዓመቱ ካቦሬ ለሃገራቸው የተሻለ የወደፊት እድል ለመፍጠር እንደሚሠሩ በፓርቲያቸው ጽሕፈት ቤት ለተሰበሰቡት ደጋፊዎቻቸው ቃል ገብተዋል። በምርጫው ዋነኛ ተፎካካሪያቸው የነበሩት እና 29,65% የመራጭ ድምፅ ያገኙት የመሻሻል እና ለውጥ ህብረት ፓርቲ እጩ የቀድሞው የገንዘብ ሚንስትር ዲያብሬ ሴፍሪን ሽንፈታቸውን በመቀበል ለአሸናፊው የደስታ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

«ባሌ ሲትዋያ» የተባለው የሕዝብ ንቅናቄ መሪ ስሞኪ ስዩሙ ፕሬዚደንት ሃገራቸውን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለማገልገል የገቡትን ቃል ካልጠበቁ ሕዝቡ እንደሚነሳባቸው አስጠንቅቀዋል።

«ዴሞክራሲያዊ ደንቦችን ካልተከተሉ በብሌዝ ካምፓዎሬ ላይ የደረሰው ዓይነት ዕጣ ይጠብቃቸዋል። የስልጣን ዘመናቸውን መጨረስ አይችሉም። ደንቦቹን አንዴ፣ ሁለቴ ላይከተሉ ይችሉ ይሆናል በሶስተኛው ግን በሕዝብ ግፊት እናስወጣቸዋልን። የሚሠሩት ስህተት እየበዛ በሄደ ቁጥር ስልጣን ላይ እንዳይቆዩ ለማካላከል ሕዝቡ በአንፃራቸው እንዲነሳ እንቀሰቅሳለን።»

የሀገሪቱ ነፃ ብሔራዊ አስመራጭ ኮሚሽን ፕሬዚደንት ባርተሌሚ ኬሬ በ45 የቡርኪና ፋሶ ግዛቶች ሰፊ የመራጭ ተሳትፎ የታየበት አጠቃላዩ ምርጫ በአንዳንድ ቦታዎች ከታዩ ያልተስተካከሉ አሠራሮች በስተቀር በመልካም ሁኔታ መካሄዱን ገልጸዋል።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ