የበጎ ፈቃድ የኤቦላ ተዋጊ ጀግኖች | ጤና እና አካባቢ | DW | 23.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የበጎ ፈቃድ የኤቦላ ተዋጊ ጀግኖች

ምዕራብ አፍሪቃ ዉስጥ ከአንድ ዓመት በፊት የተቀሰቀሰዉ የኤቦላ ወረርሽኝ ከ11ሺህ በላይ ሕይወት ሲቀጥፍ፤ 27ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ በተሐዋሲዉ ተይዘዋል። ስለበሽታዉ መዛመትና ስላደረሰዉ ጉዳት ብዙ ቢወራም የራሳቸዉን ሕይወት ለአደጋ አጋልጠዉ ሰዎችን ለመርዳት ስተሰማሩ የበጎ ፈቃድ ሠራተኞች ብዙም አልተነገረም።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ፍሪታዉን ዉስጥ ሁለት ሰዎች አዲስ በኤቦላ ተሐዋሲ መያዛቸዉ መረጋገጡ ሴራሊሆን በተለይም ዋና ከተማዋ ከኤቦላ ነፃ ሆናለች የሚለዉን ግምት ዉድቅ ያደረገ አጋጣሚ ነዉ የሆነዉ። በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ባለፈዉ ዓመት የተቀሰቀሰዉ የኤቦላ ወረርሽኝ 11 ሺ በላይ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ከእነዚህ መካከል አንድ ሶስተኛዉ ሴራሊዮን ዉስጥ የተከሰተ ነዉ። ላይቤሪያ ባለፈዉ ግንቦት ወር ነዉ ከኤቦላ ነፃ መሆኗ የተረጋገጠዉ። ጎረቤቶቿ ሴራሊዮንና ጊኒ ግን አሁንም ከተሐዋሲዉ ጋ እየታገሉ ነዉ። የሴራሊዮን የኤቦላ ምላሽ ሰጪ ማዕከል ቃል አቀባይ ፍሪታዉን ዉስጥ ተሐዋሲዉ ሲከሰት አካባቢዎችን ዘግቶ ለተወሰነ ጊዜ አግልሎ የማቆየቱ አሠራር ለተወሰኑ ሳምንታት አዲስ የተመዘገበ ታማሚ ባለመኖሩ ተዘግተዉ እንደነበር ይናገራሉ። በቅርቡ የተገኙት ሁለት አዲስ የኤቦላ ታማሚዎች እጅግ በተጨናነቀዉ ማጋዚን በተሰኘዉ የንፅሕና መጠበቂያ ስልቶች ባልተመቻቹበት ጎስቋላ መንደር ኗሪ በመሆናቸዉ ተመልሶ ያንን አስከፊ ጊዜ እንዳያመጣ ስጋታቸዉንም አልሸሸጉም። የታማሚዎች ቁጥር ቀነሰ ቢባልም ግን ወረርሽኙ የኅብረተሰቡን ሕይወት ማናጋቱ አልቀረም።

Sierra Leone Rotes Kreuz Haja Kargbo

ሃጃ ካርግቦ

ካለፈዉ ዓመት አንስቶ የኤቦላ ተሐዋሲ ሴራሊዮን ዉስጥ አሁንም መስፋፋቱ አልቀረም። እስካሁንም የ4,000 ሰዎችን ሕይወት አጥፍቷል። ከበሽታዉ ለተረፉትም ራሱ ኑሮዉ ከብዷል። አብዛኞቹ የኤቦላ ሰለባ የሆኑ ገበሬዎች የዐይን ብርሃን በማጣት፤ በጡንቻ ሕመም እንዲሁም በተመሳሳይ የሕመም ምልክቶች እየተሰቃዩ ነዉ። አብዛኞቹ ወዳጅ ዘመዶቻቸዉን በማጣታቸዉ ኑሯቸዉ ተመሰቃቅሷል፤ ብዙዎቹም ቤተሰቦቻቸዉን እንዴት መመገብ እንደሚችሉ ሁሉ መላዉ ጠፍቷቸዋል። በእነዚህ መካከል ደግሞ በአስደናቂ ሁኔታ ከገጠማቸዉ መከራ ወጥተዉ ሌሎችን ለመርዳት የሚጥሩ ሰዎች አሉ። ለምሳሌ ሃጃ ፋትማታ ካርግቦ አንዷ ናት። የ31ዓመቷ ወጣት በኤኮላ ተሐዋሲ ተይዛ ከበሽታዉ ድናለች። አሁን በተራዋ በበጎ ፈቃደኝነት ከቀይ መስቀል ጎን ተሰልፋ የበሽታዉን ሰለባዎች ለመርዳት ትንቀሳቀሳለች።

ሃጃ ካርግቦ እጆቿን በባልዲ ከተቀመጠዉ ዉኃ ወስዳ በሚገባ በመታጠብ ለሁሉም አሳየች። ወዲያዉ ወደፍሪታዉን ዉስጥ የወደሚገኘዉና ሁሉም ወደሚፈራዉ የኤቦላ ታማሚዎች ወደሚበዙበት ጎስቋላ መንገድ ገባች። ፖሊስ በሰማያዊ እና ነጭ ፕላስቲክ አካባቢዉን አጥሯል።

Sierra Leone Ebola

በኤቦላ የተጠረጠረ መንደር

ፖሊስ ከሚለዉ ምልክት ፊት ለፊት አንድ ወታደር ቆሟል። እዚያ አጠገብ በሚገኘዉ ቤት ያሉት ኗሪዎች በተሐዋሲዉ ከተያዙ ሰዎች ጋ በመገናኘታቸዉ ለጊዜ ለ21 ቀናት ተገልለዉ እየተጠበቁ ነዉ። ወደዚያ መግባት የሚፈቀድለት እንደ ሃጃ ያለ የቀይ መስቀል የበጎ ፈቃድ ሠራተኛ ብቻ ነዉ። እሷና ሌሎች ባልደረቦቿ እነዚህ ቤተሰቦች በየቀኑ ይጎበኛሉ። በኤቦላ የተያዘ ሰዉ የሚታይበት የህመም ምልክቶች እንዳሉ ያያሉ ይከታተላሉ። ሰዎቹንም ያረጋጋሉ። ሃጃ ከማንኛቸዉ በበለጠ ይህ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ጠንቅቃ ታዉቃለች።

«በኤቦላ በተያዝኩበት ወቅት ጥሩ ስሜት አልነበረኝም፤ በጣም አለቅስ ነበር። ወደማከሚያዉ ማዕከል ሲወስዱኝ በጣም ፈርቼ ነበር። ጥሩ ነገር አልተሰማኝም ነበር። ነገር ግን የቀይ መስቀል ባልደረቦች ባደረጉልን ድጋፍ የተሻለ ደህና ስሜት ይሰማኝ ጀመር።»

እሷ ገብታ የምትጎበኛቸዉ ሰዎች እጅግ ተቆጥተዋል። ለ21 ቀናት ቤት ዉስጥ ተገልለዉ መቆየታቸዉ ሳያንስ በተሐዋሲዉ ተለክፈ ይሆናል የሚለዉ ጥርጣሩ አበሳጭቷቸዋል። ሃጃ ፈገግ ብላ የታጠረዉን ላስቲክ አልፋ ወደሰዎቹ ተጠግታ ታነጋግራቸዉ ጀመር። የበጎ ፈቃደኞቹ ቡድን መሪ ራማታ ጃሎ በቅርብ ርቀት ታስተዉላታለች። ራሷ ከኤቦላ ተሐዋሲ ድና አሁን ሌሎች ለመርዳትና ለማበረታታት በፈቃደኝነት በምታገለግለዉ ሃጃ ተግባር የኮራች ይመስላል። ከወራት በፊት ወደእሷ ቡድን የገባችዉ የኤቦላ ታማሚ የነበረችዉ ሃጃን በፈገግታ እየተመለከት እንዲህ አለች።

«በየሁለት ቀኑ ወደቤቷ እየሄድኩ እጎበኛት ነበር። ያኔ ስመለከታት፤ በሄድኩኝ ቁጥር ብቻዋን ወይ መሬት ላይ ተንጋላ ወይም ቁጭ ብላ ከማንም ሳትነጋገር አያት ነበር። ጥያቄዎችን መጠየቅ ጀመርኩ፤ ጠየኩ፤ እንደገናም ጠየኩ፤ እናትየዉ ምንም ነገር አትሠራም ደስተኛም አይደለችም ብለዉ እስኪነግሩኝ ድረስ ጠየኩ። ሳሙናና የመሳሰሉ ነገሮችን እንኳ መግዣ የሚሆናት ምንም ገንዘብ አልነበራትም። ከዚያም እሺ ቆይ እናስብበታለን አልኩኝ።»

አሁን ሃጃ ምንም ጊዜ የላትም። ለዛሬ የቀይ መስቀል ስራዋ አብቅቷል። ማንጎዎቹን ከፌስታል ዉስጥ አወጣችና ከቤታቸዉ በራፍ በሚገኝ መደርደሪያ ላይ ዘረጋቻቸዉ። ገንዘብ ለማግኘት ስትል ብቻም አይደለም የምትሸጣቸዉ። የቤታቸዉ ዋነኛዉ አስተዳዳሪ ባሏን የኤቦላ ተሐዋሲ ነጥቋታል። የሰባት ወር የነበረዉን ሁለተኛ ልጇንም እንዲሁ በዚሁ ወረርሽኝ አጥታለች። አሁን አዛዉንት እናቷንና የአምስት ዓመት ብቸኛ ልጇን ለመመገብ በቂ ገንዘብ ማግኘት ይኖርባታል። በሥራ መወጠሯ ሃዘኗን ቀስ በቀስ ሊያስረሳት ይችላል። አንዳንዴም ከሴራሊዮን ራቅ ብላ የተሻለ ሕይወት ለመምራት ታልማለች።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic