የቅማንት ህዝበ ውሳኔ ውጤት በየምርጫ ጣቢያው እየተገለፀ ነው | ኢትዮጵያ | DW | 18.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

የቅማንት ህዝበ ውሳኔ ውጤት በየምርጫ ጣቢያው እየተገለፀ ነው

በ8 ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ የአማራም የቅማንትም ህዝቦች ናቸው ድምጽ የሰጡት ።የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደሚለው ከ 23 ሺህ 283 ተመዝጋቢዎች መካከል 20 ሺህ 824ቱ ድምጻቸውን ሰጥተዋል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:16

የቅማንት ህዝበ ውሳኔ

በቅማንት ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ላይ ትናንት የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ ውጤት በየምርጫ ጣቢያዎች  ህዝብ እንዲያውቀው መደረጉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ዛሬ አስታወቀ ። ሆኖም አጠቃላዩ ውጤት የህዝበ ውሳኔውን ዘገባ ቦርዱ ለኢትዮጵያ ፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ ከፀደቀ በኋላ ይፋ እንደሚደረግ ቦርዱ ለዶቼቬለ ገልጿል። በሌላ በኩል ህዝበ ውሳኔ ታቅዶ ባልተካሄደባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አማሮች ይፈጸምብናል ባሉት ዛቻ እና ማስፈራሪያ ወደ ጎንደር እየተሰደዱ መሆኑን ለዶቼቬለ ተናግረዋል። ስለ ተባለው ማስፈራሪያ እና ዛቻ መረጃ የለንም ያለው የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ችግር ካለም በአካባቢው አመራር ሊስተካከል ይችላል ሲል ለዶቼቬለ ገልጿል። ኂሩት መለሰ

የቅማንት ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ላይ ትናንት ህዝበ ውሳኔ የተካሄደው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ 8 ቀበሌዎች ውስጥ ነው። በነዚሁ ቀበሌዎች ስር ባሉ 24 የምርጫ ጣቢያዎች የተሰጠው ድምጽ ተቆጥሮ ውጤቱ በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች ዛሬ ይፋ ተደርጓል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንደሚለው ግን አጠቃላዩን ውጤት አሁን አያሳውቅም። የቦርዱ ጸሐፊ እና የጽህፈት ቤቱ ዋና ሀላፊ አቶ ነጋ ዱፌሳ ምክንያቱን ለዶቼቬለ አስረድተዋል።

አቶ ነጋ የህዝበ ውሳኔው ሂደት በጣም የተረጋጋ እንደነበር ገልጸዋል። የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ህዝበ ውሳኔው  በሠላማዊ መንገድ ነው የተካሄደው ሲሉ ለዶቼቬለ ተናግረዋል።የህዝበ ውሳኔውን ሂደት ለመታዘብ ከሦስት ክልሎች እና ከአዲስ አበባ ገለልተኛ የተባሉ ተወካዮች ተገኝተው እንደነበረ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህዝበ ውሳኔውን የመታዘብ እድል አልተሰጠንም ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል። ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት አቶ ነጋ የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል።

አቶ ነጋ እንዳሉት በ8 ቱ ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ የአማራም እና የቅማንትም ህዝቦች ናቸው ድምጽ የሰጡት ። ድምጽ ለመስጠት ከተመዘገቡት 23 ሺህ 283 ሰዎች መካከል 20 ሺህ 824ቱ ሰዎች ድምጻቸውን መስጠታቸውን አቶ ነጋ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም በወጣው እቅድ የአማራ እና የቅማንት ህዝቦች ተቀላቅለው በሚኖሩባቸው 12 ቀበሌዎች ነበር ህዝበ ውሳኔው ሊካሄድ የታቀደው። ሆኖም የ4 ቱ ቀበሌዎች ህዝብ በጉዳዩ ላይ የበለጠ ውይይት እንዲካሄድ በመፈለጉ ውሳኔው እንዲዘገይ መደረጉን ምርጫ ቦርድ አስታውቀዋል። በነዚህ አካባቢዎች በተለይም በአይከል የሚገኙ አማሮች ሰዎችን አደራጅታችኋል እየተባሉ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ስለ ሚሰነዘርባቸው ወደ ጎንደር እንደተሰደዱ  ራሳቸውም የችግሩ ሰለባ መሆናቸው የተናገሩ አንድ ግለሰብ ለዶቼቬለ አስረድተዋል ። እኚሁ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሰው ዛቻ እና ማስፈራሪያው የሚሰነዘረው ከቅማንት ኮሚቴ  መሆኑን እና እስካሁን 43 ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጸዋል። ዶቼቬለ ስለ ጉዳዩ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁንን ጠይቆ የሚከተለውን መልስ ሰጥተዋል።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic