1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የእሳት ቃጠሎ በቂሊንጦ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 28 2008

ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግለትና ፖለቲከኞች በሚገኙበት የቂሊንጦ እስር ቤት የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ ቢያንስ 20 ሰዎች በጥይት ተመትተው እና ተረጋግጠው መሞታቸውን አዲስ ፎርቹን የተሰኘው ጋዜጣ በድረ-ገጽ እትሙ ዘገበ። ለመንግስት ቅርበት ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን የአንድ ሰው ሕይወት ማለፉንና «6 ሰዎች መጠነኛ ጉዳት» እንደደረሰባቸው ዘግበዋል።

https://p.dw.com/p/1JvOR
Karte Äthiopien englisch

የእሳት ቃጠሎ በቂሊንጦ

የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች በአደጋው 14 ሰዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው በማሕበራዊ መገናኛ አውታሮች ፅፈዋል። በእስር ቤቱ ቃጠሎ ሦስት የእሳት አደጋ መከላከያ ሰራተኞች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውም በፎርቹን ተዘግቧል። ጋዜጣው የእሳት ቃጠሎው «ለማምለጥ በተደረገ ጥረት» ሆን ተብሎ የተቀሰቀሰ መሆኑን ምንጮቼ ነግረውኛል ብሏል። ከሟቾቹ መካከል ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት በመከታተል ላይ የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ስለመኖራቸው እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የወንዶች ብቻ እስር ቤት ሲሆን ጉዳያቸው በፍርድ ቤት የሚታይ ተጠርጣሪዎች ይገኙበታል። ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የዐይን እማኝ የእሳት ቃጠሎው እንደደረሰ ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ እና ከእስረኞቹ የድረሱልን ጥሪ መስማታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

በአካባቢው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የፖሊስ እና የመከላከያ አባላት መምጣታቸውንም የዐይን እማኙ አክለው ተናግረዋል። በኦሮሚያ ክልል በተቀሰቀሰው ተቃውሞ እና የመብት ጥያቄ በሽብር የተከሰሱት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ዋና ጸሐፊ አቶ በቀለ ገርባ እና በርካታ የፓርቲው አባላት በዚሁ እስር ቤት እንደሚገኙ ይገለጣል።

በግል የፌስቡክ ገፃቸው በጻፉት ፅሑፍ የተከሰሱት የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ የሙስሊም መፍትኄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና በርካታ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች በቂሊንጦ እስር ቤት እንደሚገኙ እስር ቤቱን በቅርበት የሚያውቁ ሰዎች ተናግረዋል። በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በካባቢው ወደ ሚገኘው ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተሰምቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡን ያደረግንው ጥረት አልተሳካም።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ