የሼህ አላሙዲን እስር በሳዑዲ ቅምጥል ሆቴል | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 10.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የሼህ አላሙዲን እስር በሳዑዲ ቅምጥል ሆቴል

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በሙስና የጠረጠራቸዉን የተለያዩ የሀገሪቱ ልዑላን፤ ባለሥልጣናትን እና ነጋዴዎችን በቊጥጥር ስር ሲያውል ሼህ አል አሙዲንም ታስረዋል መባሉ የበርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች መነጋገሪያ ሆኗል። ዋነኛ ትኩረታችን ነው።

ሳዑዲ ዓረቢያ ከሙስና ጋር በተያያዘ በሚል በርካታ የሀገሪቱን ልዑላን እና ባለሥልጣናትን አስራለች።ከታሳሪዎቹ ሳዑዲ-አረቢያዊዉ-ኢትዮጵያዊዉ ቢለየነር ሼህ ሙሃመድ አልአሙዲም አሉበት መባሉ በደጋፊዎቻቸው እና ነቃፊዎቻቸው ዘንድ ሰፊ መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። 11 የሣዑዲ ልዑላን እንዲሁም 38 ባለሥልጣናት እና ባለሐብቶች በሣዑዲ ዓረቢያው አልጋ ወራሽ በሚመራው ጸረ-ሙስና ግብረ ኃይል በቁጥጥር ስር የዋሉበት ዋነኛ ምክንያት ፖለቲካዊ ነው ሲሉም አስተያየት የሰጡ አሉ። የዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት አበይት ትኩረት ነው። አብራችሁን ቆዩ!

ኢትዮጵያዉያንን ያስገረመዉ በርካታ የሳዑዲ ዓረቢያ ባለሥልጣናት በሀገሪቱ አልጋ ወራሽ ልዑል ሙሐመድ ቢን ሳልማን ታሰሩ የሚለው ዜና አይደለም። 11 የሀገሪቱ ልዑላን በቁጥጥር ስር ዋሉም መባሉ አልነበረም ያስደነቀው። ኢትዮጵያውያን የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎችን እጅግ ያስደመመው፤ በደጋፊ ነቃፊዎቻቸው ዘንድ ይበልጥ ያስተጋባው የሼህ መሐመድ ሁሴን አል-አሙዲንም ከታሳሪዎቹ ውስጥ ይገኙበታል የሚለው ነበር።

ምንም እንኳን ዜናው ሲወጣ የሼህ መሐመድ ሁሴን አል-አሙዲን ስም እና የንግድ ሰው ከሚለው ውጪ ዝርዝር ነገር ባለመኖሩ በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ዘንድ ብዥታ ፈጥሮ ነበር። ቆየት ብሎ በዓረቢኛ ጽሑፍ የታሳሪዎቹ ዝርዝር ከነምስላቸው ወጣ። እናም ሪያድ የሚገኘው ባለ አምስት ኮከቡ «ሪትዝ ካርልተን» ቅምጥል ሆቴል ውስጥ ቅዳሜ ዕለት የመታሰራቸዉን ዜና በርካቶች ተቀባበሉት።

ለመንግሥት ድጋፍ እንደሚሰጥ በሚነገርለት ግለሰብ የሚመራው ኢትዮጵያ ፈርስት ድረ-ገጽ፦ «የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ የሆኑት ሼህ ሙሓመድ አል-አሙዲም ቃላቸውን እንዲሰጡ ወደ ግዙፉ ሆቴል መወሰዳቸውን ሰምተናል። በቀጣይም ተጨማሪ መረጃ እንደደረሰን የምናቀርብ ይሆናል» ሲል ሼሁ በታሰሩ ማግስት በመጻፍ ፌስቡክ ላይ አስነብቧል።

ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጎዳና፦ «ስለ ሼህ መሐመድ አላሙዲን ዝም አንልም!‘እየተባለ ይገኛል። በግፍ ያለኃጥያታቸው ‘አሸባሪ‘ ተብለው ለሚሰቃዩ ወገኖቻችንም ጭምር ‘ዝም አንልም!‘ ብትሉ፣ እንዴት ባከበርኳችሁ፣ በወደድኳችሁ!የእኛ ‘አሸባሪዎች‘ በቅንጦት ሳይሆን በግድ የሚሰቃዩ ናቸውና ቀልቤ እነርሱ ጋር ነው ብሏል በፌስቡክ ጽሑፉ።

«የሼሁ መታሰር» በሚል ርእስ የተንደረደረው የቀድሞው የቅንጅት የምክር ቤት ተወካይ ሞሐመድዓሊ ሞሐመድ፦ «የሼሁ መታሰር ጮቤ ያስረገጠን በርግጥ የገዥው ፓርቲ ደጋፊ በመሆናቸው ብቻ ነው? ወይስ የሀብታቸው ምንጭ አነጋጋሪ ስለሆነ? ወይስ የዘር ሀረጋቸው ከዐረብ ስለሚመዘዝና የሳዑዲ ዜግነት ስላላቸው?» ሲል ጥያቄ አቅርቧል። «እርግጥ ነው ሸሁ ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚሞዳሞዱ ከበርቴ መሆናቸው በገሃድ የሚታወቅ ነው» ያለው መሐመድ የፌስቡክ ዝርዝር ጽሑፍን የሚያጠቃልለው፦ «አሁን ግን ሰውዬው በትውልድ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ሲቻል ተገቢውን ድጋፍ መስጠት አሊያም ደግሞ ቢያንስ በዝምታ ማለፍ እንዴት ያቅታል? ኧረ ያስተዛዝባል!» በማለት ነው። 

አሞራው ኢትዮ የሳዑዲ ዓረቢያ የባለሥልጣናት የመታሰር ዜና በተሰማበት ቀን ፌስቡክ ላይ ባሰፈረው ጽሑፉ ከታሳሪዎቹ ሼህ ሙሐመድ አላሙዲን የሉበትም ሲል ሞግቷል እንዲህ ሲል፦ «የኢትዮጵያን መልካም ነገር የማይፈልጉ የኢትዮጵያ ጠላቶች በደጉ ታላቅ ሰው ሼህ ሙሐመድ ሑሴን አላሙዲን ላይ ያላወሩትና ያልፈጠሩት የስድብ ዘመቻ የለም! በሳውዲ ታሰሩ የተባሉት ሌላ ባለሐብት ሙሐመድ አላሙዲ ሲሆኑ የኛው ሙሐመድ ሑሴን አላሙዲን አልታሰሩም!»

የማኅበራዊ የመገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ሳዑዲ ዓረቢያ ሙስናን በተመለከተ ንብረታቸው እንዲታገድ ትእዛዝ ካስተላለፈችባቸው ባለ ሐብቶች መካከል ሼክ ሙሐመድ አል አሞዲም ይገኙበታል ብለዋል። የባንክ ሒሳባቸውም ከታሳሪዎቹ ጋር መታገዱን ጠቅሰዋል። ሳዑዲ ዓረቢያ ከሙስና ጋር በተያያዘ 800 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ዝውውር ልታግድ እንደምትችል ራሺያ ቱዴይ ዎል ስትሪትን ጠቅሶ ከትናንት በስትያ ዘግቧል። 

«የሼክ መሀመድ አላሙዲ የባንክ ሂሳብ እንዳይንቀሳቀስ ታገደ» በሚል ርእስ በፖድካስት የሚሰራጨው ዋዜማ ራዲዮ ያቀረበውን ዘገባ በትዊተር እና በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል። የተለያዩ የማኅበራዊ ተጠቃሚዎችም ተመሳሳይ መልእክት አስነብበዋል።  የሳዑዲ ዓረቢያ ንጉሣዊ አስተዳደሩ የሙስና «ጉዳዩ ይመለከታቸዋል» ያላቸውን ሰዎች ንብረት በሀገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጥያቄ መሰረት ማገዱን የሚገልጹ ጽሑፎችም ተነበዋል።

በሼህ አላሙዲ ታሰሩ መባል ዜና ደስታቸውንም ሐዘናቸውንም የገለጡ አልታጡም። ምንተስኖት ቸሩ አምላክ ከተደሰቱት አንዱ ይመስላል። «እርቃናችንን እስክንቀር ድረስ ሙልጭ ተደርገን የተዘረፍነው እኛ፣ ሳውዲ ደግሞ ምኔ ተነካብኝ ብላ ነው አላሙዲንን ያሰረችው?» ሲል ጽፏል ምንተስኖት።ጽሑፉን የሚቋጨውም «ለማንኛውም በሳውዲ በመቀደማችን ተበሳጭተናል!» በማለት ነው።

«የጣናን አረም መንቀያ ማሽን ሳይገዙ በመታሰራቸው አዝኛለው» ሠላም ሠላም ኢትዮጵያ በሚል ስም የተሰጠ አጭር አስተያየት ነው።  ሲራጅ ሙደሲር፦ «እናንተ እዛው ተሳሰሩ የኛን ሽህ መሀመድን ልቀቁልን፤ ለኢትዮጵያ የችግራችን ደራሽ ነው» ሲል ጽፏል።

አስተያየት ሰጪዎችን በመተቸት የሚንደረደረው ደግሞ በድሩ ነስሮ ነው። «አንዳንድ አስተያየት ሰጪወች ግን ምናለ አፋችሁ ክፋትን ብቻ ባያወራ?» ያለው በድሩ «ሼኩ ምን ያድርጋችሁ? ሲሰራና ሲሰጥ ሁሉ ተረብና ትችት ታበዛላችሁ» ሲል አክሏል። «እናንተ ምን አደረጋችሁ ለኢትዮጲያ? ቢያንስ አንድ ሰው ሕይወት አድናችሁዋል? ስራስ በሕይወታችሁ ለስንት ሰው ፈጥራችሁዋል? ሁሌ ምን ተደረገልን ብቻ ነው ወሬያችሁ» በማለት ተቺዎችን ነቅፏል።

በትዊተር ከቀረቡ አስተያየቶች መካከል የጂጂን እናስቀድም። «ሙሐመድ ሁሴን አል አሙዲ በኢትዮጵያ የጋምቤላ ገበሬዎችን አደህይቷል፤ አጎሳቊሏል። የተፈጥሮ ሀብታቸውን አውድሟል። አሁን ሙሰኛ ሆኖ ተገኝቷል። ሕወኃት ስለአጋርነቱ ይጨነቅበት» ሲል በእንግሊዝኛ አስነብቧል።

የብሉምበርግ የቀድሞ የኢትዮጵያ ዘጋቢ የነበረው ዊሊያም ዳቪሰን፦ «አል አሙዲ በሳዑዲ የእስር ዘመቻ በቁጥጥር ስር ነው። ህም። ከአዲስ አበባ አነስ ያለም ቢሆን ሊኖር የሚችለውን መርበትበት አስቡት»

በሳምንቱ በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የተነሱ አንድ ሁለት ርእሰ-ጉዳዮችን እንመልከት። ሳምንቱ የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል አመራር ከቅራኔ እና ጥላቻ ይልቅ አንድነት ይበጀናል የሚል መልእክት ያስተጋቡበት ነው። ከኦሮሚያም አባገዳዎችን ጨምሮ የሀገር ሽማግሌዎችና ነዋሪዎች ወደ ባህር ዳር በማቅናት በጋራ መምከራቸው ተሰምቷል። በማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ዘንድ አጋጣሚው በመልካም የመታዩትን ያህል የጥርጣሬ ሰበብም መሆኑ አልቀረም።

በመልካም ጎኑ የተመለከቱት ርምጃው የቆዩ ቅራኔዎችን ለማስወገድ ጥሩ ጅማሮ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። በኅብረተሰብ መካከልም ግጭቶችን አስወግዶ መግባባት ለማስፈን ይረዳል ሲሉም ተከራክረዋል። ለአብነት ያህል ታዬ ደንዳ በዝርዝር ያሰፈረው የፌስቡክ ጽሑፉ ላይ፦«መቼም በዝህ የተቀደሰ ተግባር የማይደሰት ኢትዮጵያዊ ይኖራል ተብሎ አይገመትም። ቅር ያለዉ ካለ ኢትዮጵያዊነቱ እንደገና መመረመር አለበት» ብሏል።

የለም የጉብኝቱ ዓላማ ግልብ ነው፤ በደንብ የተብራራ አይደለም ሲሉ የተከራከሩም ነበሩ። እነዚህኞቹ ዘላቂነቱስ ምን ይመስላል ሲሉ በማጠየቅ ጥርጣሬያቸውን አጉልተዋል። በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከአንዱ ወደ አንዱ ቦታ መሄዳቸው ሌላ ሃገር የተኬደ ያህል ሊራገብ አይገባም ሲሉ ርምጃውን አጣጥለዋል። ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ የኦህዴድና የብአዴን ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ አንድነት ተቆርቋሪ መስለው መምጣታቸውን በጥርጣሬ ብንመለከተውም የምንደግፈው ነው ሲሉ ጽፈዋል። 

ከምሥጋና ለገሰ የተቀነጨበው ጽሑፍ ግንኙነቱን በጥርጥሬ የሚመለከቱትን ሐሳብ ጠቅልሎ የያዘ ይመስላል። ምሥጋና «የኦህዴድ ወደ ባህር ዳር ጉዞ ጤናማ አይደለም ፤ የሚያመጣው የተለየ ነገርም የለም የሚሉ በርከት ያሉ ወንድምና እህቶቼን አይቻለሁ፡፡ እውነት ነው! ሁለቱም (ብአዴን እና ኦህዴድ) የህውሃት የእጅ ስራ ውጤቶች ናቸውና ያነገቡት አላማ ለህውሃት ምቹ መደላድል ለመፍጠር ነው እንጂ ህዝባዊ አጀንዳ የለውም ብሎ መስጋት ተፈጥሯዊ ነው» የሚል አስተያየት በፌስቡክ አስፍራለች።

በኢትዮጵያ ስላለው የኢንተርኔት አቅርቦት በተለይ ኢንስታግራም ስለተባለው እና በይበልጥ ፎቶግራፎችን የመለጠፍ እና ለወዳጆች የማሰራጨት አገልግሎት የሚሰጠው ማስተናበሪያ በሞባይል ከእንግዲህ መሥራት አለመቻሉን በመጥቀስ ተጠቃሚዎች አማረዋል።  አንዳንዶች ምንም ፖለቲካ የሌለበት ፎቶግራፍ መለጠፉ በምን ምክንያት ነው የተዘጋው ሲሉ አጠይቀዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

 

Audios and videos on the topic