የሶማሊያ ምክር ቤቶች ተመራጮች ቃለ መሃላ ፈጸሙ | አፍሪቃ | DW | 27.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሶማሊያ ምክር ቤቶች ተመራጮች ቃለ መሃላ ፈጸሙ

መረጋጋት ርቋት የቆየችው ሶማሊያ ዛሬ ታኅሳስ 18/2009 ዓ.ም. ልታካሄደው የነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለአራተኛ ጊዜ መራዘሙ እና ወደ ጥር አጋማሽ ተገፍቷል፡፡ አጠቃላይ ምርጫው ማጭበርበሮች እና ማስፈራራቶች እየተደረጉበት ነው በሚል ክስ እየቀረበበት ይገኛል፡፡ ዛሬ የህግ መወሰኛ እና ተወካዮች ምክር ቤቶች ተመራጮች ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:37

የሀገሪቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለአራተኛ ጊዜ ተራዝሟል

የእርስ በእርስ ጦርነት ያደቀቃት ሶማሊያ አንገቷን ቀና ማድረግ ከጎረቤቶቿ እና ከዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ጋር መቀላቀል ጀምራ ነበር፡፡ በመስከረም ወር ልታካሂደው አቅዳ የነበረው የተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና የፕሬዝዳንት ምርጫ ሀገሪቱ ወደ ተረጋጋ ህይወት ለመመለሷ ማመላከቻ ልታደርገው አስባም ነበር፡፡ እርሱም ቢሆን ግን በሰበብ አሰባቡ እየተደነቃቀፈ ከአንድም አራት ጊዜ መራዘሙ ግድ ሆኗል፡፡

ሶማሊያ ፕሬዝደንቷን እንዳትመርጥ ሲጎትታት የነበረው የነበረው የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቅ ነበር፡፡ የፌደራላዊ አወቃቀርን መተግበር የጀመረችው ሶማሊያ የምክር ቤት አባላት ምርጫን በአምስት ክልሎቿ ስታከናውን ቆይታለች፡፡ 275 መቀመጫዎች ላሉት የተወካዮች ምክር ቤት ከሚወዳደሩት ዕጩዎች ውስጥ 80 በመቶው ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ላይ እንደተመረጡ ተገልጾ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ሊከናወን ቀን ተቆርጦለት የነበረውን የምክር ቤት መክፈቻ ዕውን ያደርገዋል የሚል ግምት አሳድሮ ነበር፡፡ ሆኖም የታሰበው ሳይሆን ቀርቷል፡፡

የዓለም አቀፍ ጉዳዮች የጥናት ተቋም በሆነው ቻታም ሀውስ የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪ አህመድ ሱሌማይን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ወደ ሚቀጥለው ዓመት እንደሚገፋ አስቀድመው ተንበይው ነበር፡፡ ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ለዶይቸ ቨለ እንዲህ ገልጸዋል፡፡

“የእዚህን ምርጫ ደረጃዎች ከተመለከትህ፣ የላይኛው እና የታችኛው ምክር ቤት መቀመጫዎች ማሟላት ላይ ያሉ መጓተቶች፣ ጥያቄ የተነሳባቸው ለውድድር እንደገና የቀረቡ መቀመጫዎች ጉዳይ እና ፕሬዝዳንት ለመምረጥ የሚያስፈልጉ መስፈርቶች ምንድናቸው ለሚሉት መፍትሄ መስጠት ጊዜ መውሰዱ አይቀርም” ይላሉ ምክንያቶችን ሲያብራሩ፡፡

ነግቶ በመሸ ቁጥር አዳዲስ አወዛጋቢ ጉዳዮች ብቅ የሚሉበት የሶማሊያ ምርጫ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ ሁለት አከራካሪ ጉዳዮችን ጨምሯል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ የሶማሊያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት በጋራ ሆነው ከአንድም ሁለቴ መግለጫ ያወጡበት ጉዳይ አወዛጋቢ የሆኑ የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ነገር ነው፡፡

አከራካሪ የምርጫ ጉዳዮችን የሚመለከተው የሀገሪቱ ተቋም 24 የምክር ቤት አባላት የምርጫ ውጤት ላይ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አሳውቆ ነበር፡፡ በበርካታ ሀገራት የሚሰራበትን የ“አንድ ሰው አንድ ድምጽ”ን የምርጫ ስርዓት የማትከተለው ሶማሊያ የምክር ቤት አባላትን ምርጫ የምታካሄደው በሀገር ሽማግሌዎች የተመረጡ 14 ሺህ ገደማ ሶማሊያውያን በሚሰጡት ድምጽ ነው፡፡

የጎሳ ውክልና ትልቅ ጉዳይ በሆነባት ሶማሊያ የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ለእያንዳንዱ ጎሳ በ4.5 ቀመር መሰረት እንዲከፋፈል ተደርጎ ተወዳዳሪዎች ለምርጫ የሚቀርቡበት ነው፡፡ የሀገሪቱ የምርጫ ስርዓት የሴቶችን ተሳትፎ ለማስጠበቅ በሚል ከሶስት መቀመጫዎች አንዱ ሴት ዕጩዎች ብቻ የሚወዳደሩበት እንዲሆን ደንግጓል፡፡ አንዳንዶቹ የምርጫ ውጤቶች እንዲሰረዙ እና ድጋሚ ለውድድር እንዲቀርቡ ቅሬታ የቀረበባቸው ይህን ድንጋጌ ጥሰዋል በሚል እንደሆነ ሲዘገብ ቆይቷል፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ በስልጣን ላይ ያለው አስተዳደር ደጋፊዎችን ለመጥቀም ሲባል “በማስፈራራት፣ በሙስና እና በማጭበርበር” የምርጫው ውጤት እንዲቀየር ተደርጓል በሚል ክስ የቀረበባቸው ናቸው፡፡

ውዝግቦቹን የሚዳኘው ተቋም ቅሬታ የቀረበባቸው መቀመጫዎች 24 ናቸው ሲል ቢቆይም ዘግየት ብሎ ድጋሚ ምርጫ የሚደረግባቸው 11 ብቻ መሆናቸውን አሳውቆ ነበር፡፡ ከቀናት በፊት ደግሞ የመቀመጫዎቹን ቁጥር ወደ አምስት መቀነሱ በዓለም አቀፍ ማህበረሰቡ ዘንድ ጥያቄ አስነስቷል፡፡ ይህ አይነት የተሸፋፈነ አካሄድ የምርጫውን ተቀባይነት ሊጎዳ እንደሚችል ያስጠነቀቁ ሲሆን ግልጽ ማብራሪያም ጠይቀዋል፡፡  

የአፍሪቃ ቀንድ ተመራማሪው ግን ሶማሊያ የምርጫ ውዝግቦችን ለመፍታት እየተከተለች ያለችው አካሄድ መሻሻል ከታየባቸው ምርጫ ነክ ጉዳዮች አንዱ ነው ይላሉ፡፡ እየሆነ ያለውን ለመረዳትም በሀገሪቱ ፖለቲካ አውድን መገንዘብ እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ፡፡

“እኔ እንደማስበው ይህ የሚያመለክተው የፌደራል ባለስልጣናት በምርጫው ስህተቶች ሲከሰቱ ምላሽ ለመስጠት ያላቸውን አቅም እና ተአማኒነቱን የጠበቀ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ነው፡፡ በአንዳንድ ሁኔታዎች እንደታየው የፖለቲካ ውሳኔ አሰጣጥ ያለምንም ጥርጥር ይህን ቴክኒካዊ አቅም ደፍልቆታል፡፡ ምርጫው በመዘግየቱ ምክንያት ባለው ግፊትና ወደፊት ለመራመድ በሚል በእነዚህ ውዝግቦች ላይ በብሔራዊው የአመራር መድረክ እና በፖለቲካው ወገን ባሉት የመፍትሄ ውሳኔ ሲሰጡ ይታያል፡፡ የቁጥጥር ስርዓት ለዚህ ምርጫ ተዓማኒነት በጣም አስፈላጊ ነው” ሲሉ ሱሌማይን ሀሳባቸውን ያጋራሉ፡፡      

የአወዛጋቢዎቹ የምክር ቤት መቀመጫዎች ጉዳይ በእንጥልጥል ላይ እንዳለ የህገ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት ቁጥር በህገ መንግስቱ ከተደነነገው በላይ ሊጨምር ነው መባሉ ተቃውሞ ቀስቅሷል፡፡ ከዚህ ቀደም በተካሄዱት ሁለት ምርጫዎች ያልነበረው የህግ መወሰኛ ምክር ቤት ከ54 አባላት ያልበለጡ አባላት እንዲኖረው የሀገሪቱ ህገ መንግስት ቢደነግግም ቁጥራቸውን ወደ 72 ለማሳደግ ዕቅድ መኖሩ ተሰምቷል፡፡ ይህ ዕቅድ በፕሬዝዳንታዊ ዕጩዎች ሳይቀር ህገ ወጥ እንደሆነ እየተተቸ ነው፡፡

በዚህ ሁሉ ውዝግብ ውስጥ ያለው የሶማሊያ የምርጫ ሂደት ዛሬ አንድ ተስፋ ሰጪ ክንውን አስተናግዷል፡፡ ከሁለቱ ምክር ቤቶች የተውጣጡ 284 ተመራጮች ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ የምክር ቤት አባላት ቀሪዎቹን ደምረው አፈ-ጉባኤዎቻቸውን እና የሀገሪቱን ፕሬዝዳንት በቀጣዩ ወር አጋማሽ ላይ ይመርጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic