የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 17.10.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

እግር ኳስ፣ ቴኒስ፣ የአውቶሞቢል እሽቅድድም

default

የማንቼስተር ሢቲ ደጋፊዎች

በእግር ኳስ እንጀምርና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ በሁለቱ የማንቼስተር ክለቦች መካከል ሲካሄድ በቆየው የአመራር ትግል ማንቼስተር ሢቲይ ሰንበቱን በሁለት ነጥብ ብልጫ ግንባር ቀደም መሆኑ ተሳክቶለታል። ሢቲይ አመራሩን ለብቻው የያዘው ኤስተን ቪላን 4-1 በመርታት ነው። ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ ከሊቨርፑል ጋር ባካሄደው ግጥሚያ ከእኩል ለእኩል ውጤት ከ 1-1 ሊያልፍ አልቻለም። ማኒዩ ለዚያውም አንዷን ነጥብ በዕድል ሊያተርፍ የቻለው በተቀያሪ ተጫዋቹ በሃቪየር ሄርናንዴስ አማካይነት ባስቆጠራት የዘገየች ጎል ነው። ሁለቱም የማንቼስተር ክለቦች እስካሁን በየፊናቸው ያካሄዷቸውን ስምንት ግጥሚያዎች አንዴም ሳይሽነፉ ሲያሳልፉ ሣምንት በማኒዩ ኦልድ-ትሬፎርድ ስታዲዮም እርስበርሳቸው ይገናኛሉ።

ይሄው የፕሬሚየር ሊጉ የቀደምቶች ግጥሚያም በሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች ብቻ ሣይሆን በአጠቃላይ በእንግሊዝ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ዘንድ በታላቅ ጉጉት እየተጠበቀ ነው። ከፕሬሚየር ሊጉ ስምንተኛ ግጥሚያዎች በኋላ ማንቼስተር ሢቲይ በ 22 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ማንቼስተር ዩናይትድ በሃያ ሁለተኛ ነው። ኤቨርተንን 3-1 ያሽነፈው ቼልሢይ ደግሞ አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ በሶሥተኝ’ነት ይከተላል። ከቶተንሃም ሆትስፐር በቤቱ 2-2 የተለያየው ኒውካስል ዩናይትድ በ 16 ነጥቦች አራተኛ ሲሆን ሊቨርፑል በ 14 ነጥቦች አምሥተኛ ነው። በተቀረ ዘንድሮ መጥፎ አጀማመር ያደረገው አርሰናል መልሶ ለማንሰራራት በያዘው ትግል በዚህ ሰንበት ሰንደርላንድን 2-1 መርታቱ ሰምሮለታል። ሆኖም ገና አሥረኛ ነው። በጎል አግቢነት የማንቼስተር ዩናይትድ አጥቂ ዌይን ሩኒይ ዘጠኝ አስቆጥሮ ይመራል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ዘንድሮ ታዛቢዎችን ማስደነቅ የያዘው ሌቫንቴ ትናንት ማላጋን 3-0 በማሸነፍ የቀደምቱ ክለቦች የአመራር ተጋሪ እንደሆነ ቀጥሏል። ሌቫንቴ በሰባት ግጥሚያዎች 17 ነጥቦችን ሲሰበስብ የትናንቱ ድል በተከታታይ አምሥተኛው መሆኑ ነው። ሻምፒዮኑ ባርሤሎናም ሬሢንግ ሣንታንዴርን በተመሳሳይ ውጤት 3-0 ሲረታ በ 17 ነጥቦች አመራሩን እንደያዘ ለመቀጠል በቅቷል። ጎሎቹን ያስቆጠሩት ሊዮኔል ሜሢና ሻቪ ነበሩ። በተመሳሳይ ነጥብ ሆኖም በጎል በመመበለጥ ሁለተኛው ሌቫንቴ ነው። ሬያል ማድሪድ ደግሞ ቤቲስን 4-1 በመርታት አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ በሶሥተኝነቱ ቀጥሏል።
እንዳለፈው ሣምንት ሁሉ በአንድ ጨዋታ ሶሥት ጎሎች በማስቆጠር የቡድኑ የድል ዋስትና የነበረው አርጄንቲናዊው አጥቂ ጎንዛሎ ሂጉዌይን ነበር። ሤቪያ ደግሞ ትናንት በሜዳው ስፖርቲንግ ጊዮንን 2-1 ሲረታ ከሬያል ማድሪድ አንዲት ነጥብ ዝቅ ብሎ በአራተኝነት ይከተላል። በተቀረ ሬያል ማዮርካ ከቫሌንሢያ 1-1፤ ግራናዳ ከአትሌቲኮ ማድሪድ 0-0፤ ጌታፌ ከቪላርሬያል 0-0፤ ኤስፓኞል ከቫሌካኖ 1-0፤ እንዲሁም ሣራጎሣ ከሬያል ሶሢየዳድ 2-0 ተለያይተዋል። በጎል አግቢነት የባርሣው ሜሢ አሥር አስቆጥሮ የሚመራ ሲሆን የሬያል ማድሪዱ ኮከቦች ጎንዛሎ ሂጉዌይን ስምንት፤ እንዲሁም ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ሰባት በማስገባት ይከተላሉ።

Fußball Bundesliga Bayern München - Hertha BSC Berlin

የጀርመን ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ዘንድሮ ቀደምቱ ክለብ ባየርን ሙንሺን ቀስ በቀስ ከራሱ ጋር ብቻ የሚፎካከር እየመሰለ ነው። ባየርን ባለፈው ሰንበትም ሄርታ በርሊንን 4-0 በመሸኘት ፍጹም ልዕልናውን አረጋግጧል። አጥቂው ማሪዮ ጎሜስ፣ ፍራንክ ሪቤሪይና ባስቲያን ሽቫይንሻይገር የመጀመሪያዎቹን ሶሥት ጎሎች ለማስቆጠር ሩብ ሰዓት እንኳ አልፈጀባቸውም። ይህም የሚያሳየው ማሪዮ ጎሜስ እንዳመለከተው የቡድኑን ጥንካሬ ነው።

“ዛሬ በጣም ጥሩ ነው የተጫወትነው። ጨዋታችን ገና ከመጀመሪያው አንስቶ ፍጥነት፣ ማጥቃትና ፈጠራ የተመላው ነበር። እና ብዙ የጎል ዕድሎችን ለማግኘትም ችለናል። በመጀመሪያ ቀደም ብለን ለመምራታችን እርግጥ ዕድል ያስፈልጋል። ግን ይህ ዝም ብሎ የአጋጣሚም አልነበረም። ዛሬ በጣም ግሩም ጨዋታ ነው ያሳየነው”
ሌላው የቡድኑ ጥንካሬ መለኪያ በስምንት ተከታታይ የሊጋ ግጥሚያዎች አንዲት ጎልም ሳይገባበት መቅረቱ ነው። ባየርን ዘንድሮ ወደ ሻምፒዮናው ለመዝለቅ የብቻ ጉዙ የሚያደርግ ነው የሚመስለው። ቡድኑ በጠቅላላው ከዘጠኝ ግጥሚያዎች 22 ነጥቦችን ሲሰበስብ ሊጋውን በወቅቱ በአምሥት ነጥቦች ልዩነት ይመራል። በ 17 ነጥቦች ሁለተኛው ከሌቨርኩዝን 2-2 የተለያየው መንሸንግላድባህ ነው። ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ዶርትሙንድ ደግሞ ደከም ካለ አጀማመር በኋላ ባለፉት ጥቂት ሣምንታት ባሳየው መሻሻል ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ሊል ችሏል።
ሽቱትጋርት ሆፈንሃይምን 2-0 በመርታት አራተኛ ሲሆን የባየርን የቅርብ ተከታይ ሆኖ የቆየው ብሬመን በአንጻሩ በአንድ ሣምንት ውስጥ ከሁለተኛው ወደ አምሥተኛው ቦታ ማቆልቆል ግድ ሆኖበታል። ብሬመን ከዚህ የደረሰው በገዛ ሜዳው በዶርትሙንድ 2-0 በመረታቱ ነው። ዶርትሙንድ ለዚያውም አንድ ተጫዋቹ በ 47ኛዋ ደቂቃ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቶበት በአሥር ሰዎች ሲጫወት ለብሬመን ዕድሉን ሊጠቀም አለመቻሉ ማስቆጨቱ አልቀረም። ያለፈው ሰንበት ከሁለተኛው ዲቪዚዮን ለመጣው ክለብ ለአውግስቡርግ ደግሞ በጣሙን የተለየ ነበር። ቡድኑ ማይንስን 1-0 በማሸነፍ ለመጀመሪያ የቡንደስሊጋ ድሉ በቅቷል። የድሉ ዋስትናም ግሩም በረኛው ሢሞን የንሽ ነበር።

“በሊጋው ውስጥ አንድም ድል ያላገኘው ቡድን እስካሁን የኛ ብቻ ነበር። እናም አሁን መሳካቱ ግሩም ነገር ነው። ከሁለት ሣምንታት በፊት በዶርትሙንድ በሰፊው ተቀጥተን መሸነፋችን ሲታወስ ይህም በጣሙን ነበር ቅስማችንን የሰበረው። የሆነው ሆኖ ወደምናውቀው ትግል መመለሳችንን ዛሬ በሚገባ አሳይተናል። በበኩሌ በተለይ ሶሥቱንም ነጥቦች በማግኘታችን እጅግ ደስተኛ ነኝ”

በተቀሩት ግጥሚያዎች ሃምቡርግ ከፍራይቡርግ 2-1፤ ኮሎኝ ከሃኖቨር 2-0፤ ካይዘርስላውተርን ከሻልከ 2-1፤ ቮልፍስቡርግም ከኑርንበርግ እንዲሁ 2-1 ተለያይተዋል። በጎል አግቢነት ሊጋውን የሚመራው ባለፉት ዘጠኝ ግጥሚያዎች አሥር ያስቆጠረው የባየርን አጥቂ ማሪዮ ጎሜስ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ከስድሥት ግጥሚያዎች በኋላ ጁቬንቱስና ኡዲኔዘ ሁለቱም የየበኩላቸውን የሰንበት ግጥሚያ ባዶ ለባዶ በመፈጸም በእኩል ነጥብ መምራታቸውን ሲቀጥሉ በፈረንሣይ ፓሪስ-ሣንት-ጀርማን ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ በማሽነፍ በሶሥት ነጥብ ብልጫ ቁንጮነቱን አረጋግጧል። በኔዘርላንድ ደግሞ አልክማር ቀደምቱ እንደሆነ ነው።

በተረፈ በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር የምድብ ዙር ነገና ከነገ በስቲያ በርካታ ግጥሚያዎች ,ይካሄዳሉ። ከነዚሁ መካከል ዋና ዋናዎቹም ነገ ናፖሊ ከባየርን ሙንሺን፤ ማንቼስተር ሢቲይ ከቪላርሬያል፤ ሊል ከኢንተር ሚላንና ሬያል ማድሪድ ከኦላምፒክ ሊዮን ናቸው። በማግሥቱ ረቡዕ ምሽት ከሚደረጉት መካከልም ኦላምፒክ ማርሤይ ከአርሰናል፤ ሌቨርኩዝን ከቫሌንሢያ፤ ኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ ከዶርትሙንድ፤ እንዲሁም ቼልሢይ ከጌንክ ይገኙበታል። በአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታዎች ደግሞ የናይጄሪያው ኤኒምባ ከካዛብላንካ 0-0፤ የቱኒዚያው ኤስፔራንስም ከሱዳኑ አል ሂላል 2-0 ተለያይተዋል። በአጠቃላይ ውጤት ኤስፔራንስና ካዛብላንካ ልቀው ሲገኙ በሚቀጥለው ወር በፍጻሜው ግጥሚያ ይገናኛሉ።

Flash-Galerie Andy Murray

ቴኒስ

የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ ትናንት በቻይና የሻንግሃይ ማስተርስ ፍጻሜ ግጥሚያ የስፓኝ ተጋጣሚውን ዴቪድ ፌሬርን 7-5, 6-4 በማሸነፍ በወቅቱ ግሩም በሆነ ጥንካሬ ላይ እንደሚገኝ አስመስክሯል። ለ 24 ዓመቱ ስኮች የትናንቱ የሻንግሃይ ድል በዚህ ወር ከባንግኮክና ከቶኪዮ ቀጥሎ ሶሥተኛው መሆኑ ነው። መሪይ በዚሁ ስኬቱ ከሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪችና ከስፓኙ ራፋኤል ናዳል ቀጥሎ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ሶሥተኛውን ቦታ ይዟል። በሻንግሃዩ ውድድር ያልተሳተፈው ሮጀር ፌደረር ወደ አራተኛው ቦታ ሲያቆለቁል የስዊሱ ተወላጅ ከሶሥተኛው ቦታ ዝቅ ሲል በስምንት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።

በጃፓን የሴቶች-ኦፕን ፍጻሜ ደግሞ ፈረንሣዊቱ ማሪዮን ባርቶሊ በቅርቡ የዩ.ኤስ.ኦፕን ባለድል የነበረችውን አውስትራሊያዊት ሣማንታ ስቶሱርን በፍጹም የበላይነት አሸንፋለች። ባርቶሊ 6-3, 6-1 በሆነ ውጤት ስታሽንፍ ጨዋታው ከ 74 ደቂቃዎች በላይ የዘለቀ አልነበረም። ለፈረንሣዊቱ ኮከብ ይሄው ድል በዘንድሮው የውድድር ወቅት ሁለተኛው መሆኑ ነው። የትናንቱን አያርደውና ስቶሱርም ለመጀመሪያ የዓለም ቴኒስ ማሕበር የድል ማዕረግ የበቃችው በዚያው በጃፓን ነበር። ከዚሁ ሌላ በአውስትሪያ የሊንስ-ኦፕን ደግሞ የቼኳ ፔትራ ክቪቶቫ የስሎቫኪያ ተጋጣሚዋን ዶሚኒካ ቹልኮቫን 6-4, 6-1 በማሸነፍ በዚህ ዓመት ለአምሥተኛ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ድሏ ለመብቃት ችላለች። በተረፈ የዴንማርኳ ካሮሊን ቪዝኒያችኪ ሩሢያዊቱን ማሪያ ሻራፖቫን በማስከተል በዓለም የሴቶች የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ መምራቷን እንደቀጠለች በዛሬው ዕለት የወጣ አዲስ መረጃ አመልክቷል።

ሰንበቱን ፖላንድ-ግዳንስክ ውስጥ በተካሄደው የጠረጴዛ ቴኒስ የአውሮፓ ሻምፒዮና ውድድር ፍጻሜ ግጥሚያ ጀርመናዊው ቲሞ ቦል የክለብ ባልደረባውን ፓትሪክ ባውምን 4-1 በማሸነፍ ለአምሥተኛ ድሉ በቅቷል። የፍጻሜው ግጥሚያ እንዳለፈው ዓመት ሁሉ ዘንድሮም የተካሄደው በሁለት ጀርመናውያን መካከል ነበር። ቲሞ ቦል ካለፈው ረቡዕ የቡድን ብር ሜዳሊያ ወዲህ በጠቅላላው ለ 15 የአውሮፓ ሻምፒዮና ድልና ለሃያ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሜዳሊያዎች መብቃቱ ነው። ስፖርተኛው በውድድሩ ፍጻሜ ተከታይ ታላቅ ግቡ የኦሎምፒክ ጨዋታ እንደሆነ ነው የገለጸው። በሴቶችም ለፍጻሜ የደረሰችው የጀርመን ተወዳዳሪ ኢሬነ ኢቫንቻን ለብር ሜዳሊያ ስትበቃ ውድድሩ ለጀርመን የተሳካ ሆኖ አልፏል። ኢቫንቻን ለጥቂት 4-3 የተሽነፈችው ለኔዘርላንድ በምትወዳደረው በሊ ጂያዎ ነበር።

ዘገባችንን በአውቶሞቢል ስፖርት ለማጠቃለል ጀርመናዊው የፎርሙላ-አንድ የዓለም ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል ትናንት በደቡብ ኮሪያ ግራንድ-ፕሪ በማሸነፍ የተሽከርካሪውን ገምቢዎችም ለአንደኝነት አብቅቷል። የሬድ-ቡሉ ዘዋሪ ምንም እንኳ ከሁለተኛው ቦታ ቢነሣም ሉዊስ ሃሚልተንን አልፎ እስከግቡ 55 ዙሮችን በመሪነት መፈጸሙ አልከበደውም። ፌትል ባለፈው ሣምንት ከዘንድሮው ውድድር ፍጻሜ ቀድሞ በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን መሆኑ አይዘነጋም። በአጠቃላይ ውጤት የብሪታኒያው ጄሰን ባተን ሁለተኛ ሲሆን ሶሥተኛው ደግሞ የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ነው።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic