የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 03.10.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውስጥ የሚካሄደው የእግር ኳስ ውድድር ጠንካራውን ከደካማው በመለየቱ ረገድ ቀስ በቀስ መልክ እየያዘ በመሄድ ላይ ነው።

default

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ እንጀምርና ባርሣ በሰንበቱ የውጭ ግጥሚያው ስፖርቲንግ ጊዮንን 1-0 ሲረታ ከስድሥት ጨዋታዎች በኋላ በ 14 ነጥቦች የሊጋው ቁንጮ መሆኑ ሰምሮለታል። ለዝነኛው ክለብ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው አድሪያኖ ኮሬያ ነበር። የሚያስደንቅ ሆኖ ሁለተኛው ሬያል ቤቲስን በተመሳሳይ 1-0 ውጤት ያሽነፈው ሌቫንቴ ነው። ሌቫንቴ በነጥብ ከባርሤሎና እኩል ሲሆን በጎል ብልጫ ብቻ ነው ባርሣ የሚመራው። ሬያል ማድሪድ ደግሞ ኤስፓኞልን 4-0 በማሸነፍ አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ ሶሥተኛ ነው።
ለሬያል ከአራት ሶሥቱን ጎሎች በማስቆጠር የድል ዋስትና የሆነው የአርጄንቲናው ኮከብ ጎንዛሎ ሂጉዌይን ነበር። ማላጋና ቫሌንሢያም እንዲሁ ከሬያል እኩል 13 ነጥቦች በመያዝ አራተኛና አምሥተኛ ሆነው ይከተላሉ። እርግጥ በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ውስጥ በወቅቱ አንደኛውን ከሰባተኛው የሚለዩት ሁለት ነጥቦች ብቻ ሲሆኑ በመጪዎቹ ሣምንታት ብዙ ተለዋዋጭነት መኖሩ እንደማይቀር የሚጠበቅ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቀደም ሲል እንዳመለከትነው ማንቼስተር ዩናይትድና የከተማ ተፎካካሪው ማንቼስተር ሢቲይ የሊጋው መሪና ዘዋሪ እንደሆኑ ቀጥለዋል። ሢቲይ ብላክበርን ሮቨርስን 4-0 ሲቀጣ ማንቼስተር ዩናይትድም ኖርዊች ሢቲይን በፍጹም የበላይነት 2-0 አሸንፏል። ሁለቱም ክለቦች ከሰባት ግጥሚያዎች በኋላ እኩል 19 ነጥቦች ሲኖሯቸው ማኒዩ የሚመራው በአንዲት ጎል ብልጫ ነው። ፉክክር ማለት እንዲህ ነው። በነገራችን ላይ ሣምንቱ ለማንቼስተር ሢቲይ አርጄንቲናዊ ጎል አግቢውን ካርሎስ ቴቬዝን በማገዱ ቀላል ሣምንት አልነበረም። ሆኖም ለስኬት መብቃቱ አልተሳነውም። በአዳም ጆንሰን፣ በማሪዮ ባሎቴሊ፣ በሣሚር ናስሪና በስቴፋን ሣቪች አማካይነት ጎሎቹን ሊያስቆጥር በቅቷል።
ሌላው ቀደምት ክለብ ቼልሢይም በቦልተን ወንደረርስ ሜዳ 5-1 በማሽነፍ በሻምፒዮናው ጠንካራ ተፎካካሪ መሆኑን አሳይቷል። ለቼልሢይ ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው ድንቁ ፍራንክ ላምፓርድ ነበር። ከዚሁ ሌላ በሰሜን ለንደን ክለቦች የአካባቢ ፉክክር ቶተንሃም ሆትስፐር አርሰናልን 2-1 ሲረታ በምዕራብ ለንደን ክለቦች ግጥሚያም ፉልሃም ኩዊንስ ፓርክ ሬንጀርስን 6-0 አከናንቦ ሸኝቷል። ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ ኒውካስል ዩናይትድ የማንቼስተርን ሁለት ክለቦችና ቼልሢይን ተከትሎ አራተኛ ሲሆን ኤቨርተንን 2-0 ያሽነፈው ሊቨርፑልም አምሥተኛ ነው። አርሰናል ግን እንዳለፉት ሣምንታት ስኬት አልባ ሆኖ ከቀጠለ ቀደምቱን ክለቦች ለመፎካከር መብቃቱ በጣሙን ያጠራጥራል። አሠልጣኙ አርሰን ቬንገር ቀላል ጊዜ የሚጠብቃቸው አይመስልም።

Fußball Bundesliga 8. Spieltag TSG 1899 Hoffenheim Bayern München

የጀርመን ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ የቀደምቱ ክለብ የባየርን ሙንሺን የድል ጉዞ ከአሥር ግጥሚያዎች በኋላ ተገትቷል። ይሁንና ባየርን ከሆፈንሃይም ባዶ-ለባዶ ቢለያይም ሊጋውን መምራቱን አሁንም እንደቀጠለ ነው። ቀደምቱ ክለብ ደከም ብሎ ለመታየቱ በረኛው ማኑዌል ኖየር የሰጠው ምክንያት በሣምንቱ አጋማሽ ከማንቼስተር ሢቲይ ጋር የተደረገው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ጨዋታ ብዙ ጉልበት ወስዷል የሚል ነው።
“ሁላችንም ሰዎች ነን፤ ሊደክመን ይችላል። በሣምንቱ ሂደት ከከባድ ተጋጣሚ ጋር መጫወት ነበረብን። ደግሞም ግሩም ጨዋታ ነበር ያሳየነው። ግን ሁልጊዜ ጥሩ መጫወት አይቻልም። ይህ እርግጥ ከዚህ ቀደም አንዳንዴ ተሳክቶልናል። ግን ዛሬ ጨዋታው ከባድ ነበር”

በሌላ በኩል የቅርብ ተከታዮቹ ብሬመንና መንሸንግላድባህ ሁለቱም በሰንበቱ ግጥሚያዎቻቸው በመሸነፋቸው ከባየርን ሙንሺን ጋር በነጥብ እኩል የመሆኑ ዕድል አምልጧቸዋል። ባየርን ከስምንት ግጥሚያዎች በኋላ ሊጋውን ለብቻው በ 19 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ብሬመንና ግላድባህ ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብለው ይከተላሉ። ቨርደር ብሬመን በመጨረሻ በተሰጠች ቅጣት ምት በሃኖቨር 3-2 ሲሸነፍ ግላድባህም ብዙ ዕድሎቹን መጠቀም ባለመቻሉ በፍራይቡርግ መረታቱ ግድ ነው የሆነበት። በተለይ የብሬመን ሽንፈት እንደ አሠልጣኙ እንደ ቶማስ ሻፍ ሁሉ ብዙ ደጋፊዎቹን ማስቆጨቱ አልቀረም።

“ዛሬ እዚህ በመሸነፋችን በጣሙን ነው ያዘንኩት። ምክንያቱም መሸነፋችን አስፈላጊ አልነበረም። ሁሉንም ነገር እንዳሰብነው አላደረግንም”

ያም ሆነ ይህ ከሰንበቱ ግጥሚያዎች በኋላ በተለይ ጠቃሚ ዕርምጃ ያደረጉት ክለቦች በአጀማመር ደከም ብለው የነበሩት ያለፈው ውድድር ወቅት ሻምፒዮን ቦሩሢያ ዶርትሙንድና ሻልከ ናቸው። ዶርትሙንድ ከሁለተኛው ዲቪዚዮን የወጣውን አውግስቡርግን 4-0 ሲያሸንፍ ሻልከም በኔዘርላንዳዊ አዲስ አሠልጣኑ በሁብ ስቴቨንስ አመራር ሃምቡርግን 2-1 በመርታት ወደ ላይ አሻቅቧል። በነገራችን ላይ ለሻልከ ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረውም እንደ አሠልጣኙ ሁሉ የኔዘርላንድ ተወላጅ የሆነው ክላስ-ያን-ሃንቴላር ነበር። የሻልከ ሣምንት የሆላንድ ሣምንት ነበር ሊባል ይቻላል። ሻልከ በ 15 ነጥቦች ወደ አራተኛው ቦታ ከፍ ሲል ዶርትሙንድም ሁለት ነጥቦች ወረድ ብሎ ስድሥተኛ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ የቀድሞ ተፎካካሪውንና ያለፈውን ወቅት ሻምፒዮን ኤ.ሢ.ሚላንን 2-0 በማሸነፍ አመራሩን ሊጠብቅ ችሏል። ለጁቬንቱስ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ክላውዲዮ ማርኪሢዮ ነበር። ኡዲኔዘም እንዲሁ በተመሳሳይ ,ውጤት ቦሎኛን ሲያሸንፍ በእኩል ነጥቦች ሁለተኛ ነው። ናፖሊ ደግሞ ያስገርማል ኢንተር ሚላንን ለዚያውም በገዛ ሜዳው 2-0 በመቅጣት በአሥር ነጥብ ሶሥተኛ ሲሆን ፓሌርሞና ካልጋሪም በተመሳሳይ ነጥብ ይከተላሉ። ማን አሰበው በወቅቱ ቀደምቱ ክለቦች ኤ.ሢ.ሚላን 15ኛ ኢንተር ሚላንም 17ኛ በመሆን ከታች ወደ ላይ ተመልካቾች ናቸው። እርግጥ የውድድሩ ሂደት ገና ረጅም በመሆኑ አልቆላቸዋል ማለት አይደለም። ቢሆንምመልሶ ግንባር-ቀደም ለመሆን ጠንክረው መታገል ይኖርባቸዋል።

በተረፈ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ፓሪስ-ሣንት-ዣርማን ኦላምፒክ ሊዮንን 2-0 ረትቶ አመራሩን ሲነጥቅ ያለፈው ሻምፒዮን ሊል አምሥተኛ ነው። ኦላምፒክ ሊዮን ሞንትፔልዬን ተከትሎ ሶሥተኛ ሲሆን ሌሎቹ ቀደምት ክለቦች ኦላምፒክ ማርሤይና ዢሮንዲን ቦርዶው ደግሞ እጅጉን በማቆልቆል 13ኛና 14ኛ ናቸው። በኔዘርላንድ ሻምፒዮና አልክማር ፈንሎን 3-1 በማሸነፍ የሊጋ አመራሩን በአራት ነጥቦች ልዩነት አስፍቷል። በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ቤንፊካ ሊዝበንና ፖርቶ የሊጋው ቁንጮዎች ናቸው።

በአፍሪቃ የእግር ኳስ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ትናንት በተካሄዱ ሁለት የግማሽ ፍጻሜ ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያዎች የሱዳኑ አል-ሃሊል ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ 0-1 በመለያየት በሜዳው ሲሽነፍ የሞሮኮው ዋክ-ካዛብላንካ ደግሞ የናይጄሪያ ተጋጣሚውን ኤኒምባን 1-0 ረትቷል። ሁለቱ የማግሬብ ክለቦች ለመልሱ ግጥሚያ አመቺ ሁኔታን የፈጠሩ ነው የሚመስለው።

NO FLASH Volleyball Volley Spieler Hände Ball

ቮሊይቦል የአውሮፓ ሻምፒዮና

ሰርቢያ ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው የሴቶች ቮሊይቦል የአውሮፓ ሻምፒዮና ትናንት በአስተናጋጇ አገር አሸናፊነት ተፈጽሟል። የስቢያው ቡድን ለዚህ ታላቅ ድል የበቃው ቤልግሬድ ውስጥ በተካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያ የጀርመን ተጋጣሚውን በጥቅሉ 3-2 በማሸነፍ ነው። የጀርመን ቡድን ዘጠኝ ሺህ ተመልካች በተገኘበት አዳራሽ በተካሄደው ግጥሚያ ለመጀመሪያው የአውሮፓ ሻምፒዮና የነበረውን ሕልም ዕውን ለማድረግ ባይችልም ለብር ሜዳሊያ በመብቃቱ በዚህ በአገሩ በጣሙን ነው የተወደሰው። አሠልጣኙ ጆቫኒ ጉዊዴቲ ውጤቱን፤ ቀደም ሲል ያለምነው አልነበረም፤ “አስደናቂ” ነው’ ብሎታል።

Köln Marathonläufer Sport Kölner Marathon Flash-Galerie

የኮሎኝ ማራቶን

በትናንትናው ዕለት በዚሁ በጀርመን በተካሄደው 15ኛ የኮሎኝ ማራቶን ሩጫ ድሉ በወንዶች የኬንያ እንዲሁም በሴቶች የኢትዮጵያ ሆኗል። በወንዶች ኪፕሮኖ ባርማዎ ሁለት የአገሩን ልጆች በማስከተል ሲያሸንፍ በሴቶች ለድል የበቃችው አበሩሜ መኩሪያ ነበረች። እርግጥ በኮሎኙ ማራቶን ታላላቅ አትሌቶች ባለመሳተፋቸው ውጤቱ ያን ያህል ያስደነቀ አልነበረም። ባርማዎ ለምሳሌ ሩጫውን በሁለት ሰዓት ከስምንት ደቂቃ 53 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም ይህም በቅርቡ በአገሩ ልጅ በርሊን ላይ ከተመዘገበው የዓለም ክብረ-ወሰን አንጻር ከአምሥት ደቂቃዎች በላይ የረዘመ መሆኑ ነው። በተረፈ 22 ሺህ ሰዎች የተሳተፈበት የከተማ ማራቶን በተለይም በግሩም የአየር ሁኔታ የተነሣ የደመቀ ሆኖ አልፏል።

ዘገባችንን በቴኒስ ለማጠቃለል የሰርቢያው ኮከብ ኖቫክ ጆኮቪች በወንዶች የማዕረግ ተዋረድ ላይ ቀደምቱ ሆኖ እንደቀጠለ በዛሬው ዕለት የወጣ የኤቲፒ ዝርዝር አመልክቷል። በዝርዝሩ መሠረት ጆኮቪች በ 14,720 ነጥቦች አንደኛ ሲሆን ከአራት መቶ ነጥቦች በላይ ዝቅ ብሎ ሁለተኛው የስፓኙ ራፋኤል ናዳል ነው። የስዊሱ ሮጀር ፌደረርና የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ ደግሞ ሶሥተኛና አራተኛ ሆነው ይከተላሉ። በሴቶችም እንዲሁ የዴንማርኳ ካሮሊን ቮዝኒያችኪ በአመራሯ ስትቀጥል ሁለቱ የሩሢያ ተጫዋቾች ማሪያ ሻራፖቫና ቬራ ዝቮናሬቫ ሁለተኛና ሶሥተኛ ናቸው። አራተኛዋ ደግሞ የቤላሩሷ ቪክቶሪያ አዛሬንካ ናት።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic