የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 11.07.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በዚህ በጀርመን የሚካሄደው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር አስተናጋጇን አገር ሳይጠቀልል ወደ ግማሽ ፍጻሜው ተሸጋግሯል።

default

በዚህ በጀርመን በመካሄድ ላይ ባለው በስድሥተኛው የሴቶች የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር እንጀምርና የአገሪቱ ብሄራዊ ቡድንና ደጋፊዎቹ ለሶሥተኛ ጊዜ በተከታታይ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ጸንሰውት የነበረው ሕልም ከትናንቱ ሽንፈት ወዲህ ቅዠት ነው የሆነው። የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ከትናንት በስቲያ ምሽት በሰዓት ጭማሪ በትክክል በ 107ኛው ደቂቃ ላይ ካሪማ ሙሩያማ ባስቆጠረቻት ጎል በጃፓን 1-0 ተረትቶ ከውድድሩ ሲወጣ ሽንፈቱ በመጪው ዓመት ለንደን ላይ ለሚካሄደው የኦሎምፒክ ጨዋታ እንዳያልፍም ተጨማሪ መሰናክል ሆኖበታል። ቡድኑ ከዓለም ዋንጫው ውድድር ከተሰናበተ ከሁለት ቀናት በኋላም ተጫዎቹና ሃላፊዎቹ የሽንፈቱን መንስዔ ለመለየት መሞከራቸውን እንደቀጠሉ ሲሆን አሠልጣኛ ሢልቪያ ናይድ በበኩሏ ተጫዋቾቹ ዋንጫ የመውሰድ የመንፈስ ግፊቱን መቋቋም ተስኗቸዋል ባይ ናት።

“እንደማስበው ቡድኑ የሚጠበቅበትን ከፍተኛ ውጤትና ግፊት በማጤኑ የተነሣ እንደተለመደው ተዝናንቶ ሊጫወት አልቻለም። በተለይም በመጨረሻው ግጥሚያ ያየነው ድክመት በቡድናችን ዘንድ የተለመደ ነገር አልነበረም”

ሽንፈቱ ለጀርመን የሴቶች ብሄራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ላይ ባለፉት 12 ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው ሲሆን አሠልጣኟ ናይድ ጭምር እንዳለችው በተለይ አሁን በአገሪቱ መስተንግዶ ወቅት መድረሱ ጥቂት ማስቆጨቱ አልቀረም።

“በጥቅሉ ሲታይ ሽንፈቱ አሁን የዓለም ዋንጫው ውድድር በእኛ አስተናጋጅነት ጀርመን ውስጥ በሚካሄድበት ሰዓት መድረሱ በጣም የሚያሳዝን ነው”

እርግጥ ለፍጻሜ ይደርሳሉ ተብለው ከተጠበቁት ቀደምት አገሮች መካከል ጀርመን ብቻ ሣትሆን ባለፈው ምሽት ብራዚልም በአሳዛኝ ሁኔታ በፍጹም ቅጣት ምት በዩ.ኤስ. አሜሪካ 7-5 ተሸንፋ ተመሳሳይ ጽዋ ደርሷታል። የሚያሳዝነው የብራዚል ቡድን እስከ ሰዓት ጭማሪው መጨረሻ እስከ 120ኛው ደቂቃ ድረስ 2-1 ሲመራ ቆይቶ ባለቀ ሰዓት ለዚያውም ከ 120ኛው ደቂቃ በኋላ በአሥር ሰው በተጫወተችው በአሜሪካ ሁለተኛ ጎል ድሉን መነጠቁ ነው። በሌሎቹ ሁለት የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ስዊድን አውስትራሊያን በመደበኛ ጊዜ 3-1 ስታሸንፍ ፈረንሣይ ደግሞ እንግሊዝን በፍጹም ቅጣት ምት 5-4 ረትታ አስወጥታለች።
ሁለቱ የግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያዎች ከነገ በስቲያ ረቡዕ ምሽት የሚካሄዱ ሲሆን እርስበርስ የሚገናኙት ፈረንሣይ ከዩ.ኤስ.አሜሪካ እንዲሁም ጃፓን ከስዊድን ናቸው። የፍጻሜው ግጥሚያ ደግሞ በፊታችን ዕሑድ ፍራንክፉርት ውስጥ ይካሄዷል። በጥቅሉ የዘንድሮው የሴቶች የዓለም ዋንጫ ውድድር በእስካሁን ሂደቱ በቴሌቪዥንም ሆነ በስታዲዮም ተመልካቾችን በሰፊው በመሳብ አቻ ያልታየለት ነበር ለማለት ይቻላል። ለዚህ ደግሞ በተለይም የጀርመን የእግር ኳስ ፌደሬሺንና የዝግጅቱ ኮሚቴ ላደረጉት ያልተቆጠበ ጥረትና ታላቅ አስተዋጽኦ ሊወደሱ ይገባቸዋል። እርግጥ በውድድሩ ጎልቶ የታየው የእግር ኳስ አጨዋወት ዕድገትና ማራኪነትም ለሴቶች እግር ኳስ ተወዳጅነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም አንድና ሁለት የለውም።

Brasilien gewinnt Copa América

ኮፓ አሜሪካ

በእግር ኳሱ ዓለም እንቆይና በላቲን አሜሪካ ውድድር ኮፓ-አሜሪካ ቢቀር በወቅቱ የምድብ ዙር ብራዚልንና አስተናጋጇን አርጄንቲናን የመሳሰሉት ሃያላን አገሮች ሣይሆን ግንባር ቀደምትነቱን ይዘው የቀጠሉት ትናንሾቹ ናቸው። በምድብ-አንድ ኮሉምቢያ ትናንት ቦሊቪያን 2-0 በማሸነፍ በሰባት ነጥቦች በአመራሯ ስትቀጥል ኮስታ ሪካ በሶሥት ነጥቦች ሁለተኛ ናት። እንግዲህ በዚሁ ምድብ ውስጥ እስካሁን ከሁለት እኩል-ለእኩል ውጤቶች ያላለፈችው ሶሥተኛዋ አርጄንቲና በሁለተኝነት ወደ ሩብ ፍጻሜው ዙር ለማለፍ እንድትችል ዛሬ ማምሻውን ኮስታ ሪካን ማሸነፍ ይኖርባታል።

በምድብ-ሁለትም ሁኔታው ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው። ከብራዚል ባዶ-ለባዶ የተለያየችው ቬኔዙዌላ ምድቡን በአራት ነጥቦች የምትመራ ሲሆን ብራዚል ሁለተኛ ቦታዋን እንዳታጣ በፊታችን ረቡዕ ኤኩዋዶርን ማሸነፏ ግድ ነው። በሶሥተኛው-ምድብ ውስጥ ደግሞ ቺሌና ፔሩ በእኩል አራት ነጥቦች ተከታትለው የሚመሩ ሲሆን አንዲት ነጥብ ወረድ ብላ ሶሥተኛ የሆነችው ኡሩጉዋይም ወደ ሩብ ፍጻሜው የመዝለቅ ትልቅ ዕድል አላት። ለግንዛቤ ያህል ወደ ሩብ ፍጻሜው የሚያልፉት የሶሥቱ ምድቦች አንደኛና ሁለተኞች እንዲሁም ሁለት ጠንካራ ሶሥተኞች ይሆናሉ።

ሜክሢኮ ደግሞ ከቅርቡ የሰሜን ማዕከላዊ አሜሪካና ካራይብ እግር ኳስ ማሕበራት ኮንፌደሬሺን የኮንካካፍ ወርቃማ ዋንጫ አስደናቂ ድል ባሻገር ትናንት ከ 17 ዓመት በታች ወጣቶች የዓለም ዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቅታለች። ሜክሢኮ ለዚህ ክብር የበቃችው መቶ ሺህ ሰዎችን በሚይዘው የሜክሢኮ ሢቲይ ዝነኛ የአስቴኮች ስታዲዮም ኡሩጉዋይን 2-0 በመርታት ነው። ሜክሢኮ በግማሽ ፍጻሜው ጀርመንን ስታሸንፍ ኡሩጉዋይም ለፍጻሜው የደረሰችው ብራዚልን 3-0 በሆነ ውጤት በማሰናበት ነበር። ለሶሥተኝነት በተካሄደው ግጥሚያ ደግሞ አውሮፓን በብቸኝነት የወከሉት የጀርመን ወጣቶች ብራዚልን 4-3 በማሸነፍ የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።

EM Leichtathletik in Spanien

አትሌቲክስ

በብሪታኒያ-በርሚንግሃም ትናንት በተካሄደው የዳያመንድ-ሊግ አትሌቲክስ ውድድር በተለይ በአጭር ርቀት ጃማይካውያንና አሜሪካውያን ፈጣኖቹ ሆነው ታይተዋል። በወንዶች አንድ መቶ ሜትር ሩጫ አሣፋ ፓውል በ 9,91 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በሁለተኛና በሶሥተኛነት ተከትለውት የገቡትም ጃማይካውያን ናቸው። በሴቶች ሁለት መቶ ሜትር ደግሞ የአሜሪካ ሴቶች ቀደምቱ ነበሩ። ቢያንካ ናይት አንደኛ፣ ማርሸቬት ማየርስ ሁለተኛ፣ ካሜሊታ ጄተር ሶሥተኛ፤ እንዲሁም አሌክሣድራ አንደርሰን አራተኛ፤ ሁሉም ከዩ.ኤስ.አሜሪካ! በወንዶች አራት መቶ ሜትር መሰናክል የብሪታኒያው ዴቪድ ግሪን ሲያሸንፍ በስምንት መቶ ሜትር ደግሞ የሱዳኑ አቡባከር ካኪ ባለድል ሆኗል። በሴቶች አራት መቶ ሜትር የቦትሱዋና አማንትል ሞንቾ ስታሸንፍ የብሪታኒያዋ ጄኒይ ሚዶውስ በስምንት መቶ ሜትር ቀደምቷ ሆናለች።

ለወትሮው የኢትዮጵያና የኬንያ አትሌቶች ጠንክረው በሚታዩበት በወንዶች አምሥት ሺህ ሜትር ከሶማሊያ የመነጨው የብሪታኒያ ዜጋ ሞ ፋራህ አንደኛ ሲሆን አሜሪካዊው ጋለን ሩፕ ሩጫውን በሁለተኝነት ፈጽሟል። በዚሁ ርቀት የኢትዮጵያ ተወዳዳሪዎች ኢማነ መርጋና የኔው አላምረው ሶሥተኛና አራተኛ ሲወጡ አበራ ኩማም ሰባተኛ ሆኗል። የኢትዮጵያ አትሌቶች በአንጻሩ ጠንክረው የታዩት በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ሩጫ ነበር። ሶፊያ አሰፋና አልማዝ አያና አንደኛና ሁለተኛ በመሆን ሲያሸንፉ ብርቱካን አዳሙም በሰባተኝነት ጥሩ ውጤት አስመዝግባለች። የኢትዮጵያን ሴት አትሌቶች ካነሣን ትዝታ ቦጋለም ባለፈው ቅዳሜ በስፓኝ-ማድሪድ ላይ በተካሄደ ዓለምአቀፍ ውድድር በ 1,500 ሜትር ሩጫ ሶሥተኛ ወጥታለች። በዚህ ሩጫ የስፓኟ ኑሪያ ፈርናንዴዝ ስታሸንፍ ሁለተኛ የሆነችው ሩሢያዊቱ ኤካቴሪና ማርቲኖቫ ነበረች።

Formel 1 SIlverstone 2011 Fernando Alonso

ቴኒስ/ቱር-ዴ-ፍራንስ/ፎርሙላ-አንድ

በቴኒስ ዴቪስ-ካፕ ዓለምአቀፍ ውድድር ስፓኝ አሜሪካን ትናንት ቴክሣስ-አውስቲን ላይ በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሜው ለማለፍ በቅታለች። ስፓኝ አሜሪካን በአጠቃላይ ነጥብ በ 3-1 ስታሸንፍ ዴቪድ ፌሬር ማርዲይ ፊሽን 7-5, 7-6, 5-7, 7-6 መርታቱ በውጤቱ ላይ ወሣኝ ነበር። ስፓኝ እስካሁን አራት ጊዜ የዴቪስ-ካፑን ውድድር ስታሸንፍ በፊታችን መስከረም በግማስ ፍጻሜው ፈረንሣይን ታስተናግዳለች። ስፓኝ ባለፈው ዓመት በሩብ ፍጻሜው በፈረንሣይ ደርሶባት ለነበረው 5-0 ሽንፈት አጸፋውን ለመመለስ ግጥሚያውን በጉጉት ነው የምትጠባበቀው። ፈረንሣይ ለአሁኑ ግማሽ ፍጻሜ ያለፈችው ጀርመንን 4-1 በመርታት ነበር። ሌሎቹ የፍማሽ ፍጻሜ ተጋጣሚዎች ደግሞ ሰርቢያና አርጄንቲና ናቸው።

ፈረንሣይ ውስጥ በመካሄድ ላይ ባለው በታላቁ የቢስክሌት ውድድር ቱር-ዴ-ፍራንስ ትናንት ከኢሱዋር እስከ ሣን ፍሎር በተካሄደው ዘጠነኛ ደረጃ የ 208 ኪሎሜትር እሽቅድድም የስፓኙ ሉዊስ ሣንቼዝ አሸናፊ ሆኗል። የኔዘርላንዱ ጆኒ ሆገላንድ በተራራ መውጣት ቀደምቱ ሲሆን በአጠቃላይ 217 ነጥብ ውድድሩን የሚመራው የቤልጂጉ ፊሊፕ ጊልበርት ነው። በቡድን ደግሞ የፈረንሣዩ ኤውሮካር ይመራል። በነገራችን ላይ የኔዘርላንዱ ጆኒ ሆገላንድ ትናንት በመኪና ተገጭቶ በእግሩ ላይ ከቆሰለ በኋላ አስፈላጊው ሕክምና ተደሮለት ነበር። በውድድሩ የዛሬው ዕለት የዕረፍት ቀን ሲሆን ስምንተኛው ጀርመናዊ አንድሬያስ ክሎደን ከጀርባ ሕመሙ አገግሞ ነገ በአሥረኛው ውድድር እንደሚካፈል ተሥፋውን ገልጿል። ክሎደን የተጎዳው ትናንት በዘጠነኛው ደረጃ እሽቅድድም ከሌሎች ተዋዳሪዎች ጋር ከተጋጨ በኋላ ነበር።

ሰንበቱን በብሪታኒያ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ እሽቅድድም ደግሞ የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ አሸናፊ ሆኗል። ሻምፒዮኑ ዜባስቲያን ፌትል ሁለተኛ ሲወጣ የአውስትራሊያው ዘዋሪ ማርክ ዌበር ሶሥተኛ ሆኗል። በዚሁ ዜባስቲያን ፌትል በዘጠነኛው ውድድር ሰባተኛ ድል ማስመዝገቡ አልሆነለትም። በአጠቃላይ ነጥብ ፌትል በ 204 የሚመራ ሲሆን ዌበር በ 124 ሁለተኛ ነው።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic