የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 27.09.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር አነስተኛው ክለብ ማይንስ የሰንበቱን ስድሥተኛ ግጥሚያውንም በድል በመወጣት የአገሪቱን የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ማስገረሙን ቀጥሏል።

default

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የቼልሢይ የድል ጉዞ በማንቼስተር ሢቲይ ሲገታ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶ እንደ ጀርመኑ ማይንስ ሁሉ ከስድሥት ግጥሚያዎች በኋላም አንዲት ነጥብ ሳያስነካ እንደመራ ነው። ትናንት በዚህ በጀርመን የተካሄደው የበርሊን ማራቶን ሩጫ ደግሞ በኬንያና በኢትዮጵያ አትሌቶች የበላይነት ተፈጽሟል።

የአውሮፓ ክለቦች የእግር ኳስ ሻምፒዮና

በዘንድሮው የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር የወቅቱ ድንቅ ቡድን ማንም ያላሰበው ማይንስ 05 እንደሆነ ቀጥሏል። ማይንስ በስድሥተኛ ግጥሚያው ስድሥተኛ ድሉን ያረጋገጠው ደግሞ ቀላል ክለብን ሣይሆን የጀርመኑን ሬኮርድ ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺንን ለዚያውም ሚዩኒክ ውስጥ 2-1 በማሸነፍ ነው። ማይንስ በዚህ ሰንበትም ግሩም ጨዋታ ሲያሳይ አሠልጣኑ ቶማስ ቱሸል በበኩሉ ከቡድኑ ብቃትና የትግል ስሜት አንጻር በድሉ ብዙም አልተደነቀም።

“ቡድኑ ታላቅ ክብር የሚሰጠው ነው። ብዙ የቴክኒክ ችሎታና የትግል ስሜት በማሳየቱ በመጨረሻ ለማሽነፍ መብቃቱም ተገቢ ነበር”

Fußball Bundesliga 6. Spieltag FC Bayern München - 1. FSV Mainz 05

የማይንስ ቱኒዚያዊ ጎል አግቢ አላጉዊ

ማይንስ በ 18 ነጥቦች ሊጋውን የሚመራ ሲሆን ዶርትሙንድ ሶሥት ነጥቦች ወረድ ብሎ በሁለተኝነት ይከተላል፤ ሶሥተኛው ባለፈው የውድድር ወቅት ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ከመከለስ ለጥቂት ያመለጠው ሃኖቨር 96 ነው።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ውድድር ሬያል ማድሪድ ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ከወጣው ዝቅተኛ ክለብ ከሌቫንቴ ባዶ-ለባዶ በመለያየቱ አመራሩን ለቫሌንሢያ አስረክቦ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ወርዷል። ቫሌንሢያ ጊዮንን 2-0 ሲረታ የሣምንቱን ጥሩ ዕርምጃ ያደረገው በተለይ ያለ ኮከብ ዘዋሪው ያለ ሊዮኔል ሜሢ ቢልባዎን 3-1 ያሸነፈው ባርሤሎና ነበር። ባርሣ በአምሥተኛው የሊጋው ግጥሚያ ካገኘው ከዚህ ጠቃሚ ድሉ በኋላ ሁለተኛ ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን ምንም እንኳ በመጨረሻ ሰዓት ላይ በተቆጠረች ግብ በሮማ 1-0 ቢሽነፍም አመራሩን እንደጨበጠ ቀጥሏል። በአንጻሩ ለሮማ ባለፉት አምሥት ግጥሚያዎቹ ከሁለት ሽንፈትና ከሁለት እኩል ለእኩል ውጤቶች በኋላ የመጀመሪያ ድሉ መሆኑ ነበር። ሊጋውን ኢንተርና ላሢዮ በእኩል አሥር ነጥብ የሚመሩ ሲሆን ማንም ያልጠበቀው ቺየቮ ቬሮና አንዲት ነጥብ ወረድ ብሎ በሶሥተኝነት ይከተላል። በነገራችን ላይ ሮማ 18ኛ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ደግሞ በተለይም ቀደምቱ ክለቦች በሰንበቱ ያሳዩት ድክመት ብዙ የተጠበቀ አልነበረም። ቼልሢይ ከአምሥት ተከታታይ ድሎች በኋላ በማንቼስተር ሢቲይ ለመጀመሪያ ጊዜ አርጄንቲናዊው ካርሎስ ቴቬዝ ባስቆጠራት ግብ 1-0 ሲረታ አመራሩ በሶሥት ነጥቦች ሊወሰን ችሏል። ማንቼስተር ዩናይትድ ትናንት ከቦልተን ወንደረርስ ጋር 2-2 በመለያየቱ ጠቃሚ ነጥቦችን ቢያጣም ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ማለቱ ተሳክቶለታል። አርሰናል በአንጻሩ በገዛ ሜዳው በአልቢዮን 3-2 በመረታቱ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ማቆልቆሉ ግድ ነው የሆነበት። ሊቨርፑል ከሰንደርላንድ ከእኩል ለእኩል ውጤት ባለማለፉ ይገርማል 16ኛ ነው።

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ያለፉት ዓመታት ሃያል ክለብ ኦላምፒክ ሊዮን በገዛ ሜዳው በሣንት ኤቲየን 1-0 መረታቱ ጥልቅ ቀውስ ላይ ጥሎታል። ሊዮን ከሰንበቱ ሽንፈት በኋላ 18ኛ ነው። በአንጻሩ ሣንት ኤቲየን በሰባተኛ ግጥሚያው አጠቃላይ ነጥቡን ወደ 16 ከፍ በማድረግ በቁንጮነቱ ቀጥሏል። አንዳንድ ነጥብ ወረድ በማለት ሁለተኛ ሬንስ እንዲሁም ቱሉዝ ሶሥተኛ ነው። የተቀሩት ቀደምት ክለቦች ኦላምፒክ ማርሤይ ስድሥተኛ፤ እንዲሁም ቦርዶው 13ኛ ሲሆን ጨርሰው እንዳያቆለቁሉ ከባድ ትግል ይጠብቃቸዋል።
በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶ ከስድሥት ግጥሚያዎች ሙሉ 18 ነጥቦችን በመያዝ አካዴሚካን በሰባት ነጥብ ልዩነት በርቀት አስከትሎ በፍጹም የበላይነት የሚመራ ሲሆን በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ደግሞ አያክስ አምስተርዳም የበላይነቱን እንደያዘ ነው። በተቀረ በዚህ ሣምንት የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የምድብ ዙር ሁለተኛ ግጥሚያዎች የሚካሄዱ ሲሆን ተመልካቹን በርካታ ማራኪ ግጥሚያዎች ይጠብቁታል። ከብዙ በጥቂቱ በነገው ምሽት ቼልሢይ ከኦላምፒክ ማርሤይ፤ አያክስ አምስተርዳም ከኤ.ሢ.ሚላንና ኦግዜር ከሬያል ማድሪድ የሚጋጠሙ ሲሆን የማግሥት ረቡዕ ሃያል ግጥሚያዎች ደግሞ ኢንተር ሚላን ከብሬመን፤ ቫሌንሢያ ከማንቼስተር ዩናይትድ፤ እንዲሁም ሩቢን ካዛን ከባርሤሎና ናቸው።

የበርሊን ማራቶንና የኢትዮጵያ አትሌቶች

BdT Deutschland 37 Berlin Marathon der Inline Skater

በዚህ በጀርመን ትናንት የተካሄደው 37ኛው የበርሊን ማራቶን ውድድር በወንዶች ኬንያውያንና በሴቶች ደግሞ የኢትዮጵያ አትሌቶች ለድል በበቁበት ሁኔታ ተፈጽሟል። በወንዶች ኬንያዊው ፓትሪክ ማካው የአገሩን ልጅ ጆፍሪይ ሙታይን በሁለተኝነት አስከትሎ ሲያሸንፍ ከኢትዮጵያ በዙ ወርቁ ሶሥተኛ፤ እንዲሁም የማነ ጸጋይ አራተኛ ሆነዋል። ታደሰ አብርሃም ከኤርትራ ሰባተኛ! በሴቶች ደግሞ አበሩ ከበደና ብዙነሽ በቀለ በመከታተል የኢትዮጵያን ድል ድርብ አድርገዋል። ሩጫውን በቅርብ የተከታተለው የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ሃይለ ሚካኤል ሶሥቱን የኢትዮጵያ አትሌቶች አነጋግሮ ያጠናቀረው ዘገባ የሚከተለው ነው።

Formel 1 GB in Singapur - Fernando Alonso

የሢንጋፑር ፎርሙላ አንድ እሽቅድድም

ሢንጋፑር ውስጥ ትናንት የተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ የስፓኙ ተወላጅ የፌራሪ አብራሪ ፌርናንዶ አሎንሶ ሆኗል። አሎንሶ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እየመራ ነበር ውድድሩን በግሩም የበላይነት የፈጸመው። የሁለት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን በዘንድሮው የውድድር ወቅት ሲያሽንፍ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን በጠቅላላውም 25ኛ ድሉ መሆኑ ነው። ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል ሁለተኛ ሲሆን የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ሶሥተኛ ወጥቷል። በሌላ በኩል ወደ ውድድሩ መድረክ የተመለሰው የሰባት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን ሚሻኤል ሹማሸር 13ኛ ሲወጣ አሁንም የመሻሻል አዝማሚያ ሳይታይበት እንደቀጠለ ነው።
ከ 19ኙ የፎርሙላ-አንድ እሽቅድድሞች 15ቱ ተካሄደው በወቅቱ በተጠናቀረው አጠቃላይ ነጥብ ማርክ ዌበር በ 202 የሚመራ ሲሆን ፌርናንዶ አሎንሶ 191፤ የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን 182፤ እንዲሁም ዜባስቲያን ፌትል 181 ነጥቦች በመያዝ ይከተላሉ። ሁሉም ገና የዓለም ሻምፒዮን የመሆን ዕድል ሲኖራቸው ውድድሩ ትግል የተመላበት ሆኖ መቀጠሉ እርግጠኛ ነገር ነው።

መሥፍን መኮንን