1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ውስጥ በዚህ ሰንበትም መደበኞቹ ግጥሚያዎች ሲቀጥሉ በተለይ የጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ የተገላቢጦሽ ገጽታ ይዞ እየተራመደ ነው።

default

ያለፈው ሣምንት የዩኤፋ ሻምፒዮና ሊጋ የመጀመሪያ የምድብ ግጥሚያዎች የተሄዱበትም ነበር። በዓለምአቀፉ የአትሌቲክሱ መድረክ ደግሞ ትናንት በብሪታኒያ በተካሄደ የግማሽ ማራቶን ሩጫ ሃይሌ ገ/ሥላሴና ብርሃኔ አደሬ ኢትዮጵያን ለድርብ ድል አብቅተዋል።

እግር ኳስን በማስቀደም በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እንጀምርና ቼልሢይ በዚህ ሰንበት በአምሥተኛ ግጥሚያውም ብላክፑልን 4-0 በማሸነፍ በሙሉ 15 ነጥቦችና 21 ጎሎች በበላይነት መምራቱን ቀጥሏል። ጎሎቹን በመጀመሪያው አጋማሽ ውስጥ ያስቆጠሩት ፍሎሬንት ማሉዳ ሁለቱን፣ እያንዳንደው አንድ ደግሞ ዲዲየር ድሮግባና ሶሎሞን ካሉ ነበሩ። ሁለተኛው አርሰናል ከሰንደርላንድ 1-1 ብቻ በመለያየቱ ከቼልሢይ ጋር ያለው ልዩነት ወደ አራት ነጥቦች ሲሰፋ ሁኔታው በተለይ የጠቀመው ሊቨርፑልን በኦልድ-ትሬፎርድ ስታዲዮሙ 3-1 የሸኘው ማንቼስተር ዩናይትድን ነው።
ለማኒዩ ሶሥቱንም ጎሎች ያስቀጠረው የቡልጋሪያው ኮከብ ዲሚታር ቤርባቶቭ ነበር። በተረፈ ማንቼስተር-ሲቲይ ዊጋን አትሌቲክን 2-0 በመርታት ወደ አራተኛው ቦታ ከፍ ሲል አምስተኛው ዎንደረርስን 3-1 ያሸነፈው ቶተንሃም ሆትስፐር ነው። ካለፈው የውድድር ወቅት ወዲህ ማቆልቆል የያዘው የአንዴው ቀደምት ክለብ ሊቨርፑል በአንጻሩ በውድቀቱ በመቀጠል ወደ 16ኛው ቦታ ወርዷል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ላ-ሊጋ ገና ጨቅላ በሆነው የውድድር ወቅት ቫሌንሢያ ሶሥቱንም ግጥሚያዎቹን አሸንፎ በዘጠኝ ነጥቦች እየመራ ሲሆን ሤቪያና ሬያል ማድሪድ በሰባት ነጥቦች በቅርብ ይከተሉታል። ሬያል ማድሪድ ትግል በተመላው ግጥሚያ ሬያል ሶሲየዳድን 2-1 ሲያሸነፍ የድሉ ዋስትና የሆነው ሁለተኛዋን ጎል በቅጣት ምት ያስቆጠረው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ነው። በተቀረ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ ቪላርሬያል፣ ባርሤሎናና ኤስፓኞል እያንዳንዳቸው ስድሥት ነጥቦች ይዘው ይከተላሉ። ያለፈው ወቅት ሻምፒዮን ባርሣ ሜሢና ፒኬ ባስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች አትሌቲኮ ማድሪድን ሲያሸንፍ ለቁንጮነት ወደሚደረገው ትግል ተመልሷል።

Fußball Bundesliga Bremen Mainz

በቀደምቱ የአውሮፓ ሊጋዎች የዘንድሮ ውድድር የጀርመኑን ቡንደስሊጋ ያህል በወቅቱ ማንም ያልተነበየው ሂደት የሚታይበት የለም። በቡንደስሊጋው አመራር ላይ የሚገኙት እንደተለመደው ዝነኞቹ ክለቦች ሣይሆኑ ማይንስ፣ ሆፈንሃይም፣ ዶርትሙንድና ፍራይቡርግ ናቸው። ማጋነን አይሁንና የቅደም ተከተሉ ሰንጥረዥ የአንደኛው ሣይሆን የሁለተኛው ዲቪዚዮን መምሰሉ አልቀረም። አንደኛው ማይንስ ባለፈው ሰንበት አራተኛ ግጥሚያውንም ብሬመንን ለዚያውም በገዛ ሜዳው 2-0 በመቅጣት በድል ሲፈጽም ዕርምጃው በችሎታ እንጂ በአጋጣሚ እንዳልሆነ ተፎካካሪዎቹ ቀስ በቀስ እየተረዱ ነው።
ሆፈንሃይምም እንዲሁ እስካሁን ሶሥት ጨዋታዎችን በማሽነፍና በአንዱ እኩል ለእኩል በመውጣት በሁለተኝነቱ ቀጥሏል። በአንጻሩ በውድድሩ ሂደት በዚህ ደረጃ ቀደምቶቹ ባየርን ሙንሺን ዘጠነኛ፣ ብሬመን 11ኛ፣ በተለይም ሻልከ የመጨረሻ፤ 18ኛ ይሆናል ብሎ የጠበቀ ማንም አልነበረም። ሻልከ በአራት ግጥሚያዎች አራቴም ሲሽነፍ የዶቼ ቬለ የስፖርት ፕሮግራም ባልደረባ ቮልፍጋንግ ፋን-ካን እንደሚለው የውድቀቱ ምክንያት በተለይም የሰበሰባቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች በቡድን መልክ ለመቅረጽ አለመቻሉ ነው።

“አዎን፤ አሠልጣኙ ፌሊክስ ማጋት ባለፈው ዓመት ወደ ሻልከ ሲመጣ በጊዜው በነበሩት ተጫዋቾች ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ብቁ የሚሆን ቡድን ለመቅረጽ እንደማይችል ዕምነት ነበረው። እናም 15 ገደማ የሚጠጉ ተጫዋቾችን አሰናብቶ የዚያኑ ያህል አዳዲስ ይገዛል። እናም የዚህ ውጤት አሁን ጎልቶ እየታየ ነው። እርግጥ በርካታ፤ በከፊልም ጥሩ ተጫዋቾችን ነው የሰበሰበው። ግን እነዚህን አንድ ቡድን አድርጎ ለመቅረጽ አልተቻለም። ይህ ደግሞ ባለፈው ቅዳሜ ከዶርትሙንድ ጋር በተደረገው ግጥሚያ በሚገባ ነው የታየው”

ሻልከ ትናንት በዶርትሙንድ የበላይነት 3-1 ሲረታ ተጫዋቾቹ በመጪዎቹ ግጥሚያዎች ድንጋጤ ላይ እየወደቁ ይብስ እንዳይዳከሙ በጣሙን ያሰጋል። ክለቡ የዘንሮውን ውድድር ሲጀምር ግቡ በቀደምትነት ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ መብቃት ነበር። አሁን ግን ፈተናው ከባድ የሚሆን እየመሰለ ነው። እንደ ፋን-ካን ከሆነ እንዲያውም ሊታሰብም ያዳግታል።

“ለነገሩ የዘንድሮው ውድድር እስካሁን ማንም ባላሰበው ሁኔታ እየተራመደ ነው ያለው። ሁሉም በመሠረቱ ቀደምት የሚባሉት ክለቦች ችግር ላይ ሲወድቁ በቅደም ተከተኩ ተዋረድ ላይ ቁንጮ ሆነው የሚገኙት የተጠበቁት አይደሉም። ባየርን ሙንሺን፣ ብሬመን ወይም ሌቨርኩዝን መካከለኛ ቦታ ላይ ሲሆኑ ሻልከ እንዲያውም መጨረሻው ነው። ከሁለት ዓመታት በፊት ሻምፒዮን የነበረው ቮልፍስቡርግም ከሻልከ የሚሻለው በአንዲት ቦታ ብቻ ነው። በጥቅሉ ብዙ ክለቦች እንዳሰቡት እየተራመዱ አይደሉም። እርግጥ ገና ከአራት ግጥሚያዎች በኋላ መጪውን እንዲህ ብሎ በትክክል ለመተንበይ አይቻልም። ሆኖም ግን ለሻልከ መውጫው እየጠበበ ነው የሚሄደው። ከአውሮፓ ሻምፒዮና ቦታ ላይ መድረሱን በጣሙን እጠራጠራለሁ”

የጀርመን ቡንደስሊጋ ሶሥት ቀደምት ክለቦች በብሄራዊው ውድድር የተለመደ ቦታቸውን መልሶ ለመያዝ ብዙ ትግል የሚጠብቃቸው ሲሆን በሣምንቱ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ግጥሚያዎችም ቢሆን ጅማሯቸው ብዙም የሚያረካ አልነበረም። ቬርደር ብሬመን ከእንግሊዙ ቶተንሃም ሆትስፐር በገዛ ሜዳው በእኩል ለእኩል 2-2 ውጤት ሲወሰን ሻልከ ደግሞ በፈረንሣዩ ኦላምፒክ ሊዮን 1-0 ተረትቶ ተመልሷል። ብሬመንን በተመለከተ አጥቂው አሮን ሃንት እንደሚለው ውጤቱ የጨዋታውን ሂደት በሚገባ ያንጸባረቀ ነበር።

“እንደ ጨዋታው አካሄድ ከሆነ በውጤቱ መርካት ይኖርብናል። አንድ ቡድን 2-0 ከተመራ በኋላ፤ በመጀመሪያው ግማሽ ሰዓት ውስጥ በቦታው እንዳልነበረ ከሆነ አንድ ነጥብ ይዘን በመውጣታችንም መደሰት አለብን”

በአውሮፓው ከፍተኛ መድረክ ጀርመንን በሚገባ የወከለው የኢጣሊያውን ክለብ ሮማን በፍጹም ልዕልና 2-0 ያሸነፈው ባየርን ሙንሺን ብቻ ነበር። እርግጥ በመለስተኛው የዩኤፋ ሊግ ውድድር ሶሥቱም ተሳታፊ የቡንደስሊጋ ክለቦች መልካም ጅማሮ ማድረጋቸውም አልቀረም።

በተረፈ በተቀሩት የሣምንቱ የአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ኢንተር ሚላን አመራሩን ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ከመጣው ክለብ ከቼሤና ጋር እየተጋራ ነው። ሶሥተኛው ቬሮና ሲሆን ኤ.ሢ.ሚላን ወደ አሥረኛው ቦታ አቆልቁሏል። በፈረንሣይ ሊጋ ገደ ቢስ በሆነ አጀማመሩ የቀጠለው ኦላምፒክ ሊዮን በዚህ ሰንበትም በቦርዶው 2-0 በመረታት ከታች ወደ ላይ ተመልካች እንደሆነ ነው። በአንጻሩ በወቅቱ ከስድሥት ግጥሚያዎች በኋላ በእኩል 13 ነጥቦች ሊጋውን በቀደምትነት የሚመሩት ሣንት-ኤቲየንና ቱሉዝ ናቸው። በተቀረ በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን አያክስ አምስተርዳም፤ በፖርቱጋል ሻምፒዮና ደግሞ ፖርቶ በቀደምትነት ይመራሉ።

Haile Gebrselassie Äthiopien gewinnt am Sonntag den 36. Berlin - Marathon

አትሌቲክስ “ታላቁ የሰሜን ሩጫ”

አትሌት ሃይሌ ገብረ ሥላሴና ብርሃኔ አደሬ ትናንት “ግሬት-ኖርዝ-ራን” በመባል በሚታወቀው በታላቁ የብሪታኒያ የግማሽ ማራቶን ሩጫ ውድድር በየፊናቸው በማሽነፍ ድርብ ድል አስመዝግበዋል። ሃይሌ ከግማሽ ርቀት በኋላ ተፎካካሪዎቹን ጥሎ ሲያመልጥ ሩጫውን የፈጸመው በ 59 ደቂቃ ከ 33 ሤኮንድ ጊዜ ነው። የኬንያው ኪፕሊሞ ኪሙታይና የሞሮኮው የሁለት ጊዜ የኦሎምፒክ የዓለም ሻምፒዮን ጃዋድ ጋሪብ ደግሞ ሁለተኛና ሶሥተኛ ሆነዋል።
ሃይሌ ከውድድሩ በኋላ በታላቁና ድንቅ በሆነው ሩጫ ለመሳተፍ ለዓመታት ሲያልም እንደቆየ ለቢቢሲ ሲገልጽ አብዛኛውን መንገድ ለብቻው በማቋረጡ የአዲስ ክብረ-ወሰን ዕድል እንዳልነበረውም አስረድቷል። ፉክክሩ ጠበቅ ባለበት በሴቶቹ ሩጫ ብርሃኔ አደሬ የፖርቱጋል ተፎካካሪዎቿን በመቅደም በታላቁ ሩጫ ለሁለተኛ ድሏ በቅታለች። ብርሃኔ አደሬ መጀመሪያ ያሽነፈችው ከአራት ዓመታት በፊት ነበር። ከኒውካስል እስከ ደቡብ ሺልድስ በሚዘልቀው በሰላሣኛው ታላቅ የሰሜን ሩጫ በጠቅላላው 54 ሺህ ገደማ የሚጠጉ አትሌቶች ተሳትፈዋል።

Timo Boll Tischtennis EM Sieg Flash-Galerie

የጠረጴዛ ቴኒስ የአውሮፓ ሻምፒዮና

ቼክ ሬፑብሊክ ኦስትራው ውስጥ ሲካሄድ የሰነበተው የጠረጴዛ ቴኒስ የአውሮፓ ሻምፒዮና ግሩም በሆነ የጀርመናውያን የፍጻሜ ግጥሚያ ተጠናቋል። ውድድሩ የተፈጸመው በተለይም የጀርመኑ ኮከብ ተወዳዳሪ ቲሞ ቦል ልዩ ክብረ-ወሰን በተጎናጸፈበት ሁኔታ ነው። ቦል በተናጠል አራተኛ የአውሮፓ ሻምፒዮና ድሉን ሲጎናጸፍ በጥንድና በቡድንም አሸናፊ ሆኗል። ድሉ ለ 29 ዓመቱ ቦል ሶሥተኛው የሶሥት ዓይነት ግጥሚያዎች ጥቅል ድሉም መሆኑ ነው። ግሩሙ ቲሞ ቦል ታዲያ ትናንት አድካሚ ከነበረው ውድድር በኋላ ሲናገር ከሁሉም በተቀዳሚ የዕረፍትን ያህል የታየው ሌላ ነገር አልነበረም።

“22 ግጥሚያዎች በስምንት ቀናት ውስጥ፤ በጣም ከባድ ነገር ነበር። ግን ሁሉንም ማሽነፉም ግሩም ስሜትን የሚሰጥ ነው። በዚህ ላይ ሶሥት የወርቅ ሜዳሊያዎች መውሰዱ ደግሞ ሊያምኑት ያዳግታል። አሁን ግን በመጀመሪያ የአውሮፓው ሻምፒዮና በማለፉና ጥቂት ለማከር በመቻላችን ደስተኛ ነኝ”
የቲሞ ቦል የፍጻሜ ተጋጣሚ የ 23 ዓመት ወጣቱ ጀርመናዊ ፓትሪክ ባውምም በአጨዋወቱ ታላቅ አድናቆትን ነው ያተረፈው።

መሥፍን መኮንን