የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 06.09.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ሰንበቱ በአውሮፓና በአፍሪቃ የእግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ ውድድርም እንዲሁ ክሮኤሺያ ውስጥ ተካሂዷል።

default

የጀርመን ብሄራዊ ቡድን በብራስልስ

በኡክራኒያና በፖላንድ የጋራ አስተናጋጅነት በመጪው 2012 ዓ.ም. ለሚካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ በዘጠኝ ምድቦች በሚደረገው ፉክክር ባለፈው ሣምንት በርካታ ግጥሚያዎች ተካሂደው ነበር። በምድብ-አንድ ውስጥ ቱርክ ካዛክስታንን 3-0 አሸንፋ በጎል ብልጫ አመራሩን ስትይዝ ጀርመንም ቤልጂግን 1-0 ረትታለች። የተቀሩት የምድቡ ተሳታፊዎች አውስትሪያና አዘርባይጃን ሲሆኑ ጀርመንና ቱርክ ከዝና አንጻር ከፍተኛ የማለፍ ዕድል ያላቸው ነው የሚመስለው።

በምድብ-ሁለት አየርላንድ አርሜኒያን 1-0 ስታሸንፍ ሩሢያ ከአንዶራ 2-0፤ እንዲሁም ስሎቫኪያ ከማቄዶኒያ 1-0 ተለያይተዋል። ምድቡን ሩሢያ በጎል ብልጫ የምትመራ ሲሆን አየርላንድና ስሎቫኪያም እያንዳንዳቸው እኩል ሶሥት ነጥብ ይዘው ይከተላሉ። በምድብ ሶሥት ግጥሚያዎች ሰርቢያ ፌሮው ደሴቶችን 3-0 ስትረታ ኢጣሊያ ከኤስቶኒያ 2-1፤ እንዲሁም ሰሜን አየርላንድ ከስሎቬኒያ 1-0 ተለያይተዋል።

በምድብ-አራት የፈረንሣይ ብሄራዊ ቡድን ከዓለም ዋንጫው ውርደት በኋላ ዝናውን መልሶ ለማደስ ያደረገው ጥረት በገዛ ሜዳው በቤላሩስ 1-0 በመሸነፉ ዕውን ሳይሆንለት ቀርቷል። አዲሱ አሰልጣኝ ሎራን ብላንክ ነገ ቦስና ውስጥ በሚደረገው ተከታይ ግጥሚያ ቀላል ትግል አይጠብቀውም። ለሎራን ብላንክ በወቅቱ አስደሳች ዜና ቢኖር ምናልባትም ጎል አግቢው ካሪም ቤንዜማ ከቁስሉ አገግሞ ለመጫወት ዝግጁ መሆኑ ነው። ለማንኛውም ምድቡን ቦስናና ቤላሩስ በእኩል ሶሥት ነጥብ የሚመሩ ሲሆን ፈረንሣይ በወቅቱ አምሥተኛ ናት።

ምድብ-አምሥት ውስጥ ኔዘርላንድ ሣን ማሪኖን በመርታት እንደ ደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ውድድር ወቅት ሁሉ ጥንካሬዋን ስታስመሰክር ከጅምሩ አመራሩንም ለመያዝ በቅታለች። በተቀረ ስዊድን ሁንጋሪያን፤ ሞልዶቫም ፊንላንድን በተመሳሳይ ሁለት-ለባዶ ውጤት ሲያሸንፉ የኔዘርላንድ ተፎካካሪዎች ሆነው ይቀጥላሉ። በምድብ-ስድሥት ክሮኤሺያ ላትቪያን 3-0 ስታሸንፍ ግሪክና ጆርጂያ ደግሞ 1-1 ተለያይተዋል። ምድቡን በቀደምትነት የሚመሩት እኩል ሶሥት ነጥብ ያላቸው ክሮኤሺያና እሥራኤል ናቸው።

እንግሊዝ ቡልጋሪያን 4-0 ስታሸንፍ ምድብ-ሰባትን ትመራለች። በዚሁ ምድብ ውስጥ ሞንቴኔግሮም ዌልስን 1-0 በመርታት ሶሥት ጠቃሚ ነጥቦችን ለመያዝ በቅታለች። ምድብ-ስምንት ውስጥ ኖርዌይ አይስላንድን ሁለት-ለአንድ አሸንፋ አመራሩን ስትይዝ ፖርቱጋል ከቆጵሮስ እኩል ለእኩል መለያየቷ የተጠበቀ ውጤት አልነበረም። በሌላ በኩል የአውሮፓና የዓለም ዋንጫ ባለቤት ስፓኝ በልዕልናዋ እንደቀጠለች ነው። የስፓኝ ብሄራዊ ቡድን ሊሽተንሽታይንን 4-0 ሲያሸንፍ ምድብ ዘጠኝን ለብቻው እየመራ ነው። በዚሁ ምድብ ውስጥ ሊቱዋኒያና ስኮትላንድ ደግሞ ባዶ-ለባዶ በመለያየት አንዳንድ ነጥብ ተከፋፍለዋል።

ባለፈው ሰንበት የአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ግጥሚያዎችም ተካሂደዋል። የዘንድሮው ማጣሪያ ጅማሮ በተለይም ለቀደምቷ አገር ለግብጽ የቀና አልነበረም። ግብጽ ከሢየራሌዎን ጋር ባካሄደችው የመጀመሪያ ግጥሚያ ለዚያውም ካይሮ ላይ አንድ-ለአንድ ስትለያይ ላለፈው ዋንጫ ባለቤት ውጤቱ መሪር ነው የሆነው። ግብጽ ላለፈው የዓለም ዋንጫ በተደረገው ማጣሪያ በመጀመሪያ ግጥሚያዋ በተመሳሳይ ሁኔታ ከዛምቢያ አቻ-ለአቻ መለያየቷ በመጨረሻ ከደቡብ አፍሪቃ እንዳስቀራት የሚዘነጋ አይደለም።

በሌላ በኩል በዓለም ዋንጫው ውድድር እስከ ሩብ ፍጻሜ ዘልቆ የነበረው የጋና ብሄራዊ ቡድን ስዋዚላንድን 3-0 በማሸነፍ ጥሩ ጅማሮ አድርጓል። ሴኔጋል ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎን 4-2 ስትረታ ዛምቢያም ኮሞሮ ደሴቶችን 4-0 በመሸኘት ጠቃሚ ነጥቦችን ለመሰብሰብ በቅታለች። ለኢትዮጵያ በአንጻሩ የአፍሪቃው ዋንጫ ማጣሪያ ውድድር ቢቀር በጅማሮው የሰመረ አልሆነም። ብሄራዊው ቡድን ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በጊኒ 4-1 ሲረታ በሣምንቱ ተከታይ ግጥሚያው ማዳጋስካርን ካላሽነፈ ዕድሉ እየመነመነ የሚሄድ ነው የሚመስለው። ጨዋታውን የተከታተለው የአዲስ አበባ ወኪላችን ታደሰ እንግዳው እንደሚለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የፉክክር ብቃት ለማግኘት ገና ብዙ ይቀረዋል።

ሣምንቱ በዓለምአቀፍ ደረጃም የወዳጅነት ግጥሚያዎች የተካሄዱበት ነበር። በላቲን አሜሪካ ኤኩዋዶር ሜክሢኮን 2-1 ስትረታ ኮሉምቢያ ደግሞ ቬኔዙዌላን 2-0 አሸንፋለች። ጃፓን ፓራጉዋይን 1-0 ስታሸንፍ ፖላንድና ኡክራኒያ ደግሞ 1-1ተለያይተዋል።

ክሮኤሺያ ውስጥ በተካሄው የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የዓለም ዋንጫ ውድድር ትናንት በወንዶች የሚከተሉት ውጤቶች ተመዝግበው ነበር። በክፍለ-ዓለማቱ ውድድር በወንዶች በአራት ጊዜ አራት መቶ ሜትር አሜሪካዎች ሲያሸንፉ አውሮፓ ሁለተኛ እንዲሁም አፍሪቃ ሶሥተኛ ሆነዋል። በምርኩዝ ዝላይ ስቲቭ ሁከር በ 5,95 ሜትር ለእሢያ-ፓሢፊክ ሲያሸንፍ ሬኖው ላቪሌኒ አውሮፓን ለሁለተኝነት አብቅቷል። በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ድሉ የአፍሪቃ ነበር። ሪቻርድ ኪፕኬምቦይ አንደኛ ጋሪ ሮባም ሁለተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል።

በሶሥት ሺህ ሜትር መደበኛ ሩጫ በርናርድ ላጋት ለአሜሪካዎች ሲያሽንፍ ሞሰስ ኪፕሢሮ አፍሪቃን ለሁለተኝነት አብቅቷል፤ ታሪኩ በቀለ አራተኛ! በተረፈ የዲስከስና የጦር ውርወራው ድል የአውሮፓ ሲሆን በሁለት መቶ ሜትር አሜሪካዎችና፤ በስምንት መቶም አፍሪቃ አሸንፈዋል። በሴቶች አውሮፓና እሢያ-ፓሢፊክ አይለው ሲታዩ የአፍሪቃ ድል የተመዘገበው በአምሥት ሺህ ሜትር ነበር። ቪቪያን ቼሩዮትና ስንታየሁ እጅጉ ቀዳሚ ሆነዋል።

በክፍለ-ዓለማቱ ዋንጫ ውድድር በአጠቃላይ ውጤት አውሮፓ በ 429 ነጥቦች ስታሽንፍ አሜሪካዎች በ 419 ሁለተኛ፤ አፍሪቃ በ 292 ሶሥተኛ፤ እንዲሁም እሢያ-ፓሢፊክ በ 286 ነጥቦች አራተኛ ሆነዋል። በቅይጥ ቡድን ደግሞ አሜሪካዎች በ 219 ነጥብ ሲያሸንፉ፤ አውሮፓ በ 210 ሁለተኛ፤ አፍሪቃ በ 148 ሶሥተኛ፤ እሢያ-ፓሢፊክ በ 134 ነጥብ አራተኛ ወጥተዋል።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ