የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 10.05.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት እየተቃረበ ነው። ውድድሩ ሊጀመር አራት ሣምንታት ያህል ብቻ ናቸው የቀሩት።

default

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር በፊታችን ሰኔ አራት ቀን ጆሃንስበርግ ውስጥ በአስተናጋጇ አገርና በሜክሢኮ ግጥሚያ ይከፈታል። ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪቃ ምድር መካሄዱ ታሪካዊ ሲሆን ክፍለ-ዓለሚቱን ወክለው የሚሳተፉት አገሮች ቢቀር እስከ ሩብ ፍጻሜ በመድረስ ስኬታማ ውጤት እንዲያስመዘግቡ የሚሹት ደጋፊዎቻቸው ብዙዎች ናቸው።

እስካሁን ታላቁ የአፍሪቃ ስኬት እ.ጎ.አ. በ 1990 ዓ.ም. ካሜሩን ኢጣሊያ ውስጥ እስከ ሩብ ፍጻሜ በመዝለቅ ያስመዘገበችው ውጤት ነበር። በጊዜው ያ ድንቅ የካሜሩን ብሄራዊ ቡድን ጀርመንንና እንግሊዝን የመሳሰሉትን ታላላቅ ቡድኖች ብርክ ሲያስይዝ የአውሮፓውያኑ ብልጠት ባይጎለው ኖሮ ለፍጻሜ በደረሰም ነበር። ግን አልሆነም። እርግጥ ዛሬ በርካታ የአፍሪቃ ኮከቦች በአውሮፓ ቀደምት ክለቦች ውስጥ የሚጫወቱ ሲሆን የተጋጣሚን ጨዋታ ማሰናከልና ማክሽፍን የመሳሰለውን ዘዴ ሁሉ ተክነውታል። የአፍሪቃ እግር ኳስ ጥበብም ከፍተኛ ዕርምጃ ማድረጉ የተመሰከረለት ነገር ነው።

እንደ ዶቼ ቬል የስፖርት ፕሮግራም ክፍል ባልደረባ እንደ አርኑልፍ በትቸር ከሆነበ አፍሪቃ ምድር በሚካሄደው በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ውድድር ከክፍለ-ዓለሚቱ ተሳታፊዎች በተለይም ከደቡብ አፍሪቃ ብዙ ሊጠበቅ የሚችል ነው።

“አንዱ የአፍሪቃ ቡድን ከመጨረሻዎቹ ስምንት ወይም ከዚያም አልፎ ከመጨረሻዎቹ አራት መካከል ሊሆን እንደሚችል ዕምነቴ ነው። እርግጥ ይህ በመጀመሪያዎቹ ግጥሚያዎች ሂደት ላይ ጥገኛ የሚሆን ነው። ማለት ቡድኖቹ ጥሩ ጅማሮ ማድረጋቸው ወሣኝነት አለው። አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃ ለምሳሌ ምንም እንኳ ከባድ ምድብ ቢገጥማትም በገዛ ደጋፊዎቿ ፊት ወደፊት ልትገፋ የምትችል ናት። የምድቡን ዙር ተቋቁማ ካለፈች በድንቅ ደጋፊዎቿ ስሜት እየተገፋች ወደፊት ልትራመድ ትችላለች። ጋናስ ቢሆን? በመሠረቱ የአፍሪቃ አገሮች በአጨዋወት በጠቅላላው ጠንካሮች ናቸው። ታዲያ በዚህ ለአፍሪቃ የመጀመሪያው በሆነው የዓለም ዋንጫ ውድድር ሁሉም ወደፊት ለመዝለቅ ዕድላቸውን እንደሚጠቀሙ እርግጠኛ ነኝ። አንዱ ወይም ሌላው ይሳካለታል”

በዓለም ዋንጫው ውድድር ታሪክ ውስጥ በየዋዜማው ለዋንጫ ባለቤትነት ትልቅ ዕድል ሲሰጣቸው ከቆዩት ሃያል ተብዬ ሃገራት መካከል በተለይም ብራዚል፣ ኢጣሊያና ጀርመን ይገኙበታል። ታዲያ ባለፉት ጊዜያት ምናልባትም ከብራዚል በስተቀር ሌሎቹ ያን ያህል የተለመደው ጥንካሬ የሚታይባቸው አልነበሩም። ይሁን እንጂ አርኑልፍ በትቸር እንደሚለው የጀርመን ቡድን ዘንድሮም በደቡብ አፍሪቃው የዓለም ዋንጫ ውድድር ከቀደምቱ መካከል አንዱ መሆኑ የማይቀር ነው።

“የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ሁሌም በዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ጥሩ ቡድን ነው። ተከታታይ ግጥሚያዎች ለሚደረጉበት ውድድር ተስማሚው ጽናት ያለው መሆኑ ይታወቃል። ማለት ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየጠነከረ የሚሄድ ነው። በአጀማመር በምድቡ ዙር ምናልባት ከበድ ያሉ ጨዋታዎች ቢገጥሙትም የኋላ ኋላ አብዛኛውን ጊዜ ወሣኝ ዕርምጃ ማድረጉ ሲሳካለት ነው የቆየው። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥም ሁኔታው ከዚህ የተለየ የሚሆን አይመስለኝም። የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ቢያንስ ከግማሽ ፍጻሜው መድረስ ይችላል”

ይሁንና የጀርመን ቡድን በወቅቱ ከአራት ዓመታት በፊት የነበረውን ጥንካሬ አያንጸባርቅም። የቀደምት ተጫዋቾቹም ፍቱንነት እየቀነሰ መሄዱ ነው ጎልቶ የሚታየው።

“አዎን፤ ግን አሠልጣኙ የአኺም ሉቭ ልምድ ያላቸውን በዕድሜ ገፋ ያሉትንና ወጣቶቹን በመምረጥ ጥሩ ድብልቅ የፈጠረ ይመስለኛል። እርግጥ የቆዩት ክሎዘን፣ ጎሜስንና ፖዶልስኪን የመሳሰሉት ተጫዋቾች በወቅቱ በቡንደስሊጋው ውስጥ በጥሩ ጥንካሬ ላይ አይደሉም። ጎል ማስቆጠሩ አልሆነላቸውም። ግን ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ ጠንክረው እንደሚቀርቡ አምናለሁ። በሌላ በኩል አሠልጣኙ ወጣቶቹን ተጫዋቾች የባየርኑን ቶማስ ሙለርንና ቶኒ ክሮስን ከነዚሁ ማቀላቀሉ ጥሩ ነገር ነው። ባየርን ሙንሺን የጀርመን ሻምፒዮን መሆኑና ለሻምፒዮና ሊጋና ለፌደሬሺን ዋንጫ ፍጽሜ የመድረሱ ሚስጥርም ይሄው ይመስለኛል። አንጋፋና ወጣት ተጫዋቾች መቀላቀላቸው ጀርመንን ቢቀር እስከ ግማሽ ፍጻሜ የሚያደርስ ነው”

የዶቼ ቬለ የስፖርት ክፍል ባልደረባ አርኑልፍ በትቸር ብራዚልና ኢጣሊያም ቀደምቱ እንደሚሆኑ ሲተነብይ በተለይ ቅድሚያ የሚሰጠው ግን ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ያለማቋረጥ ጠንካራ ሆኖ ለቆየው ለስፓኝ ብሄራዊ ቡድን ነው። እንደርሱ አባባል ስፓኝ በዓለም ዋንጫው ባለቤት ማንነት ላይ ወሣኝ ሚና ሳይኖራት የሚቀር አይመስልም።

“እርግጥ ነው የተጠቀሱት ሶሥት ቡድኖች በሙሉ ለዋንጫ ባለቤትነት ዕድል ያላቸው ናቸው። ብራዚል በዓለም ዋንጫ ላይ ሁሌም ከቀደምቱ መካከል አንዷ ናት። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥም ግሩም ሚና ይኖራታል። ኢጣሊያም አቅድ ባለው ስልት ስለምትጫወት በቀደምትነት የምትጠበቅ ናት። አሁን በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የኢንተር ሚላን ለፍጻሜ መድረስ የሚያመለክተው ይህንኑ ጥንካሬ ነው። ከኢጣሊያ ሌላ የአውሮፓ ሻምፒዮን የሆነችው ስፓኝ ትልቅ ሚና እንደሚኖራት እርግጠኛ ነኝ። ብሄራዊ ቡድኗ ብዙ አብሮ የቆየና የተላመደ፤ ፍቱን አጨዋወት ያለውም ነው። እና የዓለም ዋንጫ ባለቤት ለመሆን ስፓኝን ማለፍ ግድ የሚሆን ይመስለኛል። ለኔ ትልቁ የዋንጫ ዕድል ያላት ስፓኝ ናት”

እያንዳንዱ የዓለም ዋንጫ ውድድር እስካሁን ጊዜው ያፈራው የራሱ ኮከብ ነበረው። ፔሌና ማራዶና ከነዚሁ መካከል ላቅ ያሉት ነበሩ። ዘንድሮስ ተራው የማነው?

“አብዛኛውን ጊዜ በብሄራዊ ሊጋዎች ውስጥ ድንቅ የሆኑት ተጫዋቾች ይህ አይሳካላቸውም። ሌሎች ያልተጠበቁ ብቅ ይላሉ። እርግጥ ታላላቆቹ ኮከቦች እንበል ካካንና ሜሢን የመሳሰሉት ብዙውን ጊዜ ደክመው ነው ወደ ዓለም ዋንጫው ውድድር የሚሄዱት። እርግጥ ጥንካሬያቸውን ማሰየት ከቻሉ ዕድሉ አያመልጣቸውም። በተለይ ሜሢ በወቅቱ በአውሮፓ ድንቁ ተጫዋች ነው። ከርሱ ብዙ ሊጠበቅ ይችላል”

የአውሮፓ ሊጋዎች ብሄራዊ ውድድር

Fussball FC Chelsea Michael Ballack

ሚሻኤል ባላክ

በአውሮፓ ቀደምት ክለቦች ብሄራዊ የእግር ኳስ ውድድር በአንዳንዶቹ ሻምፒዮናው ሲለይለት በተቀሩት ደግሞ ከግቡ እየተቃረበ ነው። በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሺን ሰንበቱን 22ኛ ብሄራዊ ሻምፒዮንነቱን በማረጋገጥ በደመቀ ሆኔታ ሲያከብር በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ቼልሢይ የድል ባለቤት ሆኗል። ኤፍ.ሢ.ቼልሢይ የቅርብ ተፎካካሪው ማንቼስተር ዩናይትድ ለአራተኛ ጊዜ በተከታታይ ሻምፒዮን እንዳይሆን በሩን የዘጋው ዊጋን አትሌቲክን 8-0 በማሸነፍ ነበር።
ለቼልሢይ ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው የአይቮሪ ኮስቱ ኮከብ ዲዲየር ድሮግባ ነው። ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ ግጥሚያ ስቶክ ሢቲይን 4-0 ቢረታም በአንዲት ነጥብ ተበልጦ በሁለተኝነት መወሰኑ ግድ ሆኖበታል። በፖርቱጋል ሻምፒዮናም ቤንፊካ ሊዝበን ከአምሥት ዓመታት ጥበቃ በኋላ ውድድሩን በአንደኝነት ሊፈጽም ችሏል። ቤንፊካ ሪዮ አቬን 2-1 ሲረታ ብራጋ በክለቡ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለተኝነት በቅቷል።

ባለፈው ሣምንት በፈረንሣይ ማርሤይና በኔዘርላንድ ደግሞ ኤንሼዴ አዳዲሶቹ ሻምፒዮኖች ሲሆኑ በኢጣሊያና በስፓኝ ሊጋዎች ግን የዋንጫው ውሣኔ ለመጪው ሣምንት የመጨረሻ ግጥሚያ ተሸጋግሯል። ኢንተር ሚላን ሮማን በሁለት ነጥብ ልዩነት የሚያስከትል ሲሆን ባርሤሎና ደግሞ ሬያል ማድሪድን የሚመራው በአንዲት ነጥብ ብቻ ነው። እናም ውድድሩ እስከመጨረሻዋ ዕለት ማራኪ እንደሆነ ይቀጥላል።

የአዳራሽ ውስጥ የበረዶ ሆኪይ የዓለም ሻምፒዮና

Eishockey WM Russland Slowakei

ጀርመን ውስጥ የሚካሄደው የአዳራሽ ውስጥ የበረዶ-ሆኪይ የዓለም ሻምፒዮና ተመልካችን በመሳብም አስደናቂ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። ውድድሩ ባለፈው አርብ ምሽት በይፋ ሲከፈት በስታዲዮሙ ከ 77 ሺህ የሚበልጥ ተመልካች መገኘቱም ራሱ የዓለም ክብረ-ወሰን ነበር። በአራት ምድቦች ተከፍሎ በሚካሄደው የመጀመሪያ ዙር ውድድር በምድብ-አንድ ውስጥ ቤላሩስ ከካዛክስታን 5-2፤ እንዲሁም ስሎቫካይ ከሩሢያ 1-3 ሲለያዩ በምድብ-ሁለት ካናዳ ኢጣሊያን 5-1፤ ስዊዝም ሊቱዋኒያን 3-1 አሸንፋለች።

በምድብ ሶሥት ቼኮች ፈረንሣይን 6-2 ሲያሸንፉ ኖርዌይ ከስዊድን 2-5 ተለያይታለች። በምድብ አራት አስተናጋጇ ጀርመን ከተጨማሪ ሰዓት በኋላ አሜሪካን 2-1 ስታሸንፍ ፊንላንድ በዴንማርክ 1-4 ተረትታለች። ጀርመን ማምሻውን ሁለተኛ ግጥሚያዋን ከፊንላንድ ጋር የምታካሂድ ሲሆን ሌሎቹ የዛሬ ግጥሚያዎች አሜሪካ ከዴንማርክ፤ ስዊዝ ከኢጣሊያና ሊቱዋኒያ ከካናዳ ናቸው። የተቀሩት ሁለተኛ የምድብ ግጥሚያዎች ደግሞ ነገ ይካሄዳሉ።

Formel 1 Mai 2010 F1

ማርክ ዌበር

ዘገባችንን በአውቶሞቢል እሽቅድድም ለማጠቃለል ትናንት ባርሤሎና ላይ የተካሄደው የፎርሞላ-አንድ እሽቅድድም አሸናፊ የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ሆኗል። የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ እሽቅድድሙን በሁለተኝነት ሲፈጽም ሶሥተኛና አራተኛ የሆኑት ጀርመናውያኑ ዜባስቲያን ፌትልና ሚሻኤል ሹማኸር ናቸው። የሰባት ጊዜው የዓለም ሻምፒዮን ሹማኸር ዘንድሮ ወደ ውድድሩ እንደገና ከተመለሰ ወዲህ አራተኛው ቦታ ግሩም ውጤቱ መሆኑ ነው። በጠቅላላ ነጥብ የብሪታኒያው ጄሰን ባተን በ 70 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን አሎንሶ በ 67 ሁለተኛ፤ እንዲሁም ፌትል በ 60 ሶሥተኛ ነው። ሹማኸር በ 22 ነጥቦች ዘጠነኛ!

RTR/AFP
MM/HM