የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 05.05.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

አትሌቲክስ፣ እግር ኳስ፣ ቴኒስ

ቡንደስሊጋ፤ የቮልፍስቡርግ ጎል አግቢ ኤዲን ጄኮ (መሃል)

ቡንደስሊጋ፤ የቮልፍስቡርግ ጎል አግቢ ኤዲን ጄኮ (መሃል)

አትሌቲክስ

ያለፈውም ሰንበት ቀደም እንዳሉት ሁሉ በዓለም ዙሪያ የተለያዩ የአትሌቲክስ ውድድሮች የተካሄዱበት ነበር። የኬንያው አትሌት ሚካህ ኮጎ ትናንት ስኮትላንድ ኤዲንበርግ ላይ ተካሂዶ የነበረው የአደባባይ አሥር ኪሎሜትር ሩጫ አሸናፊ ሆኗል። ኮጎ ከአምሥት ሣምንታት በፊት በዚህ ርቀት የሃይሌ ገ/ሥላሴን ክብረ-ወሰን ማሻሻሉ አይዘነጋም። የቤይጂንጉ ኦሎምፒክ የአሥር ሺህ ሜትር የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ በሰባተኛው ኪሎሜትር ላይ አስደናቂ በሆነ ፍጥነት ተፎካካሪዎቹን ሲያመልጥ ሁለተኛ የሆነውም ያለፈው ዓመት የኤዲንበርግ አሸናፊ ኬንያዊ በርናርድ ኪፕየጎ ነው። የስፓኙ ቼሞ ማርቲኔዝ ደግሞ ውድድሩን በሶሥተኝነት ፈጽሟል።

በትናንቱ ዕለት በኢጣሊያ ትሪየስት በተካሄደ የአውሮፓ ማራቶን ሩጫ በወንዶች ኬንያዊው ኪፕቺርቺር ኪፕሮኖ፤ በሴቶች ደግሞ ብራዚላዊቱ ናዲር-ሣቢኖ-ዴ-ሢኩዌይራ ለድል በቅተዋል። ኪፕሮኖ ሩጫውን በ 2 ሰዓት ከ 14 ደቂቃ ከ 48 ሤኮንድ ሲፈጽም ሌላው ኬንያዊ ፊሊፕ ኪፕኮች ሁለተኛ፤ የሞሮኮው ቼርካዊ ላላሚ ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል። በሴቶች የብራዚሏን ናዲርን ተከትለው ሁለተኛና ሶሥተኛ በመሆን የፈጸሙት የኢጣሊያ አትሌቶች ስቴፋኒያ ሣቲኒና ፓኦላ ፒሎን ናቸው። የሰንበቱ የኬንያ የረጅም ርቀት ሯጮች ድል በዚህ ቭቻ አላበቃም። በዚህ በጀርመን በዱስልዶርፍ ማራቶንም ዴቪድ ላንጋት የአገሩን ልጅ ዊልፍሬድ ኪገንን አስከትሎ ከግቡ በመድረስ አሸናፊ ሆኗል። ሶሥተኛ የወጣው ጀርመናዊው አንድሬ ፑልሜሸር ነው። በሴቶች ደግሞ ጀርመናዊቱ ተወዳዳሪ ሱዛነ ሃን አሸናፊ ሆናለች።

ኬንያ በፊታችን ነሐሴ ወር በዚህ በጀርመን በርሊን ላይ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይም ከወዲሁ እያተኮረች ነው። የቤይጂንጉ ኦሎምፒክ የማራቶን ባለድል ሣሚይ ዋንጂሩና የሁለት ጊዜዋ የብር ሜዳይ ተሸላሚ ካቴሪን እንዴሬባ የአገሪቱን ቡድን እንዲመሩ መመረጣቸውን የናይሮቢ ባለሥልጣናት ሰሞኑን አስታውቀዋል። ሃያ አትሌቶችና አሥር ተቀያሪዎች በጊዜያዊነት ሲሰየሙ በዚህ ሣምንት ልምምድ ይጀምራሉ። ባለፈው ሣምንት የለንደንን ማራቶንም በጥሩ ሰዓት ያሸነፈው ዋንጂሩ በመጪው መስከረም የበርሊን ማራቶን የሃይሌ ገ/ሥላሴን የዓለም ክብረ-ወሰን ለማሻሻልም ያልማል።

በተረፈ ጃሜይካ-ኪንግስተን ላይ ባለፈው ቅዳሜ ተካሂዶ በነበረ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር አሜሪካዊው ዳርቪስ ፓተን በመቶና ሁለት መቶ ሜትር ሩጫ አሸናፊ ሆኗል። ዳርቪስ ለዚህ የበቃው ጃማይካዊው የአሎምፒኩ ባለድልና የዓለም ክብረ-ወሰን ባለቤት ኡሤይን ቦልት በአካል ጉዳት ሳቢያ በውድድሩ ሊሳተፍ ባለመቻሉ ነው። በሴቶች መቶ ሜትር ሩጫ ደግሞ ጃማይካዊቱ የኦሎምፒክ የብድ ሜዳይ ተሸላሚ ኬረን ስቱዋርት የዓመቱን ፈጣን ጊዜ በማስመዝገብ አሸንፋለች። ውድድሩ በተለይ በሴቶች ከመሰናክል ሩጫ በስተቀር ከመቶ እስከ አራት መቶ ሜትር ጃማይካ በአሜሪካ ላይ እንደገና ልዕልና ያሳየችበት ነበር።

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር ዘንድሮ ሻምፒዮን የሚሆኑት ክለቦች ማንነት ከሞላ-ጎደል ሊለይለት እየተቃረበ ነው። ኢንተር ሚላን፣ ባርሤሎናና ማንቼስተር ዩናይትድ በሰንበቱ ድላቸው በሻምፒዮንነቱ አቅጣጫ ወሣኝ ዕርምጃ አድርገዋል። በተለይ በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና የቅርብ ተፎካካሪውን ሬያል ማድሪድን ለውርደት ነው የዳረገው። ኢንተር እንዲያውም በመጪው ሣምንት ቀድሞ ሻምፒዮንነቱን ለማረጋገጥ ይችላል።

በኢጣሊያው ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን የሰባት ነጥብ ብልጫውን እንደያዘ ለመቀጠል የቻለው ላሢዮን 2-0 በመርታቱ ነው። የስዊድኑ ጎል አግቢ ዝላታን ኢብራሂሞቪች የመጀመሪያዋን ጎል ራሱ ሲያስቆጥር ሁለተኛዋንም በማዘጋጀት እንደገና የቡድኑ የድል ዋስትና ነበር። ሁለተኛው ኤ.ሢ.ሚላንም ካታኛን በተመሳሳይ ውጤት ሲያሸንፍ ሻምፒዮን የመሆን ዕድሉ ግን እየጠበበ ነው። በመጪው ሣምንት ከተሸነፈ ጨርሶ ሊያከትምለት ይችላል። ጁቬንቱስ ባለፉት ሣምንታት የመንሸራተት ሂደቱ በመቀጠል ከሌቼ ጋር 2-2 በሆነ ውጤት ሲወሰን ከኤ.ሢ.ሚላን ጋር ያለው የነጥብ ልዩነት ወደ አራት ከፍ ብሏል። ቶሪኖን 1-0 የረታው ፊዮሬንቲና በአምሥት ነጥቦች ዝቅ ብሎ በአራተኝነት ይከተለዋል።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን በሁለት ክለቦች መካከል ሲካሄድ የቆየው የሻምፒዮና ፉክክር ገጽታ ቢቀር ካለፈው ቅዳሜ ወዲህ በጣሙን ተለውጧል። ሁለቱ ቀደምት ቡድኖች እርስበርሳቸው ባደረጉት ግጥሚያ ሬያል ማድሪድ በገዛ ሜዳው በቤርናቤው ስታዲዮም በባርሤሎና 6-2 ሲቀጣ ሬያል እንደ ቅጽል ስያሜው ንጉሣዊ አልነበረም። ባርሤሎና በአንጻሩ የሊጋው ውድድር ሊፈጸም አራት ግጥሚያዎች ብቻ ቀርተው ሳለ አመራሩን ወደ ሰባት ነጥቦች ከፍ ለማድረግ ችሏል። የባርሣ ዓለምአቀፍ ከዋክብት ሊዮኔል ሜሢና ቲየሪ ኦንሪ በየፊናቸው ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥሩ የተቀሩትን ሁለት ጎሎች ያስገቡት ደግሞ ተከላካዮቹ ካርሌስ ፑዮልና ዤራርድ ፒኬ ነበሩ። ሤቪያ ቪላርሬያልን 2-0 በማሽነፍ ሶሥተኝነቱን ሲያጠብቅ አራተኛው ቫሌንሢያ በኤስፓኞል 3-0 ተረትቷል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ቮልፍስቡርግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን በያዘው ዕድል ወደፊት መገስገሱን ቀጥሏል። ቡድኑ የመጀመሪያውን ዙር ሃያል ክለብ ሆፈንሃይምን 4-0 ሲቀጣ አመራሩን ወደ ሶሥት ነጥብ ለማስፋትም ችሏል። የዕለቱ ድንቅ ተጫዋቹ በ 12 ደቂቃዎች ውስጥ ሶሥቱን ጎሎች ያስቆጠረው ኤዲን ጄኮ ነበር። የአገሪቱ የብዙ ጊዜ ሻምፒዮን ባየርን ሙንሺንም ከሣምንት በፊት አሠልጣኙን ዩርገን ክሊንስማን ካሰናበተ በኋላ በአስደናቂ ጨዋታም ባይሆን መንሸን-ግላድባህን 2-1 በማሽነፍ በሁለተኛው ቦታ ላይ ተቆናጧል። ሁለቱ ክለቦች በቀሪዎቹ አራት ግጥሚያዎች ተመሳሳይ ፕሮግራም ሲኖራቸው የቮልፍስቡርግ አሠልጣኝ ፌሊክስ ማጋት ባልተለመደ ሁኔታ ነው የቡድኑን በራስ መተማመን ያንጸባረቀው።

“በኔ አመለካከት ፕሮግራማችን አሁን ከባየርን ጋር አንድ ዓይነት ነው። ሆኖም እኛ የሶሥት ነጥቦች ብልጫ አለን። በቀደምትነት እንመራለን። እና ሁሉም ክለቦች እስከምንንሸራተት መጠበቅ አለባቸው። አለበለዚያ አልፈውን ሊሄዱ አይችሉም”

ከቀደምቱ ክለቦች መካከል በርሊንና ሃምቡርግ ትናንት እኩል ለእኩል 1-1 ሲለያዩ ውጤቱ ለሁለቱም መጥቀሙ የሚያጠያይቅ ነው። ሽቱትጋርትም ከቢለፌልድ 2-2 በመለያየቱ ከባየርን ሙንሺን ጋር ለመስተካከል የነበረውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ለማንኛውም የቡንደስሊጋው ውድድር አራት ግጥሚያዎች ቀርተውት እንዳለ አምሥቱም ቡድኖች ሻምፒዮን የመሆን ዕድል አላቸው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ሚድልስቦሮህን 2-0 በማሽነፍ በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የተቃረበ ይመስላል። ማኒዩ አንድ ግጥሚያ ጎሎት 80 ነጥቦች ሲኖሩት የቅርብ ተፎካካሪው ሊቨርፑልም ኒውካስል ዩናይትድን 3-0 በመርታት በ 77 ነጥቦች በቅርብ መከተሉን እንደቀጠለ ነው። በአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ግማሽ ፍጻሜ ላይ የሚገኙት ቼልሢይና አርሰናልም የየበኩላቸውን ግጥሚያዎች ቢያሽንፉም ከማንቼስተር ዩናይትድ ስድሥት ነጥቦች ዝቅ ላለው ለሶሥተኛው ኤፍ.ሢ.ቼልሢይ የሻምፒዮንነቱ ነገር አልቆለታል ለማለት ይቻላል።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ኦላምፒክ ማርሤይ ከ 17 ዓመታት ቆይታ በኋላ እንደገና ሻምፒዮን ለመሆን ያገኘውን ጥሩ አጋጣሚ ለመጠቀም ሰንበቱን ወኔው የከዳው መስሎ ነው የታየው። ቡድኑ በገዛ ሜዳው ከቱሉዝ ጋር 2-2 ብቻ ተለያይቷል። የማርሤይ በዚህ ውጤት መወሰን የጠቀመው ለቅርብ ተፎካካሪው ለዢሮንዲን ቦርዶ ነው። ቦርዶ ሶሾን 3-0 ሲረታ ከማርሤይ እኩል 68 ነጥቦች አሉት፤ የሚበለጠው በጎል ልዩነት ብቻ ነው። በሌላ በኩል ለስምንተኛ ጊዜ በተከታታይ የፈረንሣይ ሻምፒዮን ለመሆን በመነሣሣት ውድድሩን የጀመረው ኦላምፒክ ሊዮን በቫሌንሢየን ተሸንፏል። ሊዮን ከሣምንታት ወዲህ በሚያሣየው የማቆልቆል ሂደቱ ሶሥተኝነቱንም እንዳያጣ በጣሙን ነው የሚያሰጋው።

በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶ እንደገና ለሻምፒዮንነቱ እየተቃረበ ሲሆን የኡክራኒያው ዲናሞ ኪየቭ ውድድሩ ሊያበቃ አራት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ለ 13ኛ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የምትጎለው አንዲት ነጥብ ብቻ ናት። በስኮትላንድ ፕሬሚየር ሊግ ሤልቲክ ግላስጎውና ግላስጎው ሬንጀርስ በትንንቅ መሰል ሁኔታ ላይ ናቸው። ሤልቲክ በ 77 ነጥቦች ሲመራ ሬንጀርስ አንዲት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብለው ይከተሉታል። በፊታችን ሣምንት ሁለቱ ክለቦች እርስበርስ የሚገናኙ ሲሆን ግጥሚያው ለሻምፒዮናው ወሣኝ ሊሆን የሚችል ነው። በተቀረ የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮና ሊጋ ግማሽ ፍጻሜ የመልስ ግጥሚያዎች ነገና ከነገ በስቲያ ይካሄዳሉ። በነገው ዕለት የሚጋጠሙት ሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች አርሰናልና ማንቼስተር ዩናይትድ ሲሆኑ በማግሥቱ ረቡዕ ደግሞ ተራው የቼልሢይና የባርሤሎና ነው። በመጀመሪያው ግጥሚያ ማንቼስተር ዩናይትድ አርሰናልን 1-0 ሲረታ ባርሤሎናና ቼልሢይ ደግሞ ባዶ-ለባዶ ነበር የተለያዩት።

ቴኒስ

በቴኒስ የማዕርግ ተዋረድ ላይ ቀደምቱ የሆነው የስፓኝ ኮከብ ራፋኤል ናዳል ትናንት ሮም ላይ በተካሄደ ዓለምአቀፍ የቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ ያለፈውን ዓመት ሻምፒዮን የሰርቢያውን ኖቫክ ጆኮቪችን በሁለት ምድብ ጨዋታ ለማሸነፍ በቅቷል። ለናዳል የትናንቱ አራተኛው የሮም ማስተርስ ድል መሆኑ ነበር። ለጆኮቪች በአንጻሩ የትናንቱ ሽንፈት ሌላም ተጽዕኖ ይኖረዋል። በቴኒሱ ማዕረግ ተዋረድ ላይ የያዘውን ሶሥተኛ ቦታ ለብሪታኒያዊው ኤንዲይ መሪይ ማስረከብ ግድ ነው የሚሆንበት። በዚሁ ኤንዲይ መሪይ ከቁንጮዎቹ ሶሥት ታላል ተጫዋቾች መካከል ሲመደብ የመጀመሪያው የብሪታኒያ ቴኒስ ተጫዋች ይሆናል። በዚህ በጀርመን በሽቱትጋርት ግራን-ፕሪ የሴቶች ፍጻሜ ደግሞ ሩሢያዊቱ ስቬትላና ኩዝኔትሶቫ በዓለም ላይ በወቅቱ አንደኛ የሆነችውን የአገሯን ልጅ ዲናራ ሣፊናን በለየለት 6-4, 6-3 ውጤት ለማሸነፍ በቅታለች። ኩዝኔትሶቫ ለፍጻሜ ድል ስትበቃ ከሁለት ዓመት ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።

MM/DWAFP/RTR

መስፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ