የስፖርት ዘገባ | ስፖርት | DW | 27.08.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ

የጀርመን የእግር ኳስ ቡንደስሊጋ ከበጋው እረፍት በኋላ ባለፈው አርብ ወደ 50ኛ የውድድር ወቅቱ ሲመለስ በምሽቱ በተካሄደው የመጀመሪያ ግጥሚያም

default

ቴኦዶር ገብረ ሥላሴ

የጀርመን የእግር ኳስ ቡንደስሊጋ ከበጋው እረፍት በኋላ ባለፈው አርብ ወደ 50ኛ የውድድር ወቅቱ ሲመለስ በምሽቱ በተካሄደው የመጀመሪያ ግጥሚያም በአባቱ በኩል ኢትዮጵያዊ ምንጭ ያለው የቼክ ሬፑብሊክ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች ቴኦዶር ገ/ሥላሴ ለብሬመን አንድ ጎል በማስቆጠር ስሙ ከሊጋው ማሕደር ውስጥ ጠቃሚ ቦታ እንዲይዝ ለማድረግ በቅቷል። የዚህ ወጣት ተጫዋች ታሪክ በቅርቡ የምንመለስበት ነው።

በአፍላ ደረጃው በሚገኘው የአውሮፓ ሊጋዎች ውድድር በቅድሚያ በስፓኝ ላ ሊጋ ላይ እናተኩርና ሁለተኛ ሣምንቱን በያዘው ሻምፒዮና ያለፈው ሻምፒዮን ሬያል ማድሪድ ትናንት በጌታፌ 2-1 በመሸነፍ ይብስ ወደ 15ኛው ቦታ አቆልቁሏል። ሬያል በመጀመሪያ ግጥሚያውም በእኩል-ለእኩል ውጤት ሲወሰን አሁን ያለችው አንዲት ነጥብ ብቻ ናት። ባርሤሎና በአንጻሩ ኦሣሱናን 2-1 በመርታት ስድሥት ነጥቦች ሲኖሩት በወቅቱ የሊጋው ቁንጮ ነው። ለባርሣ ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው አርጄንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሢ ነበር። ራዮ ቫሌካኖ ደግሞ ቤቲስን በተመሳሳይ ውጤት በማሸነፍ እኩል ስድሥት ነጥብ ይዞ በሁለተኝነት ይከተላል።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ውድድሩ ሰንበት ሲል ያለፈው የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የዋንጫ ባለቤት ኤፍ ሢ ቼልሢይ ባለፈው ቅዳሜ ኒውካስል ዩናይትድን 2-0 በመርታት በጥሩ ጅማሮው ቀጥሏል። ቼልሢይ በእስካሁን ሶሥት ግጥሚያዎቹ በሙሉ ሲያሸንፍ ሊጋውን በዘጠኝ ነጥቦች ለብቻው ይመራል። ስዋንሢ ሢቲይና ኤቨርተን በሁለት ግጥሚያዎች በማሸነፍ በስድሥት ነጥቦች ተከታዮቹ ሲሆኑ ያለፈው ወቅት የፕሬሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ማንቼስተር ሢቲይም ከሊቨርፑል 2-2 በመለያየት አምሥተኛ ቦታውን ለመጠበቅ ችሏል።

ማንቼስተር ዩናይትድ በበኩሉ በሶሥት ነጥቦች ሰባተኛ ነው። ከዚሁ ሌላ በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ኢንተር ሚላን፣ በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ኦላምፒክ ማርሤይና በፖርቱጋል ሻምፒዮናም ቤንፊካ ሊዝበን በየፊናቸው ይመራሉ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ቀደም ሲል እንደጠቀስነው 50ኛው የውድድር ዓመት ሲጀመር ስለ ዘንድሮው ውድድር ሂደት፣ ስለ ሻምፒዮንነቱ ተሥፋና ኢትዮጵያዊ ምንጭ ስላለው የብሬመን ተከላካይ ስለ ቴኦዶር ገብረ ሥላሴ የዶቼ ቬለን የጀርመንኛ ፕሮግራም የስፖርት ዝግጅት ክፍል ባልደረባ አርኑልፍ በትቸርን አነጋግሬ ነበር።

በሰፊው እንደተጠበቀው ጠንካሮቹ ክለቦች ባየርን ሙንሺንና ዶርትሙንድ የየበኩላቸውን መክፈቻ ግጥሚያ በማሸነፍ ጥሩ ጅማሮ ነው ያደረጉት። ሻምፒዮንነቱ በነዚሁ መካከል ይለይለታል የሚሉት ታዛቢዎችም ታዲያ በወቅቱ ጥቂቶች አይደሉም። ለአርኑልፍ በትቸር ደግሞ የባየርን ዕድል የላቀ ነው።

«አዎን፤ ሁለቱ ትልቅ ዕድል የሚሰጣቸው ቡድኖች ዶርትሙንድና ባየርን ሙንሺን መክፈቻ ግጥሚያቸውን አሸንፈዋል። በእርግጥ እነዚህ ሁለት ክለቦች ናቸውም ሻምፒዮን ለመሆን የሚፎካከሩት። ዶርትሙንድ በተከታታይ ለሶሥተኛ ጊዜ ባለድል ለመሆን ይፈልጋል። ባየርንም ሻምፒዮንነቱን ከሶሥት ዓመታት በኋላ እንደገና ወደ ሚዩኒክ ለመመለስ መነሣቱ አያጠራጥርም። በተቀረ ሌሎቹ ቡድኖች ከነዚህ መፎካከር ይችላሉ ብዬ አላስብም። ማን ሻምፒዮን ይሆናል ስላልከኝ በዘንድሮው ውድድር ባየርን ሙንሺን መልሶ የጀርመን ሻምፒዮን እንደሚሆን ነው የማምነው። ምክንያቱን ቡድኑ በሚገባ ተጠናክሯል። እርግጥ ዶርትሙንድ መጥፎ አይደለም። ግን ጥቂት ኋላ ይቀራል ብዬ ነው የምገምተው»

ዶርትሙንድ ከተነሣ ክለቡ ባለፈው አርብ ምሽት ከወጣቱ የብሬመን ቡድን ጋር ያደረገውን ግጥሚያ ለተከታተለ በጣሙን ተንገዳግዶ ነበር፤ በዕድል ነው ያሸነፈው ለማለት ነው የሚቻለው። ሆኖም ግን እንደ በትቸር ዕምነት ከሆነ የቡድኑ አጨዋወት የድክመት ምልክት አልነበረም። በውድድሩ ሂደት እንዲያውም እየጠነከረ መሄዱ የማይቀር ነው።

«የድክመት ምልክት ነበር ብዬ አላስብም። ቨርደር ብሬመን በጣም ጥሩ ነበር የተጫወተው። ጨዋታው በከፍተኛ የቴክኒክ ደረጃ ነው የተካሄደው። እና በመጨረሻም ዶርትሙንድ ለማሸነፍ በቅቷል። እንግዲህ ቀድሞ ባየርን ሙንሺን ያደርግ እንደነበረው ወሣኝ ግጥሚያዎቹን ማሸነፉን እንደቀጠለ ነው። ዕድሉ ጠባብ ቢሆንም በአሸናፊነት ከሜዳ መውጣቱ ተሳክቶለታል።በጥቅሉ ዶርትሙንድ በአዲሱ የቡንደስሊጋ ውድድር ወቅትም ጠንካራ እንደሚሆንና በአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋም እንደሚቆናጠጥ ነው የምገምተው። ይህ የኋለኛው ባለፈው የውድድር ወቅት አልሆነለትም ነበር»

እርግጥ ሁለቱ ቀደምት ክለቦች የላቀ የሻምፒዮንነት ዕድል እንዳላቸው ይጠቀስ እንጂ የቡንደስሊጋ ታሪክ እንዳሳየው ሌሎች ያልተጠበቁ ክለቦች በመጨረሻ ቁንጮ ሆነው ሊገኙ የማይችሉበት ምክንያት በመሠረቱ አይኖርም። ለምሳሌ ሻልከ ወይም ዘንድሮ በአዳዲስ ተጫዋቾች በሰፊው የተጠናከረው ቮልፍስቡርግ በውድድሩ ሂደት ፈታኝ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም በዶቼ ቬለ የስፖርት ፕሮግራም ባልደረባ በአርኑልፍ በትቸር ግምት ዕድላቸው ውሱን ነው። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም።

«ሁለቱም ቡድኖች አከታትለው በጥንካሬ መጫወት አይችሉም። እናም ምናልባት ዕድላቸው ቢገፋ ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ተሳትፎ መብቃት ነው። ከባየርንና ከዶርትሙንድ ጋር ግን ለመፎካከር የሚችሉ አይሆኑም። ቦሩሢያ መንሸንግላድባህም ለነገሩ ራሱን በጥሩ ሁኔታ አጠናክሯል። ግን ይህም ክለብ በከፍተኛ ደረጃ መጫወቱ ባይቀርም ለሻምፒዮንነቱ ፉክክር የሚበቃ አይሆንም»

ብሬመን ላይ መለስ እንበልና ወጣት የሆነው የቡንደስሊጋ ቡድን በአጨዋወቱ እጅግ ማራኪና የወደፊት ተሥፋን የሚያዳብር ነበር ለማለት ይቻላል። ጥያቄው በዚህ ጥንካሬው መቀጠሉ ይሳካለታል ወይ ነው።

« ቨርደር ብሬመን በአጠቃላይ የውድድሩ ወቅት ሂደት እንደተባለው ወጣት ቡድን በመሆኑ ብዙ ችግር የሚገጥመው ይመስለኛል። ተጫዋቾቹ አሁን በጅምሩ በስሜት ጠንክረው ቢታዩም በሂደቱ ችግር ላይ መውደቃቸው የማይቀር ነገር ነው። ክለቡ ከአምሥተኛና ከስድሥተኛ ቦታ በላይ ይዘልቃል ብዬ አላስብም። እርግጥ በርደር ቴኦዶር ገ/ሥላሴን ወይም የአውስትሪያውን አጥቂ አናውቶቪችን የመሳሰሉ ግሩም ተጫዋቾች አሉት። ታዲያ ብሬመን የዘንድሮው ሣይሆን የወደፊቱ ቡድን ይሆናል ማለቱን ነው የምመርጠው»

ቴኦዶር ገብረ ሥላሴ በአባቱ በኩል ኢትዮጵያዊ ምንጭ ያለው በመሆኑ ለኛ ትልቅ ቅርበት ያለውና የትኩረታችን ማረፊያም ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። ቴዎ ገና በመጀመሪያ የቡንደስሊጋ ጨዋታው ለብሬመን ግሩም ጎል ሲስቆጠር ይህም በ50ኛው የውድድር ወቅት መክፈቻ ግጥሚያ ላይ በመሆኑ የተለየ ክብደት አለው። ኢትዮጵያዊ ምንጭ ያለው የመጀመሪያው የቡንደስሊጋ ተጫዋች ከአሁኑ ትልቅ ተወዳጅነትን ሲያተርፍ የወደፊት ዕድሉ ብሩህ እንደሚሆን ብዙዎች ከወዲሁ እየተነበዩ ነው።

«ቴዎ ገብረ ሥላሴ ገና ባለፈው የአውሮፓ እግር ኳስ ሻምፒዮና ላይ ለቼክ ብሄራዊ ቡድን በመጫወት ዓለምአቀፍ ትኩረትንና አድናቆትን ለመሳብ የበቃ ነው። ወጣቱ ገብረ ሥላሴ ግሩምና ቀልጣፋ ተጫዋች ሲሆን ትልቅ የወደፊት ተሥፋ ነው ያለው። ግን ለዘለቄታው በጀርመን ቡንደስሊጋ ውስጥ መቆየቱ አይታወቅም። ምናልባት ታላላቅ ዓለምአቀፍ ክለቦች ይሻሙበት ይሆናል። የሆነው ሆኖ ግን ትልቅ ዕርምጃ እንደሚያደርግ ነው የምገምተው»

የቴዎ ገብረ ስላሴን ታሪክ በቅርቡ በዝርዝር እንደምናቀርብላቸሁ ተሥፋ እናደርጋለን።

ፓራሊምፒክስ ነገ ይከፈታል

አካለ-ስንኩላን የሚሳተፉበት ፓራሊምፒክስ 30ኛው የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ ከተጠናቀቀ ከሁለት ሣምንት ተኩል ገደማ በኋላ በነገው ምሽት በደመቀ ስነ ስርዓት ይከፈታል። 11 ቀናት በሚፈጀው ውድድር ላይ 4,200 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን ጨዋታውን በይፋ የሚከፍቱት ንግሥት ኤልሣቤጥ ዳግማዊት ናቸው። የቻይና አትሌቶች ከአራት ዓመታት በፊት ቤይጆንግ ላይ እንደታየው አብዛኛውን ሜዳሊያ እንደሚወስዱ የሚገመት ሲሆን የብሪታኒያ ተሳታፊዎችም ብርቱ ተፎካካሪ ሆነው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

የፓራሊምፒክስ ታሪክ በዚያው በደቡባዊው እንግሊዝ አንድ ጀርመን-አይሁዳዊ ሃኪም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ከሶሥት ዓመታት በኋላ ለጦር ቁስለኞች ባዘጋጁት የስፖርት ውድድር ሲጸነስ የመጀመሪያው ፓራሊምፒክስ ውድድር የተካሄደው ደግሞ በ 1960 የሮም ኦሎምፒክ ጨዋታ ነበር። ይህም ድንቁ አበበ ቢቂላ በባዶ እግሮቹ ሮጦ የማራቶን ድል በተጎናጸፈበት ዓመት መሆኑ ነው።

በርሚንግሃም አትሌቲክስ

በብሪታኒያ ትናንት በርሚንግሃም ላይ በተካሄደ ግራንድ-ፕሪ የአትሌቲክስ ውድድር ከሶማሊያ የመነጨው እንግሊዛዊ ዜጋ ሞ ፋራህ የመንትዮች አባት ለመሆን ከበቃ ከጥቂት ቀናት በኋላ ባደረገው የመጀመሪያ የስፖርት ተሳትፎ በሁለት ማይል አሸናፊ ሆኗል። ሞ ፋራክ በቅርቡ የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ በአምሥትና በአሥር ሺህ ሜትር አሸናፊ በመሆን ሁለት የወርቅ ሜዳሊያዎች መሸለሙ የሚታወስ ነው። በበርሚንግሃም ውድድር ኢትዮጵያዊው መኮንን ገ/መድህንም በ 1,500 ሜትር ሩጫ ኬንያውያንን ከኋላው በማስቀረት አሸናፊ ሆኗል።

ቴኒስ

በዓለም ላይ ታላላቅ ከሆኑት የቴኒስ ውድድሮች መካከል አንዱ የሆነው ዮ-ኤስ-ኦፕን በዛሬው ምሽት ይከፈታል። ከምሽቱ መክፈቻ ግጥሚያዎች አንዱ የስዊሱ ሮጀር ፌደረር ከአሜሪካዊው ከዶናልድ ያንግ ጋር የሚያካሂደው ሲሆን ውድድሩ ፌደረር እስከመጨረሻው ከተሳካለት ለስድሥተኛ የዩ-ኤስ-ኦፕን ድሉ ሊበቃ የሚችልበት ነው። ፌደረር በቅርቡ የዊምብልደን ውድድር ብሪታኒያዊውን ኤንዲይ መሪይን በማሸነፍ በዓለም የቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ ላይ አንደኛ ቦታውን መልሶ መያዙ አይዘነጋም። ስለዚህም ዓመቱ የርሱ ነው የሚሉት ታዛቢዎች ጥቂቶች አይደሉም።

መሥፍን መኮንን


ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 27.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/15xYc
 • ቀን 27.08.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/15xYc