የስፖርት ዘገባ፤ ሐምሌ 27 ቀን፣ 2007 ዓ.ም. | ስፖርት | DW | 03.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የስፖርት ዘገባ፤ ሐምሌ 27 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

አርሰናል በእንግሊዙ «ኮሚኒቲ ሺልድ» የዋንጫ ግጥሚያ ዋነኛ ተቀናቃኙ ቸልሲን አሸንፎ ዋንጫውን ወስዷል። ሊቨርፑሎች ትንግርተኛ የሚሉት የዘመናት አምበላቸው ሽቴፋን ጄራርድን ቢሸኙም ዘንድሮ ሁለት አስተማማኝ አጥቂዎችን ማግኘታቸውን ገልጠዋል። ማንቸስተር ዩናይትዶች ለሦስተኛ ጊዜ የፕሬሚየር ሊጉን ዋንጫ ላለማጣት ቆርጠን ተነስተናል ሲሉ ተደምጠዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:51
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:51 ደቂቃ

የስፖርት ዘገባ፤ ሐምሌ 27 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.

ማንቸስተር ዩናይትድ ባለፉት 12 ወራት ብቻ ለተጨዋቾች ዝውውር $360 ሚሊዮን ዶላር አፍስሷል።

በዩናይትድ ስቴትስ ኬፕ ኤሊዛቤዝ ከተማ በሣምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወነ የ10 ሺህ ሜትር የጎዳና ሩጫ ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ውዴ አያሌው አሸናፊ ኾናለች። ከ6,000 በላይ ሯጮች በተካፈሉበት ውድድር ውዴ በአንደኛነት ያጠናቀቀችው በ31 ደቂቃ ከ56 ሠከንድ በመግባት ነው። የኬንያዋ አትሌት ዲያነ ኑኩሪ በአራት ሠከንድ ለጥቂት ተቀድማ በሁለተኛነት አጠናቃለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ስንታየሁ እጅጉ ከውዴ አያሌው በ12 ሠከንዶች ተቀድማ ሦስተኛ ወጥታለች። አትሌቶቹ በዚህ ውድድር ከ90,000 ዶላር በላይ ለማግኘት ነበር የተወዳደሩት።

የኬፕ ኤሊዛቤዙ ውድድር እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1984 ዓም የኦሎምፒክ ጨዋታ የመጀመሪያው የማራቶን ሩጫ ውድድር አሸናፊ በነበረችው አሜሪካዊት አትሌት ጆዋን ሳሙኤልሰን ተሰየመው ነው። በወንዶች የ10 ሺህ ሜትር የሩጫ ውድድር ኬኒያዊው ሽቴፋን ኪቤት አሸናፊ ኾኗል። የዩጋንዳ እና ኬንያ አትሌቶች ሁለተኛ እና ሦስተኛ በመኾን አጠናቀዋል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን 24 ቡድኖች የብሔራዊ ሊግ ውድድራቸውን ቅዳሜ፥ ሐምሌ 25 ቀን 2007 ዓም በድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ጀምረዋል። በመክፈቻው ጨዋታ የድሬዳዋከተማበዕጣ ከአርሲነገሌጋር ተገናኝቶ 2 ለዜሮ አሸንፏል። 24ቱ ቡድኖች የተደለደሉበት ዕጣ የወጣው ዓርብ ሐምሌ 24 ቀን 2007 ዓም መኾኑም ታውቋል።

24 ቡድኖች ለውድድር ከመቅረባቸው በፊት ከ80 በላይ ቡድኖች መወዳደራቸው ከጥራት ይልቅ ብዛት ላይ ማተኮር ይስተዋልበታል ሲሉ አንዳንድ የስፖርት ተንታኞች ገልጠዋል። በብሥራት 101.1 የስፖርት ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ ማርቆስ ኤልያስ።

የብሔራዊ ሊጉ ግጥሚያ ለውድድር ሙሉ ለሙሉ አመቺ ባልሆኑ የተለያዩ ቦታዎች ሲከናወን ተስተውሏል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ህዝብ ግንኙነት አቶ ወንድምኩን አላዩ።

የብሔራዊ ሊጉ ውድድር የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከሚከናወንበት ወቅት ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም። ፕሬሚየር ሊጉ የቡድኖች የቅድመ-ውድድር የሚጀምሩት አብዛኛውን ጊዜ ከነሐሴ 10 እስከ 20 ባሉት ጊዜያት ውስጥ ነው። ከዚያም ጥቅምት ወር ውስጥ ፕሬሚየር ሊጉ ይጀምራል። ጋዜጠኛ ማርቆስ የብሔራዊ ሊጉ ነሐሴ አጋማሽ መጠናቀቅ ወደ ፕሬሚየር ሊጉ ለሚያልፉ ቡድኖች አስቸጋሪ እንደሆነ ጠቅሷል።

በጥቅሉ 68 ጨዋታዎች የሚስተናገዱበት ይኽ የብሔራዊ ሊግ ውድድር በድሬዳዋ ከተማ የሚጠናቀቀው ነሐሴ 17 ቀን ነው። 24 ቡድኖችን የ ሚያስተናግደው ይኽ ውድድር ከሚቀጥለው ዓመት አንስቶ ተጨማሪ ቡድኖችን እንደሚያካትት አቶ ወንድምኩን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከፕሬሚየር ሊጉ በታች 32 ቡድኖችን አቅፎ በሁለተኛ ዲቪዚዮን ደረጃ ለማወዳደር ማቀዱ የሚበረታታ ነው።

በእንግሊዝ የኮሚኒቲ ሺልድ የዋንጫ ፍልሚያ አርሰናል ቸልሲን አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ትናንት አሸንፎ ዋንጫውን በእጁ አስገብቷል። ለአርሰናል ብቸኛዋን ግብ ያስቆጠረው የእንግሊዝ የቀድሞው ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች ልጅ የኾነው ኦክስላዴ ቻምበርላይን ነው።

ግቧን ያስቆጠረው በ24ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። «የሚገባንን አድርገናል፤ ዕድላቸው የጠበበ እንዲኾን በደንብ ተከላክለናል።» ሲል ግቧን ያስቆጠረው ቻምበርላይን አርሰናል ድንቅ መከላከል ማድረጉን ጠቅሷል። የ21 ዓመቱ የአርሰናል አማካይ ለአርሰናል በፕሬሚየር ሊጉ በርካታ ግቦችን ማግባት እንደሚፈልግ ተናግሯል። የኮሚኒቲ ሺልድ ዋንጫ ውድድር የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የኤፍ ኤ ካፕ ውድድሮች ዋንጫን ያነሱ ቡድኖች የሚያደርጉት የዋንጫ ግጥሚያ ነው።

ሩስያ ካዛን ውስጥ በተከናወነው የዓለም ሻምፒዮና የ1,500 ሜትር የነፃ ቀዘፋ የውኃ ዋና ስፖርት ውድድር አሜሪካዊቷ ታዳጊ ኬቲ ሌዴኪ የዓለም ክብር-ወሰን ሰበረች። የ18 ዓመቷ ወጣት ኬቲ ባለፈው ዓመት በራሷ ተይዞ የቆየውን ክብር-ወሰን የሰበረችው በ0.65 ሠከንድ በማሻሻል ነው። ውድድሩን ለማጠናቀቅ የፈጀባት ጊዜ 15 ደቂቃ ከ27.71 ሠከንድ መኾኑም ተዘግቧል። ኬቲ ነገ በምታደርገው የፍፃሜ ውድድር ምናልባትም ክብር-ወሰኗን በድጋሚ ልታሻሽል ትችል ይኾናል የሚል ግምት ተሰጥቷታል። ኬቲ በ1,500 ሜትር የነፃ ቀዘፋ የውኃ ዋና ውድድር ክብር-ወሰን ስትሰብር ይኽ ለአራተኛ ጊዜ ነው።

በወንዶች የ50 ሜትር በተርፍላይ የዋና ውድድር ደግሞ ፈረንሣዊው ፍሎሬንት ማናዱ አንደኛ ወጥቷል። ኢትዮጵያዊው ዋናተኛ ሮቤል ኪሮስ ሐብቴ በዚህ ዓለም አቀፍ ውድድር ከ82 ተወዳዳሪዎች 74ኛ ደረጃን አግኝቷል። የካሜሩን እና የኒጀር ሁለት ዋናተኞች ከውድድር ውጪ ተብለዋል። ከጎረቤት ሃገራት መካከል የጅቡቲ እና የሱዳን ተወዳዳሪዎች 62ኛ እና 67ኛ ወጥተዋል።

የጀርመኑየቴሌቪዥንጣቢያARD እና የብሪታንያው ጋዜጣ«ሠንደይ ታይምስ» ቁጥራቸው 5000 ከሚጠጉ ስፖርተኞች 12 000 የደም ናሙናዎችን በመመርመር በርካታ ስፖርተኞች በዶፒንግ ወይም አበረታታች ነገር መውሰዳቸውን ደማቸው እንደሚጠቁም ይፋ አድርገዋል።ምርጥ የዓለም ክብር-ወሰን ባለቤቶች እና የኦሎምፒክ አሸናፊዎችን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች ግን አንዴም በዚህ ተጠይቀው አያውቁም ተብሏል። ብርታት የሚሰጥ ነገር ተጠቅመው ውድድር አሸንፈዋል ከተባሉት አትሌቶች መካከል እጅግ በርካቶቹ የሩስያ አትሌቶች መኾናቸውን ዘገባው አትቷል።

የሩስያ ባለሥልጣናት ዘገባውን ስም ማጥፋት ነው ሲሉ ተችተዋል። አትሌቲክስ ማኅበሩ ይኽን ሁሉ ዓመታት በአትሌቶቹ ላይ ርምጃ ሳይወስድ በአሁኑ ወቅት ለምን ከዚህ ውሳኔ ላይ እንደደረሰ ብዙዎችን አነጋግሯል። ይኽ ዘገባ ይፋ የኾነው የዓለም ሻምፒዮና ውድድር በሩስያ ካዛን ከተማ ውስጥ እየተኪያሄደ ባለበት በአሁኑ ወቅት ነው። ሩስያ እና ቻይና በኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ በርካታ ሜዳሊያዎችን ከሚያገኙ የዓለማችን ጥቂት ሃገራት ውስጥ ይመደባሉ።

የሊቨርፑሉ አሠልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ ምንም እንኳን የቡድናቸው የረዥም ዘመን አምበል ሽቴፋን ዤራርድ ወደ ዩናይትድ ስቴትሱ ኤል ኤ ጋላክሲ ቡድን ቢያቀናም ቡድናቸው መጠናከሩን ተናግረዋል። በ50.77 ሚሊዮን ዶላር ከአስቶን ቪላ የመጣው ክሪስቲያን ቤንትኬ እና ሮቤርቶ ፊርሚኖ የፊት መስመሩን በማጠናከራቸው እጅግ ደስተኛ ነኝ ሲሉ አሠልጣኙ ተናግረዋል።

የማንቸስተር ዩናይቱዱ የክንፍ ተጨዋች አንጌል ዲ ማሪያ ለፈረንሳዩ ፓሪስ ሴንጀርሜን ቡድን ለመሰለፍ የህክምና ምርመራ ሊያደርግ መኾኑ ተዘግቧል። ዲ ማሪያ ከሪያል ማድሪድ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ የመጣው በብሪታንያ የዝውውር ክፍያ ከፍተኛ በተባለ 92.59 ሚሊዮን ዶላር ነበር።

ኦሎምፒያክ ሊዮን ቡድን ደግሞ የብራዚሉን ተከላካይ ራፋኤል ዳ ሲልቫን ከማንቸስተር ዩናይድ ለማስፈረም ጫፍ ላይ መኾኑ ተዘግቧል። የ25 ዓመቱ ራፋኤል ላለፉት 7 ዓመታት ግድም በማንቸስተር ዩናይትድ ቆይቷል።

ኬቪን ፕሪንስ ቦዋቴንግ ከጀርመኑ ሻልከ ቡድን ወደ ፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዝቦን ሊዛወር መኾኑ ተገልጧል። የ28 ዓመቱ የጋና ብሔራዊ ቡድን ተሰላፊ ኬቪን በቡንደስሊጋው የውድድር ዘመን ወደፊት በሻልከ ቦታ እንደሌለው ተነግሮት ነበር።

በጀርመን ሱፐር ካፕ ዋንጫ ውድድር ቮልፍስቡርግ ባየር ሙይንሽንን በፍፁም ቅጣት ምት 5 ለ4 አሸንፎታል። ባየር ሙይንሽን በአርየን ሮበን ግብ ሲመራ ቆይቶ አቻ የምታደርገውን ግብ ለቮልፍስቡርግ በ89ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ቤንድትነር ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic