የሴቶች መብት ጉዳይ | ባህል | DW | 07.11.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

የሴቶች መብት ጉዳይ

ሴቶች በፆታቸዉ ወደ ጎን ገሸሽ እንዳይደረጉ፤ ማህበረሰቡ ምን እንቅስቃሴ እያደረገ ነዉ? በዕለቱ ዝግጅታችን የምናነሳዉ ርዕስ ነዉ ።

በርግጥ ስለ ሴቶች እንድናነሳ ያነሳሳን ነገር ባለፈዉ ሰሞን ወጣት ካሚላት ማሃዲ መሞሸርዋን ሰምተን ነዉ። በቅድሚያ ለአዲስዋ ሙሽራ ካሚላት ማሃዲ እንኳ ደስ ያለሽ፤ መልካም የጋብቻ ዘመን ይሁንልሽ እንላለን። ካሚላት ማሃዲ ፍቅረኛዋ ፊትዋ ላይ አሲድ ደፍቶባት፤ ፊትዋ በፅኑ ቆስሎ፤ እንደነበር ይታወሳል። የ 21 ዓመትዋ ወጣት ዛሬ የህክምና እርዳታ አግኝታ፤ ትዳር መሥርታ አዲስ የህይወት ጉዞን በደስታ መጀመርዋን በርካታ የብዙሃን መገኛኛዎች ዘግበዋል። በርግጥ ካሚላት ያሳለፈችዉ የስቃይ ጊዜ ባይዘነጋም ስኬቱ ደግሞ የሚያስደስት ነዉ። በተቃራኒዉ እዚያዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በአንዳንድ ትምክህተኛ ወንዶች በደል የሚደርስባቸዉ፤ በጎታች ልምዶችም ተገፍተዉ የሚገኙ ግን መፍትሄ ያላገኙ ሴቶችን ቤት ይቁጠራቸዉ። በሀገራችን በተለያዩ ሚዲያዎች እና ድርጅቶች የሴቶችን መብት በተመለከተ የተለያዩ ግንዛቤ ይሰጣል ያሉን፤ የሴቶች ማረፍያና ልማት ማህበር አባል ወይዘሮ ማሪያ ሙኒር እንደሚሉት እንዲያም ቢሆን ገና ብዙ ይቀረዋል፤ ወይዘሮ ማርያ እንደሚሉት ማህበራቸዉ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነዉን ጥቃት የደረሰባቸዉ ሴቶች ቤት አቋቁሟል። የሴቶችን መብት ለማስከበር እንደሚንቀሳቀስ የነገሩን፤ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማህበር፤ የስራ አስፈፃሚ ዳይሪክተር ወ/ሮ ዜናይ ታደሰ፤ ማህበራቸዉ በተለይ ሶስት ነገሮች ላይ እንደሚሰራ ገልፀዋል። ሴቶች በደል የሚደርስባቸዉ በአንዳንድ በትምክተኛ ወንዶች ብቻ ሳይሆን በጎታች ልምዶችም ተገፍተዉ ለተለያዩ ችግሮች የሚጋለጡ ጥቂቶች አይደሉም።

በሌላ በኩል ይላሉ በሴቶች መብት ጉዳይ ላይ የሚሰሩት ወ/ሮ ማሪያ ሙኒር በሌላ በኩል አንዳንድ ሴቶችም ቢሆኑ ለአንዳን ጎታች ልምዶች እጅግ ተገዥ ናቸዉ። በሴቶች መብት ላይ በመስራት ላይ ያሉት ማህበራት አባላት እንደገለፁት ኢትዮጵያ ዉስጥ በትምህርት ረገድ ለታዳጊ ሴቶች እየተደረገ ያለዉ ድጋፍ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም አሁንም የሚታየዉን በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት ለማስቀረት ከወንዶች ጋር መተባበርና፤ የግንዛቤ ማስጨበጫ መረሃ-ግብሮችንም ማስፋፋትይኖርብናል ያሉንን የለቱን እንግዶቼን እያመሰገንኩ መሰናዶዪን ልቋጭ አዜብ ታደሰ ነኝ ጤና ይስጥልኝ!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዪ ለገሰ

Audios and videos on the topic