የሳምንቱ ጉባኤዎች፤ ተቃዉሞዉና ተስፋዉ | ዓለም | DW | 06.04.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የሳምንቱ ጉባኤዎች፤ ተቃዉሞዉና ተስፋዉ

በአምስቱ የብራስልስ ስምምነት ፈራሚዎች ዩናይትድ ስቴትስ፥ ካናዳ፥ ፖርቱጋል፥ ኢጣሊያ፥ኖርዌ፣ ዴንማርክና አይስላንድ ታክለዉ የመሠረቱት የጦር ተሻራኪ ድርጅት በስልሳ አመት ጉዞዉ የአባላቱን ቁጥር ከአስራ-ሁለት ወደ ሃያ-ስምንት አሳድጓል።

default

የኔቶ ጉባተኞች

06 04 09

የቡድን ሃያ ጉባኤ፥ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ጉባኤ፥ የአዉሮጳ ሕብረትና የአሜሪካ መሪዎች ጉባኤ፥ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ጉባኤ እንደተባለ፥ ብዙ እንደተወራበት፥ ብዙ እንደተወራለት ሳምንቱ አበቃ።ጤና ይስጥልኝ እንደምን ዋላችሁ።የአለምን ዘዋሪዎች ካሰባሰቡት ብዙ ጉባኤዎች ጥቂቱ፥ሥለ አለም ብልፅግና ሠለሰላም ደሕንነቷ ብዙ ከተነገረዉ፥ ቅንጭቡ፥ ከአለም ዘንቅ-ሐቅ ሥንጣጣሪዉ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ-አብራችሁኝ ቆዩ።

ከለንደን፥ በሽትራስቡርግ አድርጎ፥ ኪል ደርሶ፥ ፕራግ ያሳረገዉ የአለም መሪዎች ጉባኤ ለንደን ላይ አንድ ሲል ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያን ባንድ ጎራ፥ ፈረንሳይና ጀርመንን በሌላ፥ቻይና ሩሲያንና ሌሎችን በሌላ ረድፍ የማሰለፉ እዉነት አለም እየከሰረች፥እየተቸገረችም ግንባር ቀደም መሪዎቿ ባንድ ማበር ያለመቻላቸዉ ወይም ያለመፈለጋቸዉ ምልክትን፥ የአለም ኪሳራ ችግሮች ያለመወገዳቸዉ ሥጋትን አድምቆት ነበር።

ጉባኤተኞች ከዕለት ዉይይት፥ድርድር በኋላ የደረሱበትን ዉል ሲናገሩ ግን መጥፎ-ምልክት ሥጋቱን በነበር አስቀርቶታል።የጉባኤዉ ትልቅ እንግዳ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ እንዳሉት ሥጋት እንዳጠለበት የተጀመረዉ ጉባኤ ዉጤት ታሪካዊ ነበር።

«የለንደኑ ጉባኤ በየትኛዉም መመዘኛ ታሪካዊ ነበር።ምክንያቱም በገጠመን ፈተና ሥፋትና ጥልቀጥ ሲመዘን፥ በሰጠዉ መልስ ወቅታዊነትና ሥፋት ሲታይ ታሪካዊ ነበር።»

ከጉባኤዉ በፊት በተለይ በለንደን ዋሽንግተኞች አቋም ቅር ከተሰኙት መሪዎች አንዷ የጀርመኗ መራሒተ መንግሥት እጌላ ሜርክል እንዳሉት የለንደኑ ጉባኤ የአለምን ኪሳራ ለማስወገድ ይችላል ከተባለዉ ሥምምነት የደረሰዉ፥ ከጉባኤዉ በፊት የነበረዉን ልዩነት ያስወገደዉ፥ ምናልባትም ቀቢፀ-ተስፋዉን በበጎ ተስፋ የለወጠዉ ጉባኤተኞች አንዱ የሌላዉን ፍላጎት ለማስተናገድ በፈቅዳቸዉ ነበር።

«ባጠቃላይ (ዉሳኔዉ) የግንባር ቀደሞቹ ባለኢንድትሪ ሐገራት በጋራ የመቆማቸዉን መልዕክትን ያስተላለፈ ነዉ።ሠጥቶ-የመቀበልና የመካካስ ፍላጎት የነበረበት ብርቱ የትብብር ሥራን የጠየቀ ነበር።ጥሩ ዉጤት ያመጣዉም ይሕ ነዉ።»

መሪዎቹን ያስደሰተዉ ሥምምነት፥ ያደነቁት ዉሳኔ-እቅዳቸዉ ግን ጉባኤዉ ከመጀመሩ በፊት ጀምረዉን የለንደንን አደባባዮች በሰልፍ ላጥለቀለቀዉ ሕዝብና ብጤዎቹ ጥያቄ ተገቢዉን መልስ አልሰጠም።

የባንኮችን አሰራርን ከሚቃወመዉ፥ ለተፈጥሮ ሐብት መከበር እስከሚሟገተዉ፥ ለድሆች መብት ከሚከራከረዉ፥ ለፍትሕ-እኩልነት እሰከሚታገለዉ ሌሎችንም በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎችን ባንድ ያሰበረዉ ሠለፍ-መልዕክት የጉባኤተኞቹን ጆሮ ጨርሶ አላገኘም ማለት ያሳስት ይሆናል።የፖሊስን ዱላ፥ ጉሸማ፥ ግልምጫ ተጋፍጦ ቀን ከሌት ባደባባይ ሲጮሕ የሰነበተዉ ሰልፈኛ አብዛኛ ጥያቄ ግን በርግጥ ከጥያቄ አላለፈም።ብሪታንያዊቷ ሰልፈኛ እንዳለችዉ ደግሞ ሰልፈኛዉ አቀመቢስነቱን ነዉ-የተረዳዉ።

Demonstration Protest gegen Nato Gipfel in Strasburg

የኔቶ ተቃዋሚዎች

«እንደሚመስለኝ አሁን ማድረግ የምንችለዉ የተቃዉሞ ሠልፍ ብቻ ነዉ።ከዚሕ ዉጪ ማድረግ የምንችለዉ ያለ አይመስለኝም።ሁሉም አቅመቢስ እንደሆነ ነዉ-የሚሰማዉ።ሁሉም ተበሳጭቷል።እዚሕ ሐገር ሥለ ልጆቹ የወደፊት ሕይወት የማያስብ ያለ አይመስለኝም።»

የምጣኔ ሐብቱ ጉባኤ-አብቅቶ የጦር ተሸራኪዎቹ ሐገራት መሪዎች ለሌላ ጉባኤ ሲታደሙም ተቃዉሞ ሠልፍ አልተለያቸዉም።ጉባኤዉ ቀጠለ።የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ የስልሳ-ዘመን ድል-ምግባር በጎነትም ይደነቅ ገባ።

«ዛሬ የፈረንሳይና የጀርመንን ወዳጅነት አከበርን፥የአዉሮጳን አንድነት አከበርን።የአትላንቲክ ማዶ ለማዶ ሐገራትን ሽርክናን አከበርን።እና ኔቶ አዲሱን የሃያ-አንደኛዉን ክፍለ ዘመን ፈተናዎች ለመወጣት እንዲችል ዋና ፀሐፊ ሼፈር የጀመሩትን ጥሩ ሠራ ለመቀጠል ዝግጁ ነኝ።»

አንደረስ ፎግሕ ራስሙሰን፥-የዴንማርክ ጠቅላይ ሚንስትርና የወደፊቱ የኔቶ ዋና ፀሐፊ።ቅዳሜ። ከስልሳ-አመት በፊት የቅዳሜን እለት ዋሽግተን-ዩናይትድ ስቴትስ የተሰበሰቡት የአስራ-ሁለት ሐገራት መሪዎች የመሠረቱት ማሕበር ዛሬ ከደረሰበት ይደርሳል ብሎ ያኔ መገመት አጠራጣሪ ነበር።ለዋሽግተኑ ጉባኤ መሠረት የጣለዉ መጋቢት አስራ-ሰባት 1948 ብራስልስ ቤልጂግ ላይ የተፈረዉን ዉል ነበር።

የአዉዳሚ ጦርነት ትቢያዋን በማረገፍ ላይ የምትገኘዉ አዉሮጳ ሶቬት ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ በሚመሩት ሁለት ጎራ ያሰጋቸዉ የቤልጅግ፥ የኔዘርላንድስ፥ የላክሰንበርግ መሪዎች የትናንሽ ሐገሮቻቸዉን ሕልዉና ለማስከበር ከወቅቱ የአዉሮጳ ሐያላን ከብሪታንያ እና ፈረንሳይ ጋር የጋራ የመከላከያ ሥምምነት መፈረሙን እንደ ጥሩ ብልሐት ነበር ያዩት።

በአምስቱ የብራስልስ ስምምነት ፈራሚዎች ዩናይትድ ስቴትስ፥ ካናዳ፥ ፖርቱጋል፥ ኢጣሊያ፥ኖርዌ፣ ዴንማርክና አይስላንድ ታክለዉ የመሠረቱት የጦር ተሻራኪ ድርጅት በስልሳ አመት ጉዞዉ የአባላቱን ቁጥር ከአስራ-ሁለት ወደ ሃያ-ስምንት አሳድጓል።

የድርጅቱ የወደፊት ዋና ፀሐፊ ባለፈዉ ቅዳሜ እንዳሉት የኔቶ ሥልሳኛ አመት የፈረንሳይና የጀርመን ወዳጅነት ምልክት፥ የአዉሮጳ አንድነት አብነት፥ የአትላንቲክ ማዶ፥ ለማዶ ሐገራት ሽርክና ምሳሌ ይሆንም ይሆናል።ራስሙስ ራሳቸዉ እንደ ኔቶ የወደፊት ዋና ፀሐፊ ያሉትን ለማለት የበቁት በዋና ፀሐፊነት መሾማቸዉን የተቃወመችዉ ትርክን ለማግባባት ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማና ጠቅላይ ሚንስትር ሲልቪዮ ቤርሎስኮኒ በግንባር ቀደምትነት የሌሎቹ ሐገራት መሪዎች ተከትለዉና አሰልሰዉ ብዙ ከጣሩ፥ ከለፉ፥ ለቱርክ ማካካሸ ከፈቀዱ በሕዋላ መሆኑ ሊዘነጋ ግን አይገባም።

ራስሙሰን የሃያ-አንደኛዉ ክፍለ ዘመን ፈተና ካሉት ችግሮች ለጦር ተሻራኪዉ ድርጅት ግንባር ቀደሙ በአፍቃኒስታን ሰላም ማስከበር ነዉ።ተሰናባቹ የድርጅቱ ዋና ፀሐፊ ጃአብ ደ ሆፕ ሼፈር የዚያኑ እለት እንዳሉት የአባል ሐገራት መሪዎች ለአፍቃኒስታኑን ዘመቻ ለማጠናከር ያሳለፉት ዉሳኔ እጅግ ባጣም ጥሩ ነዉ።

«የዚሕ ጉባኤ ተጨባጭ ዉጤቶች፥ ገንዘብን በተመለከተ፥ የሰላማዊ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ፥ ሥልጠናን በተመለከተ፥ እና በተጨማሪም ወታደሮችን በተመለከተ በርግጥ በጣም፥ በጣም ጥሩዎች ናቸዉ።ከዚሕም ሌላ አፍቃኒስታን ዉስጥ በመጪዉ ነሐሴ ሃያ የሚደረገዉን ምርጫ፥ምናልባትም ጥቅምት የሚደረገዉን የመለያ ምርጫ ለመደገፍ ካለብን ግዴታ አኳያም የጉባኤዉ ዉጤት በጣም ጥሩ መሆኑን በርግጠኝነት ልነግራችሁ እችላለሁ።»

የኔቶ መስራቾች ያፀደቁት መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ አምስት፥-«አዉሮጳና ሰሜን አሜሪካ በሚገኙት ተፈራራሚዎች ባንዳቸዉ ወይም በብዙዎቹ ላይ የሚፈፀም ወታደራዊ ጥቃትን በሁሉም ላይ እንደተፈፀመ ጥቃት ይቆጥሩታል።» ይላል።

ይሕን የኔቶ አላማ በመቃወም ሶቬት ሕብረትና ተሻራኪዎችዋ በ1955 የዎርሶ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት የተሰኘዉን ተፃራሪ የጦር ትብብር መስርተዋል።ሁለቱ የጦር ድርጅቶች ወትሮም እሁለት የተከፈለዉን አለም ከሰወስተኛ ምናልባትም አለም እስከዚያ ዘመን አይታዉ ከማታዉቀዉ የኒክሌር ጦርነት ይዶሉታል እየተባለ የአለም ሕዝብን ሲያጨንቁት ኖረዋል።

የኔቶ ሥልሳኛ አመት ሲዘከር አደባባይ የወጡት ተቃዉሞ ሠልፈኞች እንደሚሉት የኮሚንስቶቹ ጎራ እንሲከፈረካከስ ድረስ ለአርባ አመት አለምን በጦርነት ሥጋት እንድትሸማቀቅ ካደረጉት የጦር ድርጅቶች አንዱ ቀዳሚ ተከታይ ዋና ጸሐፊዎቹ እንደሚያንቆለጳጵሱት ለሰላም የቆመ ሊሆን አይችልም።ተቃዋሚ ሠልፉት ካደራጁት አንዱ የመላዉ ጀርመን የሰላም ሕብረት የተሰኘዉ ቡድን አባል ማኒ ሽቴነር ኔቶ ለሰላም አስጊ ድርጅት ነዉ።

«ኔቶ ለአደፍራሽ ምክንያት ነበር።የቀዝቃዛዉ ጦርነት ምክንያት ነበር።ሁለቱ ተቃራኒ ወገኖች እርስ በርስ እንዲጠፋፉ፥ እኛም ሁለችንም የዚሕ ሂደት ሰለባ እንድንሆን የሚያደርግ ይሆን ነበር።የአዉቶም ቦምብ እንደታጠቀ መቆየቱ መመለሻ የማግኘለት አደጋ ነበር።ሰማይ ባናታችን ላይ ይደፋብን ነበር።»

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳት ባራክ ኦባማ የዘመኑ ብቸኛ ልዕለ ሐያል ሐገራቸዉ አለምን ከኑክሌር ሥጋት ለማላቀቅ ያደረጉት ጥሪ የኔቶን አይደለም የአለምን የእስካሁን ሂደት ለመቀየር ጥሩ ተስፋ፥ ለነሽቴነር ጥያቄም ቀጥተኛ መልስ መሆኑ በርግጥ አያከራክርም።

«ዩናይትድ ስቴትስ የኑክሌር ጦር መሳሪያ የተኮሰች ብችኛዋ ባለኑኩሌር ሐገር እንደመሆንዋ መጠን እርምጃ ለመዉሰድ የሞራል ግዴታ አለባት።ይሕን ተልዕኮ ብቻችንን ልንወጣዉ በርግጥ አንችልም።መምራት ግን እንችላለን።ሥለዚሕ ዩናይትድ ስቴትስ የአለም ሠላምና ደሕንነትን ከኑክሌር ሥጋት ለማላቀቅ ዩናይትድ ስቴትስ አበክራ እንደምትጥር ዛሬ በግልፅና ከልብ መናገር እወዳለሁ።»

Raketenstart in Nordkorea

የሰሜን ኮሪያ ሮኬት

የለንደን ጉባኤተኞች ዉሳኔ በአለም ምጣኔ ሐብት ላይ የሚኖረዉ ተፅዕኖ አወንታዊ-አሉታዊነት ለጊዜ ሂደት ነበር የተተዉ።የሽትራስ-ቡርግ ኪል ጉባኤተኞች የአፍቃኒስታንን ሠላም የሚያስከብር ያሉትን ሥልት ሲያረቁ ሠላም የማታዉቀዉ ሐገር እንደለመደችዉ በቦምብ ጥይት እያረረች።የኔቶ አባላት ከአፍቃኒስን ባልተናነሰ ሁኔታ ለሰላሟ እናስብላታለን ያሏት ፓኪስታን ርዕሠ-ከተማ ሳይቀር ቦምብ ይጋይ ነበር።ኦባማ ኑክሌር እናጥፋ ሲሉ ሰሜን ኮሪያ ሳተላይት ተሸካሚ ያለችዉን ሮኬት አወነጨፈች።የሰለም-የተስፋ-ቃል ቅጭት።

ነጋሽ መሐመድ

►◄