የሱዳን መፃኢ ተስፋ የተጣለበት ዉል | የጋዜጦች አምድ | DW | 06.01.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የሱዳን መፃኢ ተስፋ የተጣለበት ዉል

በሱዳን ከ21 አመታት የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ባለፈዉ አመት ማለቂያ የመጨረሻ እለት ላይ በአገሪቱ በተቃራኒነት ሲፋለሙ የነበሩት ወገኖች የሰላም ስምምነት ተፈራርመዋል። የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ ኮፊ አናንና የስራ ባልደረቦቻቸዉም በሱዳን የሁለት ሚሊዮን ሰዎች ህይወት የተቀጠፈበትን የእርስበርስ ጦርነት ማብቂያ ነዉ የተባለዉን የሰላም ስምምነት ዉል በደስታ ተቀበዉታል።

ተፋላሚዎቹ ለሰላም መነሳታቸዉን ለህዝባቸዉ ሲያሳዩ

ተፋላሚዎቹ ለሰላም መነሳታቸዉን ለህዝባቸዉ ሲያሳዩ

ስምምነታቸዉን በፊርማቸዉ ያረጋገጡት የሱዳን ተፋላሚ የሰላም ዉላቸዉን ለተባበሩት መንግስታት እናቀርባለን ብለዉ ቃል በገቡበት ባለፈዉ አመት ማገባደጃ ሲያደርጉ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነትን ግንባር ቀደም አድርገዉ ነዉ።
የሰላም ስምምነት ዉሉን ሁለቱ ወገኖች የተፈራረሙት በተደጋጋሚ ድርድር ባካሄዱባት በጎረቤት አገር ኬንያ የደቡብ አፍሪካዉ ታቦ እምቤኪን ጨምሮ በርካታ እማኞች በተገኙበት ነበር።
በህዳር እኔና ጠሃ የምንወያይባቸዉ ነጥቦች ላይ በተነጋገርንበት ወቅት ግጭቱን በማስወገድ ለሱዳን ህዝብ የአዲስ አመት ስጦታ የሚሆን ሁለንተናዊ ሰላም ይዘን ለመቅረብ ቆርጠን ነበር።
ዛሬ የፈፀምነዉ ያንን ነዉ። በማለት ነበር ጋራንግ ሰንደቅ አላማ እያዉለበለበ የሰላም ዉሉን ለመስማት ለተሰበሰበዉ የሱዳን ህዝብ ጠሃን ከጎናቸዉ አቁመዉ የተናገሩት።
አሁን እዚህ የቆምነዉ የሰላም ስምምነት ላይ መድረሳችንን ለሱዳን ህዝብ ለመመስከር ነዉ። ለሱዳናዉያን ልንነግር የምንፈልገዉ ከእንግዲህ እነሱን በጋራ ለማገልገል እንደተዘጋጀንና ሱዳንም በአዲስ የኑሮ መስመር ዉስጥ እንደምትሆን ነዉ ያሉት ደግሞ በተሰበሰበዉ የሱዳን ህዝብ ፊት ለረጅም አመታት ከተፋለሙዋቸዉ ከአማፅያኑ መሪ ከጆን ጋራንግ አጠገብ ቆመዉ የታዩት የሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት አሊ ኦስማን ጠሃ ነበሩ።
ከእንግዲህ ወዲያ በሱዳን ጦርነት አይኖርም። ዛሬ 49ኛዉ የሱዳን የነፃነት በአል ነዉ። በነበረዉ ጦርነት ምክንያት እስካሁን የሱዳን ነፃነት ምሉዕ አልነበረም። ዛሬ ግን በቃ ጦርነቱ ስላበቃ የተሟላ ሆኗል ያሉት ደግሞ የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አህመድ አልበሺር ናቸዉ የስምምነቱን ስነስርአት ለመከታተል ለተገኙት ታዳሚዎች።
አልበሺር በመቀጠልም በሱዳን ያሉትን ችግሮች በሙሉ ለመፍታት ጠንክረዉ መስራት እንደሚኖርባቸዉ በመግለፅ ሆኖም ግን በዳርፉር ያለዉን ቀዉስ ማስተካከል ካልቻሉ ልፋታቸዉ ሁሉ ዋጋ እንደማይኖረዉ ነዉ የተናገሩት።
በምዕራባዊ ሱዳን በዳርፉር ያለዉ ግጭት በደቡብ ያለዉ የእርስ በርስ ጦርነት ማብቂያ ሂደት ላይ ጥላዉን ካጠላበት ሰነተ።
የዳርፉር ሁለት አማፂ ቡድኖች በ2003አ.ም. ላይ ነበር የሱዳንን መንግስት አካባቢዉን ችላ ብሏል በሚል የተቃዉሞ እንቅስቃሴ የጀመሩት።
ያገሪቱ መንግስትም ለተፈፀሙት ተግባራት በአካባቢዉ በሚገኙ ሶስት ጎሳዎች ላይ አማፅያኑን ትደግፋላችሁ በሚል በወሰደዉ አስከፊ የጥቃት ምላሽና የአረብ ሚሊሻዎችን በማስታጠቅ ተከሶ ነበር።
የአለም አቀፍ ግጭት ቡድን ልዩ አማካሪ እንደሚሉት በሱዳን የረጅም ግዜ ተፋላሚ ወገኖች መካከል የተደረሰዉን አዲሱን የሰላም ስምምነት በዳርፉር የሚካሄደዉ ዉጊያ ሊያደናቅፈዉ ይችላል።
እንደእሳቸዉ ትንታኔ በዳርፉር ያለዉን ችግር ለመፍታት ጊዜ በወሰደ ቁጥር ችግሩ ይባባስና የሰላም ስምምነቱን በተግባር ለማዋል ይከብዳል።
የሱዳን ሰላማዊ ዜጎችም በደቡብ የሚገኙት ተዋጊ ብድኖች በድርድሩ ባለመሳተፋቸዉ የሰላም ዉሉን የሚያደፈረስ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ የሚል ስጋት አላቸዉ።
በሱዳን በርካታ የታጠቁ ብድኖች ቢኖሩም የሰላም ድርድሩ በመንግስትና ጆን ጋራንግ በሚመሩት በሱዳን ነፃ አዉጪ ንቅናቄ መካከል ብቻ ነዉ የተካሄደዉ።
በመሆኑም በታዛቢዎች አስተያየት የሰላም ዉሉን የሚያደፈርስ እርምጃ በእነዚህ ወገኖች ከመወሰዱ አስቀድሞ ሁለቱ ወገኖች በደቡብና በሰሜን ሱዳን ከሚገኙ ታጣቂዎች ጋር መነጋገር ያስፈልጋቸዋል።
በሌላ ወገን ግን በርካቶች የሰላም ዉሉን መፈረም እንደዋነኛ መፍትሄ በመቁጠር ብሩህ ተስፋ በሱዳን መኖሩን እየተናገሩ ነዉ።
የተደረሰዉ ስምምነት ሁሉ በአገሪቱ በታማኝነት ተግባራዊ መሆን ከቻለ ሱዳን ሰላማዊ አገር መሆን ስለምትችል ለአገሪቱ ልማት ፈር ቀዳጅ ነዉ በማለት የሱዳንን እድገት ለማየት መናፈቃቸዉን ገልፀዋል።
የሰላም ዉሉ የተሳካ እንዲሆን ማድረግ የአፍሪካ ግዴታ ነዉ ያሉት ታቦ እምቤኪ አህጉሪቱ ከሱዳን ህዝብ ጋር በጋራ ለመጓዝ እንደገና ሱዳን ከነበረባት ችግር እንድታገግም መደገፍ እንደሚኖርባት ነዉ የተናገሩት።
ለተግባራዊነቱም በዘመናት ጦርነት የወደመዉን የአገሪቱን መሰረተ ልማት እንደገና በመገንባእ ከጎኗ መሆን እንደሚገባ ነዉ እምቤኪ ለማሳሰብ የሞከሩት።
ፕሪቶሪያና የደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲም የሱዳን ህዝብ ነፃ አዉጪ ንቅናቄ አባላትን በሱዳን የሽግግር መንግስት ዉስጥ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸዉ የሚያስችል ስልጠና ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
አርብ እለት ከተደረገዉ ስነስርአት ቀደም ብሎ ሁለቱ ወገኖች የሱዳንን የነዳጅ ሃብትና የሽግግር መንግስቱን ስልጣን በመካፈል ረገድና በሱዳን ማእከላዊ ግዛቶች የሚገኙትን ሶስት ዋና ዋና ስፍራዎች የመቆጣጠር ስምምነት ተፈራርመዉ ነበር።
ከዚህም ሌላ የአሁኑ የሱዳን አስተዳደር የመጨረሻዉ የሰላም ስምምነት ዉል ከተፈረመ በኋላ ለቀጣይ ስድስት አመታት እንዲመራና ከዚያ ቀጥሎ ደቡቡን ክፍል በተመለከተ ዉሳኔ ህዝብ ለማድረግ ተስማምተዋል።
በሁለቱ ወገኖች መካከል የሚደረገዉ የመጨረሻዉ የሰላም ስምምነት ዉል በጥር ወር መጀመሪያ ላይ ይፈረማል ተብሎ ይጠበቃል።