የሰዎች ውፍረትና ቅጥነት ችግር፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 11.07.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የሰዎች ውፍረትና ቅጥነት ችግር፣

ውፍረት ፤ በተለያዩ ሀገራት ፤ እንደየባህላዊ አመለካከቱ፤ የድሎት ፣ የሃብታምነት ብሎም የቁንጅና ምልክት ሆኖ የሚታይበት ጊዜ ነበረ። በምዕራቡ ዓለም ፤ ከዚህ በተቃርኖ ፣ መወፈር አደገኛነቱ ፤ ታውቆ፣ ለመቀነስና ሸንቀጥ ብሎ ለመታየት ጥረት

 መደረግ የጀመረው ፣ መላውም የተገኘው ከ 120 ዓመት ገደማ በፊት አንስቶ ነው።  እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን ፍጻሜ ገደማ ድረስ፤ ውፍረት ለመቀነስ ፣ ምንን እንደሚያካትት እምብዛም የሚታወቅ ነገር አልነበረም።  

Übergewichtiger Mann

ውፍረት በተለይ ከመጠን በላይ ውፍረት ፤ በኤኮኖሚ ዕድገት ታችኛው ጠርዝ ላይ በሚገኙ እንዳንድ አገሮችም በሚያስገርም ሁኔታ ተዛምቶ ቢገኝም ፤ በአማዛኙ የተስፋፋው በኢንዱስትሪ በበለጸጉ ምዕራባውያን አገሮች መሆኑ ሐቅ ነው። በኢንዱስትሪ እጅግ ከገሠገሡት  ምዕራባውያን አገሮች መካከል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዩናይትድ እስቴትስ፤ ከአውሮፓ ደግሞ ጀርመን የመሪነቱን ቦታ ይዘዋል።

ጀርመን እንዲህ ብዙ ወፍራም ዜጎች እንዳሏት ልብ ያላቸው መዘርዝር ጥናቶች ከቀረቡ ወዲህ ነው።  እናም ሁኔታው አያሳስብም አይባልም። ዋና ማዕከሉ በበርሊን ከተማ የሚገኘው፣  የሮበርት  ኮህ ተቋም ካካሄደው ጥናት በመነሣት፣ ከጀርመን ሴቶች 53 ከመቶው ፣ 67 ከመቶው  ደግሞ ወንዶቹ፤ ከመጠን በላይ ወፍራሞች መሆናቸውን  አስታውቋል። በአጠቃላይ ከሞላ ጎደል ከ የ 4ቱ ጀርመናዊ አንዱ ፤ ከመጠን በላይ በመወፈር፤  የጤና ጠንቅ የሚሆኑ ችግሮች ተደቅነውበታል። በጀርመን ሀገር፤ በአሁኑ ጊዜ፤ ዕድሜአቸው በ 3 እና 17 ዓመት መካከል የሚገኝ፤ 1,9 ሚሊዮን ልጆችና ወጣቶች፣ መጠን ባለፈ ውፍረት የሚቸገሩ ናቸው። 800,000 የሚሆኑት ደግሞ አደገኛ ውፍረት ያጋጣማቸው ናቸው። ምሳሌ እንጥቀስ፤ ሲስተር  ሶንያ ቤርትዝባህ ይባላሉ ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት 152 ኪሎግራም ይመዝኑ ነበር፤ በ 1,ሜትር ከ 74 ሴንቲ ሜትር ቁመት ላይ!

Dicke Frau beim Bellydance

ዛሬ ፣ ጥብቅ የኪሎ ቅነሣ እርምጃ በመውሰድ ፤ የ 34 ዓመቷ ነርስ፣ ክብደታቸው ወደ 83 ኪሎ ግራም ዝቅ ብሏል።  ሲስተር ቤርትዝባህ፤ በመጀመሪያ ፣ እንዴት ያን ያህል እስከመወፈር እንደደረሱ ሲያስረዱ፤ በሥራ በመጠመድ ብዙ እያመሹ የሚሠሩት ነርስ፤ ወደ ቤት ሲመለሱ የተዘጋጀ ፒሳ እያሞቁ ፣ እንዲያም ሲል ቸኮሌት ጭምር አዘውትረው  መመገባቸው፣ መጠን ላለፈ ውፍረት እንደዳረጋቸው አስረድተዋል። ትንሽ በስጨት ሲሉም በተጨማሪ  ይኸው ምግብ ማረሳሻም ሆነ ንዴት ማብረጃ ሆኖላቸው እንደነበረ ገልጸዋል።  የሆነው ሆኖ በወሰዱት ቆራጥ እርምጃ፤ የአመጋገብ ሥልታቸውን  መለወጣቸውንና፤ በድስፕሊን  በመታነጻ ብዙ በመንቀሳቀስ ፤ ለወጤት መብቃታቸውን ያስረዳሉ።

Argentinien Fußball Trainer Maradona

ከመጠን በላይ ክብደት መጨመርና በሰውነት የቅባት መብዛት፣

ከመጠን በላይ ክብደት ሲባል፣ በሰውነት፣ ሠራ አካላት ውስጥ የቅባት መብዛት ወይም መጠራቀም ማለት ነው።  በሰውነት ውስጥ የቅባት መብዛትንም ሆነ ማነስ መለካት የሚቻለው፣ የክብደት መጠንን ፣ እጥፍ በሚባዛ የቁመት መጠን በማካፈል ነው ። በመጠነኛ ክብደት አካባቢ ፣ የቅባት መጠን ከ 20 እስከ 25 ፣ ትንሽ ክብደት በጨመረ ሰው ደግሞ ከ 25 እስከ 30 ይሆናል ማለት ነው። በሰውነት ውስጥ የቅባት መጠን  በአንግሊዝኛው «ባዲ ማስ ኢንዴክስ» የሚሰኘው ከ 30 በላይ ከሆነ ፣ ከፍተኛ የአንደኛ ደረጃ የቅባት መጠን  መብዛት ይባላል። ከ 35 ጀምሮ ደግሞ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ፤ 40 ከደረሰ ግን ፤ ሰውየው የህክምን እርዳታ የሚያስፈልገው እጅግ ከፍተኛ ፤ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑን የእጅግ ወፍራም ጀርመናውያን ማኅበር ባልደረባ እሽቴፋኒ ጌርላህ ያስረዳሉ።

አንድ ሰው እጅግ  በጣም የሚወፍረው ባንድ በኩል የተሳሳተ አመጋገብ ይሁን እንጂ፤ ከዘር ሊወረስም ይችላል። ሰው የሚኖርበት፣ የሚሠራበት ሁኔታ፤ የትምህርት  ደረጃም፣ ተጽእኖ ሊያደርግ እንደሚችል ይታሰባል። ። የትምህርት ደረጃቸው ላቅ ያለና ጠቀም ያለ ደመወዝ የሚከፈላቸው ሰዎች ፣ በመሠረቱ ስለጤንነት የተሻለ  ንቃተ ኅሊናና  አዎንታዊ አመለካከትም ሊኖራቸው እንደሚችል  ነው የሚነገረው። 

ከመጠን በላይ ውፍረት ፣ ለምንድን ነው እንደማይበጅ  በየጊዜው በሰፊው የሚገለጠው? አደጋው ፣ የጤናና የአመጋገብ ጉዳይ ጠበብት እንደሚሉት፤ የሚያሠጋው ፣ እምብዛም ውፍረቱ ሳይሆን ፤ ውፍረትን ተከትለው የሚከሠቱት  የተለያዩ በሽታዎች ናቸው። እነርሱ ደግሞ ብዙዎች ናቸው። ከመጋጠሚያዎች እንከን አንስቶ፣  እስከ ስኳርና ብርቱ የዑደተ ደም መታወከና    የደም ግፊት ጣጣ ያጋጥማል ፤ ልጆች ደግሞ የኩላሊት መታወክ ሊደርስባቸው ይችላል። በዚህ ላይ መጥፎ ሁኔታን ሊያስከትል የሚችል ድብርትም ይፈታተናል።  ኅብረተሰቡም ቢሆን፣ በየዕለቱ፤ በገበያም ሆነ በአውቶቦስ፤ በባቡር ሆነ «ትራም» መጠን ያለፈ ክብደት ባላቸው ሰዎች ላይ በተለያየ መንገድ አድልዎ እንደሚፈጽምባቸው ይነገራል።  በዛሬው ዘመን ፤ ጎልማሶችና ውይዛዝርት ብቻ ሳይሆኑ በዛ ያሉ ልጆችም ናቸው የዚህ መጠን- ያለፈ ክብደትም ሆነ ውፈረት ሰለባዎች የሚሆኑት። በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮች፣ ልጆች፣ ፍራፍሬና ቅጣለ-ቅጠል ከመብላት ይልቅ፤ ሀምበርገርና በዘይት የተጠበሰ ድንችና የመሳሰለውን ስለሚያጋብሱ ነው ከድምቡሽነት ወደ መድበልበል የሚሸጋገሩት። ከመጠን በላይ የወፈሩ ልጆችም ሆኑ ጎልማሶች፤ እንደ ችግሩ መንስዔ ዓይነት፣ የሥነ ልቡናም ሆነ የአመጋገብ አማካሪዎች፣ በአጠቃላይ ፣  የተለያዩ ባለሙያዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። እጅግ በጣም ወፍራም  የሆኑ ሰዎች፤ ወይም መጠን ያለፈ ክብደት ያላቸው ሰዎች፤ እንበል ከ 200 በላይ እስከ 270 ኪሎግራም የሚመዝኑትን፤ ያለው አማራጭ እርዳታ ፣ በቀዶ ጥገና ህክምና እርዳታ ብቻ፣  ክብደታቸው ወደ 100 ኪሎግራም ዝቅ እንዲል ማድረግ  መሆኑ ተመልክቷል።  እንዲህ ዓይነቱ የቀዶ ጥገና እርዳታ፤ ክብደትን ግማሽ- በግማሽ መቀነስ የሚያስችል ነው።  በአንዳንድ ሁኔታ፤ 80 ከመቶ ብቻ ነው እርዳታ ማቅረብ የሚቻለው። በምዕራብ ጀርመን ኤሰን በተባለችው ከተማ ፣ ማርቲን ፕሮናድል የተባሉት የአልፍሪድ ክሩፕ ሀኪም ቤት ባልደረባ እንደሚሉት፣ በያመቱ ከ 120 -140 መጠን ያለፈ ክብደት ላላቸው ሰዎች የቀዶ ጥገና ህክምና ይደረጋል።

ሰዎች ለምን ከመጠን በላይ ይወፍራሉ? አጭሩ መልስ፤ ቅባት የበዛበትና ከመጠን በላይ ኃይልና ሙቀት  ሰጪ የምግብ ዓይነቶችን አዘውትሮ መመገብ ሊሆን ይችላል።  በመሆኑም በዚህ በምዕራቡ ዓለም እስካኒዲኔቪያዊቷ ሀገር ደንማርክ ፤ ቅባትነት ባላቸው የምግብ ዓይነቶች ላይ ፣ ከ 2,3 ከመቶ በላይ የቅባት ቀረጥ የተሰኘ ቀረጥ ካለፈው ጥቅምት ወር አንስቶ በማስተዋወቅ፤  በዓለም ውስጥ ፣ በዚህ ረገድ የመጀመሪያቱ ሀገር ለመሆን በቅታለች።   ተጨማሪ 2 ዩውሮ ከ 15 ሳንቲም ቀረጥ የተጣለባቸው የምግብ ዓይነቶች፤ በገበያ አዳራሾችም ሆነ ሱቆች የሚገኙ ፣ ወተት ፣ ሥጋ፤ ፒሳና የመሳሰሉ ብዙ ቅባት እንዲይዙ ተደርጎ የተሰናዱ የምግብ ዓይነቶች ናቸው።

ከመጠን በላይ ውፈረትም ሆነ  የክብደት መጨመር፣ በዝግጅታችን መግቢያ ላይ እንደጠቀስነው፣ ይበልጥ በኢንዱስትሪ የገፉትን አገሮች ዜጎች ያሳቸገረ ጉዳይ ይሁን እንጂ በዓለም ዙሪያ የተከሠተ ችግር ነው። ይኸው ችግር ጎልቶ የሚታይባቸው አገሮች፤ ማለትም፣

በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ ከመጠን ባለፈ የወፈሩሰዎችየሚገኙባቸው ግንባር ቀደም ሃገራት(Fattest Nations in the Word

1,ዩናትድ እስቴትስ፣

2, ሜክሲኮ

3, ብሪታንያ

4, እስሎቫኪያ

5, ግሪክ፤ ናቸው ይላል ፣ ድ የመዘርዝር ጥናት ፤ ሌላው ደግሞ

1, ዩናይትድ እስቴትስ

2, ክዌት

3,ክሮኤሺያ

4,ቓታር

5,ግብፅና -የመሳሰሉት እንደሚገኙበት ይዘረዝራል። በዛ ያሉ ዝርዝር ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ከህዝብ ብዛት መጠን አኳያ ከሆነ፣ በውፍረት ክብረ ወሰን የሚይዙ፤ ከአውስትሬሊያ በስተሰሜን ምሥራቅ፤  በሰላማዊው ውቅያኖስ የሚገኙ አንዳንድ የፖሊኔሺያ ደሴቶች ናቸው። እዚህ ላይ በአንደኛ ደረጃ የምትጠቀሰው፤ ንዑሷ ሀገር ናውሩ ናት። የህዝቧ ብዛት 14,000 ሲሆን፤ 97 ከመቶ ወንዶቹ እንዲሁም 93 ከመቶ ሴቶቹ፤ ከመጠን በላይ ወፍራሞች ናቸው።  ባጠቃላይ  94,5 ከመቶው ህዝቧ ከመጠን በላይ ወፍራም ነው። የሚክሮኔሺያ ፈደራል ጋዛቶችም ፣ ህዝባቸው 91 ከመቶው ተመሳሳይ ችግር አለበት። ከ 107,000 ው ፤ 91 ,1 ከመቶው ክብደቱ መጠን ያለፈ ነው።

እጅግ የከሱ ፤ ምናልባትም የቀጨጩ ዜጎች በባዛት ያላቸው ደግሞ፣

1,ሰሜን ኮሪያ፤

2,ካምቦዲያ፣

3, ቡሩንዲ

4,ኔፖል

5,ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ  እና የመሳሰሉት ናቸው።

ሌላ የጥናት ውጤት እንደሚጠቁመው ግን

በዓለም ውስጥ በቅጥነት  ወይም በአነስተኛ የክብደት መጠን የታወቁ አገሮች፤

1፤ ኤርትራ /ወደ  5 ሚሊዮን ከሚጠጋው ህዝቧ ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው 4,4 ከመቶ ብቻ ናቸው።

2, ኢትዮጵያ 5,6 ከመቶ ብቻ ናቸው ከመጠን በላይ ክብደት ያላቸው።

3, ባንግላዴሽ፣ 6,1 ከመቶ

4, ቪየትናም፤ 6,4 ከመቶ

5, ስሪላንካ  7,4 ከመቶ

Übergewichtiger Wassersportler auf der Warnow

በኤኮኖሚ ችግር ፤ በአጠቃላይ በሁለንተናዊ ዕድገት ኋላ ቀርነት የአንድ ሀገር ህዝብ ጤንነቱ መጥፎ ደረጃ ላይ ቢገኝ፣ ላያስደንቅ ይችላል። ከምግብ መትረፍረፍ፤ ከድሎት የተነሣ ፤ ሰው የራሱን ጤንነት የሚጎዳበት ሁኔታ ሲፈጠር ግን ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ነው። ከ 25 የአውሮፓው ኅብረት አገሮች ፤ በአሁኑ ጊዜ፤ ጀርመን፤ ከመጠን በላይ ክብደት ባላቸው ሰዎች  የመጀመሪያውን   ደረጃ ይዛ ትገኛለች፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት፤ የመሪነቱን ቦታ ይዛ የነበረች፤ ቼክ ሪፓብሊክ፤ ቀጥላ ቆጵሮስ ፤ በ3ኛ ደረጃ ብሪታንያ ነበረች። አሁን ግን ፣

1, ጀርመን ፣

2,ብሪታንያ፤

3, ቆጵሮስ

4, ቼክ ሪፓብሊክ

5, ፊንላንድ

6, እስሎቫኪያ

7, ላትቪያ

8, ሀንጋሪ

9, አየርላንድ

10,እስፔይን ---ናቸው።

በክብደት ፣ ለጤንነት በሚበጅ  ሁኔታ መጠነኛም ሆነ ዝቅተኛ ደረጃ የያዘች በመዘርዘሩ መጨረሻ ላይ የምትገኝ ኢጣልያ ስትሆን ፤ ተከታይ ፈረንሳይ ናት።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic