1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኤርትራ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን የኤርትራ መንግሥት በሃገሪቱ ያለገደብ ለተስፋፋው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠያቂ ነው ሲል ከሰሰ ። በመንግስት እርምጃ ምክንያት በየወሩ ወደ 5ሺህ ኤርትራውያን ከሃገራቸው እንደሚሰደዱ ኮሚሽኑ ትናንት ይፋ ባደረገው ዘገባ አስታውቋል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:59

የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኤርትራ

ዘገባውን ካዘጋጁት ሶስት የኮሚሽኑ አባላት አንዷ ሼይላ ኪታሩዝ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ በኤርትራ ሆነ ተብለው ከሚደርሱት የስብዓዊ መብት ጥሰቶች መካከል በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ሊገኙበት እንደሚችሉም ተናግረዋል ።
ባለ 500 ገፁ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት አጣሪ ኮሚሽን ዘገባ ባለፉት 22 ዓመታቱ «የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የብረት ጡንቻ አገዛዝ » ሰዎች በዘፈቀደ እንደታሰሩ ቁም ስቅል እንደተፈጸመባቸው እንደተገደሉ ወይም የደረሱበት እንዳልታወቀ ዘርዘሯል ። ዘገባው ለነዚህ የመብት ጥሰቶች ተጠያቂ ከሚላቸው መካከል ወታደሩ ፖሊስ የሃገሪቱ የፍትህ ሚኒስቴርና ራሳቸውን ፕሬዝዳንት ኢሳይስ አፈወርቂ ይገኙበታል ።ዘገባውን ካዘጋጁት ሶስት የኮሚሽኑ ባልደረቦች አንዷ ሼይላ ኪታሩዝ በኤርትራ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚፀሙት በመንግሥት መሆኑን ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል ።
«ኤርትራ ውስጥ በመንግሥት ትዕዛዝ ሆነ ተብሎ በተጠና ዘዴ መጠነ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፈፀማሉ ።ከነዚህ መካከል አንዳንድ በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎችም ይገኙበታል ።በምርመራችን ሆነ ተብለው በስልታዊ መንገድ የሚፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዳሉ ለይተን ለማወቅ ችለናል ።ያ ማለት ሰብዓዊ መብትን የመጣሱ ተግባር እንዲሁ በአጋጣሚ

የሚደርስ ሳይሆን በተጠና መልኩ ነው የሚከናወነው ። »
ዘገባውን ያዘጋጁት ኪታሩዝ ና ባልደረቦቻቸው ወደ ኤርትራ ለመሄድ አልቻሉም ።ዘገባውን የፃፉትም በውጭ ለሚኖሩ 550 ኤርትራውያን ያደረጉትን ቃለ መጠየቅና በፅሁፍ የደረሷቸውን 160 ማስረጃዎች መሠረት በማድረግ ነው ። አጣሪዎቹ በሃገር ውስጥ ተገኝታችሁ ያላካሄዳችሁት የዚህ ጥናት ውጤት ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል ተብለው የተጠየቁት ኪታሩዝ ኤርትራ ሳይሄዱ ጥናቱን ያካሄዱበትን ምክንያትና ተዓማኒ ዘገባ ለማቅረብ የተደረገውን ጥረት አስረድተዋል ።
«ኤርትራ ሄደን ምርመራውን በሃገር ውስጥ ማካሄድ ብንችል ደስ ባለን ነበር ። ሆኖም የኤርትራ መንግሥት መረጃ እንዲሰጠን ላቀረብነው ጥያቄአችን መልስ አልሰጠንም ። ሃገሪቱ እንድንሄድም አልተጋበዝንም ።ሆኖም ከተለያዩ ሰዎችና ከተለያዩ ቦታዎች መረጃዎችን አሰባስበናል ።መረጃዎቹ የተጠናከሩ ተዓማኒነት ያላቸው በመሆናቸው ከሩቅ የተሰበሰበ ነው በሚል እውነታውን የሚያደበዝዝ ይሆናል ብለን አናስብም ። ገሪቱ ነፃ ከወጣችበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ባለው ረዥም ጊዜ ውስጥ ሰዎች የደረሰባቸው የመብት ጥሰቶች ፣የተባሉት መሆናቸውን ለማረጋገጥ አሰፈላጊውን ሁሉ ጥንቃቄ አድርገናል ። በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች ማስረጃዎችን በፅሁፍ በመላክ ወይም ደግሞ በአካል በመቅረብ ከአጣሪው ኮሚሽን ጋር ግንኑነት ነበራቸው ። የተሰበሰቡት ቃሎች በሃገሪቱ የሚፈፀሙትን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በትክክል የሚያንፀባርቁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ

አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጓል ። »
ኪታ ሩዝ እንደሚሉት ከዛሬ 24 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ የተገነጠለችው ኤርትራ በህግ ሳይሆን በፍርሃት ነው የምትተዳደረው ። ውጭ የሚገኙት የተከፉ ኤርትራውያን ምስክርነታቸውን ለመስጠት ይከብዳቸው እንደነበር ኪታሩዝ ሳያነሱ አላላፉም ። የዚህ ምክንያቱም የኤርትራ የስለላ መረብ ከሃገር ውጭ እጅግ የተንሰራፋ በመሆኑ ትውልድ ሃገራቸው ውስጥ በቤተሰባቸው ላይ የበቀል እርምጃ ይወሰድብናል ብለው ስለሚያስቡ ነው ብለዋል ።በኤርትራም መንግሥት በዜጎቹ ላይ የሚያካሂደው ስለላ የተጠናከረ መሆኑን ተናግረዋል ።
«ጎረቤቶች ሌሎች ሰዎችን ይሰልላሉ ።ሰላዮች የሚመለመሉበት የተጠና ዘዴም አለ ። የአንድ ቤተሰብ አባላት ሳይቀሩ ማንን ማመን እንደሚችሉ አያውቁም ።ሰዎች በሰላዮች መረብ የተሰበሰበባቸው መረጃ እነርሱን ለመጉዳት ጥቅም ላይ ይውላል ብለው ይፈራሉ ፤በዚህ መንስኤ በዘፈቀደ ልንታሰር ወይም ሌላ ችግር ውስጥ ልንወድቅ እንችላለን ብለው ይሰጋሉ ። እናም ይህ የፍርሃት ድባብ ፈጥሯል» የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባለፈው ዓመት በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት በኤርትራ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ላይ የተካሄደውን ምርመራ ውጤት የያዘውን ዘገባ አጣሪዎቹ የዛሬ ሁለት ሳምንት ለምክር ቤቱ ይቀርባል ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic