1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሜርክል በኢትዮጵያ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 5 2009

የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ኢትዮጵያን ጨምሮ በሦስት የአፍሪቃ ሃገራት ያደረጉት የሦስት ቀናት ጉብኝት በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ኾኗል። በተለይ መራኂተ-መንግሥቷ ኢትዮጵያን በይፋ የጎበኙት ሀገሪቱ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተደነገገ በሁለተኛው ቀን መኹኑ ጠንካራ ትችት አስከትሎባቸዋል።

https://p.dw.com/p/2RCVs
Deutschland Merkel in Äthiopien Empfang mit militärischen Ehren
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Ayene

Fokus Africa 15.10.2016 (Merkel Afrika Besuch) - MP3-Stereo

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ወቅትየኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ክፍት እንዲያደርግ ሳይጠቁሙ አላለፉም። በእርግጥ የጉዟቸው ዋነኛ ዓላማ አውሮጳን ያስጨነቀው እና ያሰጋው የአፍሪቃውያን ፍልሰት ባለበት እንዲገታ ከአፍሪቃውያኑ መሪዎች ጋር መነጋገር ቢሆንም ማለት ነው። በአፍሪቃ የጸጥታ እና የደኅንነቱ ጉዳይ እንዲጠናከር ማድረግም የመራኂተ-መንግሥቷ አብይ አጀንዳ ነበር። 

የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ኢትዮጵያን ጨምሮ ላደረጉት የሦስት ቀናት የአፍሪቃ ጉብኝታቸው በመጀመሪያ ያቀኑት ወደ ሳህል አካባቢ ሃገራት ነበር። በማሊ የአንድ ቀን ቆይታቸው መዲና ባማኮ ውስጥ ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ኢብራሒም ቦባካር ኬታ ጋር ባደረጉት ውይይት በሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተንሰራፋውን ጽንፈኝነት ለመታገል ጀርመን ትብብር እንደምታደርግ ገልጠዋል። በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን ወደ አውሮጳ የሚደረገው ፍልሰትም ባለበት እንዲከስም ስለሚቻልበት መላ ተወያይተዋል።

Afrika Kanzlerin Merkel besucht Niger
የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከኒጀሩ ፕሬዚዳንት ማኅማዱ ኢሶፉ ጋርምስል Getty Images/AFP/B. Hama

በበነጋታው ወደ ኒጀር ያቀኑት ሜርክል እዛም ያነሱት ተመሳሳይ አጀንዳ ነበር። ጽንፈኝነትን መዋጋት እና ፍልሰትን መግታት። ለዚያ ዓላማ በሚል ደግሞ የዓለማችን እጅግ ድኃ ለሆነችው ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ኒጀር €27 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ እና የቁስ ርዳታ እንደሚለግሱ ቃል በመግባት ነበር ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት። 

ኢትዮጵያ ሲደርሱ ተመሳሳይ ግብ ይዘው ቢሆንም፤ ሌላ ነገር ግን ይጠብቃቸው ነበር። የፖለቲካ ምስቅልቅል እና  ከ25 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይዞት የመጣው ስጋት። 

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የተቃውሞ ሰልፎች በኢትዮጵያ እንዲፈቀዱ አጽንዖት ሰጥተዋል። ከአዲስ አበባ ሆነው በሰጡት መግለጫም በዴሞክራሲ ሥርዓት ፓርላማን ጨምሮ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ድምጽ ሊኖር ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

«አንድ ዴሞክራሲ የተሟላ የሚሆነው በፓርላማ ውስጥም የተቃዋሚዎች ድምጽ ሲታከልበት ነው። ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በመገናኛ ዘዴዎች አማካይነት የተለያዩ አስተሳሰቦችን ማንሸራሸር እና ውይይት ማድረግ አስፈላጊ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ገቢራዊ እንዲሆን መሠራት አለበት። አሁን የታሰበው የለውጥ እርምጃቸው ከዚህ ጋር የተያያዘ ከሆነ በምክር ቤት ውስጥም የተለያዩ ሥሜቶችን ለማንጸባረቅ ይቻል ይሆናል»  

Äthiopien Regierung Soldaten ARCHIV
ምስል picture alliance/AP Photo/ltomlinson

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በተጨማሪም የተቃውሞ ሰልፎች በኢትዮጵያ እንዲፈቀዱ አጽንዖት ሰጥተዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተቃውሞ ሰልፎችን ጨምሮ በርካታ መብቶችን የሚገድብ ነው። አዋጁ፦ «ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል፣ የመናገር ነፃነትን መገደብ፣ የመሰብሰብ መብትን ማገድ» እና የሌሎች መብቶችን ገደብንም ያካተተ እንደሆነ ተጠቅሷል። 

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል አዲስ አበባ ሲገቡ የኢንተርኔት አገልግሎት በስፋት ተቋርጦ ነው የቆያቸው። የተቃዋሚ ፖለቲከኞች አባላት እና ዜጎችም በጸጥታ ኃይላት ተይዘው እስር ቤቶች ውስጥ ይጣሉ እንደነበር ተዘግቧል። እናም በዚህ ኹኔታ ውስጥ መራኂተ-መንግሥቷ ወደ ኢትዮጵያ ማቅናታቸው ተገቢ እንዳልነበር የአውሮጳ ምክር ቤት አባል የኾኑት ወ/ሮ አና ጎሜሽ ጠንከር ባለ ትችት ገልጠዋል።

«ሌላው ቢቀር ትናንት ወ/ሮ ሜርክል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተደንግጎም ሀገሪቱን መጎብኘታቸው የሁላችንም የጋራ ሐፍረት ነው።»

ወ/ሮ አና ጎሜሽ በአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት የልማት ኮሚቴ እና የሰብአዊ መብቶች ንዑስ ኮሚቴ አባላት ባለፈው ረቡዕ እለት ባደረጉት ኢትዮጵያን የተመለከተ ውይይት ላይ በኢሬቻ በአል ላይ የሞቱትን ሰዎች ጨምሮ በሀገሪቱ የሚከናወነውን ጭቆና የሚከታተል ገለልተኛ አጣሪ ቡድን ሊኖር ይገባል ብለዋል። ኢንተርኔትን እና ሚዲያን የሚገድበው  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳም ጠይቀዋል። የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱም ጥሪ አስተላልፈዋል። በስብሰባው ላይ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወክለው የተናገሩት በቤልጂግ የኢትዮጵያ  አምባሳደር የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲ አማካሪ አቶ ዮሐንስ አብራኃ ናቸው። የመንግሥት ተወካዩ መንግሥታቸው ዲሞክራሲን ተግባራዊ ከማድረግ ውጪ ሌላ የተሻለ አማራጭ እንደሌለው ተናግረዋል። 

«ክብርት ሊቀ መንበር፣ እንዲሁም ክቡራን  እኛ ዲሞክራሲን ኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ እያደረግን ነው  ብለን እናምናለን። ይኼን የምናደርገውም ሌሎችን ለማስደሰት ሳይሆን፤ የምናደርገው ሕዝባችን እና ሀገራችን ስለሚፈልጉት ነው።»

Afrika Kanzlerin Merkel in Äthiopien Einweihung Julius-Nyerere Gebäude für Frieden und Sicherheit
የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ መርቀው ያስከፈቱት የአፍሪቃ ኅብረት ጁሊየስ ኔሬሬ ሕንጻምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

ወደ መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የኢትዮጵያ ጉብኝት ጉዳይ ስንመለስ ሜርክል አዲስ አበባ ውስጥ የአፍሪቃ ኅብረት ቅጥር ግቢ በመገኘት በጀርመን መንግሥት ድጋፍ የተገነባውን የአፍሪቃ ኅብረት የሠላም እና የፀጥታ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት ሕንጻ መርቀዋል። ሕንጻው ከጀርመን የ30 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ የተደረገበት ሲኾን፤ የተገነባውም በጀርመን ተቋም ነው። መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ከተቃዋሚ ፓርቲ  እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም ከጠቅላይ ሚንሥትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር በተለያየ ስፍራ ተወያይተዋል። 

ሜርክል ከተቃዋሚ ፓርቲ እና ሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይት ዐርባ ደቂቃ ግድም የፈጀ ውይነበር። በውይይቱ አንጋፋዎቹ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ ተሳትፈዋል፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ የጋዜጠኛ ማኅበር ተወካይ፣ ጠበቃ እና ጦማሪም በውይይቱ ተገኝተዋል። ይኽ ውይይት በአብዛኛው ትኩረት ያደረገው በኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ እና መንግስት በሚወስዳቸው እርምጃዎች ላይ እንደነበር በውይይቱ የተካፈሉ ለዶይቸ ቨለ ገልጸዋል፡፡ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና፤ 

በኢትዮጵያ መሠረታዊ ጉዳይ፤ «ሕዝቡ እየጠየቀ ያለው መሠረታዊ ለውጥ ነው።» ያሉት ዶር መረራ ጉዲና ነገሮችን «ቀባብቶ መንግሥት ኹኔታዎችን ለመቆጣጠር የሚያደርጋቸው ነገሮች መሠረታዊ ችግሩን አይፈታም» ብለው ለሜርክል መናገራቸውን አስታውቀዋል። መራኂተ-መንግሥቷ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ለውጥ ለማድረግ  ቃል እንደገባላቸው ክትትል እንደሚያደርጉም  መናገራቸውን ዶ/ር መረራ ጠቁመዋል። 

Demonstration der Semayawi-Partei in Addis Ababa Äthiopien 22.09.2013
የሰማያዊ ፓርቲ ዓርማን የሚያውለበልብ ወጣትምስል DW

ውሎም ሳያድር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚው ሰማያዊ ፓርቲ በርካታ አባላቱ በመንግሥት ፀጥታ ኃይላት መታሰራቸዉን አስታውቋል። ወ/ት ብሌን መሥፍን፣ አቶ እያስፔድ ተስፋዬ እና አቶ አወቀ ተዘራን እንዲሁም ከዋግ ህምራ ለጠቅላላ ጉባኤ የመጡ አንድ የአመራር አባል እና ሌላ አንድ አባልን ጨምሮ ስድስት አባላቶቻቸው መታሰራቸውን የፓርቲዉ የብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ይድነቃቸዉ ከበደ ለዶይቸ ቬለ በስልክ ተናግረዋል።

«የታሰሩበትን ምክንያት በግልጽ ባናውቅም ግን ይኼ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን በግልጽ ከቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ከአባሎቻችን ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው ወደ 6 የሚኾኑ አባሎቻችን ታስረውብናል።»

መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በአፍሪቃውያን ስደተኞች እና የአህጉሪቱ የጸጥታ ኹናቴ በርሊን ውስጥ የተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎችን እየተቀበሉ ሲያነጋግሩ ከተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን ደግሞ በአውሮጳ ኅብረት ፊት ለፊት ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። 

በመንግሥት ታጣቂዎች የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን ለማሰብ በተለያዩ የአውሮጳ ሃገራት ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሐሙስ እለት ቤልጅግ ብራስልስ ውስጥ ሠልፍ አድርገው ነበር። ኢትዮጵያውያኑ በኢሬቻ በዓል ላይ እንዲሁም ከበዓሉ በፊት  እና በኋላ ለሞቱት ኢትዮጵያውያን የመታሰቢያ ሻማ ማብራት ሥነስርአት አከናውነዋልም።  በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ግድያ እና  እስራትም የአውሮጳ ኅብረት እንዲያስቆም በመጠየቅ አቤት ብለዋል። በተወካዮች በኩልም የተፃፉ ደብዳቤዎችን ለአውሮጳ ኅብረት ባለሥልጣናት አድርሰዋል።  ከሰላማዊ ሰልፈኞቹ ተወካዮች መካከል አንዱ አቶ አበራ የማነአብ ከሚመለከተው የአውሮጳ ኅብረት ክፍል ባለሥልጣናት ጋር ፊት ለፊት መነጋገራቸውን ገልጠዋል። 

Berlin Merkel trifft Tschads Präsident Idriss Deby Itno
ምስል picture-alliance/AP Photo/M. Schreiber

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የአፍሪቃ ሃገራትን ጎብኝተውም ኾነ የአፍሪቃ ሃገራት መሪዎች መዲናቸው በርሊን ድረስ መጥተው ቢወያዩም ዋነኛው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እና የዲሞክራሲያዊ መብቶች እጦት እስካልተቀረፈ ድረስ የአፍሪቃውያን ፍልሰት እና የአካባቢው ጸጥታ ስጋት የሚረግብ አይመስልም። 

የዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል ኃላፊ ሉድገር ሻዶምስኪ ባቀረበው አስተያየቱ የመራኂተ-መንግስቷ ንግግርን በማጣቀስ፦ «አዲስ አበባ ላይ አፍሪቃ ግሩም የሆኑ ጭንቅላቶችን ማጣት አይኖርባትም ብለዋል። ይህ አላዋቂነት ይመስላል፤ ምክንያቱም ምርጥ የተባለ ጭንቅላት ያላቸዉ ኢትዮጵያዉያን ዛሬ በሀገራቸዉ ሊያኖራቸዉ የሚችል ተስፋ በማጣታቸዉ ዋሽንግተን ላይ ታክሲ ይነዳሉ።» ሲል የመራኂተ-መንግሥቷ ግብ እና ተግባራዊነቱ ላይ አጠያይቋል። በእርግጥም የጀርመን መራኂተ-መንግሥትም ኾኑ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ አድራጊዎች እንደመኾናቸው መጠን ሀገሪቱ የገባችበትን ውስብስብ ችግር እስካላጤኑ ድረስ ነገ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በርካታ አፍሪቃውያን በገፍ ወደ አውሮጳ ስላለመፍለሳቸው መቼም እርግጠኛ ሊኾኑ አይችሉም።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ