የሜርክል የአፍሪቃ ጉብኝት | አፍሪቃ | DW | 12.10.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የሜርክል የአፍሪቃ ጉብኝት

መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በማሊ፣ ኒዠር እና ኢትዮጵያ ያደረጉትን የሦስት ቀናት ጉብኝት አጠናቀዋል። የጉዟቸዉ ዋና አላማም ስደትን መግታት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን የሚገልጸዉ የዶቼ ቬለዉ የሉድገር ሻዶምስኪ አስተያየት፤ አስቸጋሪ ይለዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:25

ሜርክል በአፍሪቃ

መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል በአፍሪቃ ያደረጉትን የሦስት ቀናት ጉብኝት የገመድ ላይ ጉዞ ሲል ይገልጸዋል ሉድገር ሻዶምስኪ በጻፈዉ አስተያየት። አስቀድመዉ በረሃማዎቹ ሃገራት ማሊ እና ኒዠር ደርሰዉ ወደ ኢትዮጵያ ያቀኑት ሜርክል ሙቀቱ ወይም የጉዟቸዉ ሁኔታ ያስከተለዉ ሊሆን ይችላል ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ብሩህ ፊት አላሳዩም። ከመራሂተ መንግሥቷ ጉዞ አስቀድሞ ቃል አቀባያቸዉ፤ ኢትዮጵያ ዉስጥ ስላለዉ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ እንደሚናገሩ ገልጸዉ ነበር። እርግጥ የጀርመን ተጓዳኝ በሆነችዉ የአፍሪቃ ቀንድ ሀገር የዴሞክራሲ እጥረት መኖሩን በግልፅ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል መራሂተ መንግሥቷ ለሦስት ቀናት በአፍሪቃ ያደረጉት ጉብኝት ከፍተኛ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን አግኝቷል። በዚህ ወቅት የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር በናይጀሪያ  ያደረጉት ጉብኝት ላይም ጥላዉን በማጥላቱ የተዘነጋ አስመስሎታል። የጀርመን ልዑካን ማሊ እና ኒዠር የነበራቸዉ ቆይታ አዎንታዊ ከሆነ፤ በኢትዮጵያ እንዲሁ እንደታሰበዉ ከሄደ፤ አሸባሪነት እና የስደተኞችን ፍልሰት በመግታቱ ትግል አፍሪቃዉያን ከቱርክ ይልቅ የተሻሉ ተጓዳኝ በሆኑ ነበር። መራሂተ መንግሥቷ ኢትዮጵያ የገቡት በሀገሪቱ ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ በታወጀ ማግስት ነዉ። በጉብኝታቸዉ ቀን ደግሞ የኢንተርኔት አገልግሎት ተዘግቷል። ላለፉት አስርት ዓመታት በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ እየሰጠ ለኖረ አጋር የተለየ አቀባበል መሆኑ ነዉ። ፊት የስሜት ነፀብራቅ ከሆነ መራሂተ መንግሥቷ አዲስ አበባ ላይ ያሳዩት ገጽታ የተሰማቸዉን የሚያመላክት ይመስላል። ሜርክል ሁለት ሚሊየን ገደማ የሚሆኑትን የሶርያ ስደተኞች ባሉበት እንድትይዝላቸዉ ከቱርክ ጋር እንደተዋዋሉት ሁሉ፤ ፈላጭ ቆራጩ የኢትዮጵያ አገዛዝም ከሶማሊያ፣ ሱዳን እና ኤርትራ የፈለሱ 800 ሺህ ስደተኞችን እዚያዉ እንዲያቆይላቸዉ ይፈልጋሉ። ምንም እንኳን ባለፉት ወራት መንግሥት ላይ በተነሳዉ ተቃዉሞ ምክንያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢሞቱም፤ እጅግ አለመረጋጋት በሚታይበት አካባቢ ኢትዮጵያ በበርሊን ዕይታ አሁንም ዓይነተኛ የፀጥታ ጉዳይ ተጓዳኝ ናት።

ጀርመኖች ከኢትዮጵያ መንግሥት ብዙ የሚጠይቁ ከሆነ፤ ወደፊት ከኢትዮጵያ በርካታ ስደተኞች ወደ አዉሮጳ ይፈልሳሉ። ለመተኮስ የማይሳሱት የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች ጫና ያረፈበት 30 ሚሊየን የሚሆነዉን የኦሮሞ ሕዝብ እንዲሰደድ ምክንያት ሲሆኑት በርሊን ዝም ብላ አትመለከትም።   አፍሪቃ ዉስጥ ከሚገኙ ከ54 የተለያዩ ሃገራት ጋር አንድ አስማሚ መፍትሄ ማግኘት አይቻልም። በተጨማሪ በሌላ ምክንያትም በስደት ጉዳይ ላይ ተጓዳኝነት የሚለዉ ያማረ አገላለፅም አይሠራም። ጀርመን እና አፍሪቃ ዉስጥ ያሉት ተጓዳኞቿ የተለያየ አመለካከት ነዉ ያላቸዉ። መራሂተ መንግሥቷ አዲስ አበባ ላይ «አፍሪቃ ግሩም የሆኑ ጭንቅላቶችን» ማጣት አይኖርባትም ብለዋል። ይህ አላዋቂነት ይመስላል፤ ምክንያቱም ምርጥ የተባለ ጭንቅላት ያላቸዉ ኢትዮጵያዉያን ዛሬ በሀገራቸዉ ሊያኖራቸዉ የሚችል ተስፋ በማጣታቸዉ ዋሽንግተን ላይ ታክሲ ይነዳሉ። በርሊን የሥራ መርሃግብር ላይ አተኩራለች፤ የሥራ ዕድሎች በመጥፋታቸዉ በርካታ አፍሪቃዉያን ወጣቶች ሕገወጥ የሰዉ አሸጋጋሪዎች ሆነዋል። የሦስቱ ቀናት ጉብኝት ትምህር የመቅሰሚያ መሆን አለበት፤ ጀርመን እና አዉሮጳ በአፍሪቃ ጉዳይ የምር የሚሠሩ ከሆነ፤ አንድ ተጨባጭ አዉሮጳዊ መፍትሄ ያስፈልጋል። ከላይ ወደታች የማፍሰሱ ነገር ማብቃት አለበት።  የአፍሪቃ ኅብረትን በመርዳቱ በኩል ጀርመን ትክክለኛ ርምጃ ወስዳለች። ምናልባት አዲስ አበባ የሚገኘዉን የኅብረቱን የሰላም እና የፀጥታ ቢሮ ሕንፃ ለመገንባት 30 ሚሊየን ዩሮ ማዉጣት ነበረባት ወይ ብሎ የሚከራከር ይኖራል። ይህ ወጪ የአስቸኳይ ጊዜ ተወርዋሪ ኃይል ሊያቋቁምበት ይችል ነበር ሊባልም ይችላል። እዉነታዉ እና አስፈላጊዉ ነገር ግን የአፍሪቃ ኅብረትን መሰል የአካባቢ ድርጅቶች መጠናከር አለባቸዉ።  ይህ ሁሉ የሚሆነዉ ደግሞ አፍሪቃ አብራ የምትጓዝ ከሆነ ነዉ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የምርጫ ስርዓቱን ለማሻሻል እንዲሁም የፀጥታ ኃይላቸዉን በማሰልጠን ረገድ በገቡት ቃል መሠረት ሊመዘኑ ይገባል። መራሂተ መንግሥቷ በተናገሩት መሠረት «የአፍሪቃ ደህንነት ለጀርመን አስፈላጊ ነዉ።»  ስልታዊ ተጓዳኝ የሆኑት ባለከባድ ሚዛኖቹ ሁለቱ የአፍሪቃ ሃገራት የቻድ እና ናይጀሪያ ፕሬዝደንቶች በዚህ ሳምንት ወደ ጀርመን ይመጣሉ። እናም ይህ የመራሂተ መንግስቷ የገመድ ላይ ጉዞ ቀጣይነት እንዳለዉ ግልፅ ያደርጋል።

ሉድገር ሻዶምስኪ/ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic