1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊኩ ፀረ ባላካ ቡድን

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ በቀድሞ የሴሌካ ሙሥሊም ዓማፅያን አንፃር የሚንቀሳቀሱት ራሱን ፀረ ባላካ ብሎ የሚጠራ የወጣት ክርስትያን ሚሊሺያ ቡድን አባላት ሽብራቸውን አስፋፉ። ሚሊሺያዎቹ ሙሥሊሞቹን ዜጎች መግደል ብቻ ሳይሆን

አካላቸውን እንደሚቆራርጡ፣ ከነነፍሳቸው እንደሚያቃጥሉ፣ ስጋቸውን ይበላሉ። ይህንን ዘግናኝ ድርጊት የሚፈፅመው ደም ያሰከረው የወጣቶቹ ቡድን አባላት እነማን ናቸው? ለዚህ አስከፊ ተግባራቸው ያነሳሳቸው ምክንያትስ ምን ይሆን?

በባንጊ የሚገኘው ቦራፕ የተባለው ቦታ የፀረ ባላካ የወጣቶች ሚሊሺያ ቡድን ጠንካራ ሠፈር ነው። ቦራፕ ባለፈው ዓመት መጋቢት ባማፅያኑ ህብረት ፣ ሴሌካ ከሥልጣን የተወገዱት የቀድሞው ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜ የተወዳደሩበት እና ደጋፊዎቻቸው፣ ጠባቂዎቻቸው እና የፖለቲካ ተጓዳኞቻቸው በብዛት የሚገኙበት የምርጫ ጣቢያም ነው።

Zentralafrika Anti Balaka Sprecher Emotion

ኤሞሲዮን ጎሜስ

በዚህም የተነሳ የሴሌካ ዓማፅያን በዚሁ ሠፈር ብዙ ሕዝብ ገድለዋል፣ ሴቶችን ደፍረዋል፣ ዝርፊያ አካሂደዋል። በዚሁ ጊዜ የሴሌካን ጥቃት አንፃር ለመቋቋም ራሱን ፀረ ባላካ ብሎ የሚጠራ የወጣት ክርስትያን ሚሊሺያ ቡድን መቋቋሙን የቡድኑ ቃል አቀባይ ኤሞሲዮን ጎሜስ አስታውቀዋል።

« ስማችን፣ ማለትም ፣ ፀረ ባላካ ሲተረጎም ፀረ ኤ ኬ ከላሺንኮቭ 47 ጥይት ማለት ነው። ንቅናቄአችን ረጅም ታሪክ ያለው ነው። ፀረ ባላካ ወንበዴዎችን ለመታገል እና ለማሰር ከብዙ ጊዜ በፊት፣ ብሎም፣ ከፍራንስዋ ቦዚዜ ዘመን በፊት የተቋቋመ ቡድን ነው። ይሁንና፣ ሚሼል ጆቶዲያ በሴሌካ ዓመፅ ሥልጣን ከያዙ እና የሴሌካ ዓማፅያን በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎችን ከረሸኑ፣ ከገደሉ እና ካረዱ በኋላ ነበር እነዚህን ወንበዴዎች ለመታገል ስንል እንዳዲስ የተደራጀነው። »

ብዙዎቹ የፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች ያልተማሩ ወጣቶች፣ አንዳንዶቹ እንዲያውም አስራ ዓመት እንኳን ያልሞላቸው ህፃናት ናቸው። ዘመዶቹ የሴሌካ ጥቃት ሰለባ የሆኑበት አንድ ወጣት ሚሊሺያ እንዳስረዳው፣ በቀል የመውሰድ ፍላጎት የዚሁ ቡድን አባል እንዲሆን አድርጎታል።

« አሁን ብቻዬን ነኝ። የሴሌካ ዓማፅያን መጋቢት 24፣ 2013 ዓም ባንጊን በያዙበት ጊዜ አባቴን ገደሉት፣ ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ አባቴ የደበቀው መሳሪያ አለ በሚል ሰበብ እንደገና ቤታችን መጡ፣ እናቴ እና እህቴ አንድም የተደበቀ መሳሪያ እንደሌለ በነገሩዋቸው ጊዜ እነሱንም ገድለዋቸው ሄዱ። እኔ እንደዕድል እቤት አልነበርኩም፣ ስመለስ ግን ሁለቱም ሞተው አገኘኋቸው። »

ፀረ ባላካ መሪዎች እነዚህን እጓለ ማውታ የሆኑት ሕፃናት የበቀል ርምጃ እንዲወስዱ ማግባባቱ አልከበዳቸውም። እና በአስር ሺህ የሚቆጠሩትን ወጣቶች ቆንጨራ እና ገጀራ ያስታጥቋቸዋል፣ ድግምት በማድረግ እና የሚያሰክራቸው ዕፅ በመስጠትም በሴሌካ ጥይት አንፃር ከለላ እንዳላቸው ያሳምኑዋቸዋል። ግዙፉ የበቀል ጥማቸው ከዕፅ ጋ የተቀላቀለበት ሁኔታ እነዚህን ወጣቶች ፣ በሴሌካ ዓማፅያን ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሲቭል ሙሥሊሞችም ላይ ጭምር ደም አፋሳሽ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እንዲያካሂዱ እና ስጋቸውንም እንዲበሉ እንደገፋፋቸው ነው ታዛቢዎች የሚናገሩት።

ባለፈው ታህሳስ ወር መንደሮችን ከሴሌካ ጥቃት ለመከላከል ተቋቋመ የተባለው ፀረ ባላካ የወጣት ቡድን አሁን በመሀሉ በሴሌካ ዓመፅ ከሥልጣን በተወገዱ የቀድሞ ፕሬዚደንት ቦዚዜ መንግሥት ባለሥልጣናት እና የጦር መኮንኖች የሚመራ ቡድን ሆኖዋል። ቡድኑን ከቦራፕ ዋና ሠፈራቸው የሚመሩት የቀድሞው የወጣት ሚንስትር እና የብሔራዊው እግር ኳስ ቡድን ኃላፊ ፓትሪስ ንጋሶ በፀረ ባላካ የቡድናቸው ውስጥ የቡድኑ አባላት ያልሆኑ ወንበዴዎች፣ ለምሳሌ የቀድሞ ወታደሮች እና የጦር መኮንኖች የሚመሩዋቸው ሌሎች ቡድኖች መኖራቸውን እና ለዘግናኙ ድርጊት ተጠያቂ መሆናቸውን ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜ በተለያዩት የባላካ ቡድኖች መካከል ወጣቶቹን ለመቆጠጠር በመላይቱ ሀገር ውጊያ በመካሄድ ላይ ነው። ይህም ተጨማሪ ሲቭል ሕዝብ እንዲገደል እና እንዲፈናቀል የሚያደርግ አደገኛ ክስተት ሆኖ ታይቶዋል።

ዚሞነ ሽሊንድቫይን/ አርያም ተክሌ 

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic