የመንግሥታቱ ድርጅት በ70ኛ ዓመቱ | ዓለም | DW | 05.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የመንግሥታቱ ድርጅት በ70ኛ ዓመቱ

በአንደኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛ ጥፋት የደረሰበት የሰው ልጅ በእርግጥም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የገጠመው አይነት ዕልቂት እንዳይከሰትበት በወቅቱ ቆርጦ የተነሳ ይመስል ነበር። እናም ሃገራቱ ሣንፍራንሲስኮ ውስጥ የዛሬ 70 ዓመት የተመድ መመስረቻ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን በማሳረፍ በዓለማችን አዲስ ድርጅት እንዲፈጠር መንገድ ከፍተዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:54

የተ.መ.ድ. በ70ኛ ዓመቱ

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር 1945 ዓ.ም. የዓለማችን አብዛኛው ክፍል በጦርነት ወድሞ የምድራችን ነዋሪ እጅግ የተጎዳበት ዘመን። በእርግጥ ወቅቱ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያከተመበት ጊዜ ነበር፤ እናም ዓለም ከምንም በላይ ሠላምን የምትሻበት ወቅት። ከዛሬ 70 ዓመት በፊት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ነበር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እውን የሆነው። ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በዓለማችን ሠላምን ለማስከበር ላይ እታች ይላል። የዓለማችን ነዋሪዎች በዓለም አቀፍ ሕግጋት ሰብአዊ መብታቸው እንዲከበር፣ ዲሞክራሲ እንዲስፋፋ፣ እንዲሁም የልማትና የሰብአዊ ርዳታ እንዲዳረስ ጥረት ማድረግ ዋነኛ ዓላማው እንደሆነ ይገልጣል ይኸው ዓለም አቀፍ ግዙፍ ድርጅት። የከባቢ አየር ጥበቃ ጉዳይም ዋነኛ መነጋገሪያው ከሆነ ሰነባብቷል። ድርጅቱ ዘንድሮ 70ኛ ዓመቱ ላይ በተለይ ካተኮረባቸው ነጥቦች መካከል የዓለም ሠላምና ፀጥታ ጉዳይ እንዲሁም የዘላቂ ልማት ግቦችን ለመዳሰስ እንሞክራለን ነው።

እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ሰኔ 26 ቀን፣ 1945 ዓ.ም. በዩናይትድ ስቴትሷ የሣንፍራንሲስኮ ከተማ የ51 ሃገራት መሪዎች ተሰባስበዋል። ሃገራቱ በዘመናችን ለሁለት ጊዜያት የተኪያሄዱት የዓለም ጦርነቶች ተነግሮ የማያልቅ ሰቀቀን ፈጥረውብናልና አንዳች ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ያስፈልገናል ሲሉ ነበር የተሰባሰቡት።

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና አቻቸው ባራክ ዖባማ

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና አቻቸው ባራክ ዖባማበአንደኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛ ጥፋት የደረሰበት የሰው ልጅ በእርግጥም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የገጠመው አይነት ዕልቂት እንዳይከሰትበት በወቅቱ ቆርጦ የተነሳ ይመስል ነበር። እናም ሃገራቱ ሣንፍራንሲስኮ ውስጥ የዛሬ 70 ዓመት የተመድ መመስረቻ ሰነድ ላይ ፊርማቸውን በማሳረፍ በዓለማችን አዲስ ድርጅት እንዲፈጠር መንገድ ከፈተዋል። 193 አባል ሃገራትን ያቀፈው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በምኅፃሩ ተመድ የተሰኘውን ግዙፍ ድርጅትም ወለዷል። ከ70 ዓመታት በኋላ ግን ድርጅቱ በዓለም ኹነኛ ሠላም አስፍኖ ፀጥታን ለማስከበር ዛሬም መዳከሩ አልቀረም።

ድርጅቱ የተመሰረተበት እና ዋና መሥሪያ ቤቱ የሚገኝባት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ዖባማ፦ ሩስያ ኢራንን፣ ኢራቅን እና ሶሪያን አስተባብራ ሰሞኑን ሶሪያ ውስጥ የአየር ጥቃት መሰንዘሯን ተከትሎ የተናገሩት በተመድ ጥላ ሥር የተሰባሰቡት ኃያላን የገቡበትን ውጥረት አመላካች ነው።

«ዩናይትድ ስቴትስ ሩስያና ኢራንን ጨምሮ ግጭቶችን ለማስወገድ ከየትኛዉም መንግሥት ጋር ለመሥራት ዝግጁ ናት። ነገር ግን ይህ ሁሉ ደም ከፈሰሰና ጉዳት ከደረሰ በኋላ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረዉ ሁኔታ መመለስ እንደማንፈልግ ግልፅ መሆን ይኖርበታል።»

ፕሬዚዳንት ባራክ ዖባማ በተ.መ.ድ.ንግግር ሲያደርጉ

ፕሬዚዳንት ባራክ ዖባማ በተ.መ.ድ. ንግግር ሲያደርጉ

በእርግጥም የተመድ የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃ ከተመሰረተበት ዋነኛ ግቦች መካከል ቀዳሚው በዓለም ሰላም ማስፈን የሚለው ነው። እናስ ድርጅቱ ተሳክቶለት ይሆን? እጅግ አጠያያቂ ነው።

አፍጋኒስታን በተራዘመ ጦርነት ደቃለች፤ እንደማይሆን ሆናለች። ኢራቅ ባትፈርስም እራሱን «እስላማዊ መንግስት» በምኅፃሩ አይሲስ እያለ የሚጠራ ቡድን ተንሰሰራፍቶባታል። የእሥራኤል-ፍልስጤም ግጭት ያባራ እንደሁ እንጂ መፍትኄ አላገኘም። ኢራን እና እስራኤል እንደተፋጠጡ ነው። ከጎረቤት ሶማሊያ አንስቶ፣ እስከ ሊቢያ፣ ቀይ ባሕርን ተሻግሮ ከምተገኘዋ ደሃዪቱ የመን እስከ ሶሪያ የሰው ልጅ ዛሬም በጦርነት ይረግፋል፤ ደም እንደጅረት ይፈሳል።

በሶሪያ ግጭት እንኳን የተመድ አባል የሆኑት ኃያላን ሃገራት በጋራ የሚያስማማቸው ነጥብ ላይ መድረስ ተስኗቸው በየፊናቸው ትክክለኛ የሚሉትን ዕቅድ ለመተግበር ሲራወጡ ይስተዋላል። ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎቿ አምባገነን የሚሏቸው የሶሪያው ፕሬዚዳንት በሽር አል አሣድ ካልተወገዱ፣ ሶሪያ ሠላም አታገኝም ሲሉ ይሞግታሉ። የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሶሪያው ፕሬዚዳንት ዋነኛ ደጋፊ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል። ቭላድሚር ፑቲን በሶሪያ ጥቃት መሰንዘር ሲጀምሩ ግን እንዲህ ነበር ያሉት፦

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተ.መ.ድ. ንግግር ሲያደርጉ

ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በተ.መ.ድ. ንግግር ሲያደርጉ«በሶሪያና በአጎራባች ሃገራት ዓለም ዓቀፍ አሸባሪነት ተስፋፍቷል። እነዚህን ሃገራት የሚያብጡትን ዓለም ዓቀፍ አሸባሪዎች መዋጊያ ትክክለኛው መንገድ ቤታችን ድረስ እስኪመጡ መጠበቅ ሳይሆን ጥቃታቸውን መከላከልና ተዋጊዎቹንና አሸባሪዎቹን ከያዟቸው አካባቢዎች ማስወገድ ነው። »

እናም ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሶሪያ የአየር ጥቃት የሚያካሂዱበት ምክንያት የአሸባሪውን ቡድን ጥቃት ለመከላከል እንጂ እነ ዩናይትድ ስቴትስ እንደሚከሷቸው የበሽር አል አሣድን ተቃዋሚዎች ለማዳከም እንዳልሆነ መግለጣቸው አልቀረም።

ዩናይትድ ስቴትስ አይሲስን ለመዋጋት በሚል ከነፈረንሣይ እና ብሪታንያ ጋር ተባባሪዎቿን አሰባስባ በኢራቅ እና ሶሪያ በተደጋጋሚ ከጦር ጄቶች የቦንብ ናዳ ታወርዳለች። አይኤስን ለመደምሰስ የሶሪያ ፕሬዚዳንት ተቃዋሚዎችን እያሠለጠኑ ማስታጠቅ በሚል የነደፈችው ስልት ግን ሠልጣኞቹ ከነታጠቁት መሣሪያዎቻቸው አይሲስን እየተቀላቀሉ ሊሳካ አልቻለም ተብሎ ነበር።

ሩስያ ኢራንን፣ ኢራቅን እና ሶሪያን በሌላ መስመር አሰልፋ እዛው ሶሪያ ውስጥ ሌላ የአየር ድብደባ መክፈቷ ዩናይትድ ስቴትስ አልተሳካም ያለችውን ስልት አዲስ ብላ ዳግም ለመጀመር እንዳነሳሳት ተገልጧል። ሰሜን ሶሪያ ውስጥ የአይሲስ መዲና ተብላ የምትጠራው ራቃ አውራጃን ከአየር በቦንብ እየደበደበች፣ የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚዎችን እና የኩርድ ታጣቂዎችን ለማጠናከር ወስናለች። ያም ብቻ አይደለም፤ SU-34 የተባሉ ቦንብ ጣይ ጄቶቿ በአውራጃው የሚገኙ የአይሲስ ጦር ሠፈሮችን ዛሬ ከአየር መደብደባቸው ተገልጧል።

ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር

ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር

ዩናይትድ ስቴትስ የሶሪያ ፕሬዚዳንት በሽር አል አሣድ ተቃዋሚዎችን አሠልጥና ስታስታጥቅ ሩስያ የፕሬዚዳንቱን ህልውና ለማስጠበቅ ተቃዋሚዎችን ትወጋለች በሚል በምዕራባውያኑ እየተወቀሰች ነው። የተመድ አባል የሆኑት ሁለቱ ኃያላን በሰው ሀገር በእጅ አዙር ጦርነት ተጠምደዋል። ድርጊታቸው በዓለም ሠላም እና ፀጥታን ለማስፈን የተቋቋመው የተመድ ቢያንስ በሶሪያ አንዳች መፍትኄ ማግኘት እንደተሳነው አመላካች ሳይሆን አይቀርም።

የጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር በበኩላቸው ሶርያ ላይ የሚሰነዘረዉ ጥቃት ችግሩን ከማባባስ የተሻለ ዉጤት ሊያስገኝ እንደማይችል አመልክተዋል። ለሶርያ ቀዉስም ፖለቲካዊ መፍትሄና ድርድር አማራጭ እንደሌለዉ አፅንኦት በመስጠት ጥሪ አቅርበዋል።

«በሶርያ በአምስት ዓመት ዉስጥም ቢሆን ገዳዩ ጦርነት ማብቅያ ያለዉ አይመስልም። ይህን ለማብቃት የምንችለዉ በጋራ በምናደርገዉ ድርድርና ስምምነት ነዉ። የአሳድን መንግስት አስከፊ አገዛዝ፤ የቦንብ ጥቃት፤ እንግልትና ስቃይ ማብቃት አለብን። በሶርያ እራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራዉን ቡድን ይዞታ ማክተም፤ ጦርነቱን ማስቆምና ለነዋሪዎች ሰብዓዊ ርዳታ ለማድረስ መንገድ መክፈት ይኖርብናል»

የተ.መ.ድ. ዋና ጸሓፊ ባን ኪ ሙን ንግግር ሲያደርጉ

የተ.መ.ድ. ዋና ጸሓፊ ባን ኪ ሙን ንግግር ሲያደርጉየተመድ ከ70 ዓመት በኋላም በዓለማችን ሠላም የማስፈን ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሞታል። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ሰኞ መስከረም 28 ቀን፣ 2015 ጀምሮ እስከ ዐርብ ድረስ ለ6 ቀናት በዘለቀው የድርጅቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ዉጥረት በዓለም ዙርያ እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል። ለእዚያም ነበር በስብሰባው የተገኙ ከ50 የሚበልጡ ሃገራት ውጥረቱን ለመግታት ለመንግሥታቱ ድርጅት 40 ሺህ የሰላም አስከባሪ ሠራዊት እንደሚያዋጡ ቃል የገቡት።

የተመድ ሠላምና ፀጥታን ለማስከበር በሚል ካሳለፋቸው ውሳኔዎች ባሻገር ዓለማችን ሕዝቦቿ በድህነት እና በችጋር እንዳይሰቃዩ ለማድረግ በሚል የተለያዩ ዕቅዶችን እየነደፈም ይተገብራል። ድርጅቱ ዘንድሮም አዲስ ዕቅድ ይዞ ብቅ ብሏል። የጀርመኗ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በዘንድሮው የተመድ ጉባኤ ዘላቂ ልማት ግቡን በተመለከተ ኒውዮርክ ውስጥ ባደረጉት ውይይት እንዲህ ሲሉ አጠይቀዋል።

«ሁላችሁም ዝግጁ?»

የተመድ ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት የቀረፃቸዉን ስምንቱ የዐምዐቱ የልማት ግቦች ለማሳካትየተያዘው ገደብ የጎርጎሪዮስ 2015 ዓ.ም. ሲጠናቀቅ ያከትማል። የመንግሥታቱ ድርጅት ይፋ እንዳደረገዉ ስምንቱም የልማት ግቦች እንደታሰበዉ አልተደረሰባቸዉም። በጎርጎሪዮስ 2016 መባቻ ስምንቱን የልማት ግቦች የተኩት 17 ዘላቂ የልማት ግቦች ተግባራዊ መሆን ይጀምራሉ። የአውሮጳ ሕብረት ኮሚሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ክሪስታሊና ጊዮርጊቫ ዕቅዶቹን ለማሳካት የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ሃገራት ድጋፋቸውን በተግባር እንዲያሳዩ ማሳሰባቸው ቀደም ሲል ድርጅቱ የገጠመውን ተግዳሮት በማሰብ ይመስላል።

የተ.መ.ድ. ዓርማ

የተ.መ.ድ. ዓርማ«ለጋሾችንና ለተግባራዊነቱ የሚተጉትን እፈልጋለሁ፤ አሁኑኑ። ቃል መግባት ብቻ በቂ አይደለም።»

የዓለም መሪዎች የከፋ ድህነትን እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2030 ከዓለማችን ለማስወገድ ይረዳል ያሉትን የዘላቂ ልማት ግቦች አርቅቀዋል። የ15 ዓመት የጊዜ ገደብ የተሰጠው ይህ ዕቅድ ወደ ተግባር ሊቀየር የቀሩት ጥቂት ወራት ናቸው። በዓለማችን አሁን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የረሀብ አደጋ ያንዣበበባቸው ነዋሪዎች ይገኛሉ። ለአብነት ያህል በኢትዮጵያ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በሦስት ወራት ልዩነት ገደማ እንዳደገ ተገልጧል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለፈው ነሐሴ ወር በኢትዮጵያ የምግብ ርዳታ የሚሻው ህዝብ 4,5 ሚሊዮን እንደሚሆን ቢጠቅስም፤ አሁን ወደ 7,5 ሚሊዮን አድጓል። ድርጅቱ አፋጣኝ ምላሽ ካልተወሰደ የምግብ ፈላጊው ቁጥር በሚመጣው ዓመት ወደ 15 ሚሊዮን ከፍ ሊል እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።

ይህን እና ሌሎች የዓለማችን ተግዳሮቶችን ለመቋቋም የመንግሥታቱ ድርጅት ግቦቹን ተግባራዊ ለማድረግ እያንዳንዱ ሀገር ከሚጠበ ቅበት ቁርጠኝነት እና የፖለቲካ ግልጽነት ባሻገር የለጋሽ ሃገራት ልገሳም ወሳኝ እንደሆነ አጽንኦት ተሰጥቶበታል።

ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥሪ ጀርመን ምላሽ በመስጠት፤ ከሀገር ውስጥ ምርት ያልተጣራ ገቢዋ ወይንም GDP የተወሰነውን ለመለገስ ቃል ገብታለች። ይህንንም መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ለድርጅቱ ስበሰባ ኒውዮርክ በነበሩበት ወቅት ገልጠዋል።

«ጀርመን ከሀገር ውስጥ ምርት ያልተጣራ ገቢዋ 0,7 በመቶ የሚሆነውን ለልማት ርዳታ ታመቻቻለች። ለልማት የምንመድበው በጀት በሚቀጥሉት ዓመታት በተጨባጭ ያድጋል።»

መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ንግግር ሲያደርጉ

መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ንግግር ሲያደርጉጀርመን ብቻ አይደለችም ቻይናም እስከ 2030 ድረስ በታዳጊ ሃገራት ድህነትን እና ረሀብን ለመዋጋት በአጠቃላይ 10,7 ቢሊዮን ዩሮ እንደምትለግስ ቃል ገብታለች። የበለፀጉት ሃገራት በየአቅጣጫው ድጋፍ ለማድረግ በፍጥነት ቃል ገብተዋል።

የተመድ በ2030 ዓም ከዓለማችን የከፋ ድህነትን ብቻ አይደለም ለማስወገድ ቆርጫለሁ ያለው። ኢ-ፍትሓዊነትን እና በእኩል ዐይን ያለመታየትን ለመታገል፣ ለሁሉም የዓለማችን ነዋሪዎች ጥራት ያለው የትምህርት አቅርቦት በማመቻቸት ሃገራት የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲያስመዘግቡ ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል። ስኬታማነቱ ግን በተመድ ነጠላ ጉዞ ብቻ እንደማይተገበር የድርጅቱ ዋና ጸሓፊ ባን ኪሙን አሳስበዋል።

«ለ2030 አጀንዳ የተገባው ቁርጠኝነት በእርግጥም የሚፈተሸው በትግበራው ይሆናል። ሁሉም በየአቅጣጫው ለተግባራዊነቱ እንዲንቀሳቀስ እንሻለን። »

የዘላቂ ልማት ግቦች አጠቃላይ አጀንዳ ምንም እንኳን ገና ከመነሻው ከፊቱ ተግዳሮቶች ቢጋረጡበትም ይፋ ተደርጓል።

«በዚህ መልኩ ተወስኗል።»

እናስ የዘላቂ ልማት ግቦችም ሆኑ በዓለማችን የሰላምና ፀጥታ የማስፈኑ ተግባር 70 ዓመታት ባስቆጠረው አንጋፋው የተመድ እንደተወራላቸው ቀላል ይሆኑ ወይንስ ሌላ አዲስ ተግዳሮት እና ሌላ ዕቅድ ይወልዱ ይሆን? ወደፊት አብረን የምናየው ይሆናል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic