የለንደኑ ጉባኤና የሶማሊያ ሁኔታ | ዓለም | DW | 29.02.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የለንደኑ ጉባኤና የሶማሊያ ሁኔታ

«አካባቢያዊ» የተባለዉን ችግር ለመፍታት ባለፈዉ ሐሙስ ለንደን ላይ በመከረ፣ በወሰነዉ ጉባኤ የሩቋ ትንሽ አዉሮጳዊት ሐገር ላክሰምበርግ እንጂ የቅርቧ ኤርትራ አልተወከለችም።ሞሪሸስ እንጂ ሱዳን አልተካፈለችም።

default

ጉባኤተኞች


የኢትዮጵያ ጦር ሥልታዊቷን የባዶዎ ከተማን መቆጣጠሩ ለአዲስ አበባ መሪዎች ኩራት፣ለሞቃዲሾ ወዳጆቻቸዉ ብስራት፣ ለናይሮቢ-ካምፓላ፣ አቻዎቸዉ የአጋርነት ምልክት ነዉ።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ተጨማሪ ጦር ወደ ሶማሊያ እንዲምት መወሰኑ፥ ለአፍሪቃ ሕብረትና ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፕሎማቶች ደስታ፣ለምዕራባዉያኑ ለአፍሪቃ የመቆርቀራቸዉ አብነት ነዉ።ለጉባኤዉ ገፀ-በረከት የጦር-ዲፕሎማሲ ድል ኩራት-ፈገግታ ቋጥረዉ ለንደን የገቡት ጉባኤተኞች በሃያ አመት ሃያ ሁለተኛ ጉባኤቸዉ የሶማሊያን ምስቅልቅል እንደሚያስወግድ ሌላ ተስፋ ሰጥተዉ ተበተኑ።ጉባኤዉ መነሻ፣ የሶማሊያ እዉነት ማጣቀሻ፣ ተስፋዉ-ቀቢፀ ተስፋዉ ተቃርኖ መድረሻችን ነዉ።ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
             
«የሶማሊያ ችግር አካባቢዊ ችግር ነዉ።የባሕር ላይ ዘረፋ፣ አሸባሪነት፥ ሕገ-አልበኝነት ተስፋፍቷል። ሥለዚሕ አካባቢያዊ ችግር በመሆኑ፥ አካባቢያዊ መፍትሔ ሊፈለግለት ይገባል።»   

የሶማሊያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አብዲወሊ መሐመድ ዓሊ።በጉባኤ ዋዜማ።ሮብ።ችግሩን አካባቢያዊ ብቻ ሲያደርጉት በርግጥ አጥበዉታል።ግን አላበሉም።ጠብቦ «አካባቢያዊ» የተባለዉን ችግር ለመፍታት ባለፈዉ ሐሙስ ለንደን ላይ በመከረ፣ በወሰነዉ ጉባኤ የሩቋ ትንሽ አዉሮጳዊት ሐገር ላክሰምበርግ እንጂ የቅርቧ ኤርትራ አልተወከለችም።ሞሪሸስ እንጂ ሱዳን አልተካፈለችም።
                          
በሁለት ሺሕ ስድስት (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኢትዮጵያ የያኔዉን የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ሕብረት የሚወጋ ጦሯን ስታዘምት ዉጊያዉ የኢትዮጵያና የኤርትራ የእጅ አዙር ጦርነት እስከመባል የደረሰዉ ኤርትራ በሶማሊያም ይሁን ባካባቢዉ፥ አሉታዊም-ሆነ አዎንታዊ ተፅዕኖ ማሳራፍ እንደምትችል ስለሚታወቅ ነበር።የኢትዮጵያ ጦር ዘመቻ ነገሩን እስኪገለባብጠዉ ድረስ የሕብረቱና የያኔዉ የሽግግር መንግሥት ባለሥልጣናትን ድርድር ያስተናገደችዉ ደግሞ ሱዳን ነበረች።

ኤርትራና ሱዳን ሶማሊያን ከቅርብ፥ የሐሙሱን ጉባኤ ግን ከሩቅ ተመልካቾች ነበሩ።የኤርትራ ባለሥልጣናትን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ስልክ ደዉለን ማግኘት አልቻልንም።ጉባኤዉን የተከታተለዉ የአፍሪካ ኮንፊደንሻል መፅሔት ጋዜጠኛ አንድሪዉ ወይር ግን የጉባኤዉ አስተጋጆች «ጥሩ» ብለዉ የተጋበዙት እንዳሉ ሁሉ ያልተጋበዟቸዉም አሉ ባይ ነዉ።

Somalia Konferenz London 2012 Gruppenbild

ጉባኤተኞች


           
«የለም፥ የለም እኔ እስከማዉቀዉ ድረስ ኤርትራ በጉባኤዉ አልተካፈለችም።በጉባኤዉ ላይ የተወሰኑ የአካባቢዉ ሐይላት የተባሉ ወገኖች ነበሩ የተካፈሉት።(ጋባዦቹ) ጥሩ ብለዉ የሚያስቡት ብሔራዊ መንግሥቱ ማለት ፌደራላዊዉ የሽግግር መንግሥት፥ እንደ ፑንት ላንድ፥ ሶማሊ ላንድ የመሳሰሉ የመሳሰሉ ወገኖች፥ በተጨማሪም ጉሙድግ እና ባለፉት ጊዚያት እንደሰማነዉ ኬንያዎች የጁባ ላንድ ሐሳብ (የመከላከያ ቀጣና) እየመሠረቱ ነዉ።እና ከኬንያዎች ጋር የሚሠሩት ጎሳ ተጠሪዎች፥ ከኢትዮጵያዉያን ጋር የሚሠሩት ጎሳ ተጠሪዎች አስፈላጊ ተብለዉ ይታያሉ።ሥለዚሕ ገሚሶቹ ተካፍለዋል።ሌሎቹ አልተካፈሉም።»

ይሕ ነዉ በጠቅላይ ሚንስትር አብዲወሊ ቋንቋ ለአካባቢዉ ችግር አካባቢያዊ መፍትሔ የመፈለግ ቀመር።የጄኔራል መሐመድ ዚያድ ባሬን አገዛዝ ለማስወገድ ባንድ አብረዉ ይዋጉ የነበሩት ሐይላት፣ ከዚያድ ባሬ መወገድ በሕዋላ የገጠሙትን ዉጊያ ለማስቆም የመጀመሪያዉ ጉባኤ የተደረገዉ በ1991 ነበር።ጅቡቲ።የሶማሊያ እርቀ-ሠላም» የተሰኘዉ ያ ጉባኤ ከተደረገ፥ እስካሁን በተቆጠረዉ ሃያ-አንድ ዘመን ሃያ-አንድ ጉባኤዎች ተደርገዋል።

ከጅቡቲ እስከ ናይሮቢ፥ ከአዲስ አበባ እስከ ካይሮ፥ ከብራስልስ እስከ ኢስታንቡል በየአመቱ የተደረገዉ ጉባኤም ሆነ በየጊዜዉ የሚዘምተዉ የዉጪ ጦር ሶማሊያን ሉዓላዊት፥ ሰላማዊት፥ አሐዳዊት ሐገር ማድረግ አልቻሉም ወይም ወይም አልፈለጉም።

የመጀመሪያዉ የሶማሊያ ጉዳይ ጉባኤ በተደረገ በሃያ-አንደኛ አመቱ ዘንድሮ በቀደም ሐሙስ ለንደን የተሰየመዉ ጉባኤ ግን የሶማሊያዉ ጠቅላይ ሚንስትር አብዲወሊ መሐመድ ዓሊ እንዳሉት ልዩ ነዉ።
              

ከናትሲ ጀርመን ጋር ያበረችዉ ፋሽስት ኢጣሊያ በ1940 የብሪታንያ ቅኝ ተገዢ የአፍሪቃ ሐገራትን ለመቀማት በዛተች፥ በወራት ዕድሜ ከደቡብ ሶማሊያ፥ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ የዘመተዉ የኢጣሊያ ጦር የብሪታንያ ቅኝ ገዢ ሐይልን ከሶማሊ ላንድ ጠራርጎ አስወጣ።ሶማሊ ላንድን «አፍሪካ ኦሪየንታሌ ኢታሊያና» ያሉት የኢጣሊያ ንጉሳዊ-ግማደ ግዛት አካል ማድረጋቸዉን ያወጁት ቤኒቶ ሞሶሌኒ ሶማሊ ላንድን በመቀማት እንደማይቆሙ ለብሪታንያ ሹማምንት ግልፅ ነበር።

ምሥራቅ አፍሪቃ ላይ የማይቀረዉን ዉጊያ ለመጋፈጥ ለያኔዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ለአንቲኒ ኤደን ፖለቲካዉን፥ከጦር ዉጊያ፥ ዲፕሎማሲዉን፥ ከፕሮፓጋንዳዉ ዘመቻ የሚያዋድድ ሁነኛ ጉባኤ   መጥራት ተገቢ ነበር።ኤደን የኢትዮጵያዉን ስደተኛ ንጉስ ከለንደን አጉዘዉ፥ ከደቡብ አፍሪቃ እስከ ኬንያ፥ ከሱዳን እስከ ካይሮ የሚገኙ የብሪታን ጦር አዛዦችን፥ እና በየሐገሩ ለብሪታንያ ያደሩ ጎሳ ተጠሪዎችን ካርቱም ሰበሰቡ።ጥቅምት 1940።

ከጅቡቲ በመለስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ድፍን የአፍሪቃ ቀንድን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከብሪታንያ እጅ የዶለዉ ዘመቻ የታቀደ፥የተረቀቀዉ በዚሕ ጉባኤ ነበር።ብሪታንያ የአፍሪቃ ቀንድ በተለይ የሶማሊያ ጉዳይን የሚመለከት ትልቅ ጉባኤ ስታስተናግድ ከ1940 የካርቱም ጉባኤ ወዲሕ ያሁኑ ምናልባት የመጀመሪያዉ ነዉ።የመጀመሪያዉ በመሆኑም የሶማሊያዉ ጠቅላይ ሚንስትር እንዳሉት ልዩ ነዉ።የጉባኤዉ አስተናጋጅ የብሪታንያዉ ጠቅላይ ሚንስትር ዴቪድ ካሜሩን እንዳሉት ደግሞ  ጉባኤዉን ልዩ የሚያደርገዉ ሌላም ምክንያት አለ።
         
«ጉባኤዉን ልዩ የሚያደርገዉ ምድነዉ ሥለ ርዳታ ብቻ፥ ሥለ ልማት ብቻ፥ ሥለ ባሕር ላይ ዘረፋ ብቻ፥ ሥለ አሽባሪነት ብቻ አለመሆኑ ነዉ።ሥለነዚሕ ሁሉ መሆኑ እንጂ።»

ሥለሁሉም የተመከረላት ሐገር ሁሉም ይሆንባታል።ጥንት ገድለዉ-የሞቱባት ሮሞች፥አረቦች፥ቱርኮች፥  በዘመነ-ቅኝ አገዛዝ ቀዳሚዎቻቸዉን ገድለዉ፥ አጋድለዉ-የሞቱባት ኢጣሊያኖች፥ እንግሊዞች ዛሬም ከሚሆንባት ሁሉ ጥቂቱን ከሩቅ ይዘዉሩታል።ለእንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች ድል ሶማሊያ ምድር ደም አጥንታቸዉን የከሰከሱት ኬንያዎችና ዩጋንዶችች ዛሬም ገድለዉ እየሞቱባት ነዉ።

ሐበሾች እንደ ጥንቱ፥ እንደ ድሮዉ፥ እንደ ቅርቡም፥ እየገደሉ፥ ይሞቱባታል።አሜሪካኖች እንደ ዛሬ ሃያ አመቱ ባይሞቱ ይገድሉ፥ ያጋድሉባታል።ካሜሩን ያስተናገዱት ጉባኤ ያወጣዉ ባለ-ሃያ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫም የሶማሊያን ዘንቀ-ብዙ ችግሮች መጠቃቀሱ አልቀም።የዩናይትድ ስቴትስዋ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ወይዘሮ ሒላሪ ክሊንተን በጉባኤዉ ማብቂያ እንዳሉት ግን የትልቂቱ ሐገራቸዉ ትልቅ ምኞት አሁንም አሸባብን ማጥፋት ነዉ።
           

Hands off Somalia Plakat Demonstranten

ተቃዉሞዉ

«አሸባብና አል-ቃኢዳ የተደጋገፉት ሁለቱም እየተወጉ፥ እየተገለሉ በመሆናቸዉ ነዉ።በተለይ አሁን በብዙ ሐገራት በሚካሔዱት ዲሞክራሲያዊ አብዮቶች እንደታየዉ ምናልባት በፅንፈኛ ቡድናት ሊሳቡ ይችሉ የነበሩት ወጣቶች የሚሳተፉበት በጣም ገንቢ ሰፊ መንገድ ተከፍቶላቸዋል።የወደፊቱ ይሕ ነዉ።አ-ሸባባና-አል-ቃኢዳ ያላፉ ናቸዉ።»

የኢትዮጵያ ጦር ባይደዋን የተቆጣጠረዉ፥ የፀጥታ ጥበቃዉ ምክር ቤት ተጨማሪ የአፍሪቃ ጦር እንዲዘምት የወሰነዉ በርግጥ ለጉባኤዉ ድምቀት ለመስጠት መሆኑ አላጠራጠረም።ግን አሸባብና አል-ቃኢዳ ክሊንተን እንዳሉት ታሪክ ከሆኑ የኢትጵያ ጦር ባይደዋን የተቆጣጠረዉ፥ የፀጥታዉ ምክር ቤት ተጨማሪ ጦር የሚያስዘምተዉ ከማ እና ለምንደዉ።
------------------------------------------------------------
------------------------------------------------------------

የሶማሊያ የጦር አበጋዞች በ1991 ጁቡቲ ላይ የደረሱበትን ስምምነት አፍርሰዉ የገጠሙትን ዉጊያ ለማስቆም የያኔዉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቡትሩስ ቡትሩስ ጋሊ ሰብአዊዉ ርዳታ ለማድረስ የዘመተዉ ዓለም አቀፍ ሠራዊት ተፋላሚዎችን ትጥቅ የማስፈታትና ሐገሪቱን የመገንባት ተጨማሪ ተልዕኮ እንዲሰጠዉ ጠይቀዉ ነበር።

ግብፃዊዉ ዲፕሎማት በ1992 ማብቂያ ያቀረቡት ሐሳብ በሐያላኑ ተደግፎ በፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት መፅደቁ ለያኔዉ የሶማሊያ እዉቅ የጦር አበጋዝ ጄኔራል  መሐመድ ፋራሕ አይዲድ ሐገራቸዉን የሚያብጠዉን ጦርነት ምክንያት ለመናገር ጥሩ አጋጣሚ፥ ግን መጥፎ ክስተት ነበር። «የአደን ባሕረ ሠላጤና የሕንድ ዉቅያኖስን የዉሐ መተላለፊያም ሆነ የአባይን ዉሐ ለመቆጣጠር ለሚደረገዉ ሽኩቻ» አሉ አይዲድ «ከእንግዲሕ የሶማሌዎች ደም አይፈስም።»

አይዲድ የደጋፊዎቻቸዉን፣ የራሳቸዉንም ደም-ሕይወት ምናልባት ላሉት ዳፋ ገበሩ እንጂ ያሉ የተመኙትን በርግጥ አላስከበሩም።ወይም አልቻሉም።አይዲድ ላሉትና ላላሉት ብዙ ምክንያትና ለሌሎች ጥቅም የፓኪስታን፣ የአሜሪካና የሌሎች ብዙ ሐገራት ብዙ ወታደሮች ደም አጥንት እንደ አይዲድ እንደ ሚሊዮን ሶማሌዎች ሁሉ ሶማሊያ ላይ ተሰዋ-እንጂ የቡትሩስ ጋሉ እቅድ፣ የአሜሪካኖች ሥልትም ከንቱ ነዉ-የቀረዉ።

ጠቅላይ ሚንስትር አብዲወሊ በለንደኑ ጉባኤ አይዲድ ከሐያ አመት በፊት ያሉትንም ሆነ ሌላዉን ምክንያት ዘለዉ የዉጪ ሐይላትን ጣልቃ ገብነትን ፈቀዱበት።
            
«ኢላማዉን ነጥሎ የሚመታ የአየር ድብደባን እንፈቅዳለን።ሶማሊያ ዉስጥ አል-ቃኢዳን ነጥሎ የሚመታ ድብደባን።ይሁንና የሶማሊያን ሕዝብ ሕይወት፥ ደሕንነትና ንብረት መጠበቅም በጣም አስፈላጊ ነዉ።»

አብዲወሊ ልዩ ባሉት ጉባኤ አይዲድ የወጓቸዉን የዉጪ ሐይላት ጣልቃ ገብነት ሲፈቅዱበት፥ የፍሪካ ኮንፊደንሻሉ ጋዜጠኛ አንድሪዉ ወይር እንደታዘበዉ ዴቪድ ካሜሩን በዉጪም በዉስጥም ሥም ዝናቸዉን ገነቡበት።«ከትናንቱ ጉባኤ ተጨማጥ ዉጤት ማግኘት ከባድ ነዉ።በተደጋጋሚ የተሰጡ አስተያየቶች እንደሚያመለከቱት ደግሞ ጉባኤዉ ዴቪድ ካሜሩን እንደ መሪ በዓለም የነበራቸዉን እዉቅና ይበልጥ ያሳደጉበት ነዉ።ምክንያቱም ጉባኤዉን፥ ዴቪድ ካሜሩን አፍሪቃ ዉስጥ ለሚራቡ ሰዎች እንደሚያስቡ እና የኦሎምፒክ ስፖርት ከመጀመሩ በፊት አሸባሪዎችን ለመከላከል በፅኑ መቆማቸዉን ለሕዝባቸዉ ለማሳየት ተጠቅመዉበታል።»

ያም ሆኖ ካሜሩን ጉባኤዉን የሶማሊያን ችግር የሚያወገዱት ሶማሌዎች ናቸዉ አሉበት።
               
«የሶማሊያ ችግር ሊፈታ የሚችለዉ በሶማሊያ ሕዝብ ነዉ።እና እዚሕ የተሰበሰብነዉ በሐገሪቱ ላይ ከርቁ መፍትሔ ለመጫን አይደለም።ሶማሌዎች ማድረግ ያለባዉን ልንነግራቸዉም አይደለም።እዚሕ የተገኘነዉ ከጀርባችሁ ሆነን ልንረዳችሁ ነዉ።»    

አሸባብ እንደ ቡድን ፅንፈኛ አሸባሪም ነዉ።ቡድኑ ፅንፈኞችን እንደያዘ ሁሉ ለዘብተኞችን፣ አሸባሪዎችን እንዳቀፈ ሁሉ ለሐገራቸዉ ነፃነት የሚፋለሙ ሐይላትን ያሰበጠረ መሆኑ ግን አያነጋግርም።በሶማሊያ የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ልዩ መልዕክተኛ ሮበርት ቢ.ኦክሌይ በሁለት ሺሕ ሁለት በፃፉት መጣጥፍ «ሶማሌዉ የሰወስት ነገሮችን ያክል ከዚሕ ዓለም  የሚፈልገዉ የለም።ግመሉን፣ ሚስቱንና ጠመንጃዉን።»

የሥራ፣ የትምሕርት እድል አጥቶ ፥ ሐገር፣ ክብር ነፃነቱን ለማስከበር ወይም የዉጪ ጦር ሰወስቱን ወይም ከሰወስቱ አንዱን የሚቀማዉ መስሎት አሸባብን የተቀየጠዉ ሶማሌያዊ ግን የሶማሊያን ችግር የማስወገዱ መፍትሔ አካል እንዳልነበረ እንዳልነበረ ሁሉ፥ ሁሉን አቀፍ የተባለዉ የለንደኑ ጉባኤ ርዕስም አልነበረም።እና ሶማሊያ፥- ከለንደኑ ጉባኤ በሕዋላ፥ጋዜጠኛ አንድሪዉ ወይር፥ እንደሚለዉ ከጉባኤዉ በፊት እንደነበረችዉ ትቀጥላለች።
               
«የሚለወጥ ነገር አይኖርም።የፌደራሉ የሽግግር መንግሥት ዘመነ-ሥልጣን ነሐሴ ላይ ሲያበቃ ሥለሚወሰደዉ ፖለቲካዊ መፍትሔ የተባለ ነገር የለም።የኬንያና የኢትዮጵያ ወታደራዊ እርምጃን የሚደግፍም፥ የሚቃወምም አቋም በግልፅ አልተንፀባረቀም።አዲስ ነገር የለም።»

ሶማሊያ አሐዳዊ መንግስቷ ከፈረሰ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አልቆበታል።ከስምንት መቶ ሺሕ የሚበልጥ ሕዝብ ተሰዶባታል።አንድ ሚሊዮን ተኩል ተፈናቅሎበታል።የተለያዩ ወገኖች ለተለያዩ ጉዳዮች ከሐምሳ አምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከስክሰዉባታል።ዛሬም ብዙ እየተወራላት ብዙ እየወደመች ነዉ። ነጋሽ መሐመድ ቸር ያሰማን።

www.africa-confidential.com

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ


 
       


 

WWW links

Audios and videos on the topic