የህዝብ ቆጠራ በናይጀሪያ | የጋዜጦች አምድ | DW | 22.02.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

የህዝብ ቆጠራ በናይጀሪያ

በናይጀሪያ የሚታየዉን በሃይማኖት ሳቢያ የሚፈጠር ግጭት ለማርገብ ይረዳል ብለዉ መሪዎቹ የዘየዱትን የመፍትሄ ሃሳብ በያዘ መልኩ የህዝብ ቆጠራ ሊካሄድ ነዉ። የአገሪቱን ፕሬዝዳንት ጨምሮ 36 የየግዛቱ አስተዳዳሪዎችና የቀድሞ የአገሪቱ ርዕሰ ብሄር ያቀፈዉ የአገሪቱ ብሄራዊ ሸንጎ በያዝነዉ የፈረንጆቹ አመት የሚካሄደዉ የህዝብ ቆጠራ የግለሰቡን ሃይማኖትም ሆነ ጎሳ እንደማያካትት ወስኗል።

ሸንጎዉ እዚህ ዉሳኔ ላይ የደረሰዉ በሰሜናዊ ናይጀሪያ የምትገኘዉ የካዱና አስተዳዳሪ አህመድ ማካርፊ ቆጠራዉ ጎሳና ሃይማኖትን የሚያካትት ከሆነ ግዛታቸዉ በቆጠራዉ አትካትትም በማለት ከዛቱ በኋላ መሆኑ ነዉ።
እንደ እሳቸዉ አገላለፅ ካለፈዉ ቆጠራ በኋላ ይፋ የተደረገዉ ዉጤት በሃይማኖትና በጎሳ ረገድ ያቀረበዉ ቁጥር በህዝቡ መካከል መከፋፈልና የሰላም መናጋትን አስከትሏል።
የብሄራዊ የህዝብ ቆጠራ ሊቀመንበር ሳሚላ ማካማ ማካርፊ ባቀረቡት የመከራከሪያ ሃሳብ መስማማታቸዉን ነዉ የገለፁት።
እያንዳንዱ ሃይማኖትና የጎሳ ቡድን በቁጥር ሌላኛዉን በልጦ መታየትን መፈለጉ የታወቀ በመሆኑ በአሁኑ የቆጠራ ቅፅ ዉስጥ ጎሳና ሃይማኖትን ማካተቱ አንዱ በሌላዉ ላይ ሊቀዳጅ የሚመኘዉን የበላይነት እንዲያገኝ መጋበዝ ነዉ።
የአገሪቱ ሁኔታ ሲታይ በሰሜን ናይጀሪያ የሚገኙት አብዛኛዎቹ ሙስሊም ሲሆኑ በደቡብ ደግሞ ክርስቲያኖችና የባህላዊ እምነት ተከታዮች ይበረክታሉ።
ከዚህ በፊት የተደረገዉን ቆጠራ በመንተራስም ከአገሪቱ ህዝብ 50 በመቶ የሚሆነዉ ሙስሊም፤40 በመቶዉ ክርስቲያንና ቀሪዉ 10 በመቶዉ ደግሞ የልዩ ልዩ እምነት ተከታይ ነዉ ማለት ይቻላል።
ከአምስት አመት በፊት በአብዛኛዎቹ የሰሜን ናይጀርያ ክፍለ ሃገራት የእስልምናን ህግ በስራ ላይ ለማዋል በተሞከረበት ወቅት በሙስሊምና በክርስቲያኖች መካከል ግጭት ተቀስቅሶ ነበር።
የአገሪቱን የሃይማኖት ክፍፍል የሚያባብሰዉ ሌላኛዉ ምክንያት ደግሞ የጎሳ ልዩነት ነዉ። በናይጀሪያ ወደ 250 ገደማ የሚሆኑ ጎሳዎች ይገኛሉ።
በጎሳዎች መካከል ባለዉ ልዩነት የማይረሳና አስከፊ ግጭት የታየዉ በአገሪቱ በብዛቱ በሶስተኝነት ደረጃ የሚገኘዉ የኢቦ ጎሳ በ1974 ዓ.ም. ባደረገዉ የመገንጠል ሙከራ ነበር።
በአሁኑ ወቅት በመንግስት መድሎ ተደርጎብናል ብለዉ የሚያምኑ አንዳንድ የኢቦ ጎሳ አባላት ከዚህ ቆጠራ በኋላ ከፍተኛ ቁጥር በመያዝ ከናይጀሪያ የተፈጥሮ ሃብቶች ትልቁ ድርሻ ይገባናል ብለዉ ለመጠየቅ ተዘጋጅተዋል።
በመሆኑም አብዛኛዎቹ የኢቦ ጎሳ አባላት በሰፈሩበት በደቡብ ምስራቅ ናይጀሪያ የሚገኙ የየግዛቱ አስተዳዳሪዎች ሃይማኖትና ጎሳ በቆጠራዉ ቅፅ ዉስጥ መካተት አለበት እያሉ ነዉ።
እነሱም በበኩላቸዉ ሃይማኖትና ጎሳን ካላካተተ በቀር በአካባቢያቸዉ ቆጠራዉ እንደማይካሄድ ማስፈራራት ጀምረዋል።
በሌላ በኩልም በካዱና የሚገኘዉ የናይጀሪያ ክርስቲያኖች ማህበር ባለስልጣናት ቆጠራዉ ሃይማኖትና ጎሳን ማካተት አለበት ካልሆነ ግን አንቆጠርም በማለት ዝተዋል።
ለዚህ ዉዝግብ የተባበሩት መንግስታት የሰጠዉ የመፍትሄ ሃሳብ የቆጠራዉ ቅፅ ጎሳና ሃይማኖትን ቢያካትት ይሻላል የሚል ነዉ።
በናይጀሪያ ከየክልሉ በፓርላማ ዉስጥ የሚገኙ የህዝብ ተወካዮች ቁጥርና ከመንግስት የሚመደብለት በጀት በአካባቢዉ ባለዉ የህዝብ ቁጥር ይወሰናል።
በዚህም ሳቢያ ባለፈዉ ቆጠራ ወቅት በርካታ ክልሎች የህዝባቸዉን ቁጥር ከፍ አድርገዉ አስመዝግበዋል የሚል ጥርጣሬ አለ።
የዘንድሮዉ ቆጠራ ሰዎችን በነፍስ ወከፍ ከመቁጠር በተጨማሪ ያንን ችግር ሰብሮ የሚወጣበትን መንገድ ያቀናጀ ነዉ ባይ ናቸዉ አስተባባሪዎቹ።
በቆጠራዉ ወቅትም ህዝቡ የመሰረታዊ አገልግሎቶች ተጠቃሚነቱ ማለትም የንፁህ ዉሃ፤ የመብራትና የስልክ መገናኛ አገልግሎቶች መዳረሱን አብሮ ይታያል።
የዘንድሮዉ ቆጠራ በአመቱ መጨረሻ አካባቢ የሚካሄድ ሲሆን ከሁለት እስከ ሶስት ቀናት እንደሚወስድና 265 ሚሊዮን ዶላር ሊያስወጣ እንደሚችል ተገምቷል።