ዕለታዊው የኢራቅ ዓመጽ በጀርመን መገናኛ ብዙሃን ዕይታ | የጋዜጦች አምድ | DW | 06.09.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

ዕለታዊው የኢራቅ ዓመጽ በጀርመን መገናኛ ብዙሃን ዕይታ

ኢራቅ ውስጥ በተለይም በብዛት በአሸባሪዎች ጥቃት በየዕለቱ በርካታ ሰዎች ይሞታሉ። እርግጥ ቁጥራቸው ምን ያህል እንደሚሆን በትክክል አይታወቅም። የአሜሪካ መንግሥት የሚገምተው ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ባለፈው ሶሥት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ቢያንስ 30 ሺህ ኢራቃውያን መገደላቸውን ነው። የጀርመን ዜና አውታሮች አዘጋገብ ሁኔታ ምን ይመስላል?

የጀርመን ጋዜጦች

የጀርመን ጋዜጦች

ዓለምአቀፍ ታዛቢዎች በኢራቁ ዓመጽ የሞተው ሰው ብዛት በ 45 እና በ 75 ሺህ መካከል የሚንሸራሸር ነው ይላሉ። ከነዚሁ መካከልም 2,300 የሚሆኑት የአሜሪካ ወታደሮች ናቸው። ለመሆኑ በየዕለቱ ተመሳሳይና የተለመደ አሰቃቂ ዓመጽ በሚደርስባት አገር ሁኔታ ላይ እንዴት ያልተቋረጠ መረጃ ማቅረብ ይቻላል? በጀርመን አንባቢው፣ አድማጩና ቴሌቪዥን ተመልካቹ በቀውሱ አካባቢ አንድም የአገሪቱ ዘጋቢ በቋሚነት በማይገኝበት ሁኔታ በጋዜጠኞች ዘገቦች ላይ ዓመኔታ በማጣት እየቀነሰስ አይሄድም ወይ? እነዚህ ጥያቄዎች ብዙ የሚያነጋግሩ ናቸው።

እርግጥ በጋዜጠኞች የአዘጋገብ ስልት ላይ እነዚሁ ጉዳዩን የሚመለከቱበት አቅጣጫም ወሣኝነት አለው። ለምሳሌ ከትናንት በስቲያ ሰኞ የብሪታኒያው ሥርጭት ተቋም ቢ.ቢ.ሲ. ካቡል ውስጥ አንድ የብሪታኒያ ወታደር በጥይት ተመትቶ መገደሉን ዘግቦ ነበር። ይሄው ዜና በኢራን ቴሌቪዥን ደግሞ ለየት ባለ መልክ ቀርቧል። “የብሪታኒያ ወታደሮች አራት አፍጋሃኖችን ገደሉ” ተብሎ ነው የተነገረው። በመሠረቱ ሁለቱም ድርጊቶች መፈጸማቸው ትክክል ነው። ግን ቢ.ቢ.ሲ.ም ሆነ የኢራን ቴሌቪዥን ራሳቸው የሚፈልጉትን ብቻ ቆንጽለው ማውራቱን ነው የመረጡት። ይህ ሃቅ ደግሞ ሌሎች መገናኛ አውታሮችም በሌሎች ብዙዎች የዓለም ቀውስ አካባቢዎች የሚከተሉትን የአሠራር ዘይቤ የሚያንጸባርቅ ነው።

ለጀርመን መገናኛ አውታር ኢራቅ ውስጥ በአሸባሪዎች ጥቃት በብዙ ሰዎች ላይ የሚፈጸም ግድያ ጥልቅ ትንተና የማያስፈልገው አጭር ዜና የሚበቃው ጉዳይ ነው። ተወደደም ተጠላም ይህ የኢራቅ ዕለታዊ ገጽታ ነው፤ መወራቱ ያን ያህል ጠቃሚ አይደለም ለማለት የተፈለገ ይመስላል። አንዴ የቀድሞው የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሜናሂም ቤጊን በሣብራና በሻቲላ የስደተኛ መጠለያዎች በፍልሥጤማውያን ላይ ተካሂዶ የነበረውን ዜና አስመልክተው ሲናገሩ “እንዲህ ዓይነቱ ነገር የሚደርሰው በሊባኖስ ብቻ ነው” ሲሉ ጉዳዩን እንዳቃለሉት።

በኢራቅ ጉዳይም የጀርመን መገናኛ አውታሮች ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ በሌላ ነገር ማተኮሩን ሳይመርጡ አልቀሩም። ኢራቅ በጀርመን መገናኛ ዘዴዎች መተዋን በቦታው አንድም ወኪል አለመስቀመጣቸው ራሱ ያመለክታል። ምክንያቱ በአንድ በኩል እርግጥ አካባቢው ለሕይወት አደገኛ መሆኑ ነው። የአንድን ዘጋቢ ሕይወት አደጋ ላይ ከመጣል በአካባቢው ካሉ የዜና ወኪሎች በሚገኝ መረጃ መወሰኑ ይመረጣል።

በሌላ በኩል የአሜሪካና የብሪታኒያ መገናኛ አውታሮች በባግዳድ ቀጥተኛ ውክልና አላቸው። ከዋና ከተማይቱ ወጣ ካሉ ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎችም ይዘግባሉ። እርግጥ ተልዕኳቸውና ከአገራቸው ሕዝብ የሚጠበቅባቸውም የተለየ ነው። አንባቢው፣ አድማጩም ሆነ ቴሌቪዥን ተመልካቹ የአገሩ ሠራዊት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ቀጥተኛ መረጃ ማግኘት ይፈልጋል። በአጠቃላይ ለመገናኛው አውታር ቁጥብነት ሌላው ምክንያት ደግሞ ከባድ ሁኔታዎች ሣይቀር በፍጥነት የሚረሱ፤ የሚተዉ፤ በሌላ የሚተኩ እየሆኑ መሄዳቸው ነው።

የምሥራቅ አፍሪቃን የረሃብ መዘዝ ብንወስድ ለአያሌ ዓመታት ሳይቋረጥ ጸንቶ ያለ ጉዳይ ነው። ይሁንና ከዓመት አንዴ በላይ አይዘገብበትም። በቅርቡም በጋዛ ሰርጥ የተቀሰቀሰው ውጊያ በሊባኖስ ጦርነት ተተክቶ እስካለፈው ሰንበት የስቶክሆልም የለጋሽ መንግሥታት ጉባዔ ድረስ መደበኛ ቦታውን ሲለቅ ታዝበናል። ብዙዎች ተመሳሳይ ነገሮችን ለመጥቀስ ይቻላል። አንድ ችግር በመሠረቱ ያለ መገናኛው አውታር ትኩረት ክብደት የሚሰጠው ችግር አይሆንም። ምናልባት ዘግይቶ ሊሆን ይበቃ እንደሆን እንጂ!
በ 1982 ዓ.ም. በሃማ ደርሶ የነበረው የሶሪያ ዕልቂት ወይም ኢራቅ ውስጥ በ 1988 በሃላቢያ የተፈጸመው ፍጅት ለዚህ ምሥክሮች ናቸው። መገናኛ አውታሮች አንድን ሁኔታ ለታላቅ ክብደት የሚያበቁበት፤ ግን መልሰው በድን እንዲሆን የሚያደርጉበት ጊዜም አለ። እርግጥ ይህ ዛሬ የኤሌክትሮኒኩ የመገናኛ ዘዴ ዘመን ያስከተለው የትኩረት በፍጥነት መለዋወጥ እንጂ ሆን ተብሎ የሚደረግ ነገር አይደለም።