ዓለምአቀፍ ስፖርት | ስፖርት | DW | 05.11.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ዓለምአቀፍ ስፖርት

ዘገባችንን በእግር ኳስ እንጀምርና በአውሮፓው ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ባርሤሎና፣ ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ፖርቶና ማላጋ በዚህ ሣምንት አጋማሽ እንደገና ካሸነፉ 16 ቡድኖችን ወደሚጠቀልለው የጥሎ ማለፍ ዙር ማለፋቸውን ከወዲሁ ሊያረጋግጡ ይችላሉ።

ዘገባችንን በእግር ኳስ እንጀምርና በአውሮፓው ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ባርሤሎና፣ ማንቼስተር ዩናይትድ፣ ፖርቶና ማላጋ በዚህ ሣምንት አጋማሽ እንደገና ካሸነፉ 16 ቡድኖችን ወደሚጠቀልለው የጥሎ ማለፍ ዙር ማለፋቸውን ከወዲሁ ሊያረጋግጡ ይችላሉ። እነዚህ አራት ክለቦች የመጀመሪያ ሶሥት የምድብ ጨዋታዎቻቸውን በሙሉ ያሸነፉ ናቸው። ከዚሁ በተጨማሪ የጀርመኑ ክለቦች ሻልከና ዶርትሙንድ፤ እንዲሁም የኡክራኒያው ሻክታር ዶኔትስክ ከድል ጋር ወደ ተከታዩ ዙር ለመሻገር ጠቃሚ ዕርምጃ ያደርጋሉ።                                                

በሌላ በኩል የእንግሊዙ ክለቦች ያለፈው ሻምፒዮን ኤፍ ሢ ቼልሢይ፣ ለአዳዲስ ተጫዋቾች ብዙ ገንዘብ በማፍሰስ የታወቀው ማንቼስተር ሢቲይና የኢጣሊያው ሻምፒዮን ጁቬንቱስ ቱሪን ደግሞ ከባድ ግፊት ገጥሟቸው ነው የሚገኙት። የአርሰናሉ አሠልጣኝ አርሰን ቬንገር እንዳሉት ውድድሩ ወሣኝ ከሆነ ደረጃ ላይ በመድረሱ ስህተት የመስራት ብዙ ዕድል ከእንግዲህ የለም።

በነገው ማክሰኞ ምሽት በምድብ-አንድ ውስጥ ዲናሞ ኪየቭ ከፖርቶ እንዲሁም ፓሪስ-ሣንት ዠርማን ከዲናሞ ዛግሬብ የሚጫወቱ ሲሆን በምድብ-ሁለትም ሻልከ ከአርሰናልና ኦሊምፒያኮስ ፒሬውስ ከሞንትፔሊየር ይጋጠማሉ። የሻልከና የአርሰናል ግጥሚያ በተለይም በመጀመሪያው ግጥሚያ በሜዳው ለተሸነፈው ለእንግሊዙ ክለብ ወሣኝነት አለው። አሠልጣኙ አርሰን ቬንገር እንዳሉት ለስህተት ጊዜ የለም።

በነገው ምሽት ከሚካሄዱት ግጥሚያዎች መካከል በተጨማሪ ማንቼስተር ሢቲይ ከአያክስ አምስተርዳምና ሬያል ማድሪድ ከዶርትሙንድ የሚገኙበት ሲሆን በተለይ ለማንቼስተር ሢቲይ ጨዋታው የሞት የሽረትን ያህል ነው። ምድብ-ሶሥትን ሳይጠበቅ የሚመራው የስፓኙ ክለብ ማላጋ በአንጻሩ ኤ ሲ ሚላንን ካሸነፈ ወደ መጨረሻው ዙር ሰተት ብሎ ነው የሚያልፈው።                                                                                               

በፊታችን ረቡዕ በምድብ-አምሥት ውስጥ ቼልሢይ ምድቡን ከሚመራው ከዶኔትስክ የሚጋጠም ሲሆን በምድብ-ስድሥት ውስጥ እኩክ 6 ነጥቦች ያሏቸው ቫሌንሢያ፣ ቦሪሶቭና ባየርን ሙንሽን ለቀደምቱ ቦታ ገና ብርቱ ትግል ይጠብቃቸዋል። የጀርመኑ ቀደምት ክለብ ባየርን የሚጋጠመው ከመጨረሻው ከሊል ጋር ሲሆን ወደፊት መራመዱ በቀላሉ የሚሳካለት ይመስላል።  በምድብ-ስድሥት ውስጥ ባርሤሎና ሤልቲክ ግላስጎውን ከረታ በስኬት ወደ ጥሎ ማለፉ ዙር ተሻገረ ማለት ነው።

Afrika Cup Algerien Elfenbeinküste

አፍሪቃ

ወደ አፍሪቃ ክፍለ-ዓለም ሻገር እንበልና የግብጹ ክለብ አል-አህሊ በአፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ የመጀመሪያ ግጥሚያ ትናንት ከቱኒዚያው ኤስፔራንስ ጋር 1-1 በሆነ ውጤት ተለያይቷል። ያለፈው ዓመት ሻምፒዮን ኤስፔራንስ በዋሊድ ሂሽሪ አማካይነት በ 49ኛዋ ደቂቃ ላይ 1-0 ሲመራ አል አህሊ አቻ ለአቻ ለማድረግ የበቃው ወደመጨረሻው ነበር። በሊጋ እገዳ ሳቢያ በወዳጅነት ግጥሚያና በሥልጠና ካምፕ የውድድር ብቃታቸውን ጠብቀው የቆዩት የአል አህሊ ተጫዋቾች ያገኙትን ብዙ የጎል ዕድል በሚገባ አልተጠቀሙበትም።                   

የመልሱ ግጥሚያ በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ ቱኒዝ ላይ ይካሄዳል። ከካይሮ ወደ አሌክሣንድሪያ የተሸጋሸገው የትናንቱ ግጥሚያ የግብጽ ተመልካቾች በፖርት ሣይድ የስታዲዮም ዓመጽ 74 ሰዎች ከሞቱ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ጨዋታ እንዲያዩ የተፈቀደበትም ነበር። በነገራችን ላይ አል አህሊ የአፍሪካ ሻምፒዮና ሊጋ ዋንጫን ስድሥት ጊዜ በመውሰድ ቀደምቱ ሲሆን ኤስፔራንስ እስካሁን ሁለቴ ባለድል ሆኗል።

ይህ በዚህ እንዳለ የአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሽን በክፍለ-ዓለሚቱ የዓመቱን ድንቅ ተጫዋች መርጦ ለመሰየም እየተዘጋጀ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ኮንፌደሬሺኑ ራሱ የአሥር ዕጩ ተጫዋቾችን ስም ዝርዝር ሲጠቅስ ይሄው ዝርዝር የሚመራውም ባለፈው ዓመት አሸናፊ በአይቮሪ ኮስቱ ተጫዋች በያያ ቱሬ ነው። ከአይቮሪ ኮስት በተጨማሪ ዲዲየር ድሮግባና ጌርቪኞ ሲታጩ ዝርዝሩ የማንቼስተር ዩናይትድን አጥቂ ዴምባ ባን፣ የቼልሢይን ጆን-ኦቢ-ሚኬልን፣ የቀድሞውን የአርሰናል የመሃል ሜዳ ተጫዋች  አሌክሣንድር ሶንግን፤ እንዲሁም የሞሮኮውን ዩነስ ቤልሃንዳንና የዛምቢያን የአፍሪቃ ዋንጫ አሸናፊ ቡድን አምበል ክሪስ ካቶንጎን ይጠቀልላል።

አትሌቲክስ

በትናንትናው ዕለት ደቡብ ኮሪያ ውስጥ የተካሄደው የሶውል ማራቶን ሩጫ ውድድር በኬንያውያን የበላይነት ተፈጽሟል። 42ቱን ኪሎሜትር በሁለት ሰዓት ከአምሥት ደቂቃ ከሃምሣ ሤኮንድ በሆነ ጊዜ በማቋረጥ በስፍራው ያለፈውን ዓመት ድሉን የደገመው ጀምስ ኩዋምባይ ነበር። ኬንያውያኑ ከአንድ እስከ ሶሥት ሲከታተሉ ቼቦን ቼቦር ሁለተኛ እንዲሁም ቤንጃሚን ኮሉም ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል።

በሌላ በኩል ለትናንት ታቅዶ የነበረው 43ኛው የኒውዮርክ ማራቶን ሩጫ በከተማይቱ ብርቱ ጉዳት ባደረሰው አውሎ ነፋስ በሀሪኬን ሣንዲይ ጥፋት የተነሣ መሰረዙ ግድ ሆኗል። እርግጥም በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች እስካሁን ያለ ኤሌክትሪክ ብርሃንና መጠለያ መሆናቸው ሲታሰብ ዕርምጃው ትክክለኛ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። የሩጫው መካሄድ አለመካሄድ ቀደም ሲል ብዙ ቢያከራክርም በመጨረሻ የተወሰደውን ዕርምጃ ወደ ኒውዮርክ ተጉዘው የነበሩ ብዙ አትሌቶች ጭምር ከልብ ነው የተቀበሉት።

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ሻምፒዮና በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ አርሰናልን 2-1 በመርታት አመራሩን ሊይዝ በቅቷል። ማኒዩን ለግንባር ቀደምነት ያበቃው የእስካሁኑ መሪ ቼልሢይ ከስዋንሲይ ሢቲይ 1-1 በሆነ ውጤት መወሰኑ ነው። ዩናይትድ ከአሥር ግጥሚያዎች በኋላ በ 24 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ቼልሢይ በ 23 ሁለተኛ ነው፤ 22 ነጥቦች ያሉት ሶሥተኛው ማንቼስተር ሢቲይ ደግሞ ከዌስት ሃም ዩናይትድ 0-0 በመለያየቱ አመራሩን ለመጋራት የነበረውን ዕድል ሊጠቀምበት አልቻለም።

በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና በአሥር ግጥሚያዎች አንዴ እኩል ለእኩል ከመውጣቱ በስተቀር ሳይሸነፍ በአመራሩ ሲቀጥል እኩል ሲጓዝ የቆየው አትሌቲኮ ማድሪድ በአንጻሩ በቫሌንሢያ 2-0 በመረታቱ በሶሥት ነጥቦች ዝቅ ማለቱ ግድ ሆኖበታል። ቢሆንም በ 25 ነጥቦች ሁለተኛ ነው።ሬያል ማድሪድ ደግሞ ሣራጎሣን 4-0 አሸንፎ በመሸኘት ማላጋን ከሶሥተኛው ቦታ ፈንቅሏል። ማላጋ ያቆለቆለው በገዛ ሜዳው በራዮ ቫሌካኖ ከተሸነፈ በኋላ ነው።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ባየርን ሙንሽን ባለፈው ሣምንት ከዘጠኝ ድሎች በኋላ የመጀመሪያ ሽንፈት ከገጠመው በኋላ እንደገና በልዕልናው ቀጥሏል። ባየርን በግሩም ሁኔታ ሃምቡርግን 3-0 ሲረታ ሊጋውን በሰባት ነጥቦች ልዩነት ተዝናንቶ ይመራል። ሻልከ ምንም እንኳ በሆፈንሃይም ቢሸነፍም በሁለተኝነቱ  ሲቀጥል ሶሥተኛው ፋራንክፉርት ነው። ሌቨርኩዝን ደግሞ ዱስልዶርፍን 3-2 በማሸነፍ ከሽቱትጋርት ባዶ-ለባዶ የተለያየውን ዶርትሙንድን አራተኛውን ቦታ አስለቅቋል።                                                                             

በሣምንቱ ትልቅ ዕርምጃ ያደረገው ክለብ ደግሞ ትናንት ማይንስን 2-1 አሸንፎ ከ 12ኛው ወደ ሰባተኛው ቦታ ያሻቀበው ብሬመን ነው። ለብሬመን ሁለቱንም ጎሎች ያስቆጠረው ደግሞ ድንቅ ተጫዋቹ አሮን ሃንት ነበር።                                                                                   

«እርግጥ ግሩም ጨዋታ  አላሳየንም። ሆኖም ግን ትግሉና ፍላጎቱ ሰምሮልናል። ጠቃሚው ነገር ዛሬ ሶሥቱንም ነጥቦች መውሰድ መቻላችን ነው። ከዚህ አንጻር ጨዋታው ለኛ ግሩም ነበር»

ብሬመን በመጪው ሣምንት ሻልከን የመሰለ ጠንከር ያለ ተጋጣሚ ይጠብቀዋል። ለማንኛውም በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ከሁለተኛው እስከ ስምንተኛው ክለብ ድረስ ያለው የነጥብ ልዩነት በወቅቱ ስድሥት ብቻ ሲሆን በሚቀጥሉት ሣምንታት ሂደት ብዙ ለውጥ መታየቱ የማይቀር ነው የሚመስለው።

በፈረንሣይ ሻምፒዮና ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ባለፈው ቅዳሜ ለዘንድሮው የመጀመሪያ ሽንፈቱ በቅቷል። ቡድኑ በሣንት-ኤቲየን 2-1 ሲረታ ስዊድናዊ አጥቂው ዝላታን ኢብራሂሞቪች ቀይ ካርድ ተሰጥቶት ከሜዳ በመውጣቱ ጨዋታውን የፈጸመው በአሥር ሰው ነበር። የፓሪሱ ክለብ ከ 11 ግጥሚያዎች በኋላ 22 ነጥቦች ሲኖሩት ኦላምፒክ ማርሤይን በጎል ብልጫ አስከትሎ ይመራል። እርግጥ ማርሤይ ገና አንድ ትርፍ ጨዋታ አለው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ጁቬንቱስ 49 የሊጋ ግጥሚያዎችን ያለሽንፈት ካሳለፈ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢንተር ሚላን 3-1 ቢረታም አመራሩም አሁንም አልተነጠቀም። ዩቬ ከ 11 ግጥሚያዎች በኋላ በ 28 ነጥቦች ቀደምቱ ሲሆን ኢንተር በ 27 ሁለተኛ ነው፤ ናፖሊ ደግሞ አራት ነጥቦች ወረድ ብሎ በሶሥተንነት ይከተላል። አራተኛ ፊዮሬንቲና!

በፖርቱጋል ሻምፒዮና ፖርቶና ቤንፊካ እኩል ሃያ ነጥቦችን ይዘው መምራታቸውን ሲቀጥሉ  ብራጋ ሶሥተኛ ነው። በኔዘርላንድ አንደኛ ዲቪዚዮን ደግሞ ትዌንቴና አይንድሆፈን በአንዲት ነጥብ ልዩነት በመከታተልግንባር ቀደም እንደሆኑ ናቸው።

የአውቶሞቢል እሽቅድድም

ትናንት አቡ ዳቢ ላይ በተካሄደው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የፊንላንዱ ዘዋሪ ኪሚ ራይኮነን ወደ ውድድሩ ከተመለሰ ወዲህ የመጀመሪያው ለሆነ ድሉ በቅቷል። የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ሁለተኛ ሲወጣ ከሁሉም የሚያስደንቀው ከኋላ፤ ከ 24ኛው ቦታ የተነሣው የጀርመኑ የዓለም ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል ተራ በተራ ተፎካካሪዎቹን በማለፍ እሽቅድድሙን በመጨረሻ በሶሥተኝነት መፈጸሙ ነው። እንደርሱ ከሆነ ሁሉም ነገር የቡድኑ ጥረት ውጤት ነው።

«ዛሬ ግሩም እሽቅድድም ነው ያደረግነው። ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያለ የሌለ አቅማችንን ሰጥተናል። ለዚህም ነው ለስኬት መብቃታችን። የሚቀጥሉት ሁለት ቀሪ እሽቅድድሞች ምን እንደሚያመጡ ደግሞ የሚታይ ነገር ነው። በጥቅሉ አውቶሞቢላችን ግሩም፤ ቡድናችንም ጠንካራ ሲሆን እንደዚሁ ቢቀጥል ደስ ይለኛል»

ፌትል ከትናንቱ እሽቅድድም በኋላ በአጠቃላይ 255 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን አሎንሶ በ 245 በቅርብ ይከተለዋል። የዘንድሮው ውድድር ሊጠቃለል ሁለት እሽቅድድሞች ብቻ ሲቀሩ ፌትል ከሁለት ሣምንት በኋላ አሜሪካ-አውስቲን ላይ በማሸነፍ ከወዲሁ ለተከታታይ ሶሥተኛ የዓለም ሻምፒዮንነት የመብቃት ትልቅ ዕድል ነው ያለው። የትናንቱን ጥንካሬውን ላየ ለነገሩ ከአሎንሶ ይልቅ እርሱ ለዓመቱ ድል የቀረበም ነው የሚመስለው። 

ቡጢ

የጀርመኑ የቡጢ የዓለም ሻምፒዮን ማርኮ ሁክ በዚሁ በጀርመን ሃለ ላይ በተካሄደ የዓለም ቡጢ ድርጅት የመካከለኛ ክብደት ግጥሚያ በዳኞች አንድ ድምጽ የአገሩን ልጅ ፊራት አርስላንን አሸንፏል። ለ 27 ዓመቱ ሁክ የሰንበቱ ድል 35ኛው ሲሆን የዓለም ቡጢ ድርጅትም ለአሥረኛ ጊዜ ማዕረጉን በማስከበሩ ወደ ሱፐር ሻምፒዮንነት ደረጃ ከፍ አድርጎታል። አርስላን በበኩሉ የዳኞቹን ውሣኔ በመቃወም ድሉ ይገባው እንደነበር በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቁጣው ለማንም የተሰወረ አልነበረም። በዕውነትም አርስላን 12ቱን ዙር ሙሉ ተጋጣሚውን ሲያጣድፍ ነበር የታየው። ሆኖም ግን ልዕልናው በመጨረሻ አልጠቀመውም።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic

 • ቀን 05.11.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/16dAd

ተዛማጅ ዘገባዎች

 • ቀን 05.11.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink http://p.dw.com/p/16dAd