ዉኃ ያባባሰዉ የቲያንጂኑ ፍንዳታ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 19.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ዉኃ ያባባሰዉ የቲያንጂኑ ፍንዳታ

በቻይናዋ የወደብ ከተማ ቲያንጂን ባለፈዉ ሳምንት የደረሰዉ ከባድ ፍንዳታ እስካሁን ከመቶ ለሚበልጡ ሰዎች ህልፈተ ሕይወት ምክንያት ሆኗል። እሳት ለማጥፋት ከተሰማሩ የነፍስ አድን ሠራተኞችም በርካቶቹ የገቡበት አልታወቀም።

በትልቅነቷ ከዓለም አስረኛ መሆኗ በሚነገርላት የቲያንጂን ወደብ ከተማ ፍንዳታ የደረሰበት ስፍራ የተለያዩ ንጥረነገሮች የተከማቹበት ነበር። ፍንዳታዉ ሊያስከትል ይችላል የተባለዉ የአየርና ዉኃ መበከል ስጋት 6,300 የአካባቢዉን ኗሪዎች እንዲሰደዱ አስገድዷል። አጋጣሚዉ በመኖሪያ አካባቢ መርዛማ ንጥረ ነገሮችን ማከማቸት ሊያመጣ የሚችለዉን አሰቃቂ አደጋም አሳይቷል።

ባለፈዉ ሳምንት ረቡዕ ለሊት ነበር የአቶሚክ ቦምብ ያህል አካባቢዉን አናዉጧል የተባለለት የቲያንጂን ወደብ ከተማ ላይ ከባድ ፍንዳታ የደረሰዉ። ወደሰማይ የጎነዉ እሳትም አካባቢዉን በብርሃን አልብሶት እንደነበር የቻይና ብሄራዊ የመገናኛ ብዙሃን ደጋግመዉ በዘገባቸዉ ገልፀዉታል። አደጋዉ እንደደረሰም ከ300 እስከ400 የሚገመቱ ጉዳት የደረሰባቸዉ ሰዎች ሃኪም ቤት ተወስደዋል። የሟቾቹ ቁጥር በየዕለቱ እያሻቀበም 114 ደርሷል።57 ሰዎች እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም። የፍንዳታዉ ንዝረት በርካታ ማይሎችን ርቆ ከመሰማቱ በተጨማሪ የቤቶችን መስኮትና በሮች አንኮታኩቷል። ከዓለም እጅግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ከሚበዛባቸዉ ወደቦች አንዱ መሆኑ በሚነገርለት የቻይናዉ ቲያንጅን ወደብ በሚገኝ የበርካታ ንጥረነገሮች ማከማቻ መጋዘን ላይ የደረሰዉ ፍንዳታም ከቢሊየን ዶላር በላይ ኪሳራ ማስከተሉ እየተነገረ ነዉ። ፍንዳታዉ ያስከተለዉን እሳት ለማጥፋት በተደረገዉ ጥረት እሳቱ መባባሱ ታይቷል።

ይህም የነፍስ አድን ሠራተኞቹ እሳቱ ወደሌላ አካባቢ እንዳይዛመት በቁጥጥር ሥር ለማዋል ብዙ እንዲዋትቱ ግድ ብሏል። በስፍራዉ ከአደጋዉ በኋላ የደረሱበት አልታወቀም ከተባለዉ ሰዎችም አብዛኞቹ የእሳት አደጋ ተከላካይ ሠራተኞች ናቸዉ። በወደቡ አቅራቢያ በሚገኝ መጋዘን ዉስጥ የተከማቹትን ንጥረ ነገሮች ለፍንዳታ ያበቃቸዉ ምክንያት ባይገለፅም እሳቱ የተባባሰዉ ግን ሶዲየም ሳይናይድ በተባለዉ መርዛማ ንጥረ ነገር ምክንያት መሆኑ ነዉ የተሰማዉ። መርዛማዉ ንጥረ ነገር በዚህ ስፍራ ሊቀመጥ ከሚገባዉ መጠን በላይ የበረከተ ሲሆን ዘገባዎች እንደሚሉት ከ700 ቶን በላይ ሶዲየም ሳይናይድ በሁለት ሥፍራ ተከማችቶ ነበር። መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም በስፍራዉ ሊቀመጥ ከሚገባዉ 70 እጅ እጥፍ የበለጠ ክምችት ነበር። ሶዲየም ሳይናንድ በሳይንሳዊ ቀመሩ NaCA በመባል ይታወቃል። ሳይናይድ የሚለዉ ስያሜ በራሱ መርዛማነቱን የሚገልፅ ነዉ። ከመርዛማነቱ ጋር በተገናኘም እጅግም ጥሩ ስም አልነበረዉ። በተለይም በሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ናዚዎች አይሁዳዉያኑን በፖታሲየም ሳይናይድ ኪኒን መፍጀታቸዉ በታሪክ ተመዝግቧል። በቻይናዉ ታዋቂ የባህር ወደብ ቲያንጅን በከፍተኛ መጠን ተከማችቶ የተገኘዉ ሶዲየም ሳይናይድም መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሳይናይድነቱ ከዚህ ጋር በመመሳሰሉ ነዉ የመመረዝ ስጋትን ያስከተለዉ። በኒኩሊየር ፊዚክስ የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸዉ በደቡብ አፍሪቃ ኬፕታውን ከተማ፤ በኬፕ ፔኒዙዌላ የስነ-ቴክኒክ ዩኒቨርሲቲ፤ በፊዚክስ ዲፓርትመንት ውስጥ መምህር እና ተመራማሪ ዶክተር ዳዊት ሰሎሞን ወርቁ ስለሶዲየም ሳይናይድ ምንነት እንዲህ ያስረዳሉ።

በዐይን ሲታይ በንጣቱ ምክንያት ምንም የሚያስከትል የማይመስለዉ ሶዲየም ሳይናይድ የሻይ ማንኪያ አምስት በመቶ የሚሆን ቁንጣሪዉ እንኳ ሕይወትን የማጥፋት አደገኝነት እንዳለዉ ነዉ ጥናቶች የሚያመለክቱት። በቲያንጅን ወደብ በንጥረ ነገሮች ማከማቻ ስፍራ የደረሰዉን እሳት ለማጥፋት የተረጨዉ ዉኃ ፍንዳታዉን ሲያባብስ ታይቷል። ይህ ንጥረ ነገር ከዉኃ ጋር ያለዉ ግንኙነት ምን ይሆን? መርዛማነቱ የሚነገርለት ሶዲየም ሳይናይድ በተከማቸባት የቲያንጅን ወደብ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ንጥረ ነገሩ ሲቃጠል በሚፈጠረዉ ጭስም ሆነ በዉኃ አማካኝነት ሊከተል ይችላል የተባለዉ ብክለት አስግቷቸዋል። ፍንዳታዉ እንደደረሰም ከስድስት ሺህ የሚበልጡት መኖሪያ ቤታቸዉን እየተዉ ለመሸሽ ተገደዋል። ትናንት በአካባቢዉ የወረደዉ ከባድ ዝናብም የአካባቢ ብክለቱን እንዳያባብሰዉ ተፈርቷል።

በወደቡ አቅራቢያ በነበረዉ መጋዘን ዉስጥ ከተከማቹት ንጥረ-ነገሮች መካከል ካልሲየም ካርባይድ፤ ሶዲየም ሳይናይድ፤ ፖታሲየም ናይትሬት፣ አሞኒየም ናይትሬት እንዲሁም ሶዲየም ናይትሬት ይገኙበታል። ዶክተር ዳዊት እንዲህ ያሉ መርዛማ ንጥረነገሮች በሚቀመጡበት አካባቢ ለሚኖሩ ወገኖች አስቀድሞ ተገቢዉን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስተማርና ማስጠንቀቅም እንደሚገባም መክረዋል። በተቃራኒዉ የቻይና መንግሥት ግን ስለብክለቱ ስጋትና በመኖሪያ መንደር አቅራቢያ የንጥረ ነገሮቹ ክምችት መገኘት ሊያስከትል የሚችለዉን አስመልክቶ የሚዘግቡ የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመዝጋትና መከታተል ተጠምዷል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic