ወጣቶቹ ተሿሚዎች የት አሉ? | ባህል | DW | 04.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

ወጣቶቹ ተሿሚዎች የት አሉ?

በዚህ ሳምንት የተካሄደው የካቢኔ ሹም ሽር መወያያነቱ እስካሁንም አልበረደም፡፡ በጉዳዩ ላይ ከተነሱት አስተያየቶች አንዱ በሹመቱ ውስጥ የወጣቶች አለመካተት ነው፡፡ ወጣቶችን ወደ መሪነት አለማምጣት በገዢው ፓርቲ ላይ ከሚነሱበት ቅሬታዎች አንዱ ነው፡፡ ትችቱ ተቃዋሚዎችንም አይምርም፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:29

ወጣት አመራሮች ለምን ገሸሽ ተደረጉ?

ከሦስት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባው ሸራተን ሆቴል በርካቶች ተሰብስበው ነበር፡፡ መንግሰት ዘመም በሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተዘጋጀው ይህ ውይይት “የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ እና የፌደራል ስርዓት” ላይ ያተኩራል ቢባልም ወቅታዊ የሀገሪቱ ችግር ይበልጥኑ ተጭኖት ታይቷል፡፡ ጥቂት ወጣቶችን ባሳተፈው በዚህ ውይይት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመጀመሪያ ልጅ ሰምሃል የተወረወሩት አስተያየቶች መነጋገሪያ ሆነው ሰንብተው ነበር፡፡ ሰምሃል የአባቷን የፓለቲካ ጓዶች “ስልጣናቸውን ለወጣት ለመልቀቅ ዝግጁ አይደሉም” ስትል ወርፋቸዋለች፡፡

“አሁን ባለንበት ሁኔታ ድርጅቱ ያሰናበታቸው የፖሊት ቢሮ አባሎች ደግመው ፖሊት ቢሮ የገቡበት ሁኔታ ነው፡፡ መከራከሪያው የነበረው ‘መለስ ስለሞተ ክፍተት ተፈጥሯል፤ ክፍተቱን መሙላት የምንችለው ደግሞ አዛውንቶቹ ብቻ ነን’ ነው፡፡ እርሱን ስትሉ ጉባኤው ‘ክፍተት ይኑር አይኑር እርሱን የምትሞሉት እናንተ አይደላችሁም፤ ወጣቱ ነው፡፡ ያፍርስ አያፍርስ እርሱ ነው የሚሞላው’ ብሎ መልስ ሲሰጣችሁ ለምንድነው ያላዳመጣችሁት? ለምንድነው ተመልሳችሁ ፖሊት ቢሮ ውስጥ የገባችሁት” ስትል ጎምቶዎቹን የገዢውን ፓርቲ ፖለቲከኞች በድፍረት ጠይቃለች፡፡ 

ሰምሃል “ጉባኤው” እያለች የምትጠቅሰው በገዢው ፓርቲ አደረጃጀት ከፍተኛ ስልጣን ያለውን አካል ነው፡፡ ኢህአዴግ ከስድስት ዓመት በፊት “መተካካት” ሲል የሰየመውን እቅድ ይዞ ወደ መድረክ ሲመጣ አዳዲስ ፊቶች እና ወጣቶችን ወደ ስልጣን ያመጣል የሚል ግምት አሳድሮ ነበር፡፡ መተካካቱ በተወሰነ ደረጃ እንደተሳካ ፓርቲው ቢገልጽም በአመራርነት ደረጃ የተቀመጡ ወጣቶች እምብዛም አልታዩም፡፡ መተካካቱ ይበልጥኑ ያተኮረው በትጥቅ ትግሉ ወቅት ያልተሳተፉ እና ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ፓርቲውን የተቀላቀሉ ሰዎችን ወደ ፊት ማምጣት ላይ ነበር፡፡ 

ከዓመታት በኋላም ግን ቁልፍ የገዢው ፓርቲ የውሳኔ ሰጪ ቦታዎች አሁንም የ60ዎቹ ትውልድ በሚባሉት የቀድሞ ታጋዮች እንደተያዘ አለ፡፡ ኢህአዴግ መተካካቱን ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር “በክብር ተሰናበቱ” የተባሉ አባላት ጭምር ወደ ፓርቲው ቁልፍ ቦታዎች የመመለስ አዝማሚያ እያሳዩ ነው፡፡ ከፓርቲው የስልጣን ተዋረድ ባሻገር በመንግስታዊ የአመራር ቦታዎች ያለው እውነታም ተመሳሳይ ነው፡፡ በመንግስት መስሪያ ቤቶች በመሪነት የተቀመጡ ወጣቶች ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ ህዝባዊ ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስታቸውን እንደ አዲስ እንደሚያወቅሩ በገለጹበት ወቅት የወጣት ባለሙያ ሚኒስትሮች መሾሚያ ጊዜ የደረሰ የመሰላቸው ነበሩ፡፡ ማክሰኞ ዕለት የተሿሚዎች ማንነት ሲገለጽ ግን አንድም ወጣት ሚኒስትር ከዝርዝር ውስጥ አልነበረም፡፡ 

ከፌስ ቡክ ማህበራዊ ድረ ገጽ ተጠቃሚዎች መካከል ይሾማል ብሎ ያሰበው ወጣት ሚኒስትር የት ገባ ብሎ የጠየቀም ነበር፡፡ ለዚህ ጥያቄው ምላሽ የሰጠ ሌላ ተጠቃሚ “ወጣቶች ቀበሌ ከበዛም ወረዳ ካቢኔ ውስጥ ይበቃቸዋል ብለው እንዳይሆን ሲል?” ጥርጣሬውን አጋርቷል በኖርዌይ የዩኒቨርስቲ ትምህርቱን እየተከታተለ የሚገኘው የ27 ዓመቱ ምንይችል መሰረት ግን ቀድሞውኑ “የወጣቶችን ሹመት” እንዳልጠበቀ ይናገራል፡፡ ወጣቶችን ወደ አመራር ማምጣት “ብዙ ጊዜ ይወራል ግን አይተገበርም” ባይ ነው፡፡ 

“እስካሁን ካየን እንደዚህ ዓይነቱ ነገር ብዙ አልተለመደም፡፡ በእኔ ዕድሜ ወጣት ሚኒስትሮችን [አላየሁም]፡፡ ምናልባት ይሄ በጣም አሻሚ ነገር ነው፡፡ እስከ ምን ያህል ዕድሜ ያለው ነው ወጣት የሚለው ነገር የሚያጠያይቅ ቢሆንም ያን ያህል አልጠብቅም፡፡ ምክንያቱም እስካሁን ያየሁትም ነገር አልነበረም፡፡ ወጣቶችን ማሳተፍ ብዙም የተለመደ አይደለም፡፡ ሰሞኑን በተደረገው ሽግሽግም ወጣቶችን በማሳተፍ ደረጃ ብዙም አላስተዋልኩም” ይላል፡፡ 

Innovative Fahrrad-Wahlrallye der regierenden EPRDF für die Parlamentswahl in Äthiopien am 23.Mai (DW)

ምንይችል በሀገራችን ያለው የፖለቲካ ስርዓት “አንድ ሰው ወይም ጥቂት ወጣቶች ትልቅ ነገር የሚሰሩበትን ሁኔታ የሚፈቅድ አይደለም” ብሎ ያምናል፡፡ የኢትዮጵያ ወጣቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ያጠኑ ምሁራንም በዚህ ይስማማሉ፡፡ በማንችስተር ዩኒቨርስቲ የዶክትሬት ጥናቱን እያደረገ ያለው ኢዮብ ባልቻ በጉዳዩ ላይ ከዓመታት በፊት ባሳተመው አንድ ጽሁፉ ይህንኑ አንስቷል፡፡ 

በወጣት ማህበራት እና በገዢው ፓርቲ ወጣት ሊግ የሚታየው ፖለቲካዊ ተሳትፎ በአንድ ወቅት ከነበረው እንደሚሻል የሚቀበለው አጥኚው በጥልቀት ሲታይ ግን ከቁጥር ሟሟያነት የዘለለ ሚና እንደማይጫወቱ ያስረዳል፡፡ የፖለቲካ አካሄዱን ጠንቅቀው በሚያውቁ፣ አዲስ አመለካከት እና አተያይ ለማስተናገድ ዝግጁ ባልሆኑ የቀደመው ትውልድ አባላት መሞላት ይህን እንዳስከተለ የሚከራከሩ እንዳሉ ይጠቅሳል፡፡ ፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚቀላቀሉ ወጣቶች ተጽእኖ አሳዳሪ ደረጃ ከመድረስ ይልቅ በአባልነት ተወስነው እንደሚቀሩም ያብራራል፡፡

ለወጣቶች የመሪነት ቦታ አለመስጠት በተቃዋሚዎችም ጎራ የሚታይ ስር የሰደደ ችግር ነው፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ረጅም ዓመታት ያስቆጠሩት ዶ/ር መረራ ጉዲና “ተቃዋሚዎች ወጣቶችን ወደ አመራር አያመጡም” የሚለውን ትችት አይቀበሉትም፡፡ የስድሳ ዓመቱ ፖለቲከኛ ወጣቶች በፓርቲያቸው ቁልፍ ቦታዎች ውስጥ እንዳሉ ይሟገታሉ፡፡ በሊቀመንበርነት የሚመሩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ወጣት አመራሮች በእስር ላይ እንዳሉ አስታውሰው ለወጣቶች አለማደግ ጣታቸውን በገዢው ፓርቲ ላይ ይቀስራሉ፡፡

“ተቃዋሚን በሚመለከት የተቃዋሚ ወጣቶች ቃሊቲ፣ ቂሊንጦ ሄዳችሁ እዚያ መጠየቅ ትችላላችሁ፡፡ ለምሳሌ 50 በመቶ የወጣት ሊጋችን አመራሮች ቃሊቲ ነው ያሉት፡፡ ሊቀመንበሩ፣ ምክትል ሊቀመንበሩ፣ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው፣ ድርጅት ጉዳይ ኃላፊው እነዚህ ለምሳሌ ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ናቸው፤ አነርሱ ያሉት ለምሳሌ ቃሊቲ ነው፡፡ እነ ኦልባና ቃሊቲ እና ቂሊንጦ ናቸው፡፡  ስለዚህ ወጣቱን እንዳናሳድግ ያደረገው ኢህአዴግ ነው እንጂ እኛ እንዳያድጉ አድርገን አይደለም” ሲሉ በእነርሱ ላይ የሚሰነዘረውን ወቀሳ ወደ ገዢው ፓርቲ ያዞሩታል፡፡   

በአረቡ ዓለም ከተቀሰቀሰው አብዮት ወዲህ በተለያዩ ሀገራት ያሉ ወጣቶች ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ጥያቄዎችን አንግበው አደባባይ ወጥተዋል፡፡ ነገር ግን በምክር ቤቶች፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምርጫዎች እና በህዝብ አስተዳዳር ውስጥ በአግባቡ ሲወከሉ እንደማይስተዋል የተባበሩት መንግስት ልማት ድርጅት አንድ ጥናት ያመለክታል፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ በበርካታ ሀገራት ከ35 ዓመት በታች ያሉ ዜጎችን በፖለቲካ አመራር ላይ ማግኘት ብርቅ ነው፡፡ በአንዳንድ ሀገራት ለተወካዮች ምክር ቤት ለመወዳደር ከ25 ዓመት በላይ መሆን ይጠይቃል፡፡ ከ40 ዓመት በታች ያሉ ፖለቲከኞች በሙሉ ወጣት አድርጎ የመውሰድ ልምድ እንዳለም ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ 

ከህዝባቸው ገሚሱ ወጣት በሆነባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት የወጣቶች ትርጉም ባለው የውሳኔ ሰጪነት ሂደት መሳተፍ ለነገ የማይባል መሆኑን ጥናቶች ያሳስባሉ፡፡ ይህን የሚጋራው ምንይችል “ወጣቶች ተገቢው ቦታ ቢሰጣቸው ብዙ የማድረግ አቅም አላቸው” የሚል አቋም አለው፡፡       

“በእኔ አስተሳሰብ ወጣቶች በተለያየ የፖለቲካ ተሳትፎ ውስጥ የመንቀሳቀስ ዕድሉን ቢያገኙ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡ በዚህ በአዲሱ ትውልድ ለብዙ ነገሮች ወግ አጥባቂ አለመሆን አያለሁ፡፡ እነዚህን ወጣቶች ቢያካትቱ ምናልባት የተሻለ ነገር ሊመጣ ይችላል ብዬ አምናለሁ” ይላል ምንይችል፡፡  

ወጣቶችን በብዛት ያሳተፈውን ህዝባዊ ተቃውሞ እና አመጽ ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት ወጣቶች የራሳቸው የሆነ ፖለቲካዊና አስተዳዳራዊ ፍላጎቶች እና ጥያቄዎች እንዳሏቸው እንደሚገነዘብ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ሆኖም ይህን ባወጀ በሁለት ሳምንት ውስጥ ያካሄደው የሚኒስትሮች ሹመት ወጣቶችን ያገሸሸ ሆኗል፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

አዜብ ታደሰ
 
 

Audios and videos on the topic