1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወደ ባህር ከተወረወሩ ስደተኞች ውስጥ 35 ሞቱ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 9 2009

በጀልባ ወደ የመን ይጓዙ የነበሩ 160 ስደተኞች በአሸጋጋሪዎቻቸዉ ወደ ባህር መገፍተራቸዉን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ዛሬ አስታውቋል፡፡ ከእነርሱ መካከል ስድስቱ መሞታቸውን ድርጅቱ ገልጿል፡፡ ከስደተኞቹ ውስጥ 90 በመቶው ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በየመን የሚገኘው የድርጅቱ ጽህፈት ቤት ለዶይቸ ቬለ አስረድቷል፡፡

https://p.dw.com/p/2i2B9
Jemen Schlepper lassen Migranten ertrinken
ምስል picture-alliance/house 6 peter eisenmann

ከስደተኞቹ አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሏል

የመን በጦርነት አበሳዋን እያየች ነው፡፡ ጦርነቱ ዜጎቿን እና ስደተኞች መፈናፈኛ አሳጥቷቸዋል፡፡ በዚህ የሳዑዲ መራሹ የአየር ድብደባ፣ በዚያ የታጣቂዎች እስራት ወዲህ ደግሞ የኮሌራ ወረርሽኝ ሰቅዞ ይዟቸዋል፡፡ በየመን የሚገኙቱ እንዲህ በተጨነቁበት ወቅት በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አሁንም የአደን ባሕርን ተሻግረው ወደ ሀገሪቱ መግባታቸዉን አላቋረጡም፡፡ አደጋ የበዛበት ጉዟቸው የብዙዎችን ትኩረት የሚስበዉ ግን እንደ ትላንቱ እና እንደዛሬው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሞት አፋፍ መድረሳቸው ባስ ሲልም ህይወታቸውን ማጣታቸው ሲወራ ነው፡፡

እንደ ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ትላንት እና ዛሬ ብቻ 300 ገደማ ስደተኞች ወደ የመን ለመሻገር ሲሞክሩ በህገ ወጥ ሰው አሸጋጋሪዎች ሆን ተብሎ ወደ ባህር ተጥለዋል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት በሁለት ቀናት ብቻ 35 ስደተኞች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ሃምሳ የሚሆኑት ደግሞ ደብዛቸው ጠፍቷል፡፡ በየመን የIOM ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ ሳባ ማልሜ ወደ ባህር ስለተጣሉት ስደተኞች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል፡፡

“መቶ ስድሳ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ከ90 እስከ 95 በመቶ ማለት ይቻላል ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ አሁንም መረጃዎችን እያጠናቀርን ቢሆንም እስካሁን ባለው ያረጋገጥኩት ስድስት መሞታቸውን ነው፡፡ በባህሩ ተጠርገው የተወሰዱት አስክሬኖች እየመጡ ስለሆነ አሁንም እየፈለግን ነው፡፡ የሟቾቹን ማንነት ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስደተኞች ምንም ዓይነት መታወቂያ አይዙም፡፡ አብሯቸውም ዘመድ የለም” ብለዋል ሳባ ማልሜ፡፡

IOM ዛሬ ባወጣው መግለጫ ወደ ባህር  የተወረወሩት ስደተኞችን ቁጥር 180 አድርሶት ነበር፡፡ ቁጥሮቹን የሚያገኙት በህይወት ከተረፉት ስደተኞች መሆኑን የሚናገሩት ማልሜ ሙሉ መረጃው እስኪጠናቀር ድረስ የቁጥር መዋዥቅ እንደሚያጋጥም ተናግረዋል፡፡ ድርጅታቸው ስደተኞች ትላንትም ተመሳሳይ አደጋ እንደደረሰባቸው ማስታወቁን አስመልክቶ ለተጠየቁት ደግሞ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

Flüchtlinge Boot Symbolbild Jemen Äthiopien
ምስል picture-alliance/dpa/Xinhua /Landov

“ትላንት ወደ 120 ገደማ ይሆናሉ፡፡ ይህ የሆነው በምሽት ነው፡፡ ሃያ ዘጠኝ መሞታቸው ተረጋግጧል፡፡ ሃያ ሰባቱ በህይወት ተርፈዋል፡፡ በIOM በኩልም እገዛ ተደርጎላቸዋል፡፡ የሞቱትን ከቀበሩ በኋላ የተወሰኑት አካባቢውን ለቅቀዋል፡፡ ስለሌሎቹ አናውቅም ምናልባትም አሁንም በባህር ውስጥ ይሆናሉ” ሲሉ ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ካነጋገራቸው ውስጥ ሩብ ያህሉ ሶማሊያውያን፤ ቀሪዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ማልሜ ይናገራሉ፡፡ እስካሁን የሟቾቹን ዜግነት ለማረጋገጥ ግን አለመቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ ትላንት ከባህር የተገኙት ስደተኞች አማካይ ዕድሜ 16 እንደሆነ IOM በመግለጫው አትቷል፡፡ ማልሜም አብዛኞቹ በጣም ወጣቶች መሆናቸውን ለዶይቸ ቬለ አረጋግጠዋል፡፡

በዚህ ዓመት ወደ የመን ከተሰደዱት ውስጥ የታዳጊዎች ቁጥር ላቅ ያለ ነው፡፡ ድርጅቱ ባወጣው መረጃ መሰረት ካለፈው ጥር ወዲህ ወደ የመን ከገቡ 55 ሺህ ስደተኞች መካከል 33 ሺህ ገደማው ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆነ ኢትዮጵያውያን እና ሶማሊያውያን ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንድ ሶስተኛው ሴቶች መሆናቸውን ድርጅቱ አመልክቷል፡፡

ወቅቱ በህንድ ውቅያኖስ ላይ ከፍተኛ ንፋስ የሚነፍስበት በመሆኑ የጀልባ ጉዞ አደጋን ያዘለ እንደሆነ IOM ገልጿል፡፡ በየመን ካለው ችግር ባሻገር ሳዑዲ አረቢያ ስደተኞችን በምታስወጣበት  በዚህ ወቅት የስደተኞች ፍልሰት አለመገታቱ አጠያይቋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አደጋውን እያዩ ስደትን የመረጡበትን መሰረታዊ ችግር በተመለከተ የዶይቼ ቬለ የፌስ ቡክ ተከታታዮች ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡

በፍቅሩ ሠው ገዳይ የተባሉ ተከታታይ "እዚህ ሆኖ ምን ይስራ መንግሥት ሥራ ከመፍጠር ይልቅ ሥራ የፈጠሩትን በግብር ማጨናነቁን ተያይዞታል" ብለዋል።  ሳራ አማን የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ "ኢትዮጵያ ከራሷዋ ወጣቶች ይልቅ ለጎረቤት ሀገራት በጣም መልካም ናት፡፡ ለምሳሌ ብንወስድ የኤርትራና የደቡብ ሱዳን ስደተኛ ወጣቶች የነፃ ማለትም ከወጪ መጋራት ነፃ የሆነ የከፍተኛ ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ሲቀጥል ከእኛው በሚሰበሰብ ግብር ለኤርትራ ተወላጅ ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው ስራ እንዲሰሩ የገንዘብ ድጋፍ ተደርጎላቸው በአንዳንድ አካባቢዎች ስራ ላይ ናቸው፡፡ ለእኛ ያልሆነች፤ ለጎረቤት ሀገር የተመቸች ሀገር ላይ ስላለን ነው በጦር ወደ ወደቀች ሀገር ሳይቀር የሚሄዱት" ሲሉ አስተያያታቸውን ሰጥተዋል።

ሀብታሙ ለማ በበኩላቸው "ደላላ በፊታቸው ስላለው አስከፊው የበረሀ ጉዞ ሳይሆን በጣም በተደላደለ ቦታ ጥሩ ስራ ሰርተው፣ በጥቂት አመታት ዶላር አፍሰው፣ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን እንደሚለውጡ ነው ተስፋ የሚሰጣቸው።  የመን ላይ ያለውን የሰው እልቂትና ረሀብ የሚያውቁ አይመስለኝም" ብለዋል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ 

ኂሩት መለሰ