ኬንያና የሶማልያ ስደተኞች ዕጣ ፈንታ | አፍሪቃ | DW | 09.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ኬንያና የሶማልያ ስደተኞች ዕጣ ፈንታ

የኬንያ መንግሥት በሀገሩ የሚገኙትን ወደ 350,000 የሚጠጉትን የሶማልያ ስደተኞች ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንዲመለሱ እንደማያስገድድ አረጋገጠ። እንደ ኬንያ መንግሥት መግለጫ፣ ስደተኞቹ ከፈለጉ ብቻ ነው የአማፂው ቡድን አሸባብ ብዙውን ከፊል ወደ ሚቆጣጠረዉ ሶማልያ ሊመለሱ የሚችሉት።

የኬንያ መንግሥት የአሸባብ ታጣቂዎች ከጥቂት ጊዜ በፊት በጋሪሳ ጥቃት ጥለው 148 የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችና ሠራተኞች ከተገደሉ በኋላ ርምጃውን ለመበቀል ሲል የተለያዩ አፀፋ ርምጃዎችን ወስዷል። በዚሁ መሠረትም፣ የኬንያ መንግሥት በሀገሩ የሚገኙ «ሐቂ አፍሪቃ» እና «ሙስሊም ለሰብዓዊ መብት» የተባሉ ሁለት የሙስሊም የመብት ተሟጋች ድርጅቶችን ከመዝጋቱ ጎን፣ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዚደንት ዊልያም ሩቶ በዳዳብ የስደተኞች ጣቢያ ከለላ ያገኙትን ወደ 350,000 የሚጠጉትን የሶማልያ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸዉ ለመመለስና ጣቢያውን በሦስት ወራት ለመዝጋት ዛቻ አሰምተው ነበር። ኬንያ በዓለም ትልቁ መሆኑ የሚነገርለትን የዳዳብ መጠለያ ጣቢያን የአሸባብ አሸባሪዎች መፈልፈያ ቦታ አድርጋ ነው የምትመለከተው።ይህንን የኬንያ ዕቅድ በጥብቅ የተቃወመው የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶንዮ ጉተረሽ ስለዚሁ ጉዳይ ከኬንያ ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ ባለፈው ረቡዕ በናይሮቢ ከመከሩ በኋላ፣ የኬንያ መንግሥት ስደተኞቹን የርስበርስ ጦርነት ወዳዳቀቃትና አሁን መረጋጋት ለማስፈን በመጣር ላይ ወዳለችው ትውልድ ሀገራቸው በግዳጅ እንደማይመልስ ለጉተረሽ አረጋግጦላቸዋል። ስደተኞቹ ሲፈልጉ ብቻ ወደ ትውልድ ሀገራቸው እንደሚመለሱ የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መሥሪያ ቤት ከኬንያ እና ከሶማልያ ጋ ስምምነት ደርሷል። ኬንያ በተለይ አሸባብ በሚሰነዝራቸው ጥቃቶች ለሀገሯ ፀጥታ አደገኛ እና አሳሳቢ ነው ስትል በተደጋጋሚ ያሰማችውን ስጋት እንደሚረዱት የተመድ ባለሥልጣን አንቶንዮ ጉተረሽ አስታውቀዋል።

« የፀጥታ ችግር መኖሩን አውቀነዋል። እና በዳዳብ መጠለያ ጣቢያ ሥነ- ስርዓት ለማረጋገጥ በዚያ ያለውን ፀጥታ ማስጠበቂያውን ዘዴ ለማጠናከር ከመንግሥት ጋ ስምምነት ላይ ደርሰናል። ይህ ነው ገሀድ መሆን ያለበት። ከዳዳብ ስደተኛ መካከል ግማሹ ያህል ተመልሶ ሊኖርባቸው የሚችሉ አካባቢዎች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ ብለን እናስባለን። »

ከዚህ በተጨማሪ ተመላሾቹ ሶማልያውያን ስደተኞች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች መሠረተ ልማት ማስተካከል ተገቢ እንደሚሆን ጉተረሽ አክለው አስረድተዋል።


« ሶማልያውያኑ ስደተኞች የተረጋጋ ሁኔታ ይታይባቸዋል ወደሚባሉት የሀገራቸው አካባቢዎች በፈቃዳቸው የሚመልሱበትንና ደህነነታቸው ተጠብቆ በክብር መኖር የሚችሉበትን መርሀ-ግብር ለማጠናከር ተስማምተናል። ይህን እውን ለማድረግ ግን በዚያው በሶማልያ ውስጥ የትምህርቱን፣ የጤናውንና የሌሎች የኑሮ ዘርፎችን ለማሻሻል ገንዘብ ያስፈልጋል። እና መርሀ-ግብሩን ለማሳካት ከሶማልያ፣ ከኬንያ መንግሥታት እና ከሌሎች አጋሮቻች ጋ ባንድነት በመሆን የርዳታ ጥሪ ልናቀርብበት የምንችልበትን ዓለም አቀፍ ጉባዔ ለመጥራት ዝግጅት እንጀምራለን። »

በምሥራቅ አፍሪቃ የ«ዩኤንኤችሲአር» ቃል አቀባይ እአአ የ1951ዓም በተፈረመው የተመድ ውል መሠረት ስደተኞችን በግዳጅ መመለስ እንደማይቻል አስታውሰዋል። « ስደተኞች ወደ ትውልድ ሀገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ በፈቃደኝነት ላይ የተመረኮዘ መሆን አለበት። በትውልድ ሀገሩ ለስደት የዳረጉት ሁኔታዎች እስካልተሻሻሉ ድረስ አንድ ስደተኛን በግዳጅ መመለስ አይቻልም። በወቅቱ ከስደተኞቹ ጋ በቅርብ እየተገናኘን በመስራት ላይ ነን። በፈቃዳቸው መመለስ የሚፈልጉ ስደተኞችን መርዳት የሚያስችል አዲስ ፕሮዤ ጀምረናል። እገዛም አድርገንላቸዋል። በዳዳብ መጠለያ ከሚኖሩት መካከል ብዙዎቹ ከደቡብ እና ከማዕከላይ ሶማልያ የመጡ ናቸው። »

ኬንያ ስደተኞቹን በግዳጅ እንደማትመልስ ማረጋገጥዋ፣ ጣቢያውን ለመዝጋት አሰምታው የነበረውን ዕቅድ መሰረዟን በግልጽ ያሳየ ውሳኔ ተደርጎ ተወስዶዋል። ይሁንና፣ ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ የተባለው ለውዝግቦች መፍትሔ የሚያፈላልገው ድርጅት የአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት ጉዳይ ተንታኝ ሴድሪክ ባርንስ እንደሚሉት፣ ኬንያ በዚሁ ግዙፍ እየሆነ በመጣው መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩትን የሶማልያ ስደተኞች ውሎ አድሮ ወደ ሀገራቸው ሊመለሱ የሚችሉበት መንገድ እንዲገኝ ትፈልጋለች።


« አሁን ኬንያ አደረገችው የሚባለው የአቋም ለውጥ በርግጥ ሀቀኛ ለውጥ አይደለም። ብዙ ሳይጤንበት የተሰነዘረው አባባል የመንግሥቱን ፖሊሲ የሚያንፀባርቅ ነው ብየ አላስብም። በኬንያ ባለፉት ሁለት ዓመታት አሸባሪዎች ጥቃት በጣሉባቸው ጊዚያት ሁሉ ተመሳሳይ አስተተያየት መሰንዘሩ የሚታወስ ነው። ኬንያ የዳዳብ መጠለያ ጣቢያን ለመዝጋት ስትዝት ያሁኑ የመጀመሪያ ጊዜዋ አይደለም። ይሁንና፣ አንድ ግልጽ የሆነው ጉዳይ የኬንያ መንግሥት በየጊዜው እየሰፋ በሄደው የዳዳብ መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩትን ስደተኞች ለመመለስ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ መፈለጉ ነው። »

«ዩኤንኤችሲአር»፣ ኬንያ እና ሶማልያ በደረሱት ስምምነት በተዘጋጀው መርሀግብር መሠረት፣ ከዳዳብ መጠለያ ጣቢያ የመጀመሪያዎቹ ስደተኞች በፈቃዳቸው ወደ ሶማልያ ተመልሰዋል። መርሀ ግብሩ እአአ እስከ ሰኔ መጨረሻ ድረስ 10,000 ሶማልያውያን ስደተኞችን በውዴታ የመመለስ ዕቅድ ተይዞዋል። ይሁንና፣ እስካሁን 2,000 ብቻ ናቸው የአዲሱ ፕሮዤ ተጠቃሚ የሆኑት። ለዚህም በስደተኞቹ አኳያ የተስፋፋው ስጋት ተጠያቂ መሆኑን በሀምበርግ ከተማ የሚገኘው በምህፃሩ ጊጋ የሚባለው የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ቲም ግላቪየን አስረድተዋል።»« ችግሩ ብዙዎቹ በዳዳብ የሚኖሩት ስደተኞች የመጡት አሁንም በሶማልያ መንግሥት አንፃር በሚዋጋው አሸባብ ቁጥጥር ስር ካሉ አካባቢዎች መሆኑ ነው። ስለዚህ ብዙዎቹ ወደነዚህ አካባቢዎች መመለስ አይችሉም፣ ቢመለሱ ጠንካራ ጭቆና ሊደርስባቸው ይችል ይሆናል፣ ምክንያቱም ወደ ውጭ ሀገር መሰደዳቸው ራሱ እንደ ከሀዲ ነው የሚያስቆጥራቸው። ስለዚህ እነዚህን ስደተኞች መመለሱ በጣም አዳጋች ነው። » እርግጥ፣ ቲም ግላቪየን እንደሚሉት፣ ሶማልያ ውስጥ አንፃራዊ መረጋጋት የሚታይባቸው አካባቢዎች አሉ፣

«ለምሳሌ ፣ በሰሜን የሀገሪቱ ከፊል የሚገኘው ራሱን ነፃ መንግሥት ብሎ የሚጠራው እና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላገኘው ሶማሊላንድ ወይም ፑንትላንድ ይጠቀሳሉ። በደቡብ ሶማልያም የኬንያ ጦር የተቆጣጠረው አካባቢ ፀጥታም የተረጋጋ ነው። ግን፣ ሁሉም ወደነዚህ አካባቢዎች ሊሄዱ አይችሉም። ስለዚህ፣ በዚያ ሊኖሩ የሚችሉት የነዚህ አካባቢዎች ጎሳዎች አባላት የሆኑ ስደተኞች ብቻ ናቸው። »በፍላጎታቸው መመለስ የሚፈልጉትን የዳዳብ ስደተኞች የመመለሱ እና የማደራጀቱ ሂደት ብዙ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው እና ብዙ ዓመታት ሊፈጅ እንደሚችል የክራይስስ ግሩፕ ተንታኝ ሴድሪክ ባንስ ይገምታሉ። « ኬንያ ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ከዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች፣ ከተመድ ጭምር የምትጠብቀው አንድ ሁነኛ የርዳታ ፓኬት ነው። ከዚህ በተጨማሪ ስደተኞቹን ቀስ በቀስ የመመለሱን ተግባር ለመጀመር ከሶማልያ መንግሥት ጋ ባንድነት ዝግጅት ማድረግ ይኖርባታል። »

በዓለም ትልቁ የዳዳብ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ሁኔታ መለወጥ እንዳለበት የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ እንደሚስማሙ ቲም ግላቪየን አመልክተዋል። « በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ከ20 ዓመታት በላይ በአንድ ቦታ አጉሮ ማስቀመጡ ተቀባይነት የለውም። እርግጥ ስደተኞቹ ይራባሉ ማለት አይደለም፣ ግን፣ ብሩህ የወደፊት ዕድል የላቸውም። አንዳንዶቹ በዚሁ ጣቢያ ውስጥ የተወለዱ ናቸው። እና ዕድሜአችውን ሙሉ በዚሁ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያ ያሳለፉ ናቸው። »የዳዳብ ሁኔታ ከፋ ተሻሻለ አሸባብ በኬንያ ለጣላቸው ጥቃቶችc ዳዳብን ተጠያቂ ማድረግ እንደማይቻል ተንታኞቹ ባርንስ እና ግላቪየን አስታውቀዋል። እርግጥ፣ አንዳንድ ተስፋ የቆረጡ ስደተኞች አሸባብን ሊቀላቀሉ ይችሉ ይሆናል፣ ይሁንና፣ ይላሉ ባንስ እና ግላቪየን፣ የዳዳብ መጠለያ ጣቢያን የአሸባሪዎች መፈልፈያ ብሎ መጥራት አይቻልም።

የሶማልያ ስደተኞችን በፍላጎታቸው ወደተረጋጉ የሶማልያ አካባቢዎች የመመለሱን መርሀግብር ለማሳካት ከተፈለገ ፣ አሸባብን በወታደራዊ ርምጃ ማሸነፍ ይቻላል ከሚለው አስተሳሰብ ተላቆ፣ ከሀያ ዓመት በላይ ውዝግብ ያልተለያትን የአፍሪቃ ቀንድ ሀገር ፖለቲካዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ሁኔታዎችን ለማስተካከሉ ድርጊት ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ጊጋ የሚባለው የጀርመናውያኑ የፖለቲካ ጥናት ተቋም እና የክራይስስ ግሩፕ ተንታኞች ቲም ግላቪየን እና ሴድሪክ ባንስ አሳስበዋል።

አርያም ተክሌ/ዛራ ሽቴፈን

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic