1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኩርዲስታንና የመገንጠል ፖለቲካ

ሰኞ፣ መስከረም 22 2010

ንጉስ ሻዳዲድ ከአርመን  አራን እስከተባለዉ ግዛት የሚገኘዉን  አካባቢ መግዛት ከጀመሩበት ከ951 ጀምሮ የኦስማን ቱርኮች ዓለምን ማስገበር እስከ ጀመሩበት እስከ 1113 ድረስ የራዋዲድ፤ማርዋኒድስ፤ አናዚድስ፤ሐዛራስፒዲስ፤ አዩባዲስ የሚባሉ የኩርድ ሥርወ-መንግስታት ከምሥራቅ አናቶሊያ እስከ ግብፅ የሚገኘዉን ሰፊ ግዛት ገዝተዋል።

https://p.dw.com/p/2l7aX
Irak Erbil Flughafen
ምስል Reuters/A. Lashkari

ኩርዲስታንና የመገንጠል ፖለቲካ

የሰሜን ኢራቅ ግዛት ከባግዳድ ፌደራዊ መስተዳድር ነፃ እንዲወጣ የግዛቲቱ ሕዝብ ባለፈዉ ሳምንት ወስነ።በ92 በመቶ የድጋፍ ድምፅ የፀደቀዉ መገንጠል ኩርዶችን አስፈነደቀ።የኢራቅ አረቦችን አስቆጣ።ሌሎች አረቦችን፤ቱርኮችን እና ፋርሶችን አሳዝኗል፤አስደንግጧልም።የኢራቅ ኩርዶች መንግሥት አከል አስተዳደር እንዲመሰርቱ ዙሪያ-መለስ ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩት ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ የኩርዶችን ዉሳኔ ተቃወሙ። የዩናይትድ ስቴትስ ጥብቅ ወዳጅ እስራኤል ግን ሰባ ዓመት እንደኖረችበት የአረቦችን መገነጣጠል ደገፈች።                            

የሶቭየት ሕብረት የመጨረሻ መሪ ሚኻኤል ጎርቫቾቭ ሐምሌ 1990 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ባደረጉት ንግግር «አዲስ» ያሉት የዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓት አልፋ ወ ኦሜጋ «ትዕግስት» ነዉ ብለዉ ነበር።ጎርቫቾቭ ይሕን ባሉ ባመቱ አዲስ መርሕ የዘረጉላት ልዕለ ኃያል ሐገራቸዉ አንድ የመሆን ትዕግስቷ አብቅቶ እብዙ ስፍራ ተፈረካከሰች።እሁለት ተከፍላ የነበረችዉ ጀርመን ባንፃሩ አንድ ሆነች።አዲሱ የዓለም ፖለቲካዊ ሥርዓትም ተጀመረ።ወይም «ተጀመረ» ተባልን።

Irak IKRG-Referendum- Mevlud Bavemurad
ምስል picture-alliance/abaca/Y. Keles

አሮጌዉን  የዓለም ሥርዓት ከጎርቫቾቭ ጋር ሆነዉ ያፈራረሱት የያኔዉ  ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆርጅ ሔርበርት ዎኮር ቡሽ ጡረታ ከተገለሉ በኋላ እንዳሉት አዲሱን የዓለም ሥርዓት በመገንባቱ ሒደት እንደ እንደ ጀርመን ዳግም መዋሐድ ሁሉ የኢራቅ መወረር አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነበር።

                                     

«የጦር መሳሪያን በመቆጣጠር፤የጀርመንን ዳግም ዉሕደት እና በፋርስ ባሕረ-ሰላጤ የሳዳም ሁሴንን ወረራ በመዋጋት ረገድ በቅርብ በመተባበር የተዋጣለት ሥራ ሠርተናል።የአሜሪካዉ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጀምስ ቤከር እና የሶቬት ሕብረቱ አቻቸዉ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ወዳጅነት መሥርተዉ፤ እኔን ጎሮቫቾቭን በማቀራረባቸዉ ቀዝቃዛዉ ጦርነት ማንም ባላሰበዉ ሰላማዊ መንገድ እንዲያበቃ አድርገዋል።»

የቀዝቃዛዉ ጦርነት ፍፃሜ ከሶቬት ሕብረት ሌላ ይጎዝላቪን ፈረካክሷል።እስያ፤ አፍሪቃ እና ደቡብ አሜሪካ ዉስጥ እስከዚያ ዘመን ድረስ ለፖለቲካዊ ሥርዓት ለዉጥ ይፋለሙ የነበሩ ሸማቂዎችን አንድም ለሽንፈት አለያም ለቤተ-መንግሥት አብቅቷል።

እንደ ጀርመኖች ሁሉ የመኖች ሲዋሐዱ፤ ኮሪያዎች ዛሬም እንደ ቀዝቃዛዉ ጦርነት ዘመን ለዉጊያ ይጋበዛሉ።በቅዝቃዛዉ ጦርነት ወቅት ለግዛት ነፃነት ይዋጉ የነበሩ  ኃይላት አንድም ጠፍተዋል አለያም በየግዛቱ ትናንሽ መንግሥታትን መሥርተዋል።ዲሊ፤ አስመራ፤በርበራ ላይ ፕሪሽቲና ላይ አዳዲስ መንግሥታት የመሠረቱት ኃይላት እና ደጋፊዎቻቸዉ ከነፃነት በፊት ለየዝባቸዉ የገቡትን ቃል እና ተስፋን ገቢር ማድረግ አለማድርጋቸዉ አነጋግሮ ሳየበቃ፤ ጁባ ላይ ሌላ አዲስ መንግስት ተመሠረተ።

አዳዲስ መንግሥታት የመሠረቱት አብዛኞቹ ኃይላት የየሐገራቸዉን ሕዝብ የስደት፤ጦርነት፤የረሐብ ችግር አብነት የማድረጋቸዉ ምክንያት በቅጡ ተተንትኖ አላባቃም።ሰሞኑን ከኢርቤል እስከ ባርሴሎና የታየና የሚታየዉ ግን አዳዲስ ቤተ-መንግሥት ለማቆም የሚፈልጉት ኃይላትም፤ ደጋፊዎቻቸዉም  ብዙ መሆናቸዉን ጠቋሚ ነዉ።ፋላሕ ሙስጠፋ በኪር ማዕረጋቸዉ የኩርዲስታን ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ይላል።ኩርዲስታን የሚባል መንግሥት ግን ዓለም ምናልባት ምዕራቦች ሲደግፉት እንጂ  እንጂ በሕግ አታዉቅም።

«ኩርዲስታን ነፃ መዉጣቷ አይቀርም» አሉ ኃያሉ ዓለም የሚደግፈዉ ግን ሕጋዊ እዉቅና የነፈገዉ የኩርዲስታን መንግሥት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር በቀደም።«እኒያ ከዚሕ ቀደም ነፃ የወጡት፤ እኒያ ከኛ በፊት መንግስት የመሠረቱት የእኛን መንግስትነት የሚነፍጉን ለምድን ነዉ።ነፃነት ለመጠየቅ እኛ የመጀመሪያዎቹ አይደለንም።የመጨረሻዎቹም አንሆንም።እንቀዳጃለን። ኩርዲስታን በዚሕ በግጭት ጦርነት በሚታመስ ምድር የዴሞክራሲ አንፀባራቂ አብነት ትሆናለች።»

Irak Unabhängigkeitsreferendum der Kurden
ምስል picture-alliance/dpa/D. Vinogradov

ንጉስ ሻዳዲድ ከአርመን  አራን እስከተባለዉ ግዛት የሚገኘዉን  አካባቢ መግዛት ከጀመሩበት ከ951 ጀምሮ የኦስማን ቱርኮች ዓለምን ማስገበር እስከ ጀመሩበት እስከ 1113 ድረስ የራዋዲድ፤ማርዋኒድስ፤ አናዚድስ፤ሐዛራስፒዲስ፤ አዩባዲስ የሚባሉ የኩርድ ሥርወ-መንግስታት ከምሥራቅ አናቶሊያ እስከ ግብፅ የሚገኘዉን ሰፊ ግዛት ገዝተዋል።

ጠንካራዉ የቱርክ ሥርወ መንግሥት ከፈረሰ በኃላ አካባቢዉን የተቆጣጠሩት የብሪታንያና የፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች አካባቢዉን በየሐገር ሲሸነሽኑ ኩርዶችንም የዛሬዎቹ ቱርክ፤ ኢራን፤ኢራቅ እና ሶሪያ ተከፋፈሎቸዉ።የአዉሮጳ ቅኝ ገዢዎች አካባቢዉን ለቅቀዉ ሲወጡ በየሐገሩ የተከፋፈሉት ኩርዶች የነፃነት ጥያቄ እና ትግል ቀጠለ።

በጠላትነት የሚፈላለጉት የአራቱ ሐገራት መንግሥታትም አንዳቸዉ ሌላኛዉን ለማዳከም አንዳቸዉ የሌላዉን ኩርድ የነፀነት ኃይል ያስታጥቅ፤ያደራጅም ነበር።የቱርክ ኩርድ ደፈጣ ተዋጊዎች ዋና ደጋፊ ሶሪያ ነበረች።የሶሪያ ኩርድ ደግሞ ቱርክ።የኢራቅ ኩርድ ነፃአዉጪ ድርጅቶችን የምታስታጥቅ እና የምታደራጅ ኢራን ነበረች።የኢራንን ኢራቅ።

በ1991 ዩናይትድ ስቴትስ መራሹ ጦር ኢራቅን መዉረሩ የአካባቢዉን የእስከዚያ ዘመን የኃይል አሰላለፍ ያናጋ፤ ከሁሉም በላይ የኩርዶችን አወጋገን ያመሰቃቀለ ነበር።ወረራዉ ለኢራን ኩርዶች የባግዳድ ኃያል ደጋፊያቸዉን አቅም ሲያሽመደምድ፤ ለኢራቅ ኩርዶች የአዲስ ድጋፍ በር ከፈተላቸዉ።

Stimmenzählen bei Stromausfall
ምስል AP

ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ ለኢራቅ ኩርዶች ሙሉ ድጋፍ ይሰጡ ገቡ።የኢራቅ የጦር ጄቶች የኩርድ አማፂያን በሸመቁበት በሰሜናዊ ኢራቅ አየር ላይ እንዳይበሩ አገዱ።ጀላል ጠላባኒ እና መስዑድ ባርዛኒ የሚመሯቸዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድናት ሰሜናዊ ኢራቅ ኢርቤል ላይ ጠንካራ ጦር ኃይል፤ሙሉ የመንግስት መዋቅር እና ልዩ ባንዲራ ያለዉ መንግስት አከል አስተዳደር መሠረቱ።

በ2003 ፕሬዝደንት ጆርጅ ደብሊዉ ቡሽ ያዘመቱት ጦር ኢራቅን ሲወርር የኩርድ አማፂያን የቅርብ ተባባሪ፤የመረጃ ምንጭ እና ዋና ደጋፊዎቹ ነበሩ።ኢራቅ ከታላቅ ሐገርነት ወደ አሸባሪዎች መናኸሪነት ስትለወጥ ጀላል ጠለባኒ የመለዋ ኢራቅ፤መስዑድ ባርዛኒ ደግሞ መንግሥት ያልሆነዉ የኩርዲስታን መንግሥት ፕሬዝደንት ሆኑ።

የኩርድ ፖለቲከኞች ሁለት ቤተ-መንግሥት እንዲያስተዳድሩ የፈቀዱ፤ያደራጁ እና አስማማን ያሉት የዋሽግተን መሪዎች እና የኢራቅ ተባባሪዎቻቸዉ ናቸዉ።በ2014 ዩናይትድ ስቴትስ እና የዩናይትድ ስቴትሷ ኢራቅ ISIS በተባለዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ላይ ጦርነት ሲያዉጁ ምዕራባዉያን መንግሥታት የመንግሥትነት እዉቅና ለነፈጉት ለኢርቤል መንግሥት ከባግዳድ እኩል የጦር መሳሪያ ያስታጥቁ፤ ጦሩን ያሰለጥኑ፤ ያደራጁትም ገቡ።

ሽማግሌዉ የኩርድ ፖለቲከኛ ጀላል ጠላባኒ ከሳዳም ሁሴን ቤተ-መንግስት በጡረታ ሲገለሉ፤ፔሽ ሜርጋ የተባለዉ የኩርድ ጦር ኪርኩን የመሳሰሉ የዳጅ ቋት ከተሞችን ከISIS እጅ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩ ሲረጋገጥ፤የኩርዶችን ነፃ መዉጣት አጥብቃ የምትቃወመዉ ቱርክ ከምዕራብ አዉሮጶች ጋር ስትነታረክ መስዑድ ባርዛኒ የዕድሜልክ ሕልማቸዉን እዉን ለማድረግ ወሰኑ።

እርግጥ ነዉ ፕሬዝደንት የሚለዉ ክብር፤ማዕረግ ሥልጣንም አልጎደለባቸዉም።የኩርዶችን ባንዲራ እያዉለበለቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ለማድረግ ግን አንድ ነገር ይቀራቸዋል።ነፃ መንግሥት።ጊዜዉ ደግሞ አሁን ነዉ።ከባግዳድ ጋር የተፈራረሙትን ዉል አፈረሱ።ሕዝበ ዉሳኔ ጠሩ።ለምን ሲባሉ---«ከልጅነቴ ጀምሮ የተዋጋሁት ለነፃነት ነዉ።» መለሱ አንጋፋዉ ደፈጣ ተዋጊ።

                              

«የራስን ዕድል በራስ መወሰን በጣም የታወቀ ዓለም አቀፍ መብት እና ሕግ ነዉ።ሕዝበ ዉሳኔዉን እንዲዘገይ የጠየቁንን ሐገራት ሌላ ምርጫ ትሰጡናላችሁ ብለን ጠየቀናቸዉ ነበር።እስካሁን ምንም አላቀረቡልንም።ሥለዚሕ ሕዝበ ዉሳኔዉን እናደርጋለን።ጠመንጃ ስታጠቅ የአስራ-ስድት ዓመት ልጅ ነበርኩ።ለኩርዶች ነፃነት ስዋጋ እዚሕ ድርሻለሁ።አሁንም ለነፃነት ሕይወቴን ለመስጠት ዝግጁ ነኝ።»

የባርዛኒን ፍላጎት ሕዝባቸዉ በዘጠና ሁለት ከመቶ ድምፅ አፀደቀላቸዉ።ጨፈረ፤ቦረቀም።

                                       

የኢራቅ መንግስት የኩርዶችን ዉሳኔ አጣጥሎ ነቅፎታል።የጠቅላይ ሚንስትር ጀአፈር አል አባዲን መንግሥት ይበልጥ ያሳሰበዉ ግን ከሕዝበ ዉሳኔዉ ዉጤት ይልቅ በነዳጅ የበለፀገችዉ፤ከኩርዶች እኩል ወይም ይበልጥ አረቦች የሚኖርባት የኪርኩክ ከተማ በኩርዲስታን ቁጥጥር ስር መሆንዋ ነዉ።አባዲ ኪርኩክን ከኩርዶች እጅ የሚያስለቅቅ ጦር ወደ አካባቢዉ እንዲያዘምቱ የኢራቅ ምክር ቤት ሙሉ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል።

Türkei Präsident Tayyip Erdogan im Parlament in Ankara
ምስል Reuters/Yasin Bulbul/Presidential Palace

አባዲ  የምክር ቤታቸዉን ዉሳኔ አክብረዉ ጦር ያዘምቱ ይሆናል።በቅጡ ያልደረጀዉ ኢራቅ ጦር ግን ጠንካራዉን የኩርዲስታን ጦር ሊቋቋመዉ እንደማይችል ምክር ቤቱም፤አባዲም ጠንቅቀዉ ያዉቃታል።ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ሌሎች የአረብ ሐገራትም የኩርዲስታንን መገንጠል ተቃዉመዉታል።

እንደ ኢራቅ ሁሉ የኩርድ ሸማቂዎች ለነፃነት የሚፋለሙባት ቱርክ ዉሳኔዉን ገቢር ሊሆን የማይችል በማለት አዉግዛዋለች።የቱርኩ ፕሬዝደንት ጠይብ ኤርዶኸን እንዳሉት ደግሞ የኢራቅ ኩርዶች ሕዝበ ዉሳኔዉን የጠሩት እስራኤልን ለማስደሰት ነዉ።

                                      

ኢራንም ሕዝበ ዉሳኔዉን በጠንካራ ቃላት ቀደምትነት ካወገዙት ሐገራት አንዷ ናት።የአረቦች እና የፋርሶች ቀንደኛ ጠላት የምትባለዉ እስራኤል ሕዝበ ዉሳኔዉን በመደገፍ ከዓለም ብቸኛዋ ሐገር ናት።ለኢራቅ ኩርዶች ከ1990ዎቹ ጀምሮ ሁለንተናዊ ድጋፍ የሰጡ እና የሚሰጡት ዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋም ሕዝበ ዉሳኔዉን አልደገፉትም።ይሁንና መስዑድ ባርዛኒ እንዳሉት ምዕራባዉያኑ መንግሥታት ሕዝበ ዉሳኔዉ አዘግዩት እንጂ አስቀሩት ወይም የኢራቅ አንድነት ይከበር አላሉም።

የኩርድ ሕዝብ 35 ሚሊዮን ይገመታል።አብዛኛዉ ሱኒ ሙስሊም ነዉ።ኢራቅ፤ቱርክ፤ ኢራን እና ሶሪያ ተበታትነዋል።የኢራቆቹ፤  ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፋላሕ ሙስጠፋ በኪር እንዳሉት ግፋ ቢል ባንድ ዓመት እድሜ ነፃነት ያዉጃሉ።ቀጣዩ ማን ይሆን የቱርክ፤የሶሪያ፤የኢራን ኩርድ ወይስ ካታሎኒያ፤ ወይስ-----

ነጋሽ መሀመድ

አርያም ተክሌ