ከጉም ውሃ እንደወተት ለማለብ!፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 25.08.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

ከጉም ውሃ እንደወተት ለማለብ!፣

ከቶ እንዴት ተደርጎ!በብዙ መቶ ሊትር የሚለካ ፤ ጥራት ያለው የሚጠጣ ውሃ ከጉም ይቀዳል ሲባል፤ ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ነው የሚመስለው።

default

እርግጥ ነው ፤ ስለተፈጥሮ ለተመራመሩ፤ ሳይንስን መመኪያ ላደረጉ ፤ በቀላል ዘዴ እንዴት አድርጎ በገፍ ከደመና ውሃውን ማግኘት ይቻላል የሚለው ጥያቄ ያነጋግራቸው ካልሆነ በስተቀር፤ በመሠረቱ ፣ ውሃን ከጉም የማግኘቱ ጉዳይ ብርቅ አይሆንባቸውም።

እ ጎ አ ከ 1998 ዓ ም አንስቶ በ የ 3 ዓመት አንድ ጊዜ፣ ውሃ ከጉምና ጤዛ ሊጠራቀም በሚችልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረም ሆነ በዚህ ርእስ ዙሪያ የሚመክር ዓለም አቀፍ ጉባዔ ይካሄዳል። በ 1998 ፤ በቫንኩቨር፣ ከዚያም በሴንት ጆንስ፣ ንው ፋውንድላንድ፤ ካናዳ ፣ በ 2004 ኬፕታውን ፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ ከዚያም በ 2007 ላ ሴሬና ፣ ቺሌ ከተመከረ በኋላ፤ የዘንድሮው ጉባዔ ለመጀመሪያ ጊዜ ጀርመን ውስጥ ሙዑንስተር በተባለችው ሰሜናዊ የጀርመን ከተማ ከ ሐምሌ 18-23 ,2002 ዓ ም ተከናውኗል። በሙዑንስተሩ ጉባዔ፣ ከ 30 በላይ ከሚሆኑ አገሮች የተውጣጡ፤ 140 ያህል ጠበብት ነበሩ ለ 6 ቀናት መክረው የተለያዩት።

የተባበሩት መንግሥታት ፣ የትምህርት፤ የሳይንስና የባህል ድርጅት(ዩኔስኮ)በተለይ ጎርጎሪዮሳዊው 2003 ዓ ም፣ የዓለም ህዝብ፤ ንጹህ የሚጠጣ ውሃ አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማግኘት ተገቢ ጥረት የሚያደርግብት መታሰቢያ ዘመን እንዲሆን ካወጀ ወዲህ ደግሞ፤ ንፁህ የሚጠጣ ወሃ የማግኘቱ ጥያቄ የላቀ ዐቢይ ትኩረት ሳይደረግበት አልቀረም።

ከጉም ውሃ ማግኘት የሚለው ሃሳብም ሆነ መፈክር ፣በዓለም ዙሪያ በተለይ ምድረበዳ በሚገንባቸው አገሮች ትልቅ ትርጉንም ነው የሚሰጠው። ከበርሊን የቴክኒክ ዩኒቨርስቲ፣ የወሃ ልማት ጉዳይ ሊቅ ፣ፕሮፌሰር ሃይኮ ዲስተል፤

«የውሃ አዝመራ መሰብሰብ ሲባል፤ አነስተኛ በሆኑ የተለያዩ እርምጃዎች ፤ ጥረቶች የሚገኝ መሆኑን ነው የምንገነዘብ። ከመስኖ ይልቅ ይህ በጣም አድካሚ ተግባር መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። »

ከማይጨበጠው ደመና፤ ሆኖም አልፎ -አልፎ ዝቅ በማለት መሬትንና ባህርን ከሚሸፍነው ጉም እንዴት ነው ውሃ እያጠመዱ ጠብታ አጠራቅሞ የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት የሚቻለው?

የናሚብ በረሃ በሚገኝባት በናሚቢያ የሠሩት የአፈርና ቋጥኝ ተመራማሪ ኒና ግሮንኮስኪ፤ ስለአንድ የሙከራ ጣቢያ ተግባር ሲያስረዱ--

«ይህ 48 እስኩዬር ሜትር የጉም ማጥመጃ መረብ ነው። 8 ሜትር ርዝማኔ ባለው፤ (ርዝማኔው በቂ ነው)አንድ የቀድሞ የስልክ ዓምድ፤ ማጠራቀሚያዎቹ ጥቋቁር የፕላስቲክ ከረጢቶች ተሠቅለዋል። ለጤና ጠንቀኞች አይደሉም። ፕላስቲኮቹ ከረጢቶች፤ያን ያህል ዋጋ የማይጠይቁ፤ በቀላሉ የሚገኙ ናቸው። ፕላስቲኩ ከረጢት ረከስ ያለ ዋጋ እንዲኖረው ታስቦም ነው የተሠራው።»

ለማንኛውም ሙከራው መሣካቱ የተገለጠ ሲሆን፤ በያንዳንዱ እስኩዬር ሜትር የፕላስቲክ መረብ ፣ በዓመት ፤ በአማካይ በቀን አንድ ሊትር ውሃ ይገኝበታል። በያመቱ በአንድ እስኩዬር ሜትር የምድረበዳ መሬት 20 ሚሊ-ሊትር ብቻ ነው ዝናም የሚጥለው።

የጀርመን የውሃ ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት ባልደረባ ኤርንስት ፍሮስት እንደሚሉት ከሆነ፤ ጉም በሚያይልባቸው ወቅቶች፤ በተጠቀሰው ዓይነት የፕላስቲክ መረብ ፤ በቀን 170 ሊትር ያህል ጥራት ያለው ንፁህ የሚጠጣ ወሃ ማጠራቀም ይቻላል። ይህ ደግሞ ለአንድ ቤተሰብ ፍጆታ በቂ ነው። ታዲያ ከዚህ ጋር ተያይዞ ፣ ምድረበዳ ቀመስ በሆኑ አካባቢዎች፤ በገጠር የሚኖሩ አርሶ አድሮችም ሆኑ አርብቶ አደሮች የሆኑ ቤተሰቦች ከጉም እንዴት ውሃ ማጠራቀም እንደሚችሉ ትምህርት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የሚያጠራጥር አይደለም። ከጉም ውሃ ማለብ የሚቻልበት እርምጃ፤ አፍሪቃ፤ ላቲን አሜሪካም ሆነ በሌሎች ምድረበዳ በሚገኝባቸው አካባቢዎችና ፤ እስፓኝንም በመሳሰሉ አገሮች ሰፊ ትኩረት ማግኘቱ የማይቀር ነው።

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ