ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ የግንባታ መሣሪያዎች ቁጥጥር | ኤኮኖሚ | DW | 28.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ የግንባታ መሣሪያዎች ቁጥጥር

ለግንባታ ሥራ ተብለዉ ከቀረጥ ነጻ ከዉጭ ከሚገቡ የግንባታ መሳሪያዎች አንዳንዶቹ ሥራ ላይ ሳይዉሉ በሕገ-ወጥመንገድ ወደ ለገበያ እንደሚቀርቡ ይነገራል። የኢትዮጵያ የኮንሥትራክሽን ሚኒስቴር ችግሩን ለመፍታት ደንብ  እያዘጋጀሁ ነዉ ብሏል። በሀገሪቱ የመጀመርያ ነዉ የተባለ የኮንስትራክሽን ኦዲት መቋቋሙንም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ገልጿል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:43

የግንባታ መሣሪያዎች ቁጥጥር

በኢትዮጵያ የግንባታዉን ኢንዱስትሪ ለማሳደግ  በሚል  በግንባታ ሥራ ለተሰማሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከቀረጥ ነጻ የግንባታ እቃዎችን ወደ ሀገር ዉስጥ ማስገባት የተፈቀደ ነዉ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች እድሉን በመጠቀም የሚያስገቧቸዉን የግንባታ መሳሪያዎችና ተሽከርካሪዎች በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ለገበያ እንደሚያቀርቡ አንዳንድ አስተያየት ሰጭዎች ይገልጻሉ። ስማቸዉ እንዳይጠቀስ የፈለጉ  አንድ አስተያት ሰጭ እንደሚሉት በግንባታዉን ዘርፍ የተሰማሩ  አንዳንድ ባለሀብቶች ከቀረጥ ነጻ የሚያመጧቸዉን እቃዎች ወደ ገበያ በማስገባታቸዉ በሕጋዊ መንገድ ቀረጥ ከፍለዉ የሚሰሩትን እየጎዳ ነዉ።ጉዳዩን በተመለከተ ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸዉ በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የኮንስትራክሽን ኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብዱራህማን ጀማል ችግሩ ሊኖር እንደሚችል ገልጸዉ ፤ በሚንስቴር መስሪያቤቱ አዲስ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ምዝገባና ቁጥጥር ደንብ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
ከ 19 ዓመት በፊት በነበረ አዋጅና ደንብ አሁን ካሉ የግንባታ መሳሪያወችና ተሽከርካሪወች ነባራዊ ሁኔታ ያልተጣጣመ ስለነበር ለቁጥጥር አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።
ስለሆነም ብዙዎቹ የግንባታ መሳሪያዎች ምዝገባ ሳይደረግባቸዉ ወደ ግንባታ ይሰማሩ ስለነበር በሕገ ወጥ መንገድ የግንባታ መሳሪዎቹን ወደ ገበያ ለማስገባት በር እንደከፈተ ገልጸዉ  አሁን የሚወጣዉ ደንብ ግን ችግሩን እንደሚመልሰዉ አብራርተዋል።የኮንስትራክሽን እቃዎችን በአግባቡ መዝግቦ ለታለመላቸዉ ዓላማ መዋሉን ለመቆጣጠርም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ  የኮንስትራክሽን ኦዲት ክፍል መቋቋሙን ገልጸዋል። በዚህ ክፍል አማካኝነትም የሚሰሩ ግንባታዎችን ከንድፍ ሥራ ጀምሮ በመቆጣጠርና ክትትል በማድረግ ለግንባታዉ የሚያስፈልገዉን የግብአት መጠንና የግንባታ እቃዎች በባለሙያ እንዲወሰን በማድረግ ከፍጆታ በላይ የሆኑ የግንባታ መሣሪያወች  ከቀረጥ ነጻ እንዳይገቡ መቆጣጠር ይቻላል ሲሉ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።ባለሃብቶቹ ከሕግና ከደንቡ ዉጭ መንግስት የሰጣቸዉን ማበረታቻ በአግባቡ የማይጠቀሙና እድሉን ላልተገባ ጥቅም የሚያዉሉት ከሆነ  በሕግ ሊጠየቁ እንደሚችሉ አስረድተዋል።

ፀሐይ ጫኔ
አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic