ከስፖርቱ ዓለም | ስፖርት | DW | 18.03.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ከስፖርቱ ዓለም

ባለፈው ሰንበት ከተካሄዱት የተለያዩ ዓለምአቀፍ የስፖርት ውድድሮች መካከል የባርሤሎናና የሮማ ማራቶን ሩጫዎችም ይገኙበት ነበር።

በዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የሮማ ማራቶን ሩጫ ጌታቸው ተርፋ በሁለት ሰዓት ከሰባት ደቂቃ ከ 56 ሤኮንድ ጊዜ ሲያሸንፍ ይህም ሮማ ውስጥ እስካሁን የተሮጠው ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት መሆኑ ነው። በዚሁ ሩጫ ግርማይ ብርሃኑ ሁለተኛ ሲወጣ ኬንያዊው ስቴፈን ቼምላኒይ ሶሥተኛ እንዲሁም ሃይሌ ገመዳ አራተኛ ሆኗል።

በሴቶች ኬንያዊቱ ሄለና ኪሮፕ በሁለት ሰዓት ከ 24 ደቂቃ ከ 40 ሤኮንድ ስታሸንፍ ገነት ካሣ ሁለተኛ ሆናለች። የቱርኳ ተወዳዳሪ ሱልጣን ሃይዳር ሶሥተኛ ስትሆን አራተኛና አምሥተኛ የወጡት የኢትዮጵያ ሯጮች አሹ ቃሢምና ዓለም ፍቅሬ ናቸው። የባርሤሎናው ማራቶንም ለኢትዮጵያ አትሌቶች ይበልጥ የሰመረ ነበር። በወንዶች ገዛኸን አበራ ሲያሸንፍ በሴቶች ደግሞ ለምለም በርሄ ቀደምቷ ሆናለች።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊቱ የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ጥሩነሽ ዲባባ በመጨው ወር የለንደን ማራቶን ለመሳተፍ የነበራትን ዕቅድ መሰረዙ ግድ ሆኖባታል። ጥሩነሽ ከመጀመሪያ የማራቶን ሩጫዋ ወደ ኋላ ለማሸግሸግ የተገደደችው በሥልጠና ላይ ባጋጠማት የእግር ጉዳት ነው። አትሌቷ ራሷ ለለንደኑ ማራቶን በምታደርገው ዝግጅት ርቀት መጨመሯ የቀድሞ ቁስሏን መልሶ መቀስቀሱን አስረድታለች። ጥሩነሽ በፍጥነት አገግማ ወደ ውድድሩ መድረክ እንድትመለስ ጽኑ ምኞታችን ነው።

ኢትዮጵያን ካነሣን በአፍሪቃ እግር ኳስ ኮንፌደሬሺን የሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ቀደምቱ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ትናንት አዲስ አበባ ላይ የማሊ ተጋጣሚውን ጆሊባን 2-0 በመርታት ለመልሱ ግጥሚያ ጥሩ ሁኔታን ለማመቻቸት በቅቷል። ጎሎቹን ያስቆጠሩት ዮናታን ብርሃኔና ፍጹም ገ/ማርያም ነበሩ። የመልሱ ግጥሚያ ባማኮ ላይ የሚካሄደው ከመጋቢት 27 እስከ 29 ባለው ሰንበት ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ተከታዩ ዙር የማለፍ ከፍተኛ ዕድል ያለው ይመስላል።

በካፍ ኮንፌደሬሺን ዋንጫ ውድድር የሚሳተፈው ደደቢት በአንጻሩ ካርቱም ላይ በአል-አህሊ-ሻንዲይ 1-0 ተሸንፏል። ለሱዳኑ ክለብ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ሞሐመድ ባሺር ነበር። የኢትዮጵያው ክለብ በውድድሩ እንዲከርም በመልሱ ጨዋታ ውጤቱን የመገልበጥ ብርቱ ትግል ነው የሚጠብቀው። ይህ በጊዜው የሚታይ ሲሆን በአህጉራዊው ውድድር የተሳተፉት የሁለቱ ክለቦች የብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ለቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ግጥሚያ ለሚደረግ ዝግጅት ዛሬ ቀሪውን ቡድን ይቀላቀላሉ። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለ 2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከቦትሱዋና የሚጋጠመው መጋቢት 15 ቀን ነው።

በአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች ውድድር ሻምፒዮናው ሊጠቃለል እየተቃረበ ሳለ ከጀርመን እስከ እንግሊዝና ከእንግሊዝ እስከ ስፓኝ መሪዎቹ ክለቦች በቀላሉ የማይደረስባቸው እየሆኑ በመሄድ ላይ ናቸው። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ባርሤሎና ትናንት ራዮ ቫሌካኖን 3-1 በመርታት በ 13 ነጥቦች ልዩነት መምራቱን ሲቀጥል ኮከቡ ሊዮኔል ሜሢም በተከታታይ ለ 18ኛ ግጥሚያው ጎል ማስቆጠሩ ሰምሮለታል። ያለፉት ዓመታት የዓለም ድንቅ ተጫዋች ሜሢ ትናንት ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች የዘንድሮ የፕሪሜራ ዲቪዚዮን ጎሎቹን ድርሻ ወደ 42 ከፍ ለማድረግ ችሏል።

ባርሣ ውድድሩ ሊፈጸም 10 ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ በ 74 ነጥቦች በአንደኝነት የሚመራ ሲሆን ማዮርካን 5-2 የረታው ሬያል ማድረድ በ 61 ነጥቦች ሁለተኛ ነው። የከተማ ተፎካካሪው አትሌቲኮ ማድረድ ደግሞ ኦሣሱናን 2-0 በመርታት በ 60 ነጥቦች በሶሥተኝነት ይከተላል። ሁለቱ ክለቦች በቀሪው የውድድር ጊዜ ባርሤሎና ላይ ለመድረስ መቻላቸውን ማመኑ በጣሙን የሚያዳግት ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግም ቢሆን ቀደምቱ ማንቼስተር ዩናይትድ በተለይ ከሰንበቱ ግጥሚያዎች ወዲህ ለተፎካካሪዎቹ ይብሱን የራቀ ሆኗል። ማኒዩ ሪዲንግን 1-0 በማሸነፍ አመራሩን ወደ 15 ነጥቦች ሲያሰፋ ለዚህም የረዳው የማንቼስተር ሢቲይ በኤቨርተን 2-0 መረታት ነው። ለማንቼስተር ዩናይትድ ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው ዌይን ሩኒይ ነበር። ቼልሢይም ዌስት-ሃም-ዩናይትድን 2-0 በማሸነፍ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ለማለት በቅቷል። ቶተንሃም ሆትስፐር በፉልሃም 1-0 በመረታቱ ከሶሥት ወደ አራት ሲያቆለቁል አርሰናል አምሥተኛ ነው፤ ኤቨርተንና ሊቨርፑል ቀጠል አድርገው ይከተላሉ።

የጀርመን ቡንደስሊጋ

በጀርመን ቡንደስሊጋ ውድድር ሻምፒዮናው ዘንድሮ ከወዲሁ አልቆለታል ቢባል ብዙም ማጋነን አይሆንም። ቀደምቱ ባየርን ሙንሺን በሰንበቱ ግጥሚያ ሌቨርኩዝንን 2-1 ሲረታ ውድድሩ ሊያበቃ ስምንት ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ ሊጋውን በሃያ ነጥቦች ልዩነት ይመራል። ልዩ ተዓመር ካልተፈጠረ በስተቀር ጨርሶ የሚደረስበት አይደለም። ባየርን በመሠረቱ በመጪው ሣምንት ግጥሚያው ካሸነፈና ሁለተኛው ዶርትሙንድ በእኩል ለእኩል ውጤት ከተወሰነ ቀድሞ ሻምፒዮንነቱን ሊያረጋግጥ ይችላል።

እንግዲህ በጀርመን ቡንደስሊጋ ውስጥ እንደ እንግሊዝ ወይም እንደ ስፓኝ ሁሉ ፉክክሩ ይበልጡን ለአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋና ለአውሮፓ ሊግ ውድድሮች ተሳትፎ በመብቃቱ ላይ የሚያተኩር ነው የሚሆነው። በነገራችን ላይ ባየርን በቀሪዎቹ ስምንት ግጥሚያዎች በሙሉ ቢሸነፍ እንኳ ከእንግዲህ ቢቀር ሶሥተኛውን ቦታ የሚነጥቀው የለም። ይህም የዘንድሮ ጥንካሬው ምልክት ነው።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ለሣምንታት ድክመት የታየበት ናፖሊ በስድሥት ግጥሚያዎች ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ለድል በመብቃት ሰንበቱን ትንሣዔ አድርጓል። ቡድኑ አታላንታን 3-2 ሲያሸንፍ ሁለቱን ግቦች ያስቆጠረውም ሊጋውን በጎል አግቢነት ሃያ አስቆጥሮ የሚመራው ኤዲንሶን ካባኒ ነበር። መሪው ጁቬንቱስ ቦሎኛን 2-0 ሲረታ ናፖሊን በዘጠኝ ነጥቦች ልዩነት አስከትሎ በአንደኝነቱ እንደቀጠለ ነው። ኤ ሢ ሚላን ፓሌርሞን 2-0 በማሸነፍ ሶሥተኛ ሲሆን ፊዮሬንቲና ደግሞ በአራተኝነት ይከተላል።

በፈረንሣይ አንደኛ ዲቪዚዮን ሰንበቱ ከቀደምቱ ሰባት ክለቦች አንዱም ለድል ያልበቃበት ሆኖ ነው ያለፈው። እንዲያም ሆኖ ግን ከሣንት-ኤቲየን 2-2 የተለያየው ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን አመራሩን ማስፋቱ ተሳክቶለታል። አሁን በአምሥት ነጥቦች ልዩነት እየመራ ነው።ሁለተኛው ኦላምፒክ ሊዮን በባስቲያ 4-1 ሲሸነፍ ሶሥተኛው ማርሢይም ከአጃቺዮ 0-0 ተለያይቷል። የፈረንሣይ ሻምፒዮና ብርቱ ፉክክር የሰፈነበት ሆኖ የሚቀጥል ነው የሚመስለው። ስለዚህም የፓሪሱ ክለብ አመራሩን እንዳይነጠቅ ብዙ መጠንቀቅ ይኖርበታል።

በኔዘርላንድ የክብር ዲቪዚዮን አያክስ አምስተርዳም አልክማርን 3-2 ሲያሸንፍ በ 57 ነጥቦች አመራሩን ይዞ እንደቀጠለ ነው። ለአያክስ ከሶሥት ሁለቱን ጎሎች ያስቆጠረው ሢም-ዴ-ዮንግ ነበር። የኔዘርላንድ ሻምፒዮና ሊጠቃለል ሰባት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ለዋንጫ የሚደረገው ፉክክር እስከመጨረሻው መዝለቁ የማይቀር ነው የሚመስለው። አይንድሆፈንና ፋየኖርድ አያክስን በአንዲት ነጥብ ብቻ ዝቅ ብለው በ 56 ነጥቦች የሚከተሉ ሲሆን አራተኛው አርንሃይምም ከአመራሩ የሚርቀው በሶሥት ነጥቦች ብቻ ነው።

እናም ሻምፒዮናው በመጨረሻ የሚለይለት ከነዚህ አራት ክለቦች በአንዱ የበላይነት ይሆናል። በፖርቱጋል ፕሪሜራ ዲቪዚዮን በአንጻሩ ሻምፒዮናው የሁለት ክለቦች ፉክክር የሰፈነበት ሆኖ እንደቀጠለ ነው። የሊዝበኑ ቀደምት ክለብ ቤንፊካ ጊማሬሽን 4-0 በመቅጣት የበላይነቱን ሲያስጠብቅ የቅርብ ተፎካካሪው ፖርቶ ከማሪቲሞ 1-1 በመለያየት ጠቃሚ ነጥቦችን አጥቷል። ቤንፊካ በ 61 ነጥቦች ሊጋውን የሚመራ ሲሆን ፖርቶ በ 57 ያከተላል፤ በ 43 ነጥቦች ሶሥተኛው ብራጋ ነው።

የአውቶሞቢል እሽቅድድም

የዘንድሮው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም የውድድር ወቅት ትናንት አውስትራሊያ-ሜልበርን ላይ ሲጀመር አሸናፊውም የፊንላንዱ ተወላጅ ኪሚ ራይኮነን ሆኗል። ለ 33 ዓመቱ የሎቱስ ዘዋሪ ድሉ ሃያኛው የግራን-ፕሪ ድል ሲሆን እሽቅድድሙን ያሸነፈው ያለፈውን ዓመት ግንባር ቀደም ዘዋሪዎች ከኋላው በማስቀረት ነው። የስፓኙ ፌርናንዶ አሎንሶ ሁለተኛ ሲወጣ ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትልም ከፊተኛው ተርታ ቢጀምርም ቅሉ በሶሥተኝነት ተወስኖ ቀርቷል።

በተረፈ የብራዚሉ ፌሊፔ ማሣ አራተኛ፣ የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን አምሥተኛ፤ እንዲሁም የአውስትራሊያው ዘዋሪ ማርክ ዌበር ስድሥተኛ በመሆን ነበር እሽቅድድሙን የፈጸሙት። ከትናንቱ እሽቅድድም በኋላ ራይኮነን በ 25 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን አሎንሶና ፌትል 18 እና 15 ነጥቦች ይዘው ይከተላሉ። ሁለተኛው እሽቅድድም በፊታችን ሰንበት ማሌይዚያ-ሤፓንግ ላይ ይካሄዳል።

Rafael Nadal of Spain reacts after winning the men's singles final match against Novak Djokovic of Serbia at the French Open tennis tournament at the Roland Garros stadium in Paris June 11, 2012. REUTERS/Gonzalo Fuentes (FRANCE - Tags: SPORT TENNIS)

Rafael Nadal French Open

ቴኒስ

በካሊፎርኒያ-ኢንዲያን ዌልስ ሲካሄድ የሰነበተው ዓለምአቀፍ የቴኒስ ውድድር ትናንት በናዳልና በሻራፖቫ አስደናቂ ድሎች ተጠናቋል። ባለፈው ዓመት በጉልበቱ ላይ በገጠመው ጉዳት ለሰባት ወራት ከውድድሩ ርቆ የነበረው ራፋኤል ናዳል ትናንት የአርጄንቲና ተጋጣሚውን ሁዋን-ማርቲን-ዴል-ፖርቶን 4-6, 6-3,6-4 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ታሪካዊ ለሆነ ድል በቅቷል። ናዳል በዚህ ዓመት ከተመለሰ ወዲህ ለአራት ፍጻሜዎች ሲደርስ ይህም ታላቅ አድናቆትን ነው ያተረፈለት። የስፓኙ ተወላጅ ለፍጻሜ የደረሰው በመጨረሻዎቹ ስምንት ውድድር ሮጀር ፌደረርን የመሰለ ከባድ ተጋጣሚም አልፎ ነው። በመሆኑም ጨዋታው እንዳበቃ መሬት ላይ በጀርባው በመጋደምና ክንዶቹን በማወራጨት ያሳየው የደስታ ስሜት አቻ አልነበረውም።

በሴቶች ፍጻሜ ሩሢያዊቱ ማሪያ ሻራፖቫ የዴንማርክ ተጋጣሚዋን ካሮሊን ቮዝኒያችኪን ልዕልና በተመላው አጨዋወት 6-2,6-2 ቀጥታ ከሜዳ አስወጥታለች። በሁለቱ የቀድሞ የዓለም አንደኛ ተጫዋቾች መካከል የተደረገው ግጥሚያ የሻራፖቫ ፍጹም የበላይነት የሰፈነበት በመሆኑ በአንድ ሰዓት ከ 21 ደቂቃ የተወሰነ ነበር። በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ በወቅቱ ሁለተኛ ለሆነችው ሩሢያዊት የትናንቱ የፍጻሜ ድል ካለፈው ዓመት የፓሪስ-ኦፕን ወዲህ የመጀመሪያው መሆኑ ነው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic