እዉቅና ያተረፈዉ ጤፍ ምርምር | ጤና እና አካባቢ | DW | 04.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

እዉቅና ያተረፈዉ ጤፍ ምርምር

መካከለኛዉ ምስራቅና የአረቡ ዓለም ስንዴን፤ ጃፓንን ጨምሩ በጥቅሉ እስያ ሩዝን፤ አብዛኛዉ አፍሪቃ በቆሎን ከማዕዳቸዉ አያጡም። አዉሮጳና ሰሜን አሜሪካም ቢሆን ስንዴን በብዛት እንዲሁም ገብስን ማዘዉተሩ ይታወቃል። ጤፍ ደግሞ መገኛዉም ሆነ ምግብነቱ የታወቀዉ ምስራቅ አፍሪቃ ኢትዮጵያ ነዉ።

24112006 PZ TEFF.jpg

ይህ አቅም ያሳጣል ተብሎ በአንዳንዶች የተወቀሰዉ እንጀራ የሚዘጋጅበት ጤፍ ዛሬ ስሙ ከኢትዮጵያዉያኖች ጓዳ ወጥቶ፤ ለጤና ተስማሚነቱ ተመስክሮለት እየተፈለገ ነዉ። ሰሞኑንም ታዋቂ የዓለማችን ሰዎች አንድም በጓዳቸዉ አንድም በምግብ ቤት ተገኝተዉ እንደተመገቡት ይወራል። ለአንዳንዶቹ ደግሞ ለጤና ካለዉ ጠቀሜታ ሌላ ጣዕሙም ተስማምቷቸዉ ሸንቃጣ ሰዉነታቸዉን መጠበቂያ ሊያደርጉት መነሳታቸዉ ተዘግቧል።

ዋና ተመጋቢዎቹ ጤፍን ለእንጀራ፣ ለአነባብሮ ግፋ ሲልም ለቂጣ ይጠቀሙት ይሆናል፤ የጤፍ ጭማቂ ሲባል ግን ትንሽ ግር ሳይል አይቀርም። በኢንተርኔት መረጃ መፈልጊያዉ ስልት ገብቶ የፈተሸ የስፔኑን ጭማቂ ማየቱ አይቀርም። ብስኩት፣ ዳቦና ጭማቂዉ ታዲያ አሁን ለጤናቸዉ የሚጠነቀቁ የዓለማችን ታዋቂ ሰዎች ምግብ ከሆነ ዉሎ አደረ።

ጤፍ የዓለማችን ሁለተኛዉ ግሩም ምግብ መሆኑ ተነግሮለት ፈላጊዉ መብዛቱ ቢሰማም አቅርቦቱ ግን እንኳን ለዓለም ገበያ ለሀገር ዉስጥም የልብ የሚያደርስ እንዳልሆነ ነዉ የሚታየዉ። የዋጋዉ ነገር ሳይነሳ።

በጤፍ ላይ ምርምራቸዉን የሚያካሂዱትና የምርምሩንም ዘርፍ የሚመሩት ባለሙያዎች በጎርጎሪዮሳዊዉ የዘመን ቀመር በ1950ዎቹ መባቻ ጀምሮ ምርምሩ መጀመሩን ቢጠቁሙም የተወሰነ ሕዝብ ቀለብ በመሆኑ ብዙሃኑ የዓለም ሕዝብ እንደሚመገባቸዉ እንደነስንዴና ገብስ፣ ሩዝና በቆሎ እጅግም ትኩረት እንዳልተደረገለት ያስረዳሉ።

እስከዛሬ በተካሄዱ ምርምሮችም 33 የተሻሻሉ የጤፍ ዘሮች መገኘታቸዉን ሆኖም አርሶአደሮች እስካሁን ያመረቱት ስድስቱን ዓይነት ብቻ እንደሆነ አመልክተዋል።

ዶክተር ሰሎሞን ጤፍ ላይ ምርምር ለማካሄድ የፈለጉት አንድም ሀገር በቀል ሰብል ከመሆኑ ባሻገር እንደሌሎች እህሎች ዓለም ዓቀፍ ትኩረት ስላልተሰጠዉ እንደሆነ ነዉ የገለፁልን።

በደብረዘይት የግብርና ምርምር ማዕከል ጤፍ ላይ የሚካሄደዉን ምርምር የሚያስተባብሩት ዶክተር ክበበዉ አሰፋ እንደሚሉት ጤፍ በአበቃቀሉም ሆነ በሚሰጠዉ ምርት ከሌሎች ሰብሎች በጣም ይለያል።

ከዚህም ሌላ የዓለም መነጋገሪያ የሆነዉ የአየር ንብረት ለዉጥም ጤፍ ካሉት ባህርያት አንፃር እንደማያሰጋዉ ነዉ ዶክተር ክበበዉ ያመለከቱት።

Landschaft in Äthiopien Flash-Galerie

በድርቅም በጎርፍም የአየር ሁኔታ መብቀል አያዳግተዉም እንደእሳቸዉ። በአጠቃቀም ረገድ ደግሞ ጥሩ እንጀራ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ትንሹ ዱቄት በርከት ያለ እንጀራ እንደሚወጣዉ ያመለከቱት የጤፍ ተመራማሪ በምግብ ይዘቱም ከሌሎች ሰብሎች ቢሻል እንጂ እንደማያንስ ያስረዳሉ።

እንደባለሙያዎቹ ጤፍ በአሁኑ ጊዜ ከኢትዮጵያ ዉጭ በሌላዉ ዓለም እዉቅና ያመጣለት ግሉተን ከተባለዉ የፕሮቲን ዘር ነፃ መሆኑ፤ ለጤና ካለዉ ጠቀሜታና የጥሩ ጉልበት ምንጭ ተደርጎ መታየቱ ነዉ።

ዶክተር ክበበዉ በ1950ዎቹ ከተሰሩ ጥናቶች ጠቅሰዉ እንደገለፁልኝ ከወስፋት በተገናኘ የሚከሰተዉን የደም ማነስ አስመልክቶ ጤፍን አዘዉትረዉ ከሚመገቡ ከማይመገቡ መካከል በተደረገ ምርምር በአብዛኛዉ ለችግሩ የተጋለጡት ጤፍን እንደቀለብ የማይመገቡት ወገኖች ናቸዉ። ከዚህም ሌላ ከወሊድ ጋ የተያያዘ የደም መፍሰስ የሚያስከትለዉን የደም ማነስ ለመርዳት እንደሚችልም እንዲሁ በጥናት መደገፉን አመልክተዋል።

ጤፍ በእርግጥም የኢትዮጵያዉያን ምግብ ብቻ ሳይሆን እንደአረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቅ ዓላማዉ መለያቸዉም ነዉ ማለት ይቻላል። ጤፍን ሳይሆን ይቀራል የእስራኤላዉያን አባት የሚባለዉ መዝሙረኛዉ ቅዱስ ዳዊት «ለኢትዮጵያዉያን ምግባቸዉን አዘጋጀህላቸዉ» ሲል የዘመረዉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic